>
5:42 pm - Wednesday March 21, 0717

እስክንድር ''ይሰቀል - ይሰቀል'' የሚሉ ድምፆች ምነው ማቆሚያ አጡ? 

እስክንድር ”ይሰቀል – ይሰቀል” የሚሉ ድምፆች ምነው ማቆሚያ አጡ? 

እውን እስክንድር ቢሰቀል የዐማራ ህዝብ ይድናል? ከእስራቱስ ይፈታል? 

ይህ ድምፅ የማነው? የዐማራ ህዝብ ወይስ የዐማራ ህዝብ ጠላቶች? 

አብይ አህመድና ብአዴናውያን እስክንድር ነጋን ለይተው ለምን ለማጥቃት ፈለጉ? ለምን ለቅርጫ ፈለጉት? ለምን የእስክንድር ነገር ለሁለቱም  አካላት የጋራ የእግር እሳት ሆነባቸው?   ጩኽቶች ሁሉ ለምን እስክንድር ላይ አተኮሩ? 

የሚያገናዝብ አእምሮ ካለህ እነዚህን ጥያቄ ዎች ይዘህ ዱካውቸውን ተከተል።

የአብይ አህመድን ገዳይ ስርዓት ከስሩ ነቅሎ/ መንግሎ ለመጣል እና በምትኩ ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ አዲስ ስርዓት ለመመስረት በቁርጠኝነት ለዐማራ ህዝብ የሚታገለው እስክንድር ነጋ ከአብይ አህመድ ባሻገር ለምን ለዐማራ ወገኖቹ ለዘመነ ካሴ፣ ለአበበ ፈንቴ ፣ ለአስረስ ማረ፣ ለማርሸትፀሃዩ እና ለመሰሎቻቸው ጉልበት ከመሆን ይልቅ ስጋት ሊሆን ቻለ? 

እውነት እስክንድር የዐማራ ህዝብ ጠላት ነው? የዐማራን ህዝብ ይጠላል? የዐማራ ህዝብ መከራና ሰቆቃስ እንዲቀጥልስ ይፈልጋል? ለምን?

የብአዴን ወጣት ሊግ ደቀመዛሙርት እና የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች Roll model ህወሃት ነች። እነዚህ ግለሰቦች ከህወሃት ያልኮረጁት ነገር ቢኖር ምናልባት ስሟን ብቻ ነው። ለዚህም ከማንም በላይ እየሄዱበት ያለው መንገድ ምስክር ነው። 

የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች ከዛሬ ነገ ከአባታቸው ከብአዴን ውድቀት ተምረው ከዐማራ ህዝብ ጎን ይቆማሉ፣ ከክፋታቸው ይመለሳሉ ተብሎ በትዕግስት ቢጠበቅም እለት እለት በክፋት እየባሱ በአያታቸው መንገድ ጨፍነው መንጎድን መርጠዋል። 

” Once ብአዴን always ብአዴን”! 

ህወሃት “ዐማራ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን ይጨቁን ነበር” የሚለውን የሐሰት ትርክት / False narrative ፈጥራ ለኦሮሞዎችና ለሌሎች ብሔረሰቦች ስታስተምር “ጭቆናውን” በጥልቀት ተንትና ፣ አመስጥራ በመፅሃፍና በስልጠና ማኗሎች አሳትማለች። 

ትርክቱ በመማሪያ መፃህፍትም ተካቶ የኦሮሞ ህፃናት በትምህርት ቤት እንዲማሩት አድርጋለች፣ ግጥምና ዜማ ተሰርቶለት ህዝቡ በቁጭት እንዲዘምረው እና እንዲዘፍነው አድርጋለች።  እንዲሁም “በነፍጠኛው ወረራ ወቅት ጡታቸው ለተቆረጠ” የኦሮሞ እናቶች “መታሰቢያ” የአኖሌ ላይ ሃውልት አሰርታለች።

አሁን ድረስ ይህ የሐሰት ትርክት እውነት ነው ብለው የሚያምኑ ዛሬ ህወሃት ራሷ ኧረ ውሸቴን ነው ብላ እያለቀሰች ብትነግራቸው የማያምኑ በርካቶች ኦሮሞዎች አሉ። 

በዚህ የሐሰት ትርክት (False narrative) ምክንያት በርካታ ዐማራ ወገኖቻችን ህይወታቸው አጥተዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ ለስደትና ለመከራ ተዳርገዋል። 

ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው ብአዴናዊያን ከአብይ አህመድ ጋር ሳይነጋገሩ ተናበው እስክንድርን ከዐማራ ፋኖ ትግል ለማስወጣት እረፍት አጥተው፣ በጥምረት እየሰሩ ይገኛሉ። 

እጅግ በሚገርም ሁኔታ በጀት መድበው፣ “እስክንድር ነጋ ፋኖን በዶላር ገዛ” ፣ “የፋኖ አንድነት ዋነኛ እንቅፋት እስክንድር ነጋ ነው” የሚሉ የሃሰት ትርክቶች/ False narratives ፈጥረው፣ ለትርክቱ ግጥምና ዜማ ሰርተው፣ ነጠላ ዜማ አዘጋጅተው ፣ አዝማሪ ቀጥረው በዘፈን ሰንደው እንደ አያታቸው ህወሃት ወደዚህ አይነት የዘቀጠ የፕሮፓጋንዳ ጨዋታ ሲገቡ ስናይ ወይ መመሳሰል ብለን ታዝበን አልፈናል። 

መቸም ” ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም” ነውና ይህ ሳያላምጥ የሚውጠው የማህበረሰባችን ክፍል የተለቀቀለትን ዘፈን ተቀብሎ እሰ‍ከዛሬ እስክስታውን እያስነካው ይገኛል። 

ማንም ሰው እንደሚያውቀው እስክንድር ፋኖን የገዛው በሃሳብ/ በሚያራምደው ርዕዮት ማርኮ ነው። አላወቁትም እንጂ “እስክንድር ፋኖን በዶላር ገዛ” የሚለው ሃሜት ከእስክንድር ይልቅ ለነኮ/ል ፈንታሁን፣ ለሻለቃ መከታው ፣ ለነ አርበኛ ደረጀ በላይ፣ ለነ አርበኛ ሰሎሞን አጠና፣ ለነ አርበኛ ከፍያለው ደሴ፣ ለኮ/ል ማስረሻ ሰጤ እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ስር ሆነው ለሚታገሉ ፋኖዎች እና የፋኖ አመራሮች ትልቅ ንቀት እና ስድብ ነው! 

እጅግ ገራሚው ደግሞ የዐማራ ፋኖ አንድነት እንዳይመጣ እንቅፋት የሆኑት በድምፅ ብልጫ ሁለት ጊዜ ተሸንፈው ውጤቱን ባለመቀበል የዐማራ ፋኖ የአንድነት እንቅፋት እነሱ ሆነው ሳለ ፡ ከህወሃት በቀሰሟት ታርጋ የመለጠፍ፣ ስም የማጠልሸት/ character assassination ታክቲክ ሚዲያና ተሳዳቢ በመቅጠር፣ የማህበራዊ ሚዲያ ግሪሳ በማሰማራት ጥፋቱን ወደ  እስክንድር ነጋ  አሸጋግረው ህዝቡን በማደናገራቸው በሴራ ክህሎታቸው ቁጭ የአያታቸው የህወሃት የልጅ ልጅ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል! 

እነዚህ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች ለዐማራ ህዝብ የሚታገሉ ከሆነ ከዐማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ከወጡ በኋላ ሌላ የራሳቸውን ድርጅት ለመመስረት ከመጣር ይልቅ ለምን ተስርቶ ያደረ የዐማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን ለማፍረስ ፈለጉ? ለምን ከመስራት ይልቅ ለማፍረስ ተጉ? 

አየህ ቤት መስራት ቤት የማፍረስ ያህል ቀላል አይደለም! ቤት ማፍረስ እውቀት አይጠይቅም። ቤት መስራት ግን የሰርቬይንግ፣ የዲዛይን፣ የማቴሪያል፣ ኮንስትራክሽን፣ ፊኒሺንግ እና ሌላም ብዙ እውቀት እና ልምድ ይፈልጋል! 

አሁንም መጠየቅ ያለበት ቁልፍ ጥያቄ እንደ አብይ አህመድ ሁሉ እነ ዘመነ ካሴ፣ አበበ ፈንቴ፣ አስረስ ማረና ማርሸት የመሳሰሉ የብአዴን ወጣት ሊግ እና የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች በአንድ ድምፅ እሰክንድር ነጋን ለምን አምርረው ይጠላሉ?  

አስረስ ማረ በአንድ ቃለመጠይቁ “ይህን ስርዓት ለመጣል ከህወሃት ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን” ብሏል። ማርሸትም በአንድ ሚዲያ ” ህወሃት ዳግም ብትወረን እንኳን ከህወሃት ጋር አንወጋም” ብሏል። ከዚህም ባሻገር በዳንግላ እስርቤት ታስረው የነበሩ የህወሃት የጦር መኮንኖችን እስር ቤት ሰብረው አውጥተው ወደ ትግራይ አሳፍረው በመላክ ለህወሃት ባላቸው ታማኝነት “እጃችንን በአፋችን እንድንጭን” አድርገውን ነበር። 

አስረስ ማረ በመሳይ (አስመሳይ) ሚዲያ ቀርቦ ከዐማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ጋር ለመደራደር (ለመነጋገር)  በቅድሚያ ድርጅቱ እንዲፈርስ ቅድመ ሁኔታ አቅርቧል። በጣም የሚገርመው ግን ከህወሃት ጋር በጋራ ለመስራት ሲነጋገሩ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ አላቀረበም! ህወሃት ዐማራ ጨቋኝ ነበር ከሚለው ትርክቷ ባሻገር ወልቃይት እና ራያ የትግራይ መሬት ነው ብላ አሁንም ድረስ ታምናለች። ሣልሣይ ብአዴን በነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ከሌለው ሃሳቡን ይገዛዋል ማለት ነው!!

በቅርቡ ደግሞ የዐማራ እናቶችን ሊደፍር፣ ሊገድል እና ንብረት ሊያወድም የአብይ አህመድን ወንበር ጠባቂ ሰራዊት እየመራ ገብቶ የተማረከ ኮሎኔል በ15 ሚልየን ተደራድረው ለአያታቸው ለህወሃት አሳልፈው በመስጠት ለህወሃት ያላቸው ፍቅር እስከመቃብር መሆኑን አስመስክረዋል። 

በአንፃሩ የህወሃቱ ሊቀመንበር “ዶ/ር” ደብረፅዮን  “ለትግራይ ህዝብ ከዐማራ ይልቅ የሱዳን ህዝብ ይቀርበዋል” በሚለው “ዘመን ተሻጋሪ” ንግግሩ ለዐማራ ህዝብ ያለውን ጥላቻ በአንድ ወቅት በሚዲያ ገልፆ ነበር። ይህን አቋሙን ሰለመቀየሩ እስከዛሬ የታወቀ ነገር የለም። 

እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ሌላ ጥያቄ እንደ አስረስ ማረ እና መሰሎቹ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች ከእስክንድር ይልቅ “ዶ/ር” ደብረፅዮን፣ ከአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ይልቅ ህወሃት እንዴት ሊቀርባቸው ቻለ? 

Guys this isn’t a simple paradox!

These people are theoretically “Amhara” but practically Anti Amhara!!!

ሌላው አግራሞት የሚያጭር ነገር የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች እና አብይ አህመድ በአንድ ድምፅ ሁሉም እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን እስክንድር ነጋ ይሰቀል፣ ይሰቀል ይላሉ? እውን እስክንድር ቢሰቀል የዐማራ ህዝብ ይፈወሳል? አብይ አህመድስ ይሸነፋል? 

እስክንድር ከአዲስ አበባ ገለል በማለቱ ሲታገልለት የነበረው የአዲስ አበባ ህዝብ ምን አገኘ? “እብድ፣ ጭር ሲል የማይወድ” ሲለው የነበረው የአዲስ አበባ ህዝብ አሁን ላይ ምን ይላል? አብይ አህመድ “ከእስክንድር ጋር ወደ ለየለት ጦርነት እንገባለን” ያለውስ ለምን ነበር? 

ይህ ሁሉ ግሪሳ በዚህ ሰዓት ለምን አንድ ላይ ተሰባሰበ? አብይ አህመድ በድሮን፣ በእግረኛና በብረት ለበስ፤ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች በእግር በፈረስ እስክንድር ነጋን ለምን ይፈልጉታል?

ከላይ በመነሻየ እንደገለፅኩት የተነሱትን ጥያቄዎች ይዞ የዐማራን ህዝብ የህልውና ትግል እግር በእግር ለሚከታተል ሰው መልሱ በጣም ቀላል ነው። 

አንደኛው ምክንያት ሁለቱም አካላት እስክንድር እጅ ያዩት አንድ ወሳኝ እውነት አለ።  እስክንድር ነጋና ድርጅቱ የሚከተሉት እና የሚያራምዱት ጠንካራ ርዕዮተ ዓለም ነው! ይኸውም መነሻውን የዐማራ ህዝብ ነፃነት መዳረሻውን የኢትዮዽያ አንድነት ያደረገ፣ በስር ነቀል ለውጥ የሚያምን፣ በኢትዮዽያ ሀገራዊ ሉአላዊነት ላይ ብዥታ የሌለው እና የማይደራደር  የዐማራ ፋኖ ርዕዮተ ዓለም መፈጠር ሁለቱንም ወገኖች እንቅልፍ አልባ አድርጓቸዋል። 

ይህ ሃሳብ ገበያ ላይ ያለውን ውድ ዋጋ እና በዐማራ ህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከወዲሁ ስለተረዱ ሁለቱም አካላት ከባድ ድንጋጤ ወድቆባቸዋል። በተጨማሪም አብዛኛው የዐማራ ፋኖ ታጋይ ይህን ሃሳብ በቀላሉ ይገዛዋል። 

ማንኛውም ተራ የዐማራ ፋኖ ታጋይ በማንኛውም አጋጣሚ / randomly ቢጠየቅ የሚመልሰው ይህንኑ ነው። የዐማራን ህዝብ በነፃነት የመኖር ህልውና ማረጋገጥ እንዲሁም አባቶቻችን ሰርተው ያቆዩአትን ታላቅ ሀገር ኢትዮዽያን ከነአንድነቷ ማስቀጠል ህልም አለው። 

እስክንድር ነጋም ከዚህ የተለየ አጀንዳ  አልነበረውም! የለውም! ወደፊትም አይኖረውም! እንደፈለክ አገላብጠህ ብትመረምረው፣ የፈለገ ብትመራመር የእስክንድር ነጋ የመጣበት መንገድ (Track record) የሚያሳየው ይህንን ነው! 

በአንፃሩ አብይ አህመድም ሆነ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች በኋላ ኪሳቸው ተሸክመው የሚዞሩት እስክንድር በህይወት እስካለ ድረስ ሊሳካላቸው የማይችል ፣ ነገር ግን በእስክንድር መቃብር ላይ ብቻ እውን ሊሆን የምትችል የፕሮጀክት ሃሳብ አለቻቸው። ለዚህ ነው አምርረው እስክንድር ነጋን የሚጠሉት!

በመሆኑም የዐማራ ህዝብ ጠላቶች እስክንድር ነጋን ከተቻለ አዋክበው ፣ አሸማቀው፣ ቅስሙን ሰብረው፣ አንገቱን  አስደፍተው ደብዛውን በማጥፋት ይህን ሃሳብ ከምንጩ ለማድረቅ፣ የዐማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን በማክሰም ከሰው ልብ ለማውጣት ከፍተኛ በጀት እና የሰው ሃይል መድበው ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ። 

አሁን ባለው ሁኔታ ከአብይ አህመድ በላይ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች እስክንድር ነጋን ይፈልጉታል። የግድያ ሙከራን ጨምሮ በርካታ የተቀናጀ ዘመቻ ተከፍቶበታል። 

በመደበኛው ጦር እስክንድርን አድኖ መያዝም ሆነ መግደል ስላልተቻሉ የአብይ አህመድ ገዳይ ስርዓት እና የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች ሳይነጋገሩ ተናበው የሳይበር ጥምር ጦር ዘመቻ ከፍተውበታል። 

በተለይ ማረጃ ቴሌቭዥን፣ ሮሃ ሚዲያ፣ ABC ቴሌቭዥን ፣ ግዮን ቴሌቭዥን ፣ Ethio251 ሚዲያ፣ ጠለስ ሚዲያ፣ አንከር ሚዲያ በውጭ፣ በሀገር ውስጥ ደግሞ ከዋልታና  ኢቢሲ ባሻገር ዋዜማ ራድዮ፣ መሰተት መዲያ ወዘተ በአጠቃላይ አብይ አህመድ እጅግ በርካታ ገንዘብ መድቦ ያስፈረማቸው ሚዲያዎችና የሚዲያ ባለቤቶች፣ ከሣልሣይ ብአዴን አዋላጆችና የስርዓቱ ተከፋይና ወዶ ገብ ግሪሳዎች ጋር በጥምረት ያሳዪት መናበብ እጅግ የሚገርም ነው! 

ሁለተኛው እና ዋናው የዚህ ሁሉ ርብርብ፣ ብሎም የስርዐቱና የሳልሳይ ብአዴን አዋላጆች እንቅልፍ ማጣት ቁልፍ ምስጢር  እስክንድር ነጋ የዐማራ ፋኖ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ እንዲደራጅ (በሻለቃ፣ በብርጌድ፣ በክፍለጦር፣ በኮርና በእዝ) እና ግዙፍ ድርጅት (የዐማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት) ባለቤት እንዲሆን በማድረጉ ነው። 

ጠላቶቻችን የዐማራ ህዝብ የጥንካሬው ቁልፍ የት ጋር እንዳለ በሚገባ ተረድተዋል! ለዚህ ነው ድርጅት እና አመራር እንዳይኖርህ የሚተጉት። 

አየህ ስትደራጅ አመራር፣ ራዕይ፣ ዓላማና ግብ ይኖርሃል። መነሻና መዳረሻው የታወቀ ትግል ትታገላለህ። ስትደራጅ የስራ ድርሻ ፣ ዲሲፕሊን፣ አለቃ ይኖርሃል። በህግና በስርዓት ትመራለህ። ከበቃህና ከተመረጥክ ትመራለህ፣ ካልበቃህ ፣ ካልተመረጥክ፣ ትማራለህ፣ ስትመረጥ ትመራለህ። 

አልተመረጥኩም፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ብለህ የስኒ ማዕበል አታስነሳም። ካልሰራህ ተገምግመህ ትወርዳለህ። ካጠፋህ ትጠየቃለህ፣ ጥሩ ከሰራህ ትበረታታለህ፣ የበለጠ ሃላፊነት ይሰጥሃል፣ ትሾማለህ፣ ትሸለማለህ። 

ድርጅት ከሌለህ መሪ የለህም። ራዕይ ፣ መነሻና መዳረሻህ አይታወቅም። አንድነት፣ ጥነካሬ አይኖርህም። ጠላቶችህ አይፈሩህም፣ ብተጮህ የሚሰማህ የለም! ብታለቅስ ጠላቶችህ ሶፍት ያቀብሉሃል፣ ይሳለቁብሃል። እንደሰፌድ ቆሎ እየዘገኑ በየተራ ይቆረጥሙሃል። 

ለዚህ ነው ኦህዴድ/ ኦነግ ነቃ ነቃ ያሉትን የአማራ ህዝብ አመራሮች ( እንደ ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣፣እዘዝ ዋሴ፣ ምግባሩ ከበደ ፣ ጀነራል አሳምነው ፅጌ ያሉትን) በጊዜ ቀርጥፎ በመብላት የኦሮሙማ Grand ፕሮጀክቱን የጀመረው! 

ይህ ከገባህ ተደራጅተህ ታገል። መደገፍ ቢያቅትህ ቢያንስ እንቅፋት አትሁን። ወደፊት መራመድ ቢታቅትህ ጓደኛህን አትጎትት። ከወደክ ለመነሳት ሞክር፣ ጓደኛህን አትጣለው። 

ከአምስት በላይ መሪዎች ተፈራርቀውባት ህወሃት ላለፉት ሃምሳ አመታት በብዙ ውጣ-ውረድ ውስጥ ብታልፍም ጠንካራ ሆና እስከዛሬ መዝለቅ የቻለችው አባላቶቿ በድርጅት እና ድርጅታዊ አሰራር ላይ ጠንካራ እምነት ስላላቸው ነው! ጠንካራ ድርጅት ስለነበራቸውና ጠንክረው ስለተዋጉ በኢትዮ ትግራይ ጦርነት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳይቀር ተሰሚነት ነበራቸው። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትግራይ ጉዳይ ብቻ ከ10 ጊዜ በላይ  መሰብሰቡ ይታወሳል። መሪ ድርጅት እና ጠንካራ አመራር ሲኖርህ በአለም አቀፍ መድረክ ስም ይኖርሃል፣ ትደመጣለህ። 

አንዳንዴ ከጠላትም ቢሆን ጠንካራ ጎኑን አይቶ መማር ብልህነት ነው። የህወሃት ታጋዮች ለድረጅትና ለድርጅታዊ ዴሲፕሊን ያላቸው አቋም እጅግ የሚገርም ነው። እያንዳንዱ የዐማራ ፋኖ ታጋይ ከዚህ ሊማር ይገባዋል። 

ያለ ጠንካራ አመራር፣ አታጋይ መሪ ድርጅት እና ድርጅታዊ ዴሲፕሊን የፈለገ ጠንካራ ብትሆን፣ በሚልየን የሚቆጠር ታጋይ ቢኖርህ እመነኝ የትም አትደርስም። እንኳን አራት ኪሎ አራት ኪሎሜትር በፅናት መጓዝ አትችልም። 

ማንም ይምራው ፡ ድርጅት ግን ይኑርህ! ማንም ይሁን ፡መሪ ግን ይኑርህ! ምንም አይኑርህ ፡ድርጅታዊ ዴሲፕሊን ግን ይኑርህ! ሌላው በሙሉ በውስጣዊ ግምገማና በሚወሰዱ ማሻሻያዎች በሂደት እየተስተካከለ ፣ እየነጠረ ፣ እየጠነከረ ይሄዳል። 

የዐማራ ህዝብ ጠላቶች ይህ ምስጢር ስለገባቸው ላለፉት ሃምሳ በላይ አመታት የዐማራ ህዝብ ጠንካራ መሪ እና አታጋይ ድርጅት እንዳይኖረው ጠንክረው ሰርተዋል። ይህ በመሆኑ የህወሀት አመራሮች “የዐማራን ህዝብ አከርካሪውን ሰብረነዋል” ብለው በአደባባይ በኩራት እስከመናገር ደርሰው ነበር። 

ኦህዴድ/ኦነግም “የአማራን ህዝብ ሱሪውን እናስወልቀዋለን” ብለው በእብሪት ለመደንፋት የበቁት የዐማራን ህዝብ ዝርው ሆኖ ያለ ጠንካራ አመራር እና አታጋይ ድርጅት ተበትኖ ስላገኙት ነበር። 

የዐማራ እናት ማህፀን የለመለመ ይሁንና ሱሪ ሊያስወልቅ የመጣው የአብይ አህመድ ዙፋን ጠባቂ እንኩቶ ሰራዊት በዐማራ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች በሁሉም የዐማራ ግዛቶች ሱሪውን እያወለቀ እየተገረፈ ይገኛል። 

ገብቶህ ከሆነ እስክንድር ስቅላት የተፈረደበት ለዚህ ነው! ሁሌም ቢሆን የእስክንድር ነጋ ጥፋቱ ቀድሞ መንቃቱ ነው! የዐማራን ፋኖ ማደራጀቱ፣ የዐማራን ህዝብ  የድርጅት ባለቤት ማድረጉ ነው! 

እና የዐማራ ህዝብ ሆይ እስክንድር ይሰቀል? 

እስክንድር ቢሰቀል ትድን ይሆን? ለማን ተላልፎ ይሰጥ? ለአብይ አህመድ ወይስ ለዘመነ ካሴ?

ከላይ እንደተገለፀው የአዲስ አበባ ህዝብ እስክንድር ነጋ ብቻውን ባንዲራ ይዞ ሲንከራተት “መቃወም የማይሰለቸው፣ ጭር ሲል የማይወድ፣ ድከም ያለው ፣ እብድ” ይለው ነበር። በወቅቱ ከጥቂቶች በቀር ከአጠገቡ ደግፎት የሚቆም አልነበረም። ሁሉም በሚባል ደረጃ በአብይ አህመድ ፍቅር ሰክሮ የጫጉላ ሽርሽር ላይ ነበር። 

እስክንድርም የሚሰማው ቢያጣ የልባቸው እንዲሞላ ገለል አለላቸው። የአዲስ አበባ ህዝብ እውን አለፈለት? ሰላም አገኘ? አሁን ማነው ያበደው? እስክንድር ወይስ እብድ ሲለው የነበረው አዲስ አበቤ? 

ነፍሱን ይማርና ጀነራል አሳምነው ፅጌንም በተመሳሳይ “የዐማራ ህዝብ የተጋረጠበት ፈተና ከ16ኛው ክፍለዘመን የከፋ ነው፣ አማራ ሆይ ተደራጅ” እያለ ሲጮህ “እብድ ነው” የሚለው ዐማራ ነበረ! ታዲያ አሁን ማነው እብዱ? 

ይህ እፉኝት የሆነ ትውልድ ታዲያ አሁን መሪውን ካስበላ በኋላ በቁጭት ብቻውን ያንጎራጉራል፣ በየመሸታ ቤቱ ስሙን እየጠራ ይፎክራል፣ ያቅራራል፣ ግጥም እየገጠመ ይዘፍናል! እስክስታ ይወርዳል! ነገር ግን ሰሁን ድረስ ይህ ከመቆጨትና ከመብሰልሰል አላዳነውም! 

ስለዚህ ካላበድክ በስተቀር መሪህን አትብላ፣ ልጅህንም አታስበላ ። ካላበድክ በስተቀር ድርጅትህን አታፍርስ፣ እያየህ አታስፈርስ። ጠላቶችህ እንደሆን ካላጠፉህ እንቅልፍ የላቸውም። ካልነቃህ በቁምህ ያፈርሱሃል! አንድ በአንድ እየነጠሉ ይበሉሃል። 

የዐማራ ህዝብ ሆይ ምንም ይሁን ድርጅትህን፣  ማንም ይሁን መሪህን ጠብቅ!!!

@Dagmawit Getaneh

 

 

 

 

 

Filed in: Amharic