>
5:42 pm - Thursday March 21, 3472

የአፋሕድ አንበሳ ሲያገሳ ፣ ምድረ ሰገጤ ተንጫጫሳ

የአፋሕድ አንበሳ ሲያገሳ ፣ ምድረ ሰገጤ ተንጫጫሳ

 

ሃይሉ አስራት

 

ሰገጤ ምን ማለት ነው ለምትሉ ሰገጤ የማይገባው፣ የማይገባው (ሁለተኛው ገ ይጠብቃል) ማለት ነው፡፡ በትንሹ ፖለቲካ፣ የአማራ ትግል፣ የኢትዮጵያዊነት ውስብስብነት፣ የተዋህዶ ኦርቶደክሳዊነት ጠላቶችን ጠንቅቆ የማይረዳ ማለት ነው፡፡ ባጭሩ በፖለቲካ ድስት ሲቀቀል ቢውል የማይበስል ማለት ነው፡፡ ባለፉት ሰላሳ አራት ዓመታት ሰገጤ በሚባለው የሕብረተሰብ ክፍል የተሞሉ በተለይ ወያኔ-አሕዴግ-ብልጽግና በሚባሉ የግብርና ሜንታሊቲ ያላቸው ሰዎች የተደራጁና የተዋቀሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ተግተልትለው የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ በመቆጣጠራቸውና በማጨማለቃቸው ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ ከዚያ ቀደም አስራ ሰባት ዓመት ወታደሮቹም ከአቅማቸው በላይ ፖለቲካን እኛ ብቻ እንምራ ብለው እንዳጨማለቁት፡፡

 ጠለቅ ብለን ስንመረምረውና ያለይሉኝታ ስንወያይበት ያለፉት ሰላሳ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር – ትግሬ ሆነ ኦሮሞ፣ አማራ ሆነ ሲዳማ – ገበሬዎች ከአቅማቸው በላይ ፖለቲካን እኛ ብቻ እንምራ ብለው ስላጨማለቁት የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግስት አራሸ፣ ቀዳሽ፣ ተኳሽ፣ ነጋሽ ይል ነበር፡፡ ተኳሹ ነጋሽ ልሁን ብሎ አገሪቱን አድቅቆ ከሱ ለባሰ የአራሽ ቡድን አስረከበና አራሹ የትግሬና የኦሮሞ ሰገጤ ስብሰብ ደግሞ ነጋሽ ልሁን ብሎ ሕዝቡን ለማያባራ ዕልቂት ዳረጎ ይኸው እጅግ የሚዘገንን ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ መፍትሔው ተኳሽም ወደ ምሽጉ፣ አራሽም ወደ ግብርናው ተመልሶ ነጋሹን ወደ መንበር ማምጣት ነው፡፡ የአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ለንጉሰ ነገስት መንግስት የሚያበቃ ዕምነትና ብቃት ስለሌለው መንበሩን ሊይዝ የሚገባው ተወደደም ተጠላም ምሁሩ ነው፡፡ ጉዳዩ ሰፊና ረቀቅ ያለ ስለሆነ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡ ለዛሬ የሰገጤውን መደብ ከገለጽን በቂ ነው፡፡

 

እስክንድርና አፋሕድ ላይ ምነው መንጫጫት በዛ?

 

የአማራ ነገር ሲነሳ በዝቅተኝነት ምቀኝነት ስሜት የሚብከነከኑት እነደ መሳይና አንዳርጋቸው አይነቶቹ ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ወዲያው ተስፈንጥረው ሲዘባርቁ ሌሎቹም ሰገጤ የብአዴን ባንዳዎች የአፋሕድ ተጨባጭ የዲፕሎማሲ ክንውን ነርቫቸውን ስለነካውና እነርሱ ከመለፍለፍ ያለፈ ምንም ሊያበረክቱ የማይችሉ ውሽልሽሎች መሆናቸውን ስላረጋገጠባቸው ሜዲያውን በውግዘት፣ ዛቻና ቅጥፈት አጥለቀለቁት፡፡ ወናፍ ሁላ! 

ንግግሩን በግድ ድርድር ነው ብሎ ድርቅ? ለመሆኑ ተደራዳሪ በሌለበት ድርድር አለ እንዴ? ወይስ ድርድሩ ከዓለም ዓቀፉ ተቋማት ጋር ነው? ድርድር ቢሆንስ የአማራንና የኢትዮጵያን ጥቅም ካስጠበቀ ለምን አይደራደሩም? ደርሶ ከወሬ ሌላ አማራጭ ያለው ይመስል ምድረ ሰገጤ ይቀባጥራል፡፡ ነገ ትራምፕ ተደራደር ቢልህ ወደህ ነው የምትደራደረው? ሰገጤ ሁላ! እንኳን አንተ እስራኤልም ታዞ ተደራድሯል፡፡ ዓለም በትራምፕ መምጣት እንደተቀየረች እንደሆነ ምድረ ሰገጤ አልገባውም፡፡ ወቅታዊው ዓለም አቀፍ ክንውን ለገባው ፋኖ መጣም አልመጣም ብልጽግና በአጭር ጊዜ ያከትምለታል፡፡ ዘመኑ የትራምፕ ነው የሰገጤ ቀላቢና ተንከባካቢው የባይደንና ዴሞችራቶቹ ዘመን አክትሟል፡፡

 የሌሎቹ ሰገጤዎች ሲገርመን ሽማግሌዎቹም በስተርጅና ቀለሉኮ፡፡ መርሻ ዮሴፍ እንኳ ዘላበደኮ ፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ሰገጤው ዶክተር ፍቃዱ ተብየው ስለእስክንድር የጻፈው እጅግ አሳፋሪና መማርን የሚያስጠላ ነው፡፡ የአሜሪካን ኢምፔሪሊዝም ምናምን እያለ እንደሚቀባጥረው ፕራግማቲዝም የሚባል ነገር የማያውቅ  አንድ መንደር ውስጥ ቀርቶ ቤተሰብ ውሰጥ ያለውን ተጨባጭ ችግር የማያውቅ የላም አለኝ በሰማይ አካዳሚ ቅንጡ ማማ ላይ ተዘፍዝፎ የሚያላዝነው በሚኒሊክ ጊዜ የደነቆረ ዶክተር ፈቃዱ የሚባል ሰገጤ ጅል ‹‹ዕውነተኛ ፍልስፍናና  የሳንይስ መሰረት  ላይ በመሰባሰብ ትግሉን ማፋፋም ነው›› ይለናላ! ዶክተሩ ያላንዳች ማቅማማት ‹‹በአንዳቸውም የአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ በራሱ ፍልስፍናና በነጻ አስተሳሰብ እየተመራ አገሩን የሚያስተዳድር አገዛዝ በፍጹም የለም›› ይለናል፡፡ አንድም አገር የሱን የቅዠት ፍልስፍናና ነጻ አስተሳሰብ ተግባራዊ ካላደረገ ይህ አባባሉ ራሱ የሚያረጋግጠው የራስ ፍልስፍናና ነጻ አስተሳሰብ የሚለው ነገር መሬት ላይ የሌለ ቅዠት መሆኑን ነው፡፡

ይባስ ብሎ ደግሞ ‹‹የእስክንድር ነጋንና የግብረ አበሮቹን የውንብድና ሴራ…›› በማለት ስንቶች ወጣት ፋኖዎች የተሰውበትንና እየተሰዉም ያሉበትን የሞት የሽረት ትግል ከባንዳ በባሰ ወራዳ አስተሳሰቡ ዘልፏል፡፡ ይህን ያህል ዘመን ተምሮ ዶክተር ሆኖ እንደዚህ ይዘቅጣል? አድሮ ቃሪያ ማለት ይሄ ነው፡፡ የእርሱ ዓይነት ትምህርትና ዕውቀት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ምን አይነት ቅሌት ነው! እንዲህ ያለ ጉድ ሲገጥማቸው ነው አባቶቻችን አንተስ በናትህ ሆድ በቀረህ ይሉ የነበረው፡፡ አቤት ቅሌት! ዶክተር ፍቃዱ ለአዕምሮ ጂምናስቲክ ይጠቅማል ብለን የጀርመን ፈላስፎችንና ኢኮኖሚን እንዲሁም ዘመናዊ የተባሉ ከተሞችን ግንባታ ጉዳይ ብናነብለት ዕውነት የተቀበልነው መሰለው እንዴ? ኮምጨጭ ያልክ ምሁር ከሆንክና እግዚአብሔር ጤናውን ከሰጠህ የትናቱን ፍሬድሪክ ሊስት ፍልስፍና ትተህ እስኪ ስለ ክብረ-ነገሥት፣ ፍትሐ-ነገሥት መንፈሳዊ ሥጋዊ ተመራመር፡፡ የቤተክርስቲያን ዕውቀት የሌለህ ስለምትመስል ሊከብድህ ስለሚችል ከቻልክ እዚያው  ከአውሮጳ የብዙ ምሁራንን ቀልብ በመሳብ ተወዳዳሪ ስለሌለው ኒኮሎ ማኪያቪሌና ስለ ፕሪንስ ጻፍ የልሎቹን ትርኪ ምርኪ ትተህ፡፡ 

 የእስክንድር ጉዳይ የዶክተር ፍቃዱን የትኛውን ነርቩን ጠቅ አድርጎት ነው ጎጥ ይሆን እንዴ?) እንዲህ ተስፈንጥሮ እስክንድር ላይ ውርጅበኝ ያወረደው? ‹‹ እስክንድር ነጋ በሥልጣን ጥም ያበደና በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነት መንፈስ የታነፀ ግለሰብ ነው›› ይልና መልሶ ደግሞ ‹‹የወያኔና የአብይ አህመድ አገዛዝ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመደገፍ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ.. ›› ይለናል፡፡ ታዲያ እስክንድር  ነጋ  በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነት መንፈስ የታነፀ ግለሰብ ከሆነ እርሱንም አሜሪካኖቹ ለምን ደግፈው ሥልጣን ላይ አላወጡትም? ዶክተሩ እርስ በርሱ የሚቃረን ሃተታ እየደረደረ ቅሌታም ተራ ምቀኝነት ውስጥ መውረዱን አረጋግጧል፡፡  በርግጥ ከዚህ ጽሁፉ መረዳት የሚቻለው የእስክንድርን ኢትዮጵያዊ፣ ቆራጥ፣ ትሁት ማንነት በቅርበት ቀርቶ በርቀትም ጨርሶ እንደማያውቀው ነው፡፡

‹‹የእስክንድር ነጋ የትግል የሕይወት ታሪኩን ለተከታተለ የጠራ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አመለካከት የለውም›› ይለናል ዶክተሩ የቅንጦት ማማ ላይ ተቀምጦ የቅዠት የጀርመን ፈላስፎችን ዝባዝንኬ እንደ መጨረሻ ዕውቀት ቆጥሮ፡፡ ለመሆኑ እንኳን የህልውና አደጋ ላይ ያለ ሕዝብ ቀርቶ የትኛው መሪ ነው እርሱ እንዳለው  የጠራ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አመለካከት ይዞ ሥልጣን ላይ የወጣው? ዶክተሩ  ፍልስፍና ፍልስፍና እያለ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ፍልስፍናን የማያውቁ ወይም ኋላ ቀር ይመስሉታል፡፡ ያልገባው ነገር እነርሱ ፍልስፍናን ንቀውት እንጂ ከብዷቸው ወይንም ሳይሰሙት ቀርተው አይደለም፡፡ ዓለማዊው ሰውኛ  አሰተሳሰብ ሁሉ  የማይረባና በርግጥም በዓይናችን አንዳየነው መጨረሻው ግብረሰዶምና ምናምንቴነት መሆኑን ስለሚያውቁ ዕድሜያቸውን የሚፈጁት ፍጹም ረቂቅ የሆነውን ሰማያዊውን መንግስት ለመውረስ የሚያስችለውን መንፈሳዊ ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ውዳሴና ክብር ለእግዚአብሔር በመስጠት ቅዱስ እግዚአብሔርን በማገልገል ነው፡፡  

ዶክተር ተብየው በቅናት ከማበዱ የተነሳ ‹‹ማንኛውም አገር ቤትም ሆነ ውጪ ያለ በአማራው ህዝባችን ላይ የደረሰውንና የሚደርሰውን በደል የሚያወግዝ ሁሉ የእስክንድር ነጋንና የግብረ አበሮቹን የውንብድና ሥራ ሴራ ማውገዝ አለበት...የእስክንድር ነጋ የትግል አካሄድም የኢትዮጰያ ሕዝብ ዋና ጠላት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው የጥቁር ሕዝብም ጠንቅ ነው›› ይለናል፡፡ ወያኔና ብልጽግና እንኳ እንደዚህ የዘቀጠ ጽሁፍ አልጻፉም፡፡ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ያውም ዶክተር ነኝ የሚል እንደዚህ ሲዝረከረክና በአደባባይ ጸረ አማራ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ይዞ ሲጸዳዳና ሌት ተቀን በየወንዙ በየሸንተረሩ እየተጋደሉ ያሉትን እስክንድርና ጓዶቹን  ሲያወግዝ ከማየት በላይ ሕሊናን የሚጎዳ ነገር የለም፡፡  ይሄ የምዕራብ ዓለም ኑሮ አንዳንዴ ቀዥበርበር ያደርጋል፣ ያላሽቃል፤ ብዙዎቹም በቨረችዋሉ የቅዠት ዓለም ውስጥ ነው ኢትዮጵያን የሚያይዋት የዶክተር ፍቃዱ ቅሌት ግን ከመቀባዠርም አልፎ ጤነኛነቱንም ያጠራጥራል፡፡ ጀርመን አገር አማኑኤል ሆሰፒታል የለም እንዴ?  ሰውየው ከአሁን በኋላ ስለኢትዮጵያም ሆነ አማራ መጻፉን ትቶ አዕምሮ ሆስፒታል ጤናውን ቢከታተል ይሻለዋል፡፡ እግዚአብሔር ይማረው!

ምን ይሻላል?

አገሩ እኮ የሰገጤ ሆነ! ዘመነ፣ አስረስ፣ አኪላ፣ ማርእሸት፣ መዓዛ፣ ግርማ ካሳ፣ ይልቃል፣ አሳዬ፣ ትንግርቱ፣ አቻሜለህ፣… ስንቱን እንዘርዝረው? ይሄ ሁሉ ሰገጤ ቢጨፈለቅ አንድ እስክንድርን አይወጣውም! ካራክተር ይላል ፈረንጅ! ወጥ ባህሪይ፣ ወጥ ስሪት ያለው እንደእስክንድር ዓይነት ስብዕና ከየት ሊያመጡ፡፡ ለመሆኑ ይህ የሰገጤ መንጋ ትውልድ ይህን አገር ወደ ቀድሞው ከፍታው ሊመልስ ይችላል? በምን አቅሙ! ወሬ ሌላ ብቃት ሌላ! ቲክቶክና ዩቲዩብ ላይ በብአዴን በኩል የብልጽግናን ፍርፋሪ ለቃቅሞ መለፍለፍ ሌላ ዘለቄታ ያለው አስተሳሰብና ዓላማ ማራመድ ሌላ! መለኪያው ብቃት ያለው ትምህርት የተማረ በሥነ ምግባርና በተለይም በኢትጵያዊ አስተሳሰብና መንፈሳዊ ዕውቀትና ሥነ ምግባር የተገነባ ስብዕና ነው፡፡  ዘመነ የሚባለው በግድ ካልመራሁ፣ በግድ ካልመረጣችሁኝ ባይ ግንቦቴ-ብአዴን በአማራ ነጻነት ላይ የእርጎ ዝንብ የሆነ ጉድ እስክንድር ከአብይ አህመድ ጋር ይሰራል እያለ ከመቀላመድ ጀምሮ የህግ የበላይነት ያውም ፈሪሃ እግዚአብሔር በነበረበት ወርቃማ ዘመን የተከናወነን ድርጊት በለብለብ ዕውቀቱና በጎጠኛ ጎጃሜነት ደቁሶ ስለ ሲባጎ ያወራል፡፡ የሲባጎ እራት ያርገውና!  ለመሆኑ ሌሎቹ ፋኖዎች መጠጥ ያሉ ሲሆኑ እርሱ እንዴት እንደ ወደል አህያ ተነፋፋ! የጤና ነው? አስረስ የሚባለው ሌላው ለፍላፊ ቅልጥ ያለ የብአዴን ካድሬ ደግሞ የፖለቲካ ደንቆሮ መሆኑን ሲያረጋግጥ ዲያስፖራው ትግሉን ማገዝ ይችላል መምራት ግን አይታሰብም ይላል (እኛው ነን የምነመራው ማለቱ ነው፣ አቅምና ችሎታ ቢኖርህማ ማን ይቃወምሃል፣ ችግሩ ከወረዳ ያለፈ አቅም የለህም ያውም ደግሞ ባንዳነትህን፣ ብአዴንነተህን ካራገፍክ! ኮልኮሌው ብአዴን የድፍረቱ ጥግ የሚገርም ነው! )፡፡ ለነገሩ ዲያሰፖራውም ሰው አላወጣም፣ አገሩም በሰገጤ ተጥለቅልቋል ምን ያርግ አፉን ይክፈትብን እንጂ፡፡ 

እንደ አስረስና ብጤዎቹ የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵን ታሪክ እንኳ የማያቅ በመንደር አስተሳሰብ የሚመራ የኢሕአዴግ ካድሬ  ስብስብ እንዴት ኢትዮጵያን የምታክል ታሪካዊ ሃየማኖታዊ አገር ሊመራት ቀርቶ ሊረዳት ይችላል?  ቀ.ኃ.ሥ. የአምስቱን ዓመት ፀረ ፋሺስት ትግል የመሩት መራዊ ሆነው ነበር? ይሄ በብአዴን ባርነትና የጎጥ አስተሳሰብ የተበከለ ሰገጤ ትውልድ በሌላ የተባረከ ትውልድ እግዚአብሔር ፈቅዶ ካልተተካ የኢትዮጵያ ትንሳዔ የሚመጣ አይመስልም፡፡ አስረስ ጭራሽ በየቁጥቋጦው የሚደረግ ንግግር እያለ አቦሬ አፉን ከፍቷል፡፡ ታዲያ የፋኖ ቢሮው ቁጥቋጦ ነው እንጂ የት እነደሆነ ይንገረና! ምናልባት የሱ ቢሮው በየሆቴሉና መሸታ ቤት ከሆነ ይንገረና! የትግሬና የኦሮሞ ሰገጤ ጨምላቃ አስተሳሰብ አንገሸግሾን እያለ  የአማራ ሰገጤው ግትልትል ገና ወደ ሰገነት ሳይወጣ እንደ ዕብድ ያስለፈልፈው ጀመር? ሰገጤ ሰገጤ ነው ትግሬ ሆነ ኦሮሞ ሆነ አማራ ሆነ ያው ነው፡፡ ትግሉ ኢህአዴግ-ብልጽግና የሚባሉ ሰገጤ ድርጅቶች ከፈለፈሏቸው ሰገጤ ቡችሎች ጋር ነው፡፡

አፋሕድ የሚችለውን አድርጓል ሌሎቻችሁ ደግሞ ለአማራ ይጠቅማል የምትሉትን የራሳችሁን ድርሻ ለምን አትወጡም?  እንኳን እንደ አፋሕድ ተጨባጭ ድርጊት ማስመዝገብ ቀርቶ የረባ ጽሁፍ መጻፍ የማይችል ቀባጣሪ ሁላ ሚዲያው ተመቸኝ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል፡፡ ፈረሱም ሜዳውም እንደሚባለው እስኪ ራሳችሁን ችላችሁ አንድ የረባ ሥራ ስሩና አቅማችሁን አሳዩን! ከዚያም የናንተም የአፋሕድም ጥረት ተዳምሮ የአማራን የግፍ ዘመን ያሳጥረው፡፡ ከመሬት ተነስቶ መቶ ተራራ ምናም እያሉ በዩቲብ ላይ ከመንጎማለል፣ በየወረዳው የፈረደበት አማራ ገበሬ ፊት ከመቀባጠርና ከመንደር ስማርትነስ ውጡ! ወረዳችሁን ሳይሆን አባይን አሻግራችሁ እዩ፡፡ ወንድሞቻችን አቅማችሁን ዕወቁ ጎጃምም ሆነ አማራ ባጠቃላይ የስንት ሊቃውንት፣ ምሁራን፣ ጀግኖች አስተዋዮችና አዋቂዎች አገር ነው፡፡ አደብ ግዙ! ጎጃምን የሚያህል፣ አማራን የሚያህል አገር እንዲህ የማንም ኩታራ መቀለጃ አይሆንም፡፡

 የትግሬንና ኦሮሞን ማንነት ድምጥማጡን አጥፍተው መደዴ ትውልድ እንደፈጠሩት ወያኔና ኦህዴድ፣ ብአዴን አማራን ለማዋረድ በተለያየ መንገድ የሚሰራውን ሴራ ድባቅ መምታት ያስፈልጋል፡፡ ወራዳዎቹ ብአዴን፣ አብንና በውጪም እስክንድርንና አፋሕድን የሚቃወሙ ሰገጤዎች ዋና ተቀናቃኝ ብለው ያነጣጠሩባቸውን የአፋሕድ ፋኖዎችን በሜዲያ ውጊያ መከላከል የእያንዳንዱ አማራ ግዴታ ነው፡፡ አማራን መሪ አሳጥተው፣ ድርጅት አሳጥተው ሊያዋርዱት፣ ሊያጠፉት ቆርጠው የተነሱ እርጉማን መጨረሻ ላይ ወይ የሚወረወርላቸው ፍርፋሪ ሲቆም ወይ እርስ በርሳቸው ተናቁረው ብን ብለው መጥፋታቸው ባይቀርም ለጊዜው የሚያዠጎደጉዱትን ውዥንብር መክቶ ልክ ልካቸውን መንገር የእያንዳንዱ አስተዋይ አማራ የታሪክ ሃላፊነት ነው፡፡ ዕወነተኞቹን የአፋሕድ ፋኖዎች ከነድክመታቸው መደገፍ፣ማበረታት፣ ሌሎችም ድርጅቱን ያልተቀላቀሉት ፋኖዎች አፋሕድን እንዲቀላቀሉ ማሳሰብ፣ ስህተቶች እንዲታረሙ መጠቆምና በጽናት መቆም ወቅቱ የሚጠይቀው  የእያንዳንዱ አማራ ግዴታ ነው፡፡

Filed in: Amharic