>
5:42 pm - Sunday March 21, 5909

ከሚናገረው በላይ የተግባር ሰው፤ አርበኛ  ታላቁ እስክንድር ነጋ

ከሚናገረው በላይ የተግባር ሰው፤ አርበኛ  ታላቁ እስክንድር ነጋ

 

በትግሉ ሠመረ

 

በዓላማ ጽናቱ አይደለም በኢትዮጵያውያን ወዳጅና ጠላቶቹ ዘንድ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው   ጀግናው አርበኛ እስክንድር ነጋ፤ በተለይ  የአ.ፋ.ሕ.ድ መሪ ኾኖ ከተመረጠበት ጊዜ ጀምሮ በአውሬው የኦህዴድ ብልፅግና፣ በግንቦት ሰባቶቹ አስመሳይ ፀረ-አማራ ግለሰቦች ፣ እንዲሁም  በብአዴን የሳይበርና የኤሌትሮኒክ ሜዲያ ኔትወርክ የታቀፉ አክቲቪስቶች፣ ተላላኪ ጋዜጠኞች፣ ሆዳም ምሁራንና ፖለቲከኞችን ጨምሮ የተከፈተበትን የተቀናጀ የሥም ማጥፋት ዘመቻ  በመቋቋም፤   የአ.ፋ.ሕ.ድን ወታደራዊ ፣ ፖለቲካዊና  ዲፕሎማሲያዊ ትግል በከፍተኛ ትእግስትና ፅናት  ወደፊት እያራመደው ይገኛል። 

በዲፕሎማሲ ደረጃ አ.ፋ.ሕ.ድ በቅርቡ ከአሜሪካን፣ከአውሮፓና ከአፍሪካ ተወካዮች ጋር ያደረገው ውይይት አንዱ የአርበኛ እስክንድር ነጋ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለው ተቀባይነት ለዲፕሎማሲያዊ ትግሉ እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ የሚያመለክት ነው። እስክንድር ነጋ የአውሮፓ ህብረትም ኾነ አሜሪካኖቹ በተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነትና የዲሞክራሲ ትግል ለዓለም ህዝብ ያለውን ተምሳሌትነቱን በማድነቅ በተደጋጋሚ ሽልማቶችን ያበረከቱለት ብርቅዬ ኢትዮጵያዊ የፍትህና የነፃነት  የዲሞክራሲ የትግል አርማ ነው።  ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ከዚህ በፊት ገና የአማራ ፋኖ የትጥቅ ትግል ሳይጀመር ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበረው የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት፣   የፍትህ መጓደልና እጦት እንዲሁም የፕሬስ ነፃነት ግደባን በተመለከተ ለፍሎሪዳው  ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ፤  የአሁኑ የአሜሪካንን የውጭ ጉዳይ ቢሮ(state secretary office) ዋና ኃላፊ   በጽሕፈት ቤታቸው ተገኝቶ ባስረዳበት ወቅት፤ ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ቀድሞውኑ የእስክንድር ነጋን ማንነት ያውቁ ስለነበር “ከማውራት በላይ ብዙ እየሠራ ካለ ሰው ጋር መገናኘቴ ለኔ ክብር ነው(it is an honor to meet   someone who is doing more than just speaking about it)”   ሲሉ ለእስክንድር ነጋ አድናቆታቸውን ገለፀውለት ነበር።

እንደዚኽ ያሉ አንፀባራቂ ፀሐይ የሞቃቸው የእስክንድር ነጋ የትግል ታሪክ እውነታዎች እያሉ፣   በቅርቡ  አ.ፋ.ሕ.ድ  ከአሜሪካን፣ ከአውሮፓና ከአፍሪካ ተወካዮች ጋር የአማራ ፋኖ የህልውና ትግሉ ዙሪያ፣ በድርቅ ዙሪያና፣ የአብይ አህመድ መንግሥት እየፈፀመ ባለው የጦር ወንጀል ዙሪያ ያደረገውን ውይይት  በመቃወም  አንዳንድ በአማራው ትግል ውስጥ በርቀት ኾነው ሃሳብና ትችት በመስጠት የሚታወቁ   እንደ  አቻምየለህ ታምሩና እንደ ኢንጅነር ይልቃል ያሉ የታሪክና የፖለቲካ ሰዎች፣ የግንቦት 7ቱ የአንዳርጋቸው ጽጌ  ኔትወርክ  የሳይበር ሜዲያውን በመቆጣጠር ጭምብላቸው እስኪወልቅ   ድረስ በእስክንድር ነጋና በአ.ፋ.ሕ.ድ ላይ ከፍተኛ  የሥም ማጥፋት ዘመቻ አካሂደዋል። እነዚህ ግለሰብና ቡድኖች  እንደ ዋና ክስ አድርገው ያቀረቡት ውይይቱ የተመቻቸው አብይ አህመድ በሚያውቃቸው   የኢጋድ(IGAD) ሊቀመንበር በዶቶር ወርቅነህ ገበየሁና አንድ አፍሪካ ህብረት(AU) የጥበቃ ሥራ የሚሠራ ግለሰብ አማካኝነት ነው የሚል ነው። ሌላው እንደ ክስ አድርገው ያቀረቡት  አ.ፋ.ሕ.ድ  የሌሎች በአ.ፋ.ሕ.ድ ሥር ያልተካተቱና ወይም ያፈነገጡ የፋኖ አደረጃጀቶች  አልተሳተፉበትም የሚል ነው።   በርግጥ እነዚኽ በአርበኛ አስስክንድር ነጋ ላይ  ትችትና ውግዘት ያቀረቡት ግለሰቦችና ቡድኖች  አርበኛ እስክንድር ነጋ  ከአሜሪካና ከአውሮፓ ልኡካን ጋር ለመገናኘትና ለመወያየት ኢጋድ (IGAD)ን የሚመራው በእንግሊዘኛ ቁጥር ማንበብ የማይችለውን መሃይሙን ወርቅነህ ገበየሁ ወይም አፍሪካ ህብረት(AU) ውስጥ በዘበኝነት የሚያገለግል ግለሰብ እንደማያስፈልገው ሳያውቁ ቀርተው አይደለም፤ እንዲኹም አ.ፋ.ሕ.ድ በተደጋጋሚ በሥሩ ያልታቀፉትን የፋኖ አደረጃጀቶች ከብአዴን ተፅእኖ ራሳቸውን አጥርተው በአንድ ጥላ በአ.ፋ.ሕ.ድ ሥር እንዲገቡ ያደረገውን ትእግስት አስጨራሽ ጥሪ ሳይሰሙ ቀርተውም አይደለም። በሌላ በኩል  አርበኛ  እስክንድር ነጋ  ከአውሬው አብይ አህመድ ጋር ተደራድሮ የአማራን ህዝብ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ስብእና እንደሌለውም ሳያውቁም ቀርተው አይደለም። በርግጥ የእነዚኽ ግለሰቦችና ቡድኖች ከዚኽ በፊት በፋኖ ዙሪያ ይሰጡት ከነበረው አስተያየትና ትችት በመነሳት አንድ ነገር ማለት ይቻላል።   ይኸውም የተቃውሟቸው ዋናው መነሻ  ለምን በብአዴን ኮምፕሮማይዝድ (Kompromat)  የተደረገው እነሱ ከፍ ከፍ ሲያደርጉት የቆዩትና የሚደግፉት  የነዘመነ ካሴ ”የአማራ ፋኖ በጎጃም”  የአ.ፋ.ሕ.ድን መሪ እስክንድር ነጋን ከትግሉ አስወጥቶ ሳይቆጣጠር  ለምን ውይይት ተደረገ ከሚል  ቁጭት የተነሳ ነው።   የእነዚኽን ግለሰቦችና ቡድኖች ተቃውሞ ያሳየው ዋና ቁም ነገር ቢኖር የትግል አሰላለፋቸው በዋነኛነት  ከአማራ ህዝብ ጋር ሳይኾን  አንድም ከብአዴን አልያም ከፀረ-አማራው የአብይ የአውሬዎች ጎራ መኾናቸውን ነው። 

   እነዚኽ  በእስክንድር ላይ ዘመቻ የከፈቱ በአማራ ሥም የሚምሉ ፖለቲከኞች፣   የብአዴን  ምሁራን፣ ዶቶሮችና ፕሮፎች  እውነት የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል የሚያሳስባቸው ከኾነ   አርበኛ እስክንድር ነጋ ላይ፤  ነጋ ጠባ በሃሰት ያልተገባ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ከማካሄድ  እራሳቸውን በመቆጠብ፤ በመጀመሪያ እራሳቸውን ከብአዴን ተፅእኖና ጥገኝነት በማላቀቅ ከዛም ከአ.ፋ.ሕ.ድ ተገንጥሎ የወጣውን   የነዘመነ ካሴን “የአማራ ፋኖ በጎጃም”  ከነቀርሳው ብአዴን እጅ እንዲላቀቅና ጀግኖቹ የጎጃም ፋኖዎች የፀረ-ብአዴን ትግሉን እንዲያፋፍሙና ከሌሎች በአ.ፋ.ሕ.ድ ሥር ከተሳሰቡ  በጎጃም የሚንቀሳቀሱ  ወንድሞቻቸው ፋኖዎች ከነ ከነማስረሻ ሰጤ አንዲኹም  ከሸዋ ፣ ከጎንደርና ከወሎ ፋኖዎች ጎን  አብረው በመቀናጀት የአማራን ህዝብ ነፃነት ብሎም የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማብሰር እንዲችሉ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።  የአ.ፋ.ሕ.ድ መሪ ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ  አብይ አህመድ በቀጥታ የሚያዘው መከላከያውም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚመራው  የኦነግ ጦር  የአማራ ፋኖን  የሚያሸንፍ ኃይል እንዳልኾነና ነገር ግን   ለ30 ዓመታት የወያኔን ሥልጣን አስጠባቂ ኾኖ በፍፁም ታማኝነት ያገለገለው ብአዴን ለአማራ ፋኖ የህልውና ትግል ዋና መሰናክል መኾኑን ተረድቶ ፤   ብአዴን ከአማራው ጫንቃ ላይ ማላቀቅ የመጀመሪያው የሁሉም አማራ ህልውና ታጋይ  ተግባር መኾን እንዳለበት  ያቀረበውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መኾን ይገባቸዋል።

በዲፕሎማሲውም መስክ ቢኾን ከአ.ፋ.ሕ.ድ ጎን በመቆም   የዓለምን ፖለቲካ እያተረማማሰች ለማንም የማትመለስ መኾኗ እያሳየች ያለችውን የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኃያሏ አሜሪካን በመቅረብ፤  በተለይ  አርበኛ እስክንድር ነጋ ከዚኽ ቀደም ከሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ፈጥሮት የነበረውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ድልድይ በመጠቀም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን የውጪ ፖሊሲ እንድታስተካክልና የዘር ፍጅት አራማጁን የጦር ወንጀለኛው አብይ አህመድ የምተሰጠውን ፖለቲካዊም ኾነ ፋይናንሻል ድጋፍ እንድታቆም ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይጠበቅባቸዋል።

ብአዴንን ተታከን አማራን ነፃ እናወጣለን በሚል ቀቢፀ ተስፋ ከፍተኛ ሪሶርስና ምሁራዊ አቅም እያባከኑ ያሉ በውጪ ሀገር የሚገኙ  የአማራ ምሁራን  የብአዴንን የማያዋጣ  ተደራቢ ካባ  ወዲያ ጥለው የትግል አካሄዳቸውን  ከሚናገረው በላይ የተግባር ሰው ከኾነው የአ.ፋ.ሕ.ድ መሪ  ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ጎን በመቆምና በማስተካከል  “መነሻችን አማራ መዳረሻችን ኢትዮጵያ” የሚለውን መስመር በመከተል  አማራውን ከህልውና ሥጋት ለመታደግ ብሎም ኢትዮጵያን ከመፈራረስና ከመበታተን ለማዳን የሚደረገውን ትግል ከእውቀት አልባ ፀረ-አማራ  አክቲቪስቶች፣  ከግንቦት 7  አደገኛ መሰሪ ፀረ-አማራ ቡድኖች እንዲሁም  አልባሌ መናኛ የብአዴንና የብልፅግና ተከፋይ፣ በጎጥ የተቧደኑ ቅጥረኞች እጅ የፕሮፖጋንዳ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ትግሉን በማውጣት ምሁራዊ አቅማቸውን የአማራውን የፖለቲካና  የዲፕሎማሲ ትግል ወደ አንድ በማመምጣትና ከፍተኛ ደረጃ በማድረስ  የበኩላቸውን አስተወፅኦ የማድረጊያቸው ጊዜው አሁን ነው።

ድል ለአማራ ፋኖ 

ድል ለአ.ፋ.ሕ.ድ

Filed in: Amharic