>

በሥራ ስም ለጦርነት ማገዶነት

በሥራ ስም ለጦርነት ማገዶነት

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ሰሞኑን በዐዲስ አበባ ባሉ ወረዳዎች ‹‹አስደሳች ዜና ለሥራ ፈላጊዎች›› በሚል ዕድሜአቸው ከ18 እሰክ 25 የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶችን አገዛዙ አሠልጥኖ፣ የኪስ ገንዘብ ጭምር ሰጥቶ ወደ ሥራ እንደሚያሰማራ እየተለፈፈ ነው፡፡

እውን ይኼ ጥሪ በኑሮ ውድነቱ፣ ከቤት ንብረት በማፈናቀሉ፣ በሕገ ወጥ እስሩ፣ በአፈሳው፣ ባጠቃላይ ዕረፍት በመንሣቱ ቁም ስቅሉን ለሚያየው የዐዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት ነው? የዐዲስ አበባ ወጣት አስተውል! ሥራ ያገኘህ መስሎህ እሳት ውስጥ ዘለህ እንዳትገባ፡፡ በቅድሚያ አገዛዙ ይህንን ጥሪ ለምን በዚህ ወቅት አደረገው? ብለህ መርምር፡፡ ፋሺስታዊው አገዛዝ ከግብር አባቱ ከወያኔ የወረሰው የተለመደው ‹‹የምርጫ ግርግር›› አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ ሌላው ከወቅታዊው የአገሪቱ ፖለቲካ ትኩሳት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ምክንያቶቹን እንደ ቅደምተከተላቸው እናያቸዋለን፡፡ 

1ኛ/ ወያኔና ወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ ባሕርያቸው የምርጫ ፖለቲካን የሚያስተናግድ ባይሆንም ባገር ውስጥ የሕዝብን ትኩረት ለመቀየርና ለማጭበርበር፤ ባንፃሩም ‹‹ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ›› ለሚሉት ለታይታ ለሚያደርጉት የተቀነባበረ ድራማ ስለሚረዳቸው፤ በሌላም በኩል ‹‹በሕዝብ የተመረጥን መንግሥት ነን›› ለሚለው ፍጹም ቅጥፈት ይረዳናል ብለው ስለሚያስቡ  እያፈረሷት ባለች አገራችን የሐሰት ምርጫዎችን ሲተውኑ መቆየታቸው የታወቀ ነው፡፡ ለዚህም ተውኔት ባንድ ወገን ሆዳቸውን አምላካቸው አድርገው ገንዘብ ተከፍሏቸው፣ ልዩ ልዩ ገጸ ባሕርያትን ወክለው የሚጫወቱላቸው ሐሳውያን የፖለቲካ ማኅበራትን እና ከርሣም ግለሰቦችን ጠፍጥፈው ያዘጋጃሉ፡፡ አሁንም እያዘጋጁ ነው፡፡ 

በዚህ ፋሺስታዊ አገዛዝ እና ኢትዮጵያ አሁን በምትገኝበት ተጫባጭ ሁናቴ ወደ ‹‹የፓርቲ ፖለቲካ›› ሕይወት ገብቶ ወያኔ፣ ኦሕዴድ/ኦነግ እና የኹለቱ ዘላለማዊ አሽከር ብአዴን ባቆሸሹትና ባርመጠመጡት የዘር ፖለቲካ ውስጥ ዋኝቶ፣ ዐዲስ በሚደራጅ ‹ፓርቲ› ውስጥ አባል በመሆን ለውጥ ለማምጣት እታገላለሁ የሚል ግለሰብ እንዳለ ብትሰሙ ምንድን ነው የሚሰማችሁ? በሕልም ወይም በራእይ ተገልጦለት ይሆን? ማንም ዜጋ ይህን የማድረግ መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ‹‹የኔ ጀግና/እሰይ በጎ አደረግኽ›› ነው የምትሉት? ወይስ በወንጀል የተከሰሰን ግለሰብ ጥፋተኝነት ለማረጋገጥ ዳኞች (judges) እና እንደ ሁኔታው ከተራው ሕዝብ ተመርጠው ለፍርድ የሚቀመጡ ሰዎችን (jurors) አእምሮ ጥርጣሬን በማይተው መልኩ የሚያሳምን (beyond reasonable doubt) በሚባለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቀው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የማስረጃ ሕጋዊ መመዘኛ በመጠቀም ሌላ ያልተገለጠ ዓላማ (hidden motive) እንዳለው ትጠረጥራላችሁ? ዝቅ ሲል የምታደርጉት ይህ የኋላኛውን መንገድ ተከትላችሁ መመርመር ሲሆን፤ የከፋውን የነገሩን አካሔድ ካሰብን ደግሞ ራሱን ለአጃቢነት እያጨ መሆኑን ልንገምት እንችላለን፡፡ ጉዳዩ ሰንበትበት ቢልም እንዲህ ዓይነት ይዘት ያለው ቃለ መጠይቅ ባጋጣሚ አንድ ወዳጄ ልኮልኝ ‹‹ደጃፍ›› በሚባል የማኅበራዊ ሚዲያ አዳምጬአለሁ፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊውም ‹‹የምርህን ነው?›› በማለት ግርምታ የተሞላበት ጥያቄ ሲያነሣ ይደመጣል፡፡ 

ብዙዎች ታዲያ ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው›› ላገር ለሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው ስለሚመጡ ጥቂት የማይባሉ የዋሀንን ሊያስቱ ይችላሉ፡፡ ዛሬ በቃሉ ታምኖ የሚገኝ ሰው የጠፋበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ዛሬ ሰዎችን ባንደበቱ የሚያማልል የተቀደሰ የሚመስል ጉዳይ ሲያወራ የሰማችሁት ግለሰብ ነገ የለየለት ከሃዲ ሆኖ አገርን ከሚያፈርሱ ጐሠኞች ጋር ሲርመጠመጥ ታገኙታላችሁ፡፡

በሌላ መልኩ ‹‹የምርጫ ግርግሩ›› የውሸት የዕድገትና ልማት ፕሮጀክቶች በስፋት የሚወሩበትም ጊዜ ነው፡፡ ፋሺስታዊ በሆነ የጐሣ ሥርዓት የፓርቲ ፖለቲካ የሚባል አይኖርም፡፡ በመሆኑም ተቃዋሚ የሚባሉ ፓርቲዎችም ሊኖሩ አይችሉም፡፡ እቅጩን እንናገር ከተባለ አሁን ያለው የአንድ ዱያታም ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ሲሆን፣ ፈቃዱን የሚፈጽሙ በውስጥ በአፍኣ በማኅበር ወይም በግለሰብነት የተሰባሰቡ ሆዳም አጃቢዎች አገዛዝ ነው፡፡ የሌለ ፍትሕና ነፃነት ባንድ ጀምበር ሊመጣ አይችልም፡፡ ለዓመታት ያልተሠራ ልማት በሐሰት ‹‹የምርጫ ግርግር›› ሰበብ ሊሠራ አይችልም፡፡ ከኵርንችት በለስን አንጠብቅ፡፡

2ኛ/ ፋሺስታዊው አገዛዝ ህልውናው የተመሠረተው ሕዝብና አገርን ፋታ በመንሣትና በየዕለቱ ዐዳዲስ የትኩረት አግጣጫን የሚያስቀይሩ አጀንዳዎች ላይ በመጠመድ ነው፡፡ ዐምሐራውን ለማጥፋት ካወጀው ጦርነት በተጨማሪ፣ የትግራይን ሕዝብ ለኹለተኛ ጊዜ ርስ በርሱ ለማጨፋጨፍ እና በወደብ ስም ከኤርትራም ጋር ጦርነት ለመጫር ዳር ዳር እያለ መሆኑ የሰሞኑ ትኩስ ዜና ሆኗል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ቢፈልግም ባይፈልግም ወያኔ/ሕወሓት የሚባል ገዳይ ነቀርሳ ተሸክሞ ቀጥሏል፡፡ ዐቅሉን የሳተው ርጉም ‹አቢይ› ሥልጣኑን ላንድ ቀንም ቢሆን የሚያረዝምለት ምክንያት ካገኘ ሕዝብም ሆነ አገር ወድሞ ፍላጎቱን የሚያሟላለት ከመሰለው ወደ ኋላ እንደማይል በየጊዜው እየታዘብን ነው፡፡ ፋሺስቶቹ በሚገዙአት ኢትዮጵያ እንኳን ጦርነትን የሚሸከም÷ አንፃራዊ ሰላም ቢኖሮ እንኳን የዕለት ተዕለት ሕይወትን ባግባቡ ለመምራት የሚያስችል ኢኮኖሚ አለመኖሩ የጎላ የተረዳ ጉዳይ ነው፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚባለው ተቋም ፈርሶ ያለ ዓላማ፣ ያለ ፍላጎት፣ ያለ ሥልጠና በግድ ታፍሶ እንዲዋጋ የሚላክ ጥቂት ኃይል ካላ ስንቱ ቦታ እንደሚያደርገው ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ይህ ርጉም ሰውዬ የሚፈልገው ጦርነት ማስጀመሩን ብቻ ነው፡፡ ለቀጣይ የጥፋት ዕቅዱ ጊዜ መግዣ ካገኘ እንደ ስኬት ሊቆጥረው ይችላል፡፡

በሥራ አጥነት ለሚንገላቱት ወጣቶችም የተደረገው የሐሰት ጥሪ የዚህን ዕብድ ሰው የግል ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ ማገዶ ሊሆኑ የሚችሉ ኃይሎችን የማሰባሰብ አንድ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ በመሆኑም ወጣቶች ይኼ የውሸት ጥሪ አማልሎአችሁ ተሽቀዳድማቸሁ የምትመዘገቡ ከሆነ፣ ሩጫችሁ ለጥፋት ሊሆን እንደሚችል ቆም ብላችሁ እንድታስቡበት ወንድማዊ ምክሬን እለግሳችኋለሁ፡፡ ይልቁንም እንደ ሰው ተከብራችሁ ለመኖር የምትፈልጉ ከሆነ ይህን ከሰው በታች ያዋረዳችሁን ፋሺስታዊ አገዛዝ እንደ ሁናቴው ከፋኖ ጋር ተቀላቅላችሁ ወይም ተደራጅታሁ አሊያም በተናጥል በምትችሉት መንገድ ልትፋለሙት ይገባል፡፡ ‹አስደሳቹ ዜና› ለናንተም ሆነ ለወላጆች የልቅሶ የመርዶ እንዳይሆን ልትጠነቀቁ ያስፈልጋል፡፡

‹በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ ገደል ገባህ ወይ› የሚለው አባባል ተግባራዊ እንዳይሆንባችሁ ጥንቃቄ ማድረጉ አስተዋይነት ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic