ጀነራል ተፈራ ማሞ በፊትም ብአዴን አሁንም ብአዴን፤ ያዋጣዎታል?
በትግሉ ሠመረ
ጀነራል ተፈራ ማሞ የፋኖን ትግል እኛ ነን የጠነሰስነው እያሉ የሚደሰኩሩት የታሪክ ነጠቃ ትክክል አይደለም። የፋኖ ትግል በናንተ ብአዴኖች አልተጠነሰሰም። የፋኖን የትጥቅ ትግል አቅጣጫ ያስያዘው ብርጋዴል ጀነራል አሳምነው ጽጌ ነው። እናንተ ብአዴኖች የአለቃችሁን የጨፍጫፊውን አብይን ፊት እያያችሁ ፈራ ተባ ሥትሉ፤ በአማራ ፀጥታ ቢሮ በኩል የአማራ ወጣቶች በሞራልና በወታደራዊ አቅም ዝግጁ ኾነው እንዲደራጁና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲያነቃቸው የነበረው ጀነራል አሳምነው ጽጌ ነበር። እናንተ ብአዴኖች አሳምነው ጽጌን ካስበላችሁት በዃላ፤ የአሳምነው ልጆች ናቸው ተብለው እየታደኑ የታሰሩ ወጣቶችና የልዩ ኃይል አባላት በእስር ያንገላታቸው ነበር?። ከጀነራል አሳምነው ጎን በመቆማቸው በእስር ከተዳረጉትና ከተሰቃዩት ጀግኖች መካከል በአሁኑ ሰዓት የአ.ፋ.ሕ.ድ ወታደራዊ ዋና አዛዥ የኾኑትን አርበኛ ኮሎኔል ፋንታሁን ሙሃባውንስ አሥሮ ያንገላታቸው ማን ነበር?። አሁንስ ቢኾን ከጠላት ጎን ተሰልፎ ከጀርባ እየወጋቸው ያለው ማነው?።
ጀነራል!፤ እናንተ ብአዴኖች፤ እንኳን የፋኖን የትጥቅ ትግል ልትጠነስሱ ይቅርና አሳምነው የጀመረውን የትግል አቅጣጫ፤ ስታፍኑና የአብይን ዙፋን ለማስጠበቅ ስትሟሟቱ መቆየታችሁን ነው ህዝብ የሚያውቀው። ጀነራል!፤ ረስተውት ከኾነ ለማስታወስ ያህል፤ የአማራ ወጣት በቃ! ብሎ እናንተ ብአዴኖች፤ በየአደባባዩ የሰቀላችሁትን የአውሬው አብይ አህመድ ፎቶግራፍ ከየአደባባዩ ላይ ቦጫጭቆ ሲጥለው፤ እናንተ ብአዴኖች ምን ነበር ሚናችሁ? እርሶ ይመሩት የነበረው የፀጥታ፣ የልዩ ኃይልና አድማ በታኝ አልነበረም እንዴ ወጣቱን በማፈንና በመበተን ሥራ ላይ የተሠማራው።
እናም ጀነራል፤ እርሶ እንደሚተርኩት ሳይኾን፤ የአማራ ወጣት ቀዳዳ አግኝቶ እራሱን በጎበዝ አለቃ እያደራጀ፤ የአሳምነው ጽጌን ምስል በሰንደቁ ላይ እያተመ ፋኖ ኾኖ ወደ ሜዳ የወጣው፤ ወያኔ ለበቀል ወደ አማራ ክልል ስትገባና፤ ጓደኞችዎ የብአዴን ባለሥልጣናትና ካድሬዎች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር፤ የክልሉን በጀት ዘርፈው የአማራን ገበሬ ለወያኔ የበቀል እርምጃ አሳልፈው በመሥጠት ወደ አዲስ አበባ በሚፈረጥጡበት ጊዜ ነበር።
በርግጥ የአማራን ህዝብና ወጣት “የአማራ ህዝብ ተከቧል፤ አደጋ ላይ ነው” እያለ ታሪክንና ነባራዊ ሁኔታን እየተነተነ ህዝብና ወጣቱን ሲያነቃና፤ የአማራን ልዩ ኃይል ሥልጠና ሲያጧጡፍ የነበረው አሳምነው ጽጌ አልነበረምን1። ይኹንና፤ የፋኖን የትጥቅ ትግል አቅጣጫ ያስያዘውን ጀነራል አሳምነው ጽጌን፤ በሴራ ለመግደል የልዩ ጥበቃ ኮማንዶ ጦር ባህርዳር ላይ አራግፎ ተኩስ ሲከፍት በዛች ቀውጢ ሰዓት ጀነራል ተፈራ የት ነበሩ?። በቅርብ ርቀት ሬዲዮ መገናኛ ይዘው አጮልቀው ፍልሚያውን በዝምታ ሲታዘቡ እንደነበር በራሶ አንደበት ነግረውናል።
የወታደራዊ እውቀት ብቻ ሳይኾን የታሪክ፣የፖለቲካ፣የጂኦ ፖለቲክስ ልሂቅ የነበረው፤ ለአማራ ህዝብ ኽልውና ሲል የተሰዋው የጀነራል አሳምነው ፅጌን ሥም የማጠልሸትና የማሰጠን የ(demonization) ፕሮፖጋንዳ አብይ በሚያሽከረክራቸው የብአዴን ባለሥልጣናት ሲከፈት፤ ” የፌስቡክ ጀነራል፣ የፌስቡክ አርበኛ፤ የሥራ እቅድም የሌለው ፤ ምንም ሥራ ያልሠራ፤ በተደጋጋሚም ፋኖን እያደራጀ ከፍተኛ አመራሩ ሊያስመታ የነበረ…” እያሉ የጀግናውን ሥም ሊያጎድፉና ሊያጥላሉ፤ የአድርባይ አስተያየቶችን ሲሰጡ ከነበሩት ብአዴኖች ውስጥ፤ ጀነራል ተፈራ ማሞ ግንባር ቀደሙ እርሶ አልነበሩምን።
አውሬው አብይ አህመድ፤ የአሳምነውን ሥም ለማጠልሸት ከተጠቀብዎት በዃላ፤ የልዩ ኃይሉ አዛዥነት አድርጎ ሾሞት። ብዙም ሳይቆይ ወያኔ የአማራን ህዝብ እበቀላለሁ ብላ ወደ አማራ ክልል ስትገባ፤ አሳምነው ቀድሞ ያነቃውና እንዲደራጅ መንገድ የቀደደለት ፋኖ፤ ቅድሚያውን ወስዶ ከወያኔ ጋ በባዶ እጁ መፋለም ሲጀምር፤ እርሶም የአማራን ልዩ ኃይል ይዘው ወያኔን ተፋለሙ። ወያኔንም ከጣርማ በር ጀምሮ ወደ መጣችበት እንድትመለስ በወታደራዊ አመራር ችሎታዎ ውጤት አስመዘገቡ። ያኔ ትንሽም ቢኾን በአሳምነው ላይ ፈጽመውት የነበረውን በደል አስረሳልዎት። ነገር ግን፤ ጀነራል አሳምነውን መኾን ብቃት ስላነስዎ፤ ከአማራነትዎ የበለጠ ብአዴናዊነትዎ በልጦብዎት፤ ተመልሰው የአውሬው አብይ አህመድ አገልጋይነትዎን ቀጠሉበት። እንደፈለገ እንዲዘውርዎት የፈቀዱለት አብይ አህመድ በመጨረሻ ከሥልጣንዎ አባረሮት።በመባረሮ በሽቀው ሳይኾን አይቀርም፤ በሽታ ተቀሰቀሰብዎ። መባረሮትን ተከትሎ በቁጭት ወደ ፋኖ ትግል ይቀላቀላሉ ተብለው ሲጠበቁ፤ ወደ ፋኖ ሳይኾን ወደ አዲስ አበባ ተሰደዱ።
ነፍሱን ጣርማ በር ላይ እየታዘዙት ያዳኑት፤ አውሬው አብይ አህመድ ወደ ውጪ ለህክምና ለመውጣት ፈቃድ እንዲሰጥዎ ቢማጸኑትም፤ መሞቴ ነው ቢሉትም ፤ አልፈቅድልዎት አለ። ከዚኽ በዃላ ነው እንግዲኽ፤ በድንገት ከወራቶች በዃላ ከአዲስ አበባ ወደ ሜዳ ጀነራል ተፈራ ገቡ የሚባለው ዜና የተሰማው። ዜናው እንደተሰማ፤ ጥቂት የማይባሉ “ብአዴን ብአዴናዊነቱን አይለቅም” የሚሉ አንዳንድ በሳል ሰዎች ጥርጣሬ ቢያድርባቸውም፤ ከዚኽ በፊት በርሶ ላይ ቅሬታ የነበራቸው አብዛኞቹ የአማራ ፋኖም ኾነ የአማራ ህዝብ፤ ወደ ጫካ መግባትዎን እንደ በጎ ዜና ነበር የተቀበሉት። ነገር ግን፤ ጊዜ ጊዜን ወለደና፤ በሚያሳዝን ሁኔታ አገዛዙን የአውሬው አብይ አህመድ ሠራዊት ለመጣል ወታደራዊ ልምድዎትን ለፋኖ በማካፈል ውጤት ያመጣሉ ተብለው ሲጠበቁ፤ ከአራቱም ጠቅላይ ግዛት ተውጣጥቶ የተመሠረተውን የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት አ.ፋ.ሕ.ድን የሚያጥላሉ ንግግሮችን መናገር ጀመሩ። ይባስ ብለው የአ.ፋ.ሕ.ድ መሪ አርበኛ እስክንድር ነጋን “ፋኖን ከፋፈለ” እያሉ ትግሉን በብአዴን ቁጥጥር ሥር ለማድረግ የሚሟሟቱትን የብአዴን ግልገሎች አቋም ይዘው በይፋ ማራመድ ጀመሩ። ምላሶትን የደገኑት በአብይ አህመድና በወራዳው ብአዴን ላይ ሳየኾን በአውሬው አብይ አህመድ፤ ገና ድሮ ጦርነት በታወጀበት አርበኛ እስክንድር ነጋ ላይ ኾነ። አዩ ጀነራል፤ “ብአዴን ብአዴናዊነቱን አይለቅም” የሚባለው እውነት እንደኾነ አረጋገጡልን።
አማራ ፋኖ ከፍተኛ የህይወት መስዋእትነት በመክፈል፤ እራሱን በክፍለ ጦርና በብርጌድ ደረጃ በማደራጀት፤ አንድ የሚያደርገውን ድርጀት መሥርቶ፤ የብርሃኑ ጁላን ጦር በገፍ በማራገፍና መማረክ ትግሉን ባጧጧፈበት በዚኽ ሰአት፤ በአናቱ ተከስተው “ከኔ በላይ ለአማራ የሚሞትለት ሊኖር አይችልም” እያሉ ፉከራ የጀመሩት፤ አማራን ነፃ ለማውጣት ሳይኾን፤ የፋኖን ትግል ጠልፎ ብአዴናዊ ቅርፅና ይዘት እንዲኖረው በማድረግ፤ የህልውና ትግሉን በማኮላሸት፤ በድርድር መልክ ተልካሻ ጥያቄዎችን በማንሳትና ተልካሻ ምላሽ በመቀበል፤ አማራን እየጨፈጨፈ ያለውን የአውሬው አብይ አህመድ መንግሥት ህጋዊ እውቅና(Legitimacy) በማሰጠት ለማጽናት መኾኑ ግልፅ ነው። ይኽን ዓላማዎን ለማሳካት ይመስላል፣ ከዚኽ በፊት ጀነራል አሳምነው ፅጌን ለአውሬው ያስበሉበትን ብአዴናዊ የማጥላላትና የአሉባልታ ፕሮፖጋንዳ ስልት፤ አርበኛ እስክንድር ነጋ ላይ ለመተግበር እየተንቀሳቀሱ ያሉት። ጀነራል! በአሳምነው ጽጌ ላይ የፈፀማችሁት ክህደት አይበቃም ነበር?።
አርበኛ እስክንድርን ነጋ ለአማራው ህዝብ በተለይ አሁን ፋኖ ኾኖ ጫካ ገብቶ እየታገለ ካለው ወጣት እሩቅ እንዳልነበር ከርሶ በላይ የሚያውቅ አልነበረም። ሌላው ቢቀር እስክንድር ነጋ በአማራ ፋኖ ዙሪያ የነበረውን ተቀባይነት በጎንደር ፋኖዎች እንዲሁም በባህርዳር ወጣቶች ገና የትግራይ ጦርነት ሳይጀመር በየካቲት 7ና8 2012 ዓ.ም የተደረገለትን ደማቅ አቀባበል ባያዩ እንኳን አልሰማሁም ነበር አይሉም መቼም።
ጀነራል አሳምነው ጽጌና እስክንድር ነጋ የነበራቸውን መግባባትስ፤ እረሱት?። ጀግናው ጀነራል አሳምነው ጽጌ ባሕርዳር ላይ እስክንድር ነጋ፤ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲመጣና ከፍተኛ አቀባበል እንዲደረግለት ዝግጅት ሲያደርግ የነበረው ለምን ይመስልዎታል። ምን ያደርጋል ሙቱ ብአዴን አስበላው እንጂ፤ አማራው እራሱን ለመከላከል እንዲያስችለው እየሠራው ከነበረው የትጥቅና ወታደራዊ ዝግጅት ጋር ሠላማዊ ትግሉን በማቀናጀት የአማራውን ህልውና በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ከአውሬው አብይ አህመድ መዳፍ ማላቀቅ እንደነበር መቼም መገመት አይከብዶትም።
ጀነራል! እርሶ ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ ሲሰደዱ እስክንድር ነጋ ግን ፋኖን በትጥቅ ትግል ለማደራጀት አንድ አመት ከሰባት ወር በእስር ከተሰቃየበት ቂሊንጦ ተለቆ ከቤተሰቡ ጋር ትንሽ እንኳን የማገገሚያ ጊዜ ሳይወስድ፤ መጀመሪያ ፋኖዎችን ለማመስገን በአራቱም ጠቅላይ ግዛት ወደ በህርዳር፣ ጎንደር፣ደሴና ደብረብርሃን በመዘዋወር ፤ ከፋኖ መሪዎች ጋር ቀደም ሲል እስር ቤት እያለ የጀመረውን ግንኙነት አጠናከረ። ጊዜ ሳይወስድ ወደ አሜሪካን በመጓዝ የፋኖን ትግል ከሚደግፉ የተለያዩ ምሁራን ጋር ፋኖን ለማገዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አደረገ። ከአሜሪካን እንደተመለሰ በሳምንቱ፤ ፋኖን በአንድ ለማደራጀትና የህልውና ትግሉን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ፤ አዲስ አበባን ለቆ በመውጣት ወደ በረሃ ገባ። በሸዋ፣ በጎጃምና በወሎ ከአንድ አመት ከስድስት ወር በላይ ጫካ ለጫካ በረሃ ለበረኻ እየተንከራተተ በመዟዟር፤ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ህዝብን የማንቃትና የማደራጀት ሥራን በመሥራት ላይ ተጠመደ።ጎጃም ደብረ ኤሊያስ ላይ ፋኖ ከመከላከያው ጋ የመጀመሪያውን ጦርነት እንዲገጥም በማድረግ፤ የትጥቅ ትግሉን ወደ ከፍተኛ ምእራፍ እንዲሸጋገር አደረገ ። የአማራ ህዝባዊ ግንባርን በመመሥረት ሪከርድ የሰበረ የገንዘብ ድጋፍ ለፋኖ እንዲጎርፍ አስቻለ። በአራቱም ጠቅላይ ግዛት የሚገኙ ፋኖዎች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ አስደረገ። ከብዙ ውጣ ውረድ በዃላ መላው ፋኖን አንድ አድርጎ እንዲመራ የተቋቋመው አ.ፋ.ሕ.ድ ሲመሠረት የድርጅቱ መሪ ኾኖ በአብላጫ ድምፅ ተመረጠ።
ጀነራል! ይኼ ሁሉ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ከህዝብ ህሊና ያልጠፋ እውነት እያለ ነው፤ እንግዲህ፤ ብአዴናዊ ምላሶን ዘርግተው ያለ ሃፍረት እስክንድር “ሊሾልክ ፈልጎ ነው ፤ ሽምቅ ውጊያው ከብዶታል ፤ ፋኖን ሰንዳፋ ሲደርስ ሊመልሰው ነው ” የሚል የሃስት ክስና አሉባልታ እየደረደሩ ጀነራል አሳምነው ፅጌ ላይ የተፈፀመውን ብአዴናዊ ክህደት፤ በአርበኛ እስክንድር ነጋ ላይ እንዲደገም ለማድረግ እየጣሩ ያሉት።
ጀነራል! አንድ ያልተረዱት ነገር ቢኖር “ብአዴን ብአዴንነቱን አይለቅም” የሚለውን አባባል ለውጠው የተበላሸ ታሪኮን ለማደስ ያገኙትን እድል እያጡት መኾኑን ነው። የተቃጠለውን የብአዴን ካርድ ስበው፤ አማራውን ወደ ነበረበት የብአዴን ቀንበር ተሸካሚነት ለመመለስ የሚያደርጉት መሯሯጥ፤ ውርደትና ቅሌትን ያከናንብዎት እንደኾነ እንጂ፤ ክብርን አያስገኝሎትም። ምርጫው የእርሶ ቢኾንም፤ “በፊትም ብአዴን አሁንም ብአዴን” ኾነው መቀጠልዎ አያዋጣዎትም።
የሚሰማ ቅን ልቦና ካለ ጥቂት ምክር ለጀነራል ተፈራ ማሞ
ጀነራል ተፈራ ሌላው ቢቀር እድሜዎትም የማይፈቅደውን መዋሸቱን አቁሙ። አማራ በመላው ኢትዮጵያ ይገኛል ፣ በአለም ዙሪያ ይገኛል እንዲህ የሰው ሥም በሃሰት፤ በተለይ ጠላትም ኾነ ወዳጅ ጠንቅቆ የሚያውቀውን የአርበኛ እስክንድር ነጋን ሥምና ማንነት፤ ለማሳነስና ለማጥላላት በሞከሩ ቁጥር፤ እራስዎትን እያሳነሱ መኾኑን ይረዱ። የብአዴን ኬይቦርድ አርሚ በሳይበር ሜዲያው ላይ የሚያሟሙቅልዎትን፤ የቸከ ፕሮፖጋንዳ አምነው ገደል አይግቡ። የአርበኛ እስክንድር ነጋን ጽናትና የትግል ታሪክ ድፍን አዲስ አበባ ያለ አማራ ፣ በመላው ኢትዮጵያ የሚኖረው አማራ ፣ በዲያስፖራው ያለው አማራ ፣ እንዲሁም ፋኖን ለማደራጀት በተንቀሳቀሰባቸው የሸዋ የጎጃምና የወሎና የጎንደር ግዛቶች ሁሉ የእስክንድርን ማንነትና ጀግንነት በተግባር የማያውቅ አማራ የለም። የዓለም አቀፉም ማህበረሰብም ቢኾን በሰብአዊ መብት፣ በፕሬስ ነፃነትና በዲሞክራሲ ታጋይነቱ እውቅና በመሥጠት ጭምር የሚያውቀው ነው።
ጀነራል ! እርሶም ቢኾኑ እስክንድር ነጋ ማን እንደኾነ ልቦናዎ በደንብ ያውቀዋል። በመኾኑም፤ልብዎ ከሚያውቀው ከእውነተኛው አርበኛ እስክንድር ነጋ ጎን ቢቆሙ ለአማራም ህዝብ ይጠቅማሉ፣ የራሶዎትን የተበላሸ ታሪክ ያድሳሉ።የሆዳሞች ጥርቅም ከኾነው ለወያኔ ለ30 ዓመታት ሎሌ ከነበረው ፤ አሁን ደግሞ የአውሬውን አብይ አህመድ ዙፋን ለማስጠበቅ ከውስጥም ከውጪም የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አ.ፋ.ሕ.ድን፤ ቢችል ለመጥለፍ ካልቻለ ለማፍረስ ከሚሯሯጠው ከብአዴን በላይ ታላቁን የአማራን ህዝብ ያስቡ። አማራና ብአዴንን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ አድርገው ማየቶን ያቁሙ። ብአዴናዊነትዎን እርግፍ አድርገው ይጣሉና፤ ወታደራዊ ልምድዎትን ይዘው አ.ፋ.ሕ.ድን መደገፍ ይጀምሩ፤ ያኔ የአማራን ህዝብ ይጠቅሙታል። አሁን እየሄዱበት ያለው ብአዴናዊ አካሄድ መጨረሻው ቢሳካለት የፋኖን ትግል ጠልፎ መልሶ ሳልሳዊ ብአዴንን በመውለድ፤ በአማራው ጀርባ ላይ ተቀምጦ እንዲጋልብ የሚያደርገው ነው። እርሶ የጦር ሰው ነዎት፤ እንደ ብአዴን ያለ የአማራን ህዝብ ሲያስመታ የኖረን ድርጅት መገርሰስ የእርሶ ሥራ ነበር መኾን የነበረበት ፤ ይኼን ሥራ ድሮ ሠርተውት ቢኾን ኖሮ አርበኛ እስክንድር ነጋ በረሃ ገብቶ ጫካ ለጫካ በረሃ ለበረሃ ባልተንከራተተ ነበር ። ጀነራል! በመጨረሻም እየሠሩ ያሉት ስህተት የአማራን ህዝብ ካለፈበት የ50 ዓመታት መከራ የባሰ መከራ ውስጥ የሚያስገባ ነውና ፤ በቶሎ ስ ህተቶትን አርመውና ንስሃ ገብተው፤ የአማራን የህልውና ብሎም የኢትዮጵያን አንድነት ሊያስጠብቅ የሚችለውን አ.ፋ.ሕ.ድን በመደገፍና በማገዝ ታሪክዎትን እንዲያድሱ ይመከራሉ።
ማጣቀሻ ፦
የጀግና ቃል አይረሳም ይተገበራል አሳምነው ፅጌ አልገደላቸውም“ስለ ሰኔ 15ቱ ግድያ እና ስለ አሳምነው ፅጌ ታፍኖ የቆየ ቃለ መጠይቅ| ጀነራል ተፈራ ማሞ -
ለእነ እስክንድር ነጋና ሻለቃ ሰፈር መለሰ የተደረገ አቀባበል! በሰሜን ጎንደር ዞን አዳርቃይ ዛሪማ እስክንድር ነጋ በጎንድር ከተማ የተደረገለት አቀባበል | እስክንድር ነጋ በጎንድር ከተማ የተደረገለት አቀባበል | By 𝑬𝒕𝒉𝒊𝒐 𝑨𝒎𝒉𝒂𝒓𝒂 𝑴𝒆𝒅𝒊𝒂 | Facebook Ethiopia:-በጎንደር የተደረገው የጀግናው የእስክንድር ነጋ አቀባበል!!! | Ethiiopia:-#ታላቁ_የሰብዓዊ_መብት ተከራካሪ እና #እውቁ_ጋዜጠኛ_የባልደራስ #ለእውነተኛ_ዲሞክራሲ_ሊቀመንበር ፤ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት አሁንም ድረስ ታላቅ ዋጋ በመክፈል ላይ ላለው #ጀግናው እስክንድር ነጋ #በጎንደር… | By Ethio First | Facebook ጀ/ል ተፈራ ማሞ “ፋኖ በሁለት መንገድ እየተዋጋ ነው“/ ድቡቁ የብልፅግና ስልጠና / “የትግራይ ተፈናቃዮች ይመለሱ “አምባሳደሮቹ
ድል ለአ.ፋ.ሕ.ድ
ድል ለአማራ ህዝብ
ድል ለኢትዮጵያ