‹‹የአይጥ መርዝ››
ከይኄይስ እውነቱ
ድመት ለምኔ የሚያሰኝ የአይጥ መርዝ በኢትዮጵያውያን ‹ሳይንቲስቶች› ተዘጋጅቶ ገበያ ላይ ውሏል የሚል በድምፅ የተቀረፀ ማስታወቂያ ምስኪን ልጆች በአ.አ. መንደሮች ይዘው መዞር ከጀመሩ የወያኔን ዘመን አልፎ በውላጁም በኦሕዴድ ከቀጠለ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አንዳንዴም በቀን ውስጥ ከሰፈር አልፎ በየመንገዱ እስኪታክተን ልንሰማው እንችላለን፡፡ የሚያበሳጭ ከመሆኑ የተነሳ አገዛዙ ያሰማራቸው እስኪመስል በየቀኑ እስኪሰለቸን እንሰማዋለን፡፡
ኢትዮጵያን በእጅጉ ያስቸገሯት ‹አፅራረ-ኢትዮጵያ አይጦች› ግን ዓቢይ የተባለ ርጉም ‹ብልግና› ብሎ ከሰየመው ኦሕዴድ/ኦነግ ድርጅቱ ጋር፤ ብአዴን የተባለ ጭንጋፍ የኢትዮጵያ ጠንቅ እና ኢትዮጵያን ምድረ ሲዖል ያደረገ ወያኔ ሕወሓት ናቸው፡፡ እውነት ‹ሳይንቲስቶች› ካሉን እነዚህን የጠቀስናቸወን ገዳይ ‹አፅራረ-ኢትዮጵያ አይጦች› የሚያጠፋ ‹መድኃኒት› ቢሠሩልን ምንኛ በገላገሉን እና በመላው አገራችን የዕድሜ ልክ ‹ማስታወቂያ› ይዘንላቸው በዞርን ነበር?! ዛሬ ባገርና በሕዝብ አስተዳደር ረገድ ከዝቅተኛው እስከ ከፍተኛው ዕርከን ባሉ ተቋማት ከተራው ሠራተኛ እስከ ኃላፊው ‹ምንቸቶች› ‹ጋን› የሆኑበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
ሰሞኑን የዐምሐራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ‹ከዓለም አቀፍ ተቋማት› (የአፍሪቃ ኅብረት፣ ኢጋድ፣ የአውሮጳ ኅብረት እና የአሜሪቃ ኤምባሳ ተወካዮች) የተወጣጡ የቴክኒክ ቡድኖች ጋር የጦርነት ቀጣና በሆነው የዐምሐራ ክፍለ ሀገር ውይይት ማድረጉን ተከትሎ አቧራ መነሣቱን ከዜና አውታሮች እየሰማን ነው፡፡ ሁሉም እንደየ ብጤቱ ዜናውን በበጎም በክፉም የተቀበለው አለ፡፡ ‹አጽራረ-ኢትዮጵያ አይጦቹ› እና ደጋፊዎቻቸው ደግሞ አዛብተውና የሐሰት ወሬ ፈብርከው ይሔንን መከራ ያደነዘዘውን ሕዝብ በውዥንብር እየናጡት ይገኛሉ፡፡ አኅጉራዊው ድርጅት የአፍሪቃ ኅብረት ባመዛኙ የደም መጣጮች መሰባሰቢያ በመሆኑ ስሙን ከመቀየር በቀር መሥራች አባቶች እነ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ እና እነ ንክሩማ ይዘው የተነሡትን ልዕለ አሳብ ሊያሳካ ቀርቶ የምዕራቦቹ ምርኮኛ ሆኖ የነርሱን ርጥባን እየተቀበለ የወደቀ ድርጅት መሆኑ ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ የኢጋድን መናገር ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ቀድሞ የወያኔው መለስ አሁን ደግሞ የርጉም ዓቢይ ተጽእኖ ያረፈበት የማይረባ ድርጅት ነው፡፡
በእኔ ትሁት እምነት የሰማነው ዜና የሚያስጨፍርም ሆነ የሚያስወቅስ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በጉልበት የበላይነት በሚያምኑትና ዓለም አቀፉን ሥርዓት ሰይጣናዊ ባደረጉት የምዕራብ መንግሥታትና ተቋማት ላይ ቋሚ የሆነ ጥብቅ ተዐቅቦ አለኝ፡፡ ለጊዜው ‹የዓለም ፖሊስ› በመሆን በአገሮች ጉዳይ ኹሉ ጣልቃ በመግባት ፈላጭ ቆራጭ በመሆናቸው ኢትዮጵያ የምትፈልገው የሥርዓት ለውጥ የነሱን ጥቅም እንደማይነካ ለማሳመን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚያስፈልግ ይሰማኛል፡፡ ለዚህ ዓላማ ደግሞ ተገቢው ብቃት አላቸው ከምላቸው ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ዲፕሎማቶች አንዱ ጋሼ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚህ ተቋማት ፋኖ ዘንድ የሔዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ባጠቃላይ በተለይም ዐምሐራው ሕዝብ በሚገኝባቸው ክፍላተ ሀገራት ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በሙሉ የተፈጸመውን ጉልህና የረቀቀ የዘር ማጥፋት፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የጦር ወንጀሎች፣ ባጠቃላይ በዚህ ዘመን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግፍና በደል የማያውቁ ሆነው (ኤምባሲዎቻቸው፣ አንዳንድ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞቻቸው እና የስለላ ድርጅቶቻቸው በየአገሩ ያለውን ተጨባጭ ሁናቴ መከታተልና መረጃ ማቀበል መደበኛ ሥራቸው ነውና) ለማየትና ከእኛ ለመስማት አይመስለኝም፡፡ ኹለት ዐበይት ምክንያቶችን አስባለሁ፤ 1ኛ/ ከከፍተኛ ሥጋት የመነጨ – የዐምሐራ ፋኖ ትግል ግቡን ቢመታ የነሱን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችልና በቀላሉ ሊጠመዝዙት የሚችል ኃይል ብቻ ሥልጣን መያዙን ለማረጋገጥ፤ ባንፃሩም የዐምሐራው ሥሪት፣ ታሪክና ሥነ ልቦና ዓድዋን ስለሚያስታውሳቸው፣ ቢቻል ትግሉንና አመራሩን ከፋፍሎ ለማዳከም፡፡ 2ኛ/ አሁንም ከጥቅማቸው አኳያ ቀጣናው – የምሥራቅ አፍሪቃ ቀንድ – ከቊጥጥራቸው ውጭ እንዳይሆን (የምዕራብ አፍሪቃው የፖለቲካ ምስቅልቅል እንዳይዛመት) በመሥጋት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአፍሪቃ አኅጉር ለሚታየው ሁለንተናዊ ቀውስ ውሳጣዊውና የቅጥረኞቹ የአፍሪቃ ደም መጣጭ አገዛዞች መሠረታዊ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለቀውሱም መፈጠር ሆነ መቀጣጠል ምዕራቦቹ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸውና ዋነኛ አፍኣዊ ተግዳሮት እንደሆኑ ዛሬ ላይ ለእውነተኛ ታዛቢ የፖለቲካ ‹ሀ ሁ› ሆኗል፡፡ ደጋግሜ በተለያዩ መጣጥፎቼ ትዝብቴን እንዳካፈልሁት የውጭ ፖሊሲያቸው በጉልህ የሚናገረውም ኢትዮጵያን ፋታ በመንሣት ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በርጉም ዐቢይና አገዛዙ ተማምነው ሊቀጥሉ የሚችሉበት ሁናቴ እንደሌለ ሲረዱና የሚያዩት አዝማሚያ ከቊጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል ሲገነዘቡ ደረጃ በደረጃ ጣልቃ ለመግባት ሙከራ ማድረጋቸው ግን የማይቀር ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኛ የቤት ሥራችንን በሚገባ ሠርተን ወታደራዊ የበላይነቱን በፖለቲካዊ አደረጃጀት ካጠናከርነው ቆሻሻውን የዘረኛነት አገዛዝ ካስወገድነው፣ ምዕራቦቹ ሮጠው ይምጣሉ፡፡ እነሱ ሁሌም ከአሸናፊዎች ጋር መሆናቸውን መርሳት የለብንም፡፡ መርሀቸው በጉልበት የበላይነትና ትክክለኛነት ላይ የተመሠረተ ነውና፡፡ ያኔ ብሔራዊ ጥቅማችንን በሚያስከብር መልኩ መነጋገር እንችላለን፡፡
ስለሆነም በኔ እምነት ስኬትና ድል አድርጌ የማስበው የሚከተሉት ተግባራዊ ቢሆኑ ነው፤
1ኛ/ የዐምሐራ ሕዝብና ከአብራኩ የውጡ ፋኖዎች ብአዴን የተባለውን የኢትዮጵያና በተለይ የዐምሐራ ሕዝብ ነቀርሳ ያለ ርህራኄ ማስወገድና ጠላትነቱን በግልጽ ማመን ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ይቀራል፡፡ ወያኔም ሆነ ውላጁ ኦሕዴድ በተለይም ዐምሐራው በሚኖርባቸው ክፍላተ ሀገራት ቊጥሩ ቀላል የማይባል ሕዝብ በተለይም ከቀበሌ ጀምሮ ያለ የመንግሥት ሠራተኛን (መምህራንን) በግድ የብአዴን አባል አድርጓል፡፡ በርካታዎችም ሆዳቸውን አስቀድመው በፈቃደኝነት የተቀላቀሉ አሉ፡፡ የዐምሐራ ሕዝብ ህልውና ይሄ ቆሻሻ የዘረኛነት አገዛዝ ከመጥፋቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሁሉ የበድኑ ብአዴን ከርሣም አባላትም ህልውናቸውና ጥቅማቸው ከአገዛዙ መቀጠል ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ስለሆነም በአራቱም ክፍለ ሀገራት ያሉ የፋኖ አደረጃጀቶች ከተራው አርበኛ እስከ አመራሩ ራሱን ከብአዴን ጋር ንክኪ ካለቸው ኃይሎች ቢቻል ሙሉ በሙሉ ማጽዳትን ይጠይቃል፡፡ ብአዴን አይለወጥም፤ የአገር ጉድፍ ነው!!! ገዱ የተባለ ገዳዳ የዐምሐራ ጠላትና የኢትዮጵያ ፀሮች ሎሌ ተዉ ብአዴኖች ‹ምውታን› ናቸው አይለወጡም፤ እነዚህን አፅራረ ኢትዮጵያ ኃይሎች በሚመለከት ሁሌም ካለማመን እንነሣ በማለት እኔን ጨምሮ ብዙዎች ቢናገሩም የተሻለ ያውቃሉ የተባሉ በትግሉ ሚዲያ ላይ የተሠማሩ ወገኖች ቆመው ሲያጨበጭቡለት ያስተዋልነው የቅርብ ጊዜ መጥፎ ትዝታ ነው፡፡ ተማርኮም ሆነ ይቅርታ ጠይቆ እንዲሁም በፈቃዱ የተቀላቀለውን የብአዴን ኃይል በአመራር ቀርቶ በተራ አርበኝነትም ፋኖን እንዲቀላቀል መፍቀድ አያስፈልግም፡፡ የተቀላቀለውንም ከመካከሉ አውጥቶ የራሱን ሰላማዊ ሕይወት እንዲመራ መሸኘት ያስፈልጋል፡፡ ዳራቸው ብአዴን የሆኑ ቊጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኃይሎች በፋኖ ውስጥ ተሰግስገው እንደሚገኙ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ባገር ልጅነትና በዝምድና ቋጠሮ ምክር፣ ይቅርታ ወይም ዕርቅ የሚባለው የተለሳለሰ አካሔድ ድሉን ማዘግየት ብቻ ሳይሆን ትግሉን እስከማኮላሸት ሊያደርስ እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
2ኛ/ ፋኖ የፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ አደረጃጀቱን ወደ አንድነት አምጥቶ ወጥ ማድረግ ካልቻለ በአገር ውስጥ – በዐምሐራውም ሆነ በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በውጭም በዓለም አቀፍ ተቋማት በተባሉትም ዘንድ ተአማኒነትና ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት ዘበት ነው፡፡ ራሱን ከብአዴንና ከአገዛዙ ሎሌዎች ነፃ ያላወጣ ትግል ለዐምሐራው ሕዝብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ እንዴት መቆም ይችላል? በኹለት እግሩ ቆሞ የአራቱንም ክፍላተ ሀገራት ዋና ከተሞች ነፃ አውጥቶ መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡ እዛው መንደፋደፉና የዕለት ውጊያ ድል እየዘመሩ መቀጠል የሚያዛልቅ አይመስለኝም፡፡ ይሔ ለርጉም ዐቢይ ሠርግና ምላሽ ነው፡፡ ምክንያቱም ላንድ ቀንም ቢሆን ሥልጣኑን ካራዘመለት በየትኛውም ወገን ለሚያልቀው ኃይል እሱ ደንታ የለውም፡፡ ይህንን በድፍረት የምናገረው የፋኖ ወንድሞችና እኅቶችን ጀግንነትና መሥዋዕትነት ለአፍታ ዘንግቼው አይደለም፡፡ መሥዋዕትነቱ ከንቶ እንዳይሆን በመሥጋት እንጂ፡፡
3ኛ/ ከትጥቅ ትግሉ ጎን ለጎን ፋኖ መዋቅሩን በማስፋት፤ የፋኖ አርበኞችን፣ የዐምሐራውን ሕዝብ እና በሌላውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ ወገናችንን ስለ ህልውና ትግሉና ግቡ እንዲሁም ስለ ጠላት ኃይሎች ከፍተኛ ንቃተ ሕሊና የማዳበርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ከእስካሁኑ በበለጠ መንገድ በስፋት ማከናወን ያለበት ይመስለኛል፡፡ አገዛዙ ሕዝብን በጦርነት፣ በማፈናቀል፣ በሽብር፣ በእስርና በአፈሳ በማዋከብ፣ በኑሮ ውድነት፣ በፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ፋታ መንሣት ዋነኛ ስትራቴጂው አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ሁሉ በወገን በፋኖ በኩል ምን እየተደረገ ነው? በተለይም በአ.አ. እና በአራቱ የዐምሐራ ክፍላተ ሀገራት ዋና ከተሞች (ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን እና ደሴ)፡፡ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችን ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ ፋታ በመንሣት አገዛዙ በየዕለቱ የሚፈጽመውን የማይቀለበስ አገራዊ ጥፋት በማስቆም ለሕዝቡም ፋታ መስጠት ይቻላል፡፡
ሌላው ተራ ቢመስልም በትግሉ ሒደት የምንጠቀምባቸውን ንግግሮች (ከአደረጃጀት ወጥነት ጋር የተያያዘ ቢሆንም) በጥንቃቄ ብናስተውል መልካም ነው፡፡ ክልል የተባለ የዘረኝነት የከብት ጋጣ ለማጥፋት እየታገልን ይህንኑ ቃል መጠቀም ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ከወዲሁ ሕዝባችን ወያኔና ተወራጆቹ ያስለመዱትን የዘረኛነት ቃላት እንዲረሳና ለአንድነትና ለኅብረት በሚጠቅሙ ቃላትና ሐረጎች መተካት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ‹ብሔር ብሔረሰቦች› የሚለውን ትርጕም አልባና ማጭበርበሪያ ቃል በትክክለኛ ስሙ ነገድ (ጐሣ) እያልን በመጠቀም ልጆቻችንን ማለማመድ እንችላለን፡፡
በማጠቃላያ ልናገር የምፈልገው፤ ርእሰ መጻሕፍቱ መከር እስኪደርስ እንክርዳድ ከስንዴው ጋር መብቀሉ የማይቀር መሆኑን ይናገራል፡፡ የሚነቀልበትና ወደ እሳት የሚጣልበት ጊዜ ግን ይመጣል፡፡ በተቀደሰች በአገራችን ምድር በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው ሕይወት እንክርዳዶች እንደ አሸን የፈሉበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ብዙዎች ሆዳቸውን አምላካቸው በማድረግ አገርንና ሕዝብን ከሚያጠፉ የጥፋት ኃይሎች ጎን ተሰልፈዋል፡፡ ጸጸቱም ሆነ ሐዘኑ የማይጠቅም ከመሆኑ በፊት በንስሓ ለመመለስና አገርና ሕዝብን ለመካስ አሁንም ቢሆን ጊዜው አልዘገየም፡፡ ካፈርሁ አይመልሰኝ ማለት ባገርና በሕዝብ ላይ ታላቅና ይቅር የማይባል በደል ነው፡፡ በውስጥም በውጭም የምትገኙና በመልካሙ የኢትዮጵያ ማሳ ላይ የበቀላችሁ እንክርዳዶች እባካችሁ ስለምታምኑት ፈጣሪ እና በመከራ ስለሚሰቃየው ሕዝባችሁ ብላችሁ ከእኩይ ድርጊታችሁ እንድትታቀቡና ኃይላችሁን ለበጎ ተግባር እንድታውሉት እማጸናችኋለሁ፡፡