>

አፋሕድ፣ አፋብኃ፣ አፋጎ እና የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል እለታዊ እይታ!!

አፋሕድ እና አፋብኃ አንድ ይሆናሉ። አለቀ። የሚያስፈልገው አንድ ማንኪያ ቅንነት ብቻ ነው

አርበኛ ዘመነ ካሴ

አፋሕድ፣ አፋብኃ፣ አፋጎ እና የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል እለታዊ እይታ!!!

 

ወንድወሰን ተክሉ

 

  1. ዛሬ በእለተ ኪዳነ ምህረት (ነሀሴ 16 የፍልሰታ ጾም መፈሰኪያ እለት – አርብ ባይሆን ማለቴ ነው) በአርበኛ ዘመነ ካሴ በኩል የተላለፈን ባለ አንድ ገጽ አጭር ግን ትልቅ ቁም ነገር የጨበጠን መልእክትን ሁላችንም ያነበብንበት እለት ሆነ። መልእክቱ ግሩም ነው። ድንቅ ነው። ለወራት ምናልባትም ለአመታት የጮህንለትን አማራዊ አንድነትን ጥሪ ያስተጋባ ተስፋ ሰጪ መልእክት ነው።

ባለፈው ግንቦት ወር ላይ በቃራ የተመሰረተው አማራዊው አፋብኃ ድርጅት መመስረቱን ባበሰረ ማግስት አፋሕድ ያስተላለፈውን የአብረን በአንድነት እንታገልን ጥሪ የአፋጎው መሪ አርበኛ ዘመነ ካሴ ዛሬ ላይ ምላሽ በሰጠበት መልእክቱ ለአማራዊ አንድነት ጥሪውን አስተላልፋል።

በአጭሩ አርበኛ ዘመነ ካሴ አፋብኃ በቅጡ ጤናማ ሆኖ ይሰራል – ይህ ማለት አፋጎም ወደ መሰረተው ድርጅት ተመልሶ ይሰራል ማለቱ ሲሆን ለጥቆም አፋሕድ እና አፋብኃ አንድ ይሆናሉ።አለቀ። የሚያስፈልገው አንድ ማንኪያ ቅንነት ብቻ ነው በማለት ትክክለኛውን መፍትሄ አስቀምጣል።

ይህ ጸሀፊ በዚህ ባጋመስነው ነሀሴ ወር መግቢያ ላይ አፋሕድ፣ አፋብኃ፣ አፋጎ እና የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል አሁናዊ ሁኔታ በሚል ዳሰሳዊ ዘገባ በሶስቱም ድርጅቶች ውስጥ ያለን ችግሮች ነቅሶ በማስቀመጥ የህልውና ትግሉ ቅርቃር ውስጥ ገብታል በማለት መግለጹ ይታወሳል። የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል በሶስቱ አማራዊ ድርጅቶች ውስጣዊ ችግርና ድክመት ምክንያት ቅርቃር ውስጥ ገብታል ብዬ ብገልጽም ካቀረብኩት የመፍትሄ ሀሳብ ውስጥ ባለ ስድስት ነጥብ የሶስቱን አማራዊያን ፋኖ አደረጃጀቶችን የጎኒዮሽ ውጊያን የሚያስቆምና በምትኩም ድርጅታዊ ህልውናቸውን ጠብቀው በጋራና በአንድነት በጠላታችን ፋሺስታዊው የብልጽግና መንግስት ላይ የምንዘምትበትን ፕላትፎርም – ወይም – ቀመርን ያስቀመጠ የመፍትሄ ሀሳብ አቅርቤ ነበር።

በተመሳሳይ መልኩ ቀደም ብሎ በአፋሕድ፣ ለጥቆም በአፋብኃ በኩል የአንድነት ጥሪ ተላልፎ ከአፋጎ በኩል ብቻ ቀርቶ ነበር። በዚህ መካከል ውድ ዋጋ ያስከፈለንን ውስጣዊ ግጭት በጎንደር፣ በወሎና በሸዋ ሲፈጸም አይተናል። ድርጊቱም ተስፋ የሚያስቆርጥም መስሎ ነበር። ይህን መሰረት በማድረግ የህልውና ትግሉ በክፍተኛ አደጋ ላይ ወድቃል የሚሉ አማራዊን ድምጽ እጅግ በርክቶም ነበር።

ዛሬ ከአፋጎ የሰማነው መልእክት ይህንን አደጋን የተገነዘበ እና የችግር አካል መሆን ሳይሆን የመፍትሄ አካል ልሁን በሚል ቁርጠኝነት የቀረበ የአንድነት ጥሪ መሆኑን አይተናል።

ልክ ነው። በተናጥል ታግለን አይደለም አራት ኪሎ አባይንም መሻገር ያዳግተናል። ያለ አንድነት ትግሉ ብርቱ ዋጋ የሚያስከፍል፣ የአማራን ህዝብ ሞራል በእጅጉ የሚጎዳና መጨረሻም ላይ የህልውና ትግሉን ከድል የሚያርቅ መሆኑን ሁላችንም ጠንቅቀን የተረዳነው ሀቅ ነው።

ለአንድነቱ ትልቅ እንቅፋትና ተግዳሮት በመሆን ላለፉት ሁለት አመታት የዘለቀው የአርበኛ ዘመነ ካሴ መራሹ የአፋጎ ድርጅት ይህን አደጋ ተረድቶ እና አቃሙን አሻሽሎ ዛሬ ላይ መፍትሄው አማራዊ አንድነት ነው ብሎ በይፋ መምጣቱ ይበል የሚያስብልና የሚደገፍ ነው።

ሀሳቡ የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ሆኖ ተፈጻሚ እንዲሆን መላው የአማራ ህዝብ እንደየ አቅሙና እንደየድርሻው ሚናውን መወጣት አለበት። በዚህ ሁለት አመት ተለያይተን ተጉዘን ያገኘነው ድል ሳይሆን በየእለቱ ወደ ሃላ ቁልቁል መጋዝ ሆናል። መጀመሪያ ይህ የቁልቁለት ጉዞ መቆም አለበት። ለዚህ ደግሞ ለአንድነቱ ጥሪ ዘግይቶ የነበረው በአርበኛ ዘመነ ካሴ የሚመራው አፋጎ ነበር። ዛሬ ባስተላለፈው አጭር ባለ አንድ ገጽ መልእክት ይህን መለየትን የሚሰብር የአንድነት ጥሪ አስተላልፋል። ጥሪውን ሁላችንም በመተግበር አንጻር መረባረብ አለብን።

ይህ ጸሀፊ Almost ከአመት ከስድስት ወር በሃላ ለመጀመሪያ ግዜ አርበኛ ዘመነ ካሴ ብሎ የጻፈበት እለት ሆናል። የአርበኛውን ጥሪ ከአማራ ህዝብ የህልውና ትግል አንጻር ተስፋ ሰጪ መፍትሄ መሆኑን በመቀበል ግጭቱ፣ ትችቱ፣ ነቀፋውና ውግዘቱ ግላዊ ሳይሆን ህዝባዊ በመሆኑ ዛሬ በእጅጉ ስተቸው፣ ሳወግዘው የነበረ ሰው ከህልውና ትግሉ አንጻር የአንድነት ጥሪ ሲያስተላልፍ ዛሬ ያስተላለፍከውን መልእክት ተግብር በሚል አቃም ድጋፌን እሰጠዋለሁ እንጂ በትናንትናው አቃሙ ላይ ተመስርቼ ላወግዘው አይገባኝም።

ሁላችንም ማወቅ የሚገባን አንዱ ሌላኛውን ጥሎና አግልሎ ብቻውን ታግሎ ማሸነፍ አይችልም። አበቃሁ።

ድል ለአማራ ፋኖ
ድል ለአማራ ህዝብ

 

 

Filed in: Amharic