>
5:42 pm - Thursday March 21, 6909

"አዲስ ትውልድ" ፣ "አዲስ አስተሳሰብ" ፣"አዲስ ተሰፋ" ? ተግባርና ቃል ለየቅል! 

“አዲስ ትውልድ” ፣ “አዲስ አስተሳሰብ” ፣”አዲስ ተሰፋ” ?

ተግባርና ቃል ለየቅል! 

ማነው “አዲስ ትውልድ” ? ዘመነ ካሴ? አስረስ ማረ? ማርሸት ፀሃዩ ወይስ አበበ ፈንቴ? 

ለመሆኑ ከነዚህ ግለሰቦች “አዲስ አስተሳሰብ” ሊፈልቅ ይችለል? የሚገኝ “አዲስ ተስፋስ” ይኖር ይሆን? 

እስቲ በተግባር እንፈትሻቸው!

ብአዴን የዐማራውን ማህበረሰብ ለህወሃት ለማስገበር የተለያዩ የማህበረሰብ አደረጃጀቶችን ተጠቅሟል። አንዳንድ ሆድ አደር የዐማራ ወጣቶችም በብአዴን ወጣት ሊግ ተደራጅተው ስርዓቱን በትጋት አገልግለዋል።  

የዘመነ ካሴ፣ አስረስ ማረ፣ ማርሸት ፀሃዩ እና አበበ ፈንቴ የፓለቲካ ህይወት የሚጀምረው የህወሃት የበኩር ልጅ በሆነው ብአዴን ቤት በተላላኪነት ነው። እነዚህ የብአዴን ወጣት ሊግ አባላት እንደማንኛውም አባል የህወሃትን አስተምህሮ በብአዴን ቤት ገና በልጅነታቸው በጡጦ በደንብ ተግተዋል፣ በካድሬነትም በታማኝነት አቤት ፣ ወዴት ፣ ቁጭ ፣ ብድግ ብለው አገልግለዋል። 

ብአዴን ዐማራን በራሱ ልጆች ለመታገል ህወሃት ከሆዳም አማሮች ጠፍጥፋ በልኳ ለተልዕኮ ማስፈፀምያ የሰራችው ተላላኪ ድርጅት ነው። ይህን የሆዳም ዐማራዎች ስብስብ በመጠቀም ህወሃት በርካታ ጉዳዮቿን አዲስ አበባ ተቀመጣ በቀላሉ ሎሌዎቿን በማሰማራት አስፈፅማለች። 

ለምሳሌ ያክል

1ኛ. የዐማራን ታሪካዊ ግዛቶች የሚበቃትን ያህል ዘርፋለች። ለሌሎች አድላለች። ህወሃት ከዘረፈችው የወልቃይት እና የራያ መሬቶች ባሻገር የግጨውን መሬት በደስታ ፈርሞ ለትግራይ ያስረከበው እውቁ ሆዳም አማራ የብአዴኑ ገዱ አንዳርጋቸው ነበረ። 

2ኛ. “ዐማራ ጨቋኝ” እንደነበረና ሌሎችን ብሔረሰቦች ከዐማራ ቅኝ ግዛት ነፃ እንዳወጣች የሚያሳይ ” ህገ መንግስት” አርቅቃ፣ አስፀድቃ፣ “የብዐዴን ዐማሮች” እየዞሩ በራሳቸው አንደበት እንዲ ያስተምሩ አድርጋለች

3ኛ. ኤርትራ ድረስ ተጉዘው በዐማራ ህዝብ ስም ለተፈፀመው “በደል” ኤርትራውያንን ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርጋለች።

4ኛ. የዐማራ ህዝብ በጀት ተቀንሶ በዐማራ ለተጨቆኑ እንደትግራይ ላሉ ክልሎች በፌደሬሽን ም/ቤት በሚሰራ ቀመር እንዲሰጥ አድርጋለች። 

5ኛ. የዐማራ ህዝብ ቁጥር systematically እንዲቀንስ (በበሽታ፣ በወሊድ መቆጣጠሪያ ፣በማምከኛ መድሃኒት፣ በርሃብ፣ በድህነት) ብአዴን ተባብሮ ሰርቷል።

6ኛ. ማህበራዊ ተቋማት ጤና ፣ ትምህርት፣ መንገድ፣ ኤሌትሪካ ፣ የመስኖና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የእርሻና የኢንዳሰትሪ ግብአቶች እንዳያገኝ ክልሉ እንዳያድግ እና በኢኮኖሚ እንዲደቅ በትኩረት ብአዴን አብሮ ሰርቷል። 

7ኛ. የዐማራው ማህበረሰብ ከትምህርት፣ ከሃብት እና ከስልጣን እንዲገለል ብአዴን አስፈፃሚነት ታቅዶ ተሰርቷል። 

8ኛ. የዐማራ ማህበረሰብ ከሌሎች የሃገሪቱ ክልሎች እንዲፈናቀል፣ ንብረቱ እንዲወድም፣ እንዲሰደድ፣ እንዲገደል በብአዴን ተባባሪነት ተደርጓል። “ከክልሉ ውጭ ያለ ዐማራ የምንታገለው እንጂ የምንታገልለት አይደለም! ” የሚል አቋም አላቸው ብአዴናውያን። በጣም የሚገርመው ሀረር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ “ከክልሉ ውጭ ያለ ዐማራ መሬታችሁን ለመቀራመት የመጣ ወራሪ ነው!” የሚል አደገኛ ንግግር ያደረገው የቀድሞው ጠ/ሚ ብአዴኑ ታምራት ላይኔ ነበር። ከዚህ ንግግር በኋላ በበደኖ፣ በወተር፣ በአቦምሳ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በወለጋ፣ በኢሉባቦር፣ በአጠቃላይ በበርካታ የደቡብ፣አኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል አካባቢዎች ዐማራ በገፍ ታረደ፣ ተፈናቀለ ፣ ለዘመናት ያፈራውን ንብረት እና የኖረበትን ቀየ ጥሎ እግሩ ወደመራው መንገድ ተሰደደ። ተንከራተተ፣ ለማኝ ሆነ! ይህ ሁሉ ሲሆን ብአዴን ዐማራው ቀና ሲል አናት አናቱን እያለ እየወረደበት ያለውን መአት በፀጋ አሜን ብሎ እንዲቀበል፣ ይህቺን ታክል ነፃነት ተቸሮት እየኖረ ያለው በነሱ ተጋድሎና ቸርነት መሆኑን፣ በዚህም የዐማራ ህዝብ የሀገሪቱ ልማት ተጠቃሚ እንደሆነ፣ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀና ብሎ መሄድ እንደቻለ፣  በኩራት ይናገሩ ነበር። 

9ኛ. በተደረጉ ሁሉም ሀገር አቀፍ “ምርጫዎች” ኮሮጆ በመገልበጥ ስርአቱ አሸናፊ ሆኖ እንዲቀጥል ብአዴናውያን ተግተው ሰርተዋል። 

10ኛ. በክልሉ የተፈፀሙ ሁሉንም ወንጀሎችን፣ እስራቶችን፣ ቶርቸር፣ ሰብአዊ መብት ጥሰትና አሰቃቂ ግድያዎችን መርተዋል፣ ፈፅመዋል ፣ አስፈፅመዋል። 

እነዚህ የብአዴን ወጣት ሊግ አባላት ፡ ዐማራ ሆኖ ላለፉት ሰላሳ በላይ ዓመታት በተላላኪነት ዐማራን ሲታገል  ለነበረ ድርጅት በፈቃደኝነት ፈርመው፣ ታማኝ አባል እና አገልጋይ ሆነው ፣ ከዐማራ ተወልደው ዐማራን ሲታገሉ ፣ ዐማራን ሲያደሙ፣ ዐማራ መቃብር ፈንቅሎ እንዳይነሳ የዐማራን መቃብር ሌሊት እና ቀን በታማኝነት ሲጠብቁ ኖረዋል። የድርጅቱን አስተሳሰብ ተሸክመዋል፤ ፈፅመዋል ፣ አስፈፅመዋል። እነዚህ በፕሮፌሰር አስራት አጠራር “ሆዳም ዐማሮች” ወገናቸውን አስይዘው ቁማር ተጫውተዋል ፣  ከህወሃት ጋር ተሰልፈው ከዐማራ ተወልደው ዐማራ ቀና ብሎ እንዳይሄድ አድርገዋል። 

ለአጭር ጊዜ ከዚህ ድርጅት ተለይቶ የነበረው ዘመነ ካሴ ደግሞ ወደ ኤርትራ በረሃ ሄዶ ” ዐማራ የሚባል ብሔረሰብ የለም” ብለው ከሚያስቡ እና ዐማራን አምርረው ከሚጠሉ እነደ አንዳርጋቸው ፅጌ እና ብርሃኑ ነጋ ካሉ ግለሰቦች ጋር ተሰልፎ ነበር። በጣም የሚያስገርመው ይህ ግለሰብ ከኤርትራ በረሃ ተመልሶ ውሻ ወደ ትፋቱ  ፣ አሳማም ታጥቦ ወደጭቃ እንደሚመለስ ዳግመኛ ለብአዴን ለመጫወት ከግንቦት 7 ወጥቶ ዋጋ ቀንሶ በድጋሚ ለብአዴን መፈረሙ ነው። አቤት አክሮባት? ስንቴ ተገለበጠ ጃል? 

የሁለቱን ድርጅቶች የኋላ ታሪክ በመመልከት ብቻ ዘመነ ካሴ የዐማራ ታጋይ እንዳልነበረ መገመት አያዳግትም! ከሆድና ከስልጣን ያለፈ ህልም አልነበረውም ዛሬም የለውም! 

በኔ እምነት ዘመነ ካሴ፣ አስረስ ማረ ፣ ማርሸት ፀሃዪ እና አበበ ፈንቴ “የአዲስ ትውልድ” ማሳያ መሆን አይችሉም። ምክንያቱም የአሮጊቷ ህወሃት/ ብአዴን አሮጌ አስተሳሰብ ተሸካሚ ናቸውና። 

ለመሆኑ ከነዚህ ግለሰቦች አዲስና የዐማራን ህዝብ የሚያሻግር አስተሳሰብ መጠበቅ ይቻላል? እስቲ አንዳንድ ማሳያዎች እንመልከት። 

ህወሃትም ሆነ የበኩር ልጇ ብአዴን የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም / ideology አብየታዊ ዴሞክረሲ ነው። አብዮታዊ ዲሞክረሲ ደግሞ በባህሪው ሌሎች የተለዪ እሳቤዎችን አያስተናግድም፣ እንዲኖሩም በፍፁም አይፈቅድም። የተለየ ሃሳብ የመቀበልና የማስተናገድ ባህል ስለሌለው፣ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች በማሰር ፣ በማሳደድ ፣ በመግደልም ጭምር ሃሳቡን ከምድረገጽ በማስወገድ ያምናል። 

የብአዴን ወጣት ሊግ አባላት ከብአዴን ቤት የወረሱት ርዕዮት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው። ለዚህ ማሳያ ገና በጠዋቱ የተለየ ሃሳብ እና አመለካከት ያላቸውን ፋኖዎች እና የፋኖ አመራሮችን አስረዋል፣ አሳደዋል፣ በይፋ  በጠላትነት ፈርጀዋል። ጦር አዝምተው ወግተዋል። 

የማሰብ፣ የመናገር እና የመደራጀት ነፃነት ላይ ያላቸውን አቋም ይመለከታል። የብአዴን ወጣት ሊግ አባላት ከነሱ የተለየ ሃሳብ እንዲኖር አይፈቅዱም። የተለየ ሃሳብ ማራመድ አይደለም ማሰብ አይፈቅዱም! 

ለምሳሌ ጋዜጠኛ ወግደረስ ጤናው ፣ ዶ/ር እንዳላማው ፣ኮሎኔል ጌታሁን፣ አርበኛ ማስረሻ ሰጤ እንዲሁም ሌሎች በርካቶች በነፃ የማሰብና የመናገር እንዲሁም በፈለጉት አደረጃጀት የመሳተፍ ነፃነታቸው ተደፍሯል። ታሰረዋል፣ ተሳደዋል፣ የተገድሉም እንዳሉ ታውቋል።

በመሆኑም የብአዴን ወጣት ሊግ አባላት እንደገና ተጠፍጥፈው ቢሰሩም ስለ ዲሞክረሲ እና ስለ ሰው ልጆች የማሰብ ነፃነት ሊረዱ አይችሉም! 

ብአዴንም የተለየ ሃሳብ የነበራቸውን ሰዎች ያስር፣ ያሳድድ፣ ይገድል ነበር። ስለዚህ ያሳያችሁን “አዲስ አስተሳሰብ” የለም! 

ከዚህ ይልቅ “አዲሱ ትውልድ ሊኖረው የሚገባ አዲስ አስተሳሰብ ” የተለየ አመለካከት ያለውን ሰው በበለጠ ሃሳብ በመሞገት ፣ በማሳመን ፣ መመለስ ወይም የአመለካከት ልዪነትን ተቀብሎ ልዪነቶችን አክብሮ በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመስራትን ባህል ማዳበር መሆን ነበረበት።   

በዘመናዊ እሳቤ የሃሳብ ልዩነት ሊፈታ የሚችለው በሰለጠነ ንግግር እና ውይይት ብቻ ነው። ሰዎችን በማሰር፣ በማሳደድና በመግደል፣ “በእሳት በማቃጠል” ፣ አሳቢውን በማጥፋት ሃሳብን ማክሰምና ማሸነፍ አይቻልም።

የማሰብ ነፃነትን፣ ሰብዓዊነትን፣ ዴሞክረሲን፣ ውይይትንና የሃሳብ የበላይነትን በጫካ እያለ ያልተለማመደ ፋኖም ሆነ የፋኖ አመራር ወደ ስልጣን ሲመጣ ዴሞክረሲንና እና ሰብዓዊ መብቶችን የሚጨፈልቅ አምባገነን ስርዓት የሚያዋልድ ፣ የህዝብ ፣ የነፃነት እና የሀገር ህልውና ስጋት እንደሚሆን ለመገመት ነብይ መሆን አይጠይቅም። 

አሮጌ ሃሳብ ተሸክሞ አዲስ ትውልድ መሆን አይቻልም። አሮጌ ሃሳብ ከተሸከመ ትውልድ  የሚገኝ ተስፋ የለም! 

በ21ኛው ክፍለዘመን ሰው ከሃሳብም በሚበልጥ ሌላ ሃሳብ ተነጋግሮ ይተማመናል ፣ ካልሆነም ልዩነቱ ተከብሮለት ከነልዩነቱ ተከብሮ ይኖራል ። የሃሳብ ልዩነት ጠላትነት አይደለም! 

ሁለተኛው ማሳያ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ፣ ለውጤቱ ምንም ይሁን ምን የብዙሃንን ፍላጎት ማክበር፣ ለውጤቱም  የመገዛት ባህል አለመኖር። 

ሲጀመር በብአዴን ቤት ኮሮጆ እንዴት እንደሚገለበጥ ፣ የሀሰት ትርክት እንዴት እንደሚፈበረክ፣ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንዴት እንደሚሰራና እንደሚሰራጭ፣ ሰዎችን እንዴት ጥላሸት መቀባት እና መወንጀል እንደሚቻል፣ ህዝብን እንዴት ማደናገር እና ማሳመን እንደሚቻል በተግባር ሰልጥነው ብአዴን ከአምስት ጊዜ በላይ በዐማራ ክልል ሲያሸንፍ ኮሮጆ ሲገለብጡ እና ኮሮጆ ሲያስገለብጡ ኑረው ስለ ዴሞክረሲ፣ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ፣ የሀሳብ እና የህግ የበላይነት ሊረዱ በፍፁም አይችሉም! እነዚህ ግለሰቦች ስልጣን በማጭበርበር፣ በማደናገር፣ በጉልበትና በኮሮጆ ግልበጣ ብቻ እንደሚገኝ ነው የሚያውቁት/ የሚያምኑት። 

 ለዚህ ነው የዐማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ሰብሳቢ ሲመረጥ ሁለት ጊዜ ምርጫ ተደርጎ ሁለት ጊዜ በአብላጫ ድምፅ በተሸነፉበት ወቅት ውጤቱን በፀጋ በመቀበል የብዙሃንን ድምፅ ለመቀበል የተቸገሩት! በብአዴን አስተምህሮ ምርጫን እንደምንም አድርገህ ታሸንፋለህ እንጂ መሸነፍ አይታሰብም! ብትሸነፍም ኮሮጆ ገልብጠህ ማሸነፍ ፣ አሸናፊውን ማሸማቀቅ፣ ደጋፊዎችን መፈረጅ፣ ማሰር፣ ማሳደድ፣ መግደል፣ ደብዛውን ማጥፋት የተለመዱ ተግባራት ናቸው። 

አፈትልኮ ከወጣ የስልክ ልውውጥ መረዳት እንደሚቻለው ከምርጫው በፊት የኮሚቴው ሰብሳቢ የነበረው ማርሸት ፀሃዩ ከአሰግድ መኮንን ጋር ባደረገው የስልክ ንግግር እንዴት ምርጫውን ማሸነፍ የሚችሉበትን ሴራ ጎንጉነው፣ እቅድ አዘጋጅተው ፣ አማራጭ እቅዶች አስቀምጠው ወደምርጫ እንደገቡ ለማወቅ ተችሏል። 

ይሁንና እቅዱ በጠበቁት መልክ ሊሰራ አልቻለም፣ እነሱም ከመሸነፍ አላመለጡም። ሆኖም ግን የሚገለበጥ ኮሮጆ ስላልተገኘ አይናቸውን በጨው አጥበው ከምርጫው ራሳችንን አግልለናል  አሉ። የምርጫውን ውጤት ውድቅ አደረጉ። 

ከዚያም ወደተካኑበት እና ጥርሳቸውን ወደነቀሉበት የሴራ ፓለቲካ ሰተት ብለው ገቡ ። “እስክንድር ምርጫውን በዶላር ገዛው” ፣ “እስክንድር የዐማራ ፋኖ አንድነት እንቅፋት ነው” ወዘተ የሚሉ የሃሰት ትርክቶች/ False Narratives ፈበረኩ፣ ድርጅቱን ወደማጣጣል፣ የዐማራ ፋኖ አመራሮችንና ግለሰቦችን ወደ መፈረጅ/labeling ፣ ስም ማጠልሸት እና ጭቃ መቀባት  / Character assassination ሚዲያ ቀጥረው፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተሳዳቢ ግሪሳ አሰማርተው ሰፊ የማደናገር ስራ ሰሩ።  

ከነሱ ጋር ያልተሰለፉትን የፋኖ አመራሮች በማዋከብ ፣ በገንዘብና በጥቅማጥቅም በመደለል አስኮበለሉ ፣ ሰርጎ ገቦችንና የውስጥ ባንዳዎችን በመቅጠር የፋኖ አደረጃጀቶችን ለማፍረስ ማሰኑ፣ አንዳንድ የፋኖ አመራሮችን ለማስገደል ብዙ ሙከራዎች አደረጉ። የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን ለማፍረስ ብዙ ጉድጓድ ቆፈሩ። በመጨረሻም በቆፈሩት ጉድጓድ ገብተው አሁን ማጣፊያው አጥሯቸዋል፣ መውጫው ጠፍቷቸዋል። 

ሌላው ሶስተኛው መገለጫ ግትልትል ውሸት በአደባባይ በሚዲያ መዋሸትና የገለሰቦችን ስም ማጠልሸት።  ለምሳሌ

“በዚህ ምድር ላይ እኔና እስክንድር እንኳን ብንቀር አንጣለም። በእኔና በእስክንድር መካከል ያሉት ማርያም እና ልጇ ነቸው።” ዘመነ ካሴ

” እስክንድር ነጋ እኔ ለዐማራው እንደ ስብሃት ነጋ ነኝ ይላል” አስረስ ማረ

” እስክንድር ከመንግስት ጋር ድርድር ማድረጉን በEthio360 ላይ ተናግሯል” ማርሸት ፀሃዩ

ይህ ቆሻሻ መንገድ የት ያደርሳል? ይህ የወረደ አስተሳሰብስ እንዴት “አዲስ አስተሳሰብ” ተብሎ በሚያምሩ ቃላት ይጠራል? ይህ የመከነ ትውልድ እንዴት “አዲስ ትውልድ ” የሚል ያማረ መጠሪያ ይሰጠዋል? በዚህ የሚደናገር ካለ ሳያላምጥ የሚውጥ ጭፍን ደጋፊና ራሳቸው ብቻ ናቸው!

@dagmawit Getaneh

 

Filed in: Amharic