መልካም የሴቶች ቀን
የዶሮ ብልት አስራ ሁለት እንዲሆን ልኬቱን የሰሩትን ጥበበኛ ንግስት ተዋወቋቸው፡፡
እቴጌ ምንትዋብ በዙፋን ስማቸው ብርሃን ሞገስ በ1698 ዓ.ም. ከአባታቸው ደጃዝማች መንበር እና እናታቸው ልዕልት እንኮይ ተወለዱ፡፡ ምንትዋብ በ18ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያ ላይ ብዙ አሻራ ትተው የለፉ ንቁ፣ ሃይለኛና ተራማጅ መሪ ነበሩ። ከባለቤታቸው ዓፄ በካፋ ዘመን ጀምሮ እስከ ልጃቸው ዳግማዊ ዓፄ ኢያሱ እና ልጅ ልጃቸው ዓፄ እዮዋስ ዘመን ድረስ ለ40 አመታት የአገሪቱ እኩል መሪ ነበሩ። በዘመናቸው በዓጼ ልብነ ድንግል ጊዜ እንደ ነበሩት እንደ አጼ በዕደ ማሪያም ባለቤት እቴጌ እሌኒ እና እንደ ዳግማዊ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ በቤተ መንግስቱም በህዝቡም ዘንድ የተከበሩና የተፈሩ ነበሩ።
በልጃቸውና በልጅ ልጃቸው ለ40 ዓመት ሲነግሱ ብዙ ዝመን ተሻጋሪ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ተነስቶ በነበረው የቅባት እና ተዋህዶ ክርክር በማስታረቅ በአስተዳደረቸው ዘመን ሰላም ነግሶ ነበር። ብዙ አብያተ-ክርስቲያናትንና ግንቦችን በማነጽ እንዲሁም ብዙ መጻህፍት እንዲጻፉና ከወጭ ቋንቋቆችን ወደአማርኛ እንዲተረጎሙ በማድረግ እውቀት አስፋፍተዋል። ብዙ መጻህፍት በዚህ ዘመን ተጽፈዋል፣ ከአረብኛም ተተርጉመው ወደ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተሰራጩት ብዛት ስፍር ቁጥር የለውም። ለስነጥበብ ከነበራት ትኩረትና ከምታደርገው ድጎማ የተነሳ በዚሁ ዘመን በድንገት የተፈጠረ ልዩ አይነት የሥነ-ስዕል ስራ ተጀመረ። ይህ እንግዲህ እስክሁን ዘመን ድረስ የጎንደረ የስነስዕል ስልት የሚባለው ነው። ከጎንደር ከተማ 3 ኪሎሜትር ራቅ ብሎ በሚገኘውደብረ ፀሐይ (ቁስቋም) ያሰሯቸው ህንጻወች የተሰሩትም በሀገራችን ልጆች በአናጢዎች መሪ በጅሮንድ ኢሳያስ እና አዛዥ ማሞ፣ አዛዥ ህርያቆሳና አዛዥ ናቡተ መሪነት ነበር።
እቴጌ ምንትዋብ ለሙያዎች ከፍተኛ ዋጋ ይሰጡ ስለነበር ሴቶችን አሰባስበው ሙያ ያስተምሩ ነበር። አሁንም ድረስ የእቴጌ ምንትዋብ ሙያ ልኬት ሆኖ ያገለግላል። የወጥ ቤቱን ፣ የቅመማ ቅመም ዝግጅቱን፣ የጠጅና ጠላ ዝግጅቱና አቀራረቡ ጭምር በየዘርፉ ሥርዓቱ እንዲተዋወቅ ጥረዋል። ራሳቸው ጭምር በቀጥታ እየተሳተፉ የተለያዩ የወጥ አይነቶችን በማስተማር ሙያው እንዲያድግ ታትረዋል። የዶሮ ብልት አስራ ሁለት እንዲሆን ልኬቱን የሰሩት እቴጌ ምንትዋብ እንደሆኑ ይነገራል። በቤተ መንግስታቸው አጠገብ ግንብ አስገንብተው ሴቶች በተለያዩ ሙያዎች እንዲሰለጥኑ ይረዷቸው ነበር። ቀጭን ፈትል እንዲፈትሉ፤ ጥልፍ እንዲጠልፉና የአንገትና የጥርስ ንቅሳት ሙያን እንዲማሩ ያተጓቸው ነበር። ባህላዊ የመዋቢያ ጌጣ ጌጦች እንዲዳብሩም አድርገዋል።
ታሪክ ወንግስት ብርሃን ሞገሳ” የሚል አርስት በተሰጠው የእቴጌ ምንትዋብ ዜና መዋዕል እንደሰፈረው ራሳቸው ባሰሯት ቁስቋም ማሪያም ተጠግተው ለሚማሩ ተማሪዎች ትምህርቱን ለማበረታታት እንደ የደረጃቸው ለፊደል ቆጣሪ እንጀራ በወጥ ፣ ለዜማ ተማሪ እንጀራ በወጥ ከአንድ ብርሌ ጠላ ጋር ፣ ለቅኔ ተማሪ እንጀራ በወጥ ከአንድ አንድ ብርሌ ጠጅና ጠላ ጋር እንዲሁም ለትርጓሜ መጽሐፍት ተማሪ እንጀራ በወጥ ከሁለት ብርሌ ጠጅና ጠላ ጋር ከቤተ መንግስት እየላኩ ፤ ልብሳቸውን ከጠገዴ በሚመጣ እንዶድ እያሳጠቡ በማስመረቅ ከከፍተኛ ሽልማት ጋር በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እንዲያገለግሉ ያደርጉ ነበር። በዚህ ተግባራቸው ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት ባልነበሩበት በዚያ ዘመን እቴጌ ትምህርት በሊቃውንት እንዲመራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
እቴጌ ግንቦት 26 ቀን 1765 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም ራሳቸው ባሰሯት በቁስቋም ማርያም በታላቅ ድምቀት ቀብራቸው ተፈጽሟል::
ታሪኩ ከተለያዬ ቦታ የቀነጫጨብኩት ነው።
Sisay M. (Amoraw)
@amorawwuub