‹‹በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብአዊነት ማገልገል›› – የሥላቅ ጥግ
ከይኄይስ እውነቱ
በርእስነት የመረጥሁትን ኃይለ ቃል ወይም መርህ ተጽፎ ያየሁት ‹‹የፌዴራል ፖሊስ›› ሠራተኞች ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ነው፡፡ ሥላቁ ግርምት ቢፈጥርብኝ አንድ ሁለት ቃል ለመጻፍ አሰብሁ፡፡ በቃል የተገለጸውም አሳብ እነሆ፡፡
ርጉም ዐቢይ ካፈራረሳቸውና ካዋረዳቸው የኢትዮጵያ ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ነው፡፡ የአገር መከላከየ የለ፣ የፖሊስ ሠራዊት የለ አሽመድምዶታል፡፡ ወያኔ ሕወሓት ‹ክልል› የተባለ የአትድረሱብኝ አጥር ወይም ‹የከብት ጋጣ› ካዋቀረ በኋላ ብሔራዊ ስሜት ያለው፣ ሀገርን ከጠላት ሕዝብን ከጥፋት የሚታደግ የኢትዮጵያ የሚባል ሠራዊት የለንም፡፡ በተቃራኒው ቢያምንበትም ባያምንበትም ዓላማ ቢስ ሆኖ፣ ለፋሺስት አገዛዞች አድሮ ዳር ድንበራችን ሲደፈር፣ ሀገር-ጠል አገዛዞች መሬታችንን በባዕድ ኃይላት ሲያስወስዱ፣ ኢትዮጵያውያን የጋምቤላ ተወላጅ አኝዋኮችን በገዛ አገራቸው ባይተዋር አድርጎ ቁም ስቅላቸውን ሲያሳይ፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲያደርግ፣ ግማሽ ሚልዮን የሚጠጉ የደቡብ ሱዳን ኑዌሮችን ለሥልጣን ዓላማ ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ሰጥቶ ሲያሰፍር፣ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ባለውለታ ካስማና ዋልታ የሆነው የዐምሐራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋትና ዘር ማጽዳት የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጽም፣ የሲቪልና የሃይማኖት ተቋማትን ሲያወድም፣ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ከብቶችን በጦር መሣሪያ ሲፈጅና በማሳ ላይ ያለና ጎታ የገባ እህል ሲያቃጥል አባሪ ተባባሪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የጉራጌ ማኅበረሰባችን፣ የጋምቤላ ሕዝባችን፣ የአፋር ሕዝባችን፣ የትግራይ ወገኖቻችን ሌሎችም የፋሺስታዊው ኃይል አባሪና ተባባሪ በሆነ ሠራዊት ግፍና በደል ገፈት ቀማሾች ከመሆን አላመለጡም፡፡ የመጠን ጉዳይ ካልሆነ በዚህ አገር አጥፊ አገዛዝ ያልተነካ የአገራችን ክፍልና ሕዝብ የለም፡፡ የጐሣ ሥርዓቱ አለመተማመንን እና ልዩነትን አንግሦ ኅብረት ባይኖርም፣ ግፍና በደል እንዲሁም መግለጫ የሌለው የኑሮ ውድነቱ ካላስተባበረውና ካልተነሣ ባርነትን መርጦአል ከማለት በቀር ሌላ ማለት አይቻልም፡፡
በዚህ ጽሑፍ የማነሳው ሌላው ሠራዊት ፖሊስ ነው፡፡ በወያኔም ሆነ በወራሹ የርጉም ዐቢይ አገዛዝ ‹የፖሊስ ሠራዊት› የተባለ ኃይል ከስም በስተቀር የለም፡፡ እጅግ የሚያሳፍርና በማናቸውም ብሔራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ሠራዊት አባል ሰብእና እና ተቋማዊ አደረጃጀት መለኪያ የዘቀጠ፤ አፅራረ ሕዝብ የሆኑ የነፍሰ ገዳዮች፣ የዘራፊዎች፣ የአሸባሪዎች፣ ሕግና ሥርዓት የሌላቸው መረን የለቀቁ ወሮበሎች መሰባሰቢያ ሆኗል፡፡ ተቋሙ ባጭሩ ወንጀል ሊከላከል፣ የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ ሊያስጠብቅ ይቅርና በተቃራኒው የወንጀል መፈጸሚያ ድርጅት (criminal enterprise) ሆኗል፡፡
በተለይም በመዲናችን በዐዲስ አበባ የሚገኘው በፖሊስ ስም የሚጠራው ኃይል ድንቊርናው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዐዲሳቤና በከተሜ ጠልነት ተሰብኮ፣ በዘር ጥላቻ ሰክሮ፣ በጠላት ወረዳ እንደሚገኝ ተነግሮት ለዝርፊያና ለግድያ እንዲሰማራ ከየገጠሩ የተሰባሰበ ኃይል ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር በተጠቀሱት የሠራዊት ተቋማት ውስጥ አባል መሆኑ በራሱ የሚያሳፍር ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ያላት የጦር ኃይል የፋሺስታዊው አገዛዝ ‹ቅጥረኛ› ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ተራው አባል ለእንጀራውና ለቤተሰቡ ብሎ፣ የአገዛዙ በሆኑ ኃላፊዎችና ‹ደኅንነት ኃይሎች› እግር ተወርች ታስሮ ነው የሚል ምክንያት የሚያቀርብ ካለ÷ እንኳን ለታጠቀ ኃይል ለተራውም ሕዝብ አይሠራም፡፡ አገር እየጠፋ፣ ሕዝብ እያለቀ፣ የመጨረሻ መጠጊያው ሃይማኖቱ እየተደፈረ ‹አለሁ› ብሎ የሚቀጥል ሠራዊትም ሆነ ሕዝብ የተፈጠረበትን ዓላማ የዘነጋ፣ ባርነትን ገንዘቡ ያደረገ፣ ለራሱም ለቤተሰቡም የማይጠቅም የቁም ‹ሬሳ› ነው፡፡ በወያኔም ሆነ በውላጁ ፋሺስታዊ አገዛዝ በየትኛውም ክፍል ለሚገኙ የሠራዊት አባላት የሚሰጠው ማዕርግ በአመዛኙ ጐሣን መሠረት ያደረገ ስጦታ እንጂ በአገልግሎት ብቃት፣ በአመራር ብስለት፣ በጀግንነት ወዘተ. የተገኘ አይደለም፡፡ ላንድ ምርኮኛ ‹መጋቤ ዐሥር አለቃ› የመጨረሻውን ወታደራዊ የፊልድ ማርሻልነት ማዕርግ የሚሰጥ እንደ ርጉም ዐቢይ ያለ አእምሮውን የሳተ ጉድ ብቻ ነው፡፡ ይህም አስቀድሞ የጠቀረሸ ታሪኩን ይበልጥ የሚያጠለሽ እንጂ በዚህ የጥፋት ዘመን ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ወታደራዊ ማዕረግ ያለው ሰው ነበራት የሚያስብል አይደለም፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ብሔራዊ ውርደት መሠረቱን የጣለው ያለጥርጥር ጠንቀኛ ‹የጐሣ ‹ፖለቲካን› በኢትዮጵያ ምድር የዘራው ወያኔ ሕወሓት ነው፡፡ አገራችን በሌላት ዐቅም ከሕግ ውጭ የ‹ክልል ኃይል› ብሎ፣ መደበኛ ፖሊስ ያይደለ፣ ‹መደበኛ የጦር ሠራዊት› የሚመስል ኃይል በየመንደሩ ፈጥሮ ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን አድርጓል፡፡ ይህ ‹ሽፍታ› ኃይል ነው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ወልደው ከብደው ኑሮአቸውን መሥርተው ከኖሩበት የአገር ክፍል እንደ መጻተኛና ወንጀለኛ በመቊጠር ሲገድል፣ ሲያፈናቅልና ቤት ንብረታቸውን ሲያወድም የኖረው፣ አሁንም የቀጠለው፡፡ ዓላማውም በየአካባቢው ሕዝብን ማፈንና ለጐሣ አገዛዙ ተገዢ ማድረግ ነው፡፡
ዛሬ የትኛው የፖሊስ ኃይል ነው የሕዝብን ሰብአዊ መብቶች አክብሮ የሚንቀሳቀሰው? አንድ ሰው በወንጀል ተከሶ በዳኝነት አካል ጥፋተኛ እስከሚባል ድረስ በንጽሕና የመገመትን ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መርህ (principle of presumption of innocence) በመጣስ በወንጀል ጥፋተኛ ያልተባለን ሰው በገዛ ፈቃዱ ወንጀለኛ ብሎ እህል ውኃ በሚያስጨርስ ቆመጥ የሚቀጠቅጥ÷ በጫማው የሚረግጥና አካል የሚያጎድል÷ ከአንደበቱ በሚወጣ ነውረኛ ቃል ሕዝብን የሚዘልፍና የሚያዋርድ ÷ የሚያስርና ለማየትና ለመስማት የሚሰቀጥጥ ስቃይ የሚፈጽም÷ አልፎ ተርፎም የሚገድል፤ የሀገር መለያ ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ያዛችሁ÷ በነጠላ÷ በቀሚስ÷ በእጅ ጠባብ÷ በልዩ ልዩ አልባሳት ላይ አደረጋችሁ÷ በሰውነታችሁ ላይ ተነቀሳችሁ ወይም ሣላችሁ ብሎ በጥይት የሚመታ ኃይል፤ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣ ሕዝብ (በወያኔም ሆነ በተዋራጁ መብት መሆኑ በተግባር ተሠርዟል) ላይ የሚተኩስና የሚገድል ኃይል፤ ቤተ ክርስቲያንን እና መስጂድን የሚደፍር፣ በነዚህም የእምነት ተቋማት ገብቶ አማንያን የሚገል÷ የእምነት አባቶችን ካህናትን መነኮሳትን በጠራራ ፀሐይ የሚደበድብ÷ የሚያዋርድና የሚገድል ኃይል፤ ስለ መልካም አገራዊ አገልግሎትህ እናከብርሃለን እናመሰግናለን የሚባል ሳይሆን ሕዝብን የሚያስደነብርና የሚያስፈራራ ኃይል፤ የሕዝብ ወዳጅና አጋር ሳይሆን ጠላት የሆነ ኃይል፤ ከሕግ ተላላፊዎች ጋር አብሮ የሚሠራ ኃይል፤ ከላይ እስከ ታች በንቅዘት ተበልቶ ያለቀ ኃይል፤ እንዴት ሆኖ ነው ‹‹በሰብአዊነት ማገልገል›› እሤቱ÷ መርሁ የሚሆነው? እንዲህ ዓይነቱ የላሸቀ ኃይል ምንን ነው በጀግንነት የሚጠብቀው? ጀግንነትም ሆነ ሰብአዊነት በፋሺስታዊ አገዛዞች በተደራጀውና የፖሊስ ስም በተሰጠው የውንብድና ተቋም መዝገበ ቃላት የማይታወቁ እሤቶች ናቸው፡፡ በተቋሙ ተሽከርካሪ ላይ ያየሁት መርህ ታላቅ ሥላቅ የሆነብኝም ተቋሙና አባላቱ መርሁ ከሚያነሣቸው እሤቶች ጋር ሐር ዐምባና ቆቦ ስለሆኑብኝ ነው፡፡
በኢትዮጵያችን ላይ ሠልጥኖ የሚገኘው ፋሺስታዊ አገዛዝ በሕዝብ ኃይልና በእግዚአብሔር ቸርነት ሲወገድ (መወገዱ ጥርጥር የለውም) የፋሺስቶቹ የወንጀል ፍሬ የሆነው እንዲህ ዓይነቱ የወንጀል ተቋም ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ከሚያስፈልጋቸው ብልሹ ተቋማት አንዱ ሊሆን እንደሚገባው ጥርጥር የለውም፡፡ ሁሌም እንደምለው ከአገር አጥፊዎች ጋር ካለመተባበር ጀምሮ እያንዳንዱ ዜጋ አገሩን በማዳንና ሕዝብን በመታደግ ረገድ የየራሱ ድርሻ አለው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እግዚአብሔር አምላክ ከፈቀደ ስም የሌለው ዜጋ አስነሥቶ አገርን ለውጦ ታሪክ መሥራት ይችላል፡፡