>

የህክምና ባለሞያዎችን ማስራብ ወንጀል ነው !!

የህክምና ባለሞያዎችን ማስራብ ወንጀል ነው !!

 

አሥራደው ከካናዳ

     

ማስታወሻ : በዚች አጭር መጣጥፌ፤ በመላው ዓለም የህክምና ሞያ አባት፤ ተብሎ በሚታወቀውና፤ የህክምና ባለሞያዎች፤  ትምህርታቸውን  አጠናቀው፤ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት፤ ለሞያቸው ክብር፤ በስሙ መሃላ በሚያደርጉት፤ የመጀመሪያው የህክምና ባለሞያ በሆነው፤ በግሪካዊው ሂፖክራት  ጥቅሶች መንደርደርን መርጫለሁ ::  

መንደርደርያ

  • « Wherever the art of medicine is loved, there is also a love of humanity ».
  • « የህክምና ሞያ በሚፈቀርበት ቦታ ሁሉ፤ የሰው ልጆች ፍቅር ይኖራል » 
  • « Let food be thy medicine and medicine be thy food ».
  • « ምግብ ሃኪም ይሁን፤ ህክምናም ምግብ ይሁን »
  • « Opinion is the medium between knowledge and ignorance ».
  • « መልካም ሃሳብ፤ በማወቅና ባለማወቅ መሃከል አስታራቂ ነው »
  • « Make a habit of two things: to help; or at least to do no harm ».
  • « የሁለት ነገሮች  ልምድ ይኑራችሁ፤ ሌሎችን መርዳትና፤  ቢያንስ ቢያንስ  በሌሎች ላይ ጉዳትን አለማድረስ » 

መግቢያ

ሂፖክራት በእጅጉ የታወቀና የተከበረ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 460 እና 377 ዓ.ዓ መሃከል እንደኖረ የሚነገር ፤ የጥንት የግሪክ ሃኪም ሲሆን፤ የዘመናዊው የህክምና ሞያ አባት እና : መስራች እንደሆነ ታሪኩ ይመሰክራል :: 

ሂፖክራት የተወለደውና ሥራውን የጀመረው : ኮስ (kos) በተባለች የግሪክ ደሴት ላይ ሲሆን፤ የህክምና ትምህርቱንና ሞያውን : በምልከታ ( observation) እና በህክምና  (treatment) ላይ በመመስረት : ህክምና ሳይንሳዊ ይዘት እንዲኖረው እንዳደረገ ታሪኩ ይናገራል ::

ሂፖክራት፤ በዚህ ብቻ ሳያበቃ፤ የህክምና ባለሞያዎች፤ የህክምና ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ፤ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት፤ ስለህክምና ሞያቸው የሚገቡትን መሃላ ጭምር ያዘጋጀ ፤ እሱ እንደሆነ ይታወቃል ::

ሂፖክራት የመጣጥፌ መነሻ፤  እንዲሆን የመረጥኩበት ምክንያት፤ በአገራችን በኢትዮጵያ፤ የሚገኙ የህክምና ባለሞያዎች፤ በደሞዛቸው ማነስ የተነሳ፤ ተራብን  ብለው ቢጮሁ፤ የሚሰማ ጆሮ በማጣታቸው፤ ሥራ በማቆማቸው፤ የሚደርስባቸውን መዋከብና እስራት፤ ለመቃወምና ህዝብ አብሮ : ከጎናቸው እንዲቆም ለመጠየቅ ነው ::  

 በአገራችን ኢትዮጵያ፤ የህክምና ባለሞያዎች ( ዶክተሮች፤ ነርሶች፤ ድሬሰሮችና ተጓዳኝ ባለሞያዎች)  እራበን ብለው ሥራ ማቆማቸው፤ ለሁላችንም ብሔራዊ ውርደታችን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል ::  ለዚህ የጋራ ውርደት ያበቁን፤ ደንቆሮዎቹ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኖች ሲሆኑ፤ አብዛኞቹ  የጤና ባለሞያዎች የተማሩትን፤ እሩቡን  ያህል እንኳ ዕውቀት ሳይኖራቸው፤ ከድሃው ህዝብ የተሰበሰበውን ግብር፤ መቀራመት አልበቃ ብሏቸው፤ የሚቀጥለውን ሁለትና ሦስት ትውልድ በብድር እየዘፈቁ፤ ክትፎ የሚያማርጡ፤ ውስኪ እንዳሻቸው የሚጨልጡ፤ መኪና የሚለዋውጡ፤ በቅንጦት ቤት ውስጥ የሚንደላቀቁት፤ ደናቁርት ተረኞች ነን ባዮቹ : የዘርና የጎሣ ፖለቲከኖች ናቸው :: 

የበደል ግፉ እንዲከመር፤ ጭቆናው እንዲንሰራፋ፤ የመከራው ዘመን እንዲራዘም፤ አዘራፊና ዘራፊ በአገርና በህዝብ ላይ እንዲፈነጩ፤ ………… ወዘተ. ያደረግነው እኛው እራሳችን ነን ::

ሰው ሲፈናቀል ዝም ! ሰው ያለምክንያት ሲታሰር ዝም ! ሰዎች በድሮን እየታሰሱ በቦንብ ሲፈጁ ዝም !  በርሃብና በበሽታ ሲጨርሱት ዝም ! ሲታመም ዝም ! ሲሞት ዝም !  ዝም !……….. ዝም !……….ዝም !….. የዝምታ ትውልድ !! የዝምታ ሞት !!  

ኤድያ ! በዚች ዓለም አንዴ እንጂ: ሁለቴ ጊዜ ላይኖር : ይህ ሁሉ ፍራቻ ምንድነው ?!  በዝምታ: የሞትን ተራ  ቆሞ መጠበቅ !!

አቤት የትዕግስታችን ብዛቱ !!  ትናንት ትዕግስት ! ዛሬ ትዕግስት ! ነገም : ወደፊትም ትዕግስት !!  ………….ትዕግስት !………… ትዕግስት !!……….. ትዕግስት !! የህይወት ኡደት የሌለበት : እንደ ኩሬ ውሃ የረጋ ትዕግስት !!  

« የረጋ ውሃ ይገማል !! »  ብሏል በዓሉ ግርማ :  

እኛ በዝምታችንና በፍርሃታችን: ከረጋ ውሃ በባሰ: አጉል አጉል መሽተት ብቻ ሳይሆን፤  ጠንብተናል :: 

ጥንባታችን : ከራሳችን አልፎ መጪውን ትውልድ አፍንጫውን ሰንጎ : በክሎታል፤ አበስብሶታል :: 

  • በኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ : ማን ነው የህክምና ትምህርት የሚያጠና ?!
  • በኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ : ማን ነው አስተማሪ ለመሆን የሚመኝ ? 
  • ሁሉን አደንቁሮ : ትውልድ በማምከን፤ አገር መግደል ከዚህ በላይ ምን አለ ?!  

የህይወት ገል : የቁም ሟቾች ፍርክስክስ !! 

ጥላቻቸውን ሲያንቧርቁብን : አቅፈናቸው እናድራለን፤ ሲገላምጡን : እንገለፍጣለን፤ ስንሰደብ : እናጨበጭባለን፤  ጥቃትን እንደ ካባ ሲደራርቡብን: ደርበን እንጎማለላለን፤ ትከሻችን በደልን ለመሸከም ተለማምዶ በቃኝን አያውቅም ፤ ታዲያ እነሱ ምን ያድርጉ ?!  :: 

በገዛ እጁ እራሱን ያዋረደ ህዝብ ፤ የማንም ባለጌ እየመጣ፤ እንደ ቂሌ ሲለጋው፤ እንደ ኳስ ሲጠልዘው፤  ወፍራም ቆዳ አብቅሎ ፤ ጀርባውን ለዱላ እየሰጠ፤ ዝም የሚል ከሆነ ፤ ለበደሉ መንስኤው እራሱ እንጂ ሌላ ማን ሊሆን ?! 

ለህክምና ባለሞያዎች ብቻ ሳይሆን፤ ህዝብ ለራሱ ህልውና ሲል፤ ከህክምና ባለሞያዎች ጎን  በመቆም ፤ ይህን ዘረኛና ጎሠኛ ሥርዓት ከትከሻው ለማውረድ፤ በቃ !! በማለት ትግሉን ሊቀላቀል ይገባል ::  

የህክምና ባለሞያዎች ረሃብ: የሁላችንም ረሃብ ነው !!

ከህክምና ባለሞያዎች ጎን ቆሞ፤ ይኸን ዘረኛና ጎሠኛ ሥርዓት: በቃ!! የማይል፤ ሞቱን በቀጠሮ የሚጠብቅ የቁም ሟች ነው !! 

 

ፍትህ ለተራቡ የህክምና ባለሞያዎችና ለመምህራን !!

ፍትህ በኑሮ ውድነት ለሚሰቃየው ድሃው ህዝባችን !!

ፍትህ በጦርነትና በርሃብ ለሚያልቁት ወገኖቻችን !!

ፍትህ ያለ ርህራሄ ከመኖሪያ ቤታቸው ለሚፈናቀሉት ወገኖቻችን !!

ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም   (27/05/2025)

Filed in: Amharic