እውን አብይ አህመድ ይዋሻል? ውሸት ይችልበታል?
ሞገድ እጅጉ
አብይ አህመድን እንደ ውሸታም፣ አጭበርባሪ፣ አፈ ቅቤ… የሚያዩ ሰዎች ይገርሙኛል፡፡ ‹‹አታለለን፣ ‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ›… እያለ ሸወደን›› የሚሉ ሰዎች ምን ያህል አርቆ ማስተዋልና ማገናዘብ የተሳናቸው መሆናቸውን ያሳያል፡፡ እዚህ ላይ የአማራ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዋናኛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሰውየውና አገዛዙ በግልጽ ፀረ አማራ አካሄድ እየሄዱና በግልጽ እየተናገሩ ነው ‹‹ሸወደን›› የሚሉት፡፡
እርግጥ ነው አብይ አህመድ አጭበርባሪና ውሸታም ነው፣ ከሃዲነትን ሙያ ያደረገ ሰው ነው፡፡ ዳሩ ግን አሁን እየሆኑ ያሉ ነገሮችን ሊያደርግ እንደሚችል ገና ከማለዳው ግልጽ ነበር፡፡ የሚዋሻቸው ውሸቶች የምጸት እና የሹፈት ውሸቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ውሸቶች አብይ ‹‹አታለለ›› ለማለት አያስችልም፡፡ ለምሳሌ፡-
አገር አውዳሚ ጦርነት እያደረገ፣ የዘር ፍጅት እያወጀ፤ እነዚያን ሆዳም ካድሬዎችን ይሰበስብና ‹‹ጦርነት እኮ አይጠቅምም! ሰላም እኮ ጥሩ ነው! እኛ ሰላም ነው የምንፈልግ..›› ይላቸዋል፡፡ ታዲያ ይሄ ንግግር ውሸታም ያስብለዋል? የተናገረው ንግግር ውሸት ሳይሆን ማሾፍ ነው፤ በወጣቶች ቋንቋ ‹‹ሙድ›› እየያዘባቸው ናቸው፡፡ አፋቸውን ከፍተው፣ የጦጣና ዝንጀሮ ተረት እየተጣደፉ ማስታወሻ የሚይዙ ካድሬዎቹ ‹‹የኛ የሰላም አባት›› እያሉ ከልባቸው ያደንቃሉ፡፡ የአብይ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ደንባራ ፖለቲከኞች ደግሞ ‹‹አቤት ውሸት!›› ይላሉ፤ አብይ ግን እየዋሸ ሳይሆን የንቀቱ ንቀት በሕዝብ ላይ ሙድ እየያዘ ነው፡፡ ቀጣይም የከፋ ጦርነት እንደሚኖር እየተናገረ ነው፡፡
የፊት ገጽታውና አካላዊ እንቅስቃሴው ሳይቀር በሹፈትና ሙድ በመያዝ ነው ‹‹ጦርነት እኮ አይጠቅምም›› የሚላቸው፡፡ በውስጡ እየሳቀና ሙድ እየያዘባቸው ነው፡፡ ‹‹እኛ ሰላም ነው የምንፈልግ! ጦርነት ምን ይጠቅማል?›› ሲል፤ ከርሳም ካድሬዎች ያንን የሞተ አንጎል የሞላውን ጭንቅላታቸውን በአዎንታ እየነቀነቁ ያደንቃሉ፡፡ አገዛዙን እንቃወማለን የሚሉት ደግሞ ሆን ብሎ ሙድ እየያዘ መሆኑን መረዳት ተስኗቸው ‹‹እየዋሸ ነው›› ይላሉ፡፡ አብይ ግን እየዋሸ ወይም እንደ ፖለቲከኛ እያታለለ ሳይሆን፤ ሆን ብሎ እየተዝናናባቸው ነው፡፡
ውሸት ማለት አብይ አህመድ እንደሚናገው አይነት አይደለም፡፡
ውሸት መዋሸት ጥበብ ይጠይቃል፡፡ መለስ ዜናዊ ይዋሻል ቢባል ያስኬዳል፡፡ ምክንያቱም መለስ በጥበብ፣ በትህትና እና አሳማኝ በሚመስል ድምጸት የመዋሸት አቅም አለው፡፡ አብይ አህመድ ግን የመዋሸት እንኳን ጥበብ ያልታደለ ሰው ነው፡፡ አገናዛቢ እና አርቆ አሳቢ ጠፍቶ እንጂ አብይ አህመድ የሚያደርጋቸውን ንግግሮች ሁሉ የጥፋት በር ከፋቾች መሆናቸው ግልጽ ነበር፡፡
አብይ አህመድ ሥልጣን ከያዘ ዓመት ጀምሮ ‹‹የትርክት ግንባታ›› የሚለው ነገር ከወንጌላዊው የብልጽግና ፓርቲ አፍ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ በየመግለጫው ‹‹የትርክት ግንባታ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ…›› የሚል ቃል አይጠፋም፡፡ እነሆ የዛሬውን የብልጽግና ወንጌል ፓርቲ ያወጣውን ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫም ልብ ማለት ይቻላል፡፡ የመግለጫው ይዘት በአጭሩ፡-
በዋናነት ከፍተኛ የሆነ ሹፈት እና ሙድ መያዝ ይታይበታል፡፡ ‹‹ባለፉት ዓመታት…. ›› እያለ ኢትዮጵያ ከሰማየ ሰማያት ዓለም ውስጥ ይከታታል፡፡ በአገሪቱ ኮሽ የሚል ነገር እንደሌለ፣ አገሪቱ አይታው የማታውቀው ብልጽግና ውስጥ እንደገባች ይገልጻል፡፡ አንድ እውነት ብቻ ተናግሯል፡፡ ይሄውም በቀጣይ የሚዲያ አፈናው ከዚህም በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡ በፌስቡክ ጽሑፎች ሳይቀር ከፍተኛ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግሯል፡፡ ይህንንም በተግባር አሳይቷል፡፡ የብልጽግና ወንጌል ጉባኤውን በሚያደርግባቸው ቀናት በማህበራዊ ሚዲያ ማህበራዊ ሒስ በማቅረብ የሚታወቀው ሰመረ ካሳዬ (ሰመረ ባሪያው) ታስሮ ነበር። ‹‹ጦቢያ ግጥምን በጃዝ›› የተሰኘ ፕሮግራም የምትመራው ምሥራቅ ተረፈ ታስራለች፡፡ ይህን ያደረገው አገዛዝ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሚዲያ ነፃነት እንደተገኘ አድርጎ ሲያሾፍ ከቆዬ በኋላ፤ በቀጣይ ግን ከፍተኛ እርምጃ እንደሚወሰድ ሀቁን ተናግሯል፡፡
ብልጽግና ‹‹በቀጣይ እርምጃ እወስዳለሁ›› ሲል ምን ማለቱ ነው?
እስከዛሬም ቢሆን እርምጃ ሲወስድ ነበር፡፡ ምናልባት የቀጣዩን ለየት የሚያደርገው ግን መንግሥትን ተቻችሁ ተብሎ ሳይሆን የግል ፎቷቸውን የለጠፉትንም ያስራል ማለት ነው፡፡ አገዛዙን የሚያደንቁትንም ያስራል ማለት ነው፡፡ እንዴት በእነዚህ ቃላት ታደንቃለህ? እንዴት በትንሹ ብቻ ታደንቃለህ? ማድነቅህን ለምን የ24 ሰዓት ሥራ አላደረከውም?…. በሚል ያስራል፤ ይገላል ማለት ነው፡፡ እንዲያ ካልሆነ በስተቀር ‹‹ይሄ ይስተካከል›› ለምን አላችሁ ብሎማ እስከዛሬም ሲያስርና ሲገድል ነበር፡፡
ወንጌላዊው የአብይ አህመድ አገዛዝ ማንንም አላታለለም፣ አልዋሸም፤ ችግሩ አርቆ የማስተዋልና የማሰብ ችግር ነው፡፡ እንደ አገዛዝ፤ የኦህዴድንና የኦነግን የረምጅ ዘመን የትግል ዓላማ አለማወቅ ነው፡፡ እንደ ግለሰብ፤ የአብይ አህመድን ስድ አደግነት፣ ጋጠ ወጥነት እና ባለጌነት አለማወቅ ነው፡፡ የአብይ አህመድን መሃይምነት አለማወቅ ነው፡፡
አገዛዙ ገና ከማለዳው ጀምሮ ዋና ዓላማው አዲስ ኢትዮጵያ መፍጠር መሆኑን ተናግሯል፡፡ ይህንንም በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች የየዕለት አጀንዳ በማድረግ ተናግሯል፡፡ የአዳነች አቤቤ ሚዲያ የሆነው አዲስ ልሳን ጋዜጣ የፊት ለፊት ገጹ በተደጋጋሚ ‹‹የታላቁ ትርክት ግንባታ›› የሚል መሆኑን ደጋግመን አሳይተናል፡፡ የዓድዋ 00 ዋና ዓላማ ይህ መሆኑን አገዛዙ በግልጽ ተናግሯል፡፡ ከዓመታት በፊት በአገዛዙ ካድሬ መሃይም ‹‹ምሁራን›› የተሰጡ አስተያየቶችን ሰምተናል፡፡ ታዲያ ይህ አገዛዝ ዋሸ ማለት ይቻላል?
እነሆ ሰሞኑን ባደረገው ጉባኤ በሰጠው መግለጫ በሁሉም ነጥቦች ውስጥ ‹‹የአገር ግንባታ›› የሚል ቃል አለው፡፡ በተለይም በተራ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ በግልጽ የትርክት ለውጥ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ይህ ጉባኤ ሲካሄድ የአዲስ አበባ ጉዳናዎች ሁሉ ‹‹የወል ትርክት›› በሚል ማስታወቂያ ተጥለውልቀው ነበር፡፡
ለመሆኑ ‹‹የወል ትርክት ግንባታ›› ማለት ምን ማለት ነው?
የእስከዛሬዋ ኢትዮጵያ የጋራ አልነበረችም፣ የአማራ ብቻ ናት እያለ ነው፡፡ የኢህአዴግን ዘመን ጨምሮ የአማራ ነበር እያለ ነው፡፡ ይህን ሲል ዓላማው ምን እንደሆነ ማገናዘብ የማይችል አማራ ‹‹አብይ አህመድ አታለለኝ›› ቢል፤ መልሱ ‹‹ማገናዘብ የተሳነህ ነብራራ ስለነበርክ ነው!›› የሚል ነው፡፡
አብይ አህመድ አሾፈ እንጂ አልዋሸም!