>
5:42 pm - Sunday March 21, 1069

መሣይና - መሣዮቹ

መሣይና – መሣዮቹ

 

ይህ ሁሉ መታተር፣ መንፈራገጥ የአማራን ሕብረት ከልብ የመመሥረት ዓላማ ቢሆን ብዕሬን አላነሳም ነበር። ነገር ግን የተመሠረተው ማኅበር የተመሠረተን ድርጅት ለማፍረስ የተመሠረተ ማህበር ስለሆነ ብቻና – ብቻ ነው ለመጻፍ የተገደድኩት።ይሄውም አ ፋ ሕ ድ (አማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት) ን ለማፍረስ የተቋቋመ ማሕበር መሆኑን ስለተረዳሁኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች ይሄንን ሳይረዱ ቀርተውት አይደለም። ቢያንስ ግን እንዳወቅንባቸው ለታሪክም ቢሆን መቀመጥ ስላለበት ነው እየጫርኩ ያለሁት።

ዶሮን ሲያታልሏት ”ውኃውን እያፍለቀለቅን የምናሞቀው ገላሽን ለማጠብ  ነው” አሏት አሉ። በታጋዮቹ ደም ”ዱር ቤቴ” ብለው  መምህርነታቸውን፣ ምሕንድስናቸውን፣ ተማሪነታቸውን በአጠቅላይ እንቡጥ ወጣትነታቸውንና ነፍሥያቸውን  ለመስጠት የወጡትን አምሐራዎች ”መሰረትን” ብለው ያቋቋሙላቸው ማህበር ለዶሮዋ እንደሞቀው ውሃ መገደያቸው እና መታረጃቸው፣ መሆኑን ልብ ለማሰኘት፤ ለማስመር መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።

ይህ ”አማራ ዓለም አቀፍ ትብብር” ምሥረታ የሚል የዳቦ ስም የተሰጠው፤ ለአማራውና ለኢትዮጵያ የሚታገሉት ግለሰቦችንና ቡድኖችን ባሉት የማሕበራዊ ሚዲያዎች ሲያወግዙ የነበሩ ሰዎች ባለፉት ስምንት ወራት በዝግ ስብሰባ፣ ማለትም በዙምና በ”ዋትዝ -አፕ” ግሩፓቸው ሲዶልቱ፤ ሲያመነዥጉ እና ሲያሳልጡ ከቆዩ በኋላ በትላንትናው ዕለት በግልፅ ለመሰየም (ለመከሠት) የቻሉት። የዩቱብ ቻናላቸው ተዘግቶባቸውም ሆነ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ በማይሰጥበት ጣቢያቸው ነው ‘ገጭ’ ያሉብን። አንከር በተባለው የቱሪናፋ መስኮታቸው።

ይህን ከማለታቸው ወይም ከማወጃቸው በፊት ግን ባዋቀሩት የሚዲያ ሰዎቻቸው፣ ቻናሎቻቸው የተቻላቸውን ሁሉ የስም ማጥፋትና የማጠልሸት ዘመቻ ሲያደርጉ ነበረ።

”ትግላችን በዕውነትና በውሸት መሐል ነው።”
ኮሎኔል ፋንታሁን ሙሐቤ

ይህ ”የአማራ ዓለም አቀፍ ትብብር ”ተመሰረተ ብለው በፊት-ለፊት የተከሠቱት፤ የብአዴንና የግንቦት ሠባቶች ስብስብ ወይም ጥርቅም ናቸው። ለአብነት ያህል  በዚሁ በተከሰቱበት መስኮት በቅድሚያ የማሕበሩ (የድርጅቱ) ሕዝብ ግንኙነት ተብሎ የተሾመው   (የተሰየመው)  መሥፍን አማን በ1997 ዓም ቅንጅትን ከብርሐኑ ነጋ ጋር አፍርሰውት (እንደ አሞሌ ጨው በትነውት) ከወጡት አንዱም ይገኝበታል።

በአውሮፕላን አሸኛኘት ተደርጎለት በኔዘርላንድ አምስተርዳም ኑሮውን ያደረገውንና፤ ለውጥ በተባለው ጊዜም አብይ አህመድ የዲያስፖራ ሰዎችን በአዳራሽ ሰብስቦ በነበረበት ጊዜ ከዚሁ አገር ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ ለሰበሰባቸው ‘አብይ’ ውዳሴ ከንቱ ሲያቀርብ የነበረው ግለሰብን ‘አፍ’  በማድረግ ነው የማህበሩ ምሥረታ የታወጀው። ልብ- በሉ እስካሁን ማህበሩ በዓየር ላይ ነው። የፕሮፓጋንዳ ማሺኑን ወይም ጋኑን ነው ከእርሾ ጋር   ያስቀመጡት።

ስብስባቸው ሁሉ ይገርማል፣ ያናድዳል። ያበሽቃልም። የብአዴን አንጋፋዎቹ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ትንግርቱ ፣ ሙሉጌታ አንበርብር …ወዘተ። (ስማቸውን ከዚህ በላይ መጥራት አልፈልግም።  በደም የሚጫወቱ ሰዎች ያቅለሸልሹኛል። ይሸክኩኛል።) በዕውነቱ እነዚህ ስብስቦች በሜዳ ላይ በድሮን ስለሚጨፈጨፈው ማሕበረሰብ፣ በአብይ አህመድ ወታደሮች ስለሚንገላቱት ሕጻናት አዛውንት አረጋውያንና መሰሎች ዴንታ አይሰጣቸውም።በደማቸው ሲቆምሩ አለመሸማቀቃቸው በዲያስፖራ ያለነውን ሰዎችንም እንደምንታዘባቸው  ቢያውቁም  እንኳን  ንቀታቸው በአያሌው ያበግናል።

የግንቦት ሰባት አባላቶች ከሚግና ከሮኬት በፈጠነ መልኩ ነው የአማራውን ያጎመራ ትግል የተቀላቀሉት። የተፈታተኑት። እየገዘገዙ ያሉት። ብአዴንና ግንቦት ሰባት የተባሉ የ”ፖለቲካ ሙጄሌዎች” የአማራውን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የሚታትሩ ግለሰቦችን አጥፍተዋል። ቡድኖችን አክስመዋል። ታታሪ ግለሰቦችን ያለስማቸው ስም በመስጠት አጠልሽተዋል። አሸማቀዋል።

በፖለቲካ አንድም ነገር በአጋጣሚ የሚሆን  የለም። በዕቅድ እንጂ።ግንቦት ሰባት በተመሰረተ በአንድ ዓመቱ ነበረ ፤ ለአባላቶቹና ደጋፊዎቹ  ‘‘አዲስ አበባ ስንገባ በትሪቩንና በጥላ ፎቅ ትቀመጣላችሁ” በማለት በአውሮፓና አሜሪካ ላሉ አባላቶቹ አምስት – አምስት መቶ ዩሮና፣ ዶላር ሲሰበስብ የነበረው። ከአስር ዓመት በኋላ በተዘጋጀለት ስፍራ እንደሚገባ ያውቀው ነበርና። በትግል ሳይሆን  ከኢሕአዴግና ኢትዮጵያን ከሚዘውሯት የውጭ ኃይሎች ጋር በጥቅሴ ይሰራ ነበርና። ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ ማሰላሰል ትችላላችሁ። ዘመነ ካሤ ከብአዴን ወጥቶ ወደ ግንቦት ሰባት ሲቀላቀል በ”አጋጣሚ” ነው ካልከኝ ይሁንልህ።ታታሪው የሬዲዮ ጋዜጠኛ ደምሥ በለጠ በግንቦት ሰባት ላይ የሰላ ትች ት ብቻ በማቅረቡ በለውጡ ማግሥት አገር አማን ነው ብሎ በገባ በሶስተኛው ቀኑ መገደሉ ላይ የግንቦት ሰባት እጅ የለበትም ካልከኝም የራስህ ጉዳይ። ሌላም ሌላም ማቅረብ ይቻላል።

እንደምታውቁት ግንቦት ሰባት በኤርትራ ፍየሎች ሲጠብቁና እነ ኤፍሬም ማዴቦም ከኒያላ ሆቴል ሆነው  በሚጽፉት ድርሠት ”ከዋርካው ስር …ከወንዙ አጠገብ ከታጠረው ምሽግ” እያሉ ዘበዘባ  ሲያስነብቡን የነበረው የሩቅ ጊዜ ትዝታችን አይደለም። የቅርብ እንጂ።

አሁንም ብርሐኑ ነጋ እና ብአዴን ያዋቀረው የድርጅት ስራና የኔት- ወርክ በፀበል ወይም በፀሎት እንጂ በቀላሉ የሚለቅ ሙጀሌ አይደለም። በውጭ ሐገራት ያሉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች ”ዲሞክራሲያዊ ቼንጅ” በሚባል የግንቦት ሰባት መዋቅሮች ለመጠለፉ ብዙ ማሳያዎች ማቀረብ ይቻላል። ሌላም – ሌላም። ነገር ግን ከላይ ኮሎኔሉ እንዳሉት ትግሉ ”በውሸትና  በዕውነት” መካከል በመሆኑና የመጨረሻ አሸናፊውም ዕውነት ነውና ትግሉ መርዘሙ፣ መወሳሰቡ እርግጥ ነው። 

በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው አማራውን ምልክት ለማሣጣት ታትረው እየሰሩ ነው። የእስክንድር ነጋ በረሐ መውረድ የደም ነጋዴዎችን እንቅልፍ ነስቷቸዋል። መዐዛ መሐመድ ኑሮዋን በአማራ ደም ካደረገች ቆይታለች። ሸዋ ሮቢት ወይም ጎጃም ወይም ጎንደር መሰደድ የሚገባቸው የሚዲያ ሰዎች ‘‘በአገዛዙ በደል ደረሰብን” ብለው ጉዟቸውን ያደረጉት፥ (የከተሙት) ዑጋንዳ – ካምፖላ ነው። ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ ነው። በዕውነቱ የመረረው ሰው በአቅራቢያው ያለን ትግል ይቀላቀላል እንጂ፤ ዑጋሊና ኡፉ ለመብላት ኪሱሐሊ ተናጋሪ የጎረቤት አገሮችን አይቀላቀልም።  ነገር ግን በከተሙበት ዑጋንዳ ውስጥ ሆነው ለትግል በወጣው ፋኖ ላይ በአፋቸው ሲፀዳዱ፣ ሲያቀረሹ ይውላሉ። አሣዬ ደርቤ የሚባል ወሽከንቱን ማንሳቱ በቂ ነው። ይህ ከጀርባቸው ድጋፍ እንዳላቸው የሚያጠያይቅ አይደለም።

የሲ አይ ኤው ”ጎግልና ዩቲዩብ” ጥሩ ድጋፍም ያደርግላቸዋል። እንደልባቸው ያቀረሻሉ። ነገር ግን ቻናሎቻቸው አይዘጋም። በምትኩ ለታጋዮቹ አንደበት ሆነው የሚያገለግሉት ወይም የድርሻቸውን እየተወጡ ያሉት ኢትዮ 360 ጣና ቲቪና አዲስ ድምጽ በየዕለቱ በመዶሻ ሲቀጠቀጡ ከአየር ላይ ሲወርዱ እየተመለከትን ነው።  ትግሉ የህልውና ብቻ ሳይሆን፤ በውሸትና በዕውነት መካከል ነውና በዕውነቱ ከባድ ነው።

በምድር ያሉት ታጋዮች ማለትም ፋኖዎቹ በአለት ላይ የተመሰረት በቀላሉ የማይፈርስ ድርጅት እንደመሰረቱ ሰምተናል። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ያቃዣል። ትግሉንም ከበድ ያደርገዋል። ቅን አሳቢዎች አ ፋ ሕ ድ  (የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን) መደገፍ መርዳት የሚጠበቅባቸው ጊዜ አሁን ነው። ትግሉ በውሸትና በዕውነት መካከል ነውና ።

መሣይና – መሣዮችም የሚመራመር አድማጭ፣ የሚያገናዝብ ተመልካች ፣ ግራ – ቀኝ የሚያይና የሚያስተውል ማኅበረሰብ  እስከሚመጣ  በደም ገንዘብ መክበራቸው፣ እያየናቸው መፋፋታቸውም ይቀጥላል። መፋፋት ደግሞ ማበጥ ነው። ማበጥ ደግሞ መፈንዳቱ አይቀርም። 

 

 

ይቀጥላል

Email:

ግርማ እንድሪያስ ሙላት

ethreference@gmail.com

 

 

Filed in: Amharic