>

ባቡሬና ምርጫ [እንግዳ ታደሰ - ኦስሎ]

የኢሃዴግ/ወያኔ ደጋፊዎችን ይህ የአስፋልት ላይ ባቡር ሰሞኑን እጅግ አድርጎ እንዳስደሰታቸው በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች እየተመለከትን ነው፡፡ በልማቱ ሁሉም ተጠቃሚ ስለሆነ በዚህ ላይ የሚያለያየን ነጥብ የለም፡፡ ጉዳዩ ግን ለየቅል ነው፡፡ይህ መንግሥት እጅግ አድርጎ ከሚጠላቸው ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ጋር በዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመንም ሊወደዳደራቸውና ሊገዳደራቸውም እየሞከረ ነው፡፡

በመጀመርያ ደረጃ ዕቅዱና ፕላኑ የኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዕቅድ ነበር፡፡ ስልጣን ባይከዳቸው ኖሮ ! ህንድ አገር ሄደው ከህንድ መንግሥት ጋር በተፈራረሙት የአስር አመት ፕላን ብለው ካቀዱት ውስጥ የሚጠቃለል ነበር ፡፡ ወያኔ በለስ ቀንቶት ስልጣን ከያዘ ወዲህ በተለይ የምርጫ 97 ምርጫ ብዙ ትምህርት ስለሰጠውና የአረቡም የጸደይ አብዮት ማስገምገም ስላስፈራው አፍ ማዘጊያ ከላይም ከታችም እያለ ! ቻይና ላይ እንደ ቴምብር ተለጥፎ በከፍተኛ ብድር ኋላ ቀር በሆነ የቻይና ፕላን አዲስ አበባን እንደ በርሊን ግንብ ሁለት ቦታ ከፍሏት ! ጎረቤቶች የላይ እናውጋና ፥ የታች እናውጋ ሰፈርተኞች ሆነው ፣ ሞባይሉም ስለማይሠራ ድሮ ልጆች ሆነን በክብሪት ሳጥን ክር አስረን ሃሎ ! ሃሎ እንደምንለው ቡና በክብሪት ሳጥን እየተጠራራን ነው ያለኝ ሰው አጋጥሞኛል ስልክ አገር ቤት ደውዬ ፡፡

እጅግ ያሳቀኝም ! እጅግ ያሳዘነኝም ተጨማሪ ቀልድ ደግሞ ይህ ነበር ከአዲስ አበባ በስልክ ያገኘሁት ፡፡ የእንትና አባት ሞተዋልና ስልክ ደውለህ ያጽናህ በላቸው ፡፡ በቀብራቸው ላይ እንደ ነዋሪነታቸው ብዙ ሰው አልተገኘም ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እድር ጠሪው ጋሽ አረሩ ! የበርሊን ግንብን ተሻግሬ ጥሩንባ እንድነፋ ከተፈለገ በኪሎሜትር ይከፈለኝ አለበለዚያም ለሞባይሌ ካርድ ይሞላልኝና ለላይ እናውጋ ሰፈር sms ልላክላቸው ማለቱ ነበር፡፡ የባቡሩ አጥር ሰፈራችንን ሁለት በመግመሱ አንድ የነበረው ቀበሌ በቻይና መሃንዲስ ሁለት ሰፈር ሆኖ በመቀንጠሱ ነበር ፡፡ ሙሴ ሚናስ ነበሩ ድሮ መንገድ በመቀየስ አገር ያፈረሱት ? ግጥሙ ተዘነጋኝ ፡፡

የዚህን ባቡሬ ጉዳይ ጉድ ለማንበብ ከፈለጋችሁ ያለፈውን ቅዳሜ አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጎብኙ ፡፡ በሙስና እና በቻይና ስሪት እንደላቦራቶሪ አይጥ ቤተ ቻይና ሙከራ መሆናችን ያሳዝናል ፡፡ በተለይ ለምርጫ ፕሮፓጋንዳ ሲባል ፣ ኃይለማርያም ቀዳማዊት እመቤቱን አስከትሎ በመትረየስ ታጅቦ እዛችው ጋቤጣ ትራም ውስጥ ሲገባ ጋዜጠኛው ያሾፈበት ቃል ተጨምሮ የእየሱስ ወታደር ነኝ የምትለዋን መፈንፈሳዊ መዝሙር ኃይለማርያም መዝሙሯን እንድትደበዝዝ   አድርጓታል፡፡  አሁን ወደ ባቡሩ ጠቅላይ ሚንስቴር መለሰ ዜናዊ እየገቡ ነው ያለው ጋዜጠኛው ?

እንኳን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለሌላው የምእራብ አገር አይታመኔ አይታሰቤ ወደ ሆነ ጉዳይ ልውሰዳችሁ ፡፡ እዚህ ኖርዌይ ውስጥ ባጠቃላይ እስካንዲኔቭያ ውስጥ ማለት ይቻላል ፡፡ በአደባባይ ላይ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚንስቴር ትከሻ ለትከሻ ተገፋፍቶ መሄድ ይቻላል ፡፡ ብስክሌት እያሽከረከረ በአጠገባችሁ ያለ አጃቢ ሲሄድ ማየት የሚገርም ጉዳይ አይደለም ፡፡ ለዚህ ማሳያ አንድ ፎቶ ከነታሪኩ ላቅርብላችሁ ፡፡ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ-1973 ዓ.ም በጥቁርና ነጭ የተነሳው ፎቶ የሚያሳያችሁ የቀድሞው ንጉስ ሆኩን የክረምት በረዶ ውድድር ለማድረግ ሆልመን ኮለን ተብሎ ወደ ሚጠራው ከፍተኛ የበረዶ መንሸራተቻ ሰፈር በ አስፋልቱ ላይ ባቡር ወይም ትራም ተሳፍረው ሲያቀኑ ነው ፡፡ አጠገባቸው ያለችው በዚያን ጊዜ ወጣት የነበረችው ሴት የተሳፈረችው ማዬስቱዋ ተብሎ ከሚጠራው ፌርማታ ነበር ፡፡ ከማን ጋር እንደተቀመጠች የምታውቀውም ነገር አልነበረም ፡፡ ንጉሱ አጀብም የላቸው ፡፡ ኧንደውም ትኬት ተቆጣጣሪው የከፈሉበትን ትኬት እንዲያሳያቸው እየጠየቀ እንዳለ ምስሉ ይታያል ፡፡

King Harald & King Olav in Oslo tram በሁለተኛው የከለር ፎቶ ላይ ደግሞ የምታዩት አሁን በንግስና ላይ ያሉትን የኖርዌይ ንጉስ ሃራልድን ነው፡፡ ከአጠገባቸው ደግሞ አሁን የተቀመጠችው ከቀድሞው ንጉስ ጋር አብራ የተቀመጠችው ወጣት ሴት አሁን ደግሞ አሮጊት ሆና ከአሁኑ ንጉሥ ጋር ነው፡፡ ይህም ለክብሯ ሲባል ተፈልጋ መጥታ ነው ፡፡ ይህ አሁን የተቀመጡበት የአስፋልት ላይ ባቡር የቀድሞው የባቡር ሃዲድ እንዲስፋፋ ተደርጎ ስድስት ተቀጣጣይ ፉርጎ  በአንድ ጊዜ ጉዞ 9000 ሺህ ህዝብ ይዞ ወደ ተራራማው ሆልመን ኮለን ሰፈር ሲሄድና ሲመረቅ የሚያሳይ ፎቶ ነው ፡፡ የመትረየስ ጋጋታ አታዩም እዚህ ፎቶ ላይ ፡፡ እንኳን የመትረየስ ጋጋታ እንደሌሎቹ የምዕራብ አገር ፖሊሶች የኖርዌይ ፖሊስ ሽጉጥ ታጥቆ መሄድ አይፈቀድለትም ፡፡ ጸባየ ሰናይ የሚለው የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ኖርዌይ ውስጥ ደግሞ ተደጋግሞ ቢሰማ ኖርዌይ ይገባታል የሚያሰኝ ነው ፡፡

የባቡሬ አድናቂዎች ! አድናቆታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ ! ለምርጫ ሲባል ብዙ የተደሰኮረላት ባቡር ከነ-እንከኗ አልቃ አገልግሎት እስክትሰጥ ድረስ ጉራ ባትነሰንሱ መልካም ነው ፡፡ እርሷም እንደ ሲኖትራክ ሰው እየፈጀች ህዝባችንን እንዳትጨርስብን ጸሎታችንን ማጥበቅ ነው ፡፡ ለመሆኑ የባቡሯ ስም ማን ተባለ ?

Filed in: Amharic