>

የድህነት ጌቶች፤ መንትዮቹ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋማት

የድህነት ጌቶች፤ መንትዮቹ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋማት

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

መንትዮቹ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ያልኋቸው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund) እና የዓለም ባንክ (World Bank) ተብለው የሚታወቁት እ.አ.አ.ጁላይ 1944 በብሬተን ውድስ ጉባኤ በሀገረ አሜሪቃ ኒው ሐምፕሸር ግዛት የተቋቋሙትን ድርጅቶች ነው፡፡ ከተቋቋሙ 8 ዐሥርታትን ያስቆጠሩት እነዚህ ተቋማት በግልጽ የተቀመጠው ዓላማቸው ‹‹ዘመናዊ የኢኮኖሚ ትብብርን በመፍጠር ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ልማትን ለማምጣት›› የሚል ነው፡፡ የአይ ኤም ኤፍ ትኩረት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ሥርዓትን ለማረጋጋት፤ ባንኩ ደግሞ ለመልሶ ግንባታ እና ለልማት ፕሮጀክቶች ብድር ለመስጠት እንደሆነ ይነገራል፡፡

ታዲያ እነዚህ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አንድ ክፍለ ዘመን ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ምን ዓይነት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ/የፋይናንስ ሥርዓት ፈጠሩ? የኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ልማትን በየአገራቱ አመጡ? ተቋማቱ ግንኙነት በፈጠሩባቸው አገሮች ሁሉ ዕድገት፣ ልማትና ብልጽግናን አስገኙ? በነዚህ አንኳር ጥያቄዎች ላይ የኢኮኖሚ ሊቃውንት/ጠበብት ነን በሚሉ ሁሉ (የእኛንም ሰዎች የአገር ተቆርቋሪዎቹም ሆኑ አእምሮአቸውን በምዕራቡ አስተሳሰብ ቅኝ ያስገዙት አብዛኞቹን ጨመሮ) እንደየአመለካከታቸው አያሌ ቅጾች እንደተጻፉ ጥርጥር የለም፡፡በዚህ ዙሪያ በርካታ ንድፈ አሳቦች፣ ትንተናዎች አልፎ ተርፎም የአስተሳሰብ አድባራት (ስኩል ኦፍ ቶውትስ) እንደሚኖሩ አስባለሁ፡፡ የአሁኑ አስተያየት አቅራቢ ግን የኢኮኖሚ ሊቅ/ጠቢብ አይደለሁም፡፡ ሞያዬም ከዚህ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ በንድፈ አሳቦቹም ሆነ ትንታኔዎቹ ላይ ፍላጎት የለኝም፡፡ በጽሑፌም የኢኮኖሚ ሊቃውንት ነን የሚሉትን መጻሕፍትና ኅትመቶች በመረጃና ማስረጃነት እያጣቀስሁ ትንተና ለመስጠት ዐቅሙም ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ጊዜዬን በዚህ ለማባከንአልፈልግም፡፡ ስለሆነም አሳቤን ሙያዊ ባልሆነ ተራ ቋንቋ ለማስተላለፍ እሞክራለሁ፡፡

ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ባለቤት አልባ በሆነችው፣ ደናቊርት ፈላጭ ቆራጮች በፈነጩባት፣ ከአርባ ዓመት ወዲህም አገር በማፍረስ የተጠመዱ ዘረኛ ፋሺስቶች የሠለጠኑባት አገሬ ኢትዮጵያ ከነዚህ ምዕራባውያን ተቋማት ምን አተረፈች የሚለው ግን እንደ አንድ ተራ ኢትዮጵያው ዜጋ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡ እነዚህ ተቋማት አብዛኞቹን አዳጊ አገራት የቤተ ሙከራ አይጥ በማድረግ ሁሉንም ለማለት በሚያስደፍር ሁናቴ በድህነት ላይ ድህነት ማምጣታቸው ለዓለም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የሚያስቀምጡአቸው ቅድመ ሁኔታዎች በአገራት የውስጥ ጉዳይ  ጣልቃ በመግባት ዘላቂ ቀውስንና አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በ‹ሰብአዊ መብት› ስም የርኵሰት ጫፍ የሆነውን ግብረ ሰዶማዊነትን እንዲቀበሉ የሚያስገድዱ አንቀጾች በንግድ ስምምነቶች ውስጥ እየሰነቀሩ ነው፡፡

እንደኔ አመለካከት ለፖለቲካ ፍጆታ የሚቀናበሩ የሐሰት ቊጥሮችንና ስታቲስቲክስ መተንተን ሳይሆን ያፈጠጠ ያገጠጠ መሬት ላይ የሚታይ መሪር እውነታን በመታዘብየኢኮኖሚ ጠቢብነቱ ሳያስፈልግ አያሌ ቅጾችን መጻፍና እስኪታክተን መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የሚጻፈውም ተሐዝቦትን ለማካፈልና ለሬከርድ ዓላማ ብቻ ሲሆን፣በምንገኝበት የግልብነት ዘመን የሚናገሩ አንደበቶች እንጂ የሚያዳምጥ ዦሮ የሚያስተውል ልቡና እንደሌለ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡

ለጽሑፌ ዓውድ ለመስጠት ያህል ዛሬ የምንገኝበት ዓለም አቀፍ ሥርዓት ደጋግሜ በሌሎች ጽሑፎቼ እንደገለጽሁት ጉልበት/ጡንቻ የነገሠበት (ጉልበት ትክክል ነው ተብሎ የሚታመንበት)፣ በተግባር ሕግን መሠረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ሥርዓት የሌለበት፣ ሥርዓተ አልበኝነት የነገሠበት፣ የሞራልና የእምነት ልጓም የጠፋበት፣ በሥልጣኔ ስም የምዕራባውያን ርኵሰት የናኘበት፣ በምሥራቁም ተመሳሳይ አዝማሚያ የሚታይበት፣ ዓለም አቀፍ የሚባሉ እንደ ተ.መ.ደ. ያሉ ጥርስ የሌላቸውና የምዕራቡን ጥቅም ለማስጠበቅ በምዕራባውያኑ የተቋቋሙ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ከጥቅም ውጭ የሆኑበት፣ በውስጥ ባሉ ደም መጣቾችና በዚህ ጽሑፍ በጠቀስናቸው ዓለም አቀፍ የምዕራቡ የፋይናንስ ተቋማትጣልቃ ገብነት በርካታ አገሮች ጥልቁ የድህነት በርባሮስ የወረዱበት፣ ለጉልበተኞቹ ሲባል የተፈጥሮ ሀብታቸውና የሰው ኃይላቸው ብቻ ለዝርፊያና ለዘመናዊ ባርነት የሚፈለጉበት፣ በሁሉም ዓይነት የእምነት÷ የሞራልና ሰብአዊነት መለኪያዎች ለሰው ልጅ መኖሪያነት የማይመች ሰይጣናዊ ዓለም በምዕራባውያኑና ተባባሪዎቻቸው የተሠራ እጅግ ኢፍትሐዊ÷ ኢርቱዐዊ÷ ኢግብረገባዊ ዓለም አቀፍ ‹ሥርዓት› ውስጥ እንገኛለን፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በአገራችን በኢትዮጵያ ላለፉት ግማሽ ምዕት የዘለቀው ዓለም በሙሉ ፊቱን ያዞረበት ሰቆቃ ዋናው ማሳያ ሲሆን፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎችም ተመሳሳይ ሰቆቃዎች በስፋት የሚታዩበት ዓለም ውስጥ እንገኛለን፡፡ ያለማጋነን በርእሰ መጻሕፍቱ ለቀደሙት ሰዎች በኖኅ ዘመን እንደተነገረው (ከዛም በላቀ መልኩ) እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለምን ፈጠርሁ ብሎ ዳግም የሚጸጸትበት ዘመን አድርጌ እውስደዋለሁ፡፡

በእንቅርት ላይ ዦሮ ደግፍ እንዲሉ በዘረኛ ፋሺስቶች የምትታመሰው አገራችን ኢትዮጵያና በፍጹም ሰቆቃ የሚኖረው ሕዝቧ፣ የነዚህ የመንደር ጉልበተኞች የማያቋርጥ ጥፋት ሳያንሰን፤ ግብርና÷ የማምረቻ ኢንዱስትሪ÷ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ የሚከናወኑ አንዳች እንቅስቃሴ በሌለበት አገር፤ ከአንዱ ክ/ሀገር ወደ ሌላው በሰላም ተንቀሳቅሶ ሥራ በማይሠራበት አገር ባጠቃላይ የቅርቡን እንኳን ወስደን ላለፉት 7 ዓመታት ስለ ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ቀርቶ ቃሉን መናገር በማይቻልባት ኢትዮጵያበብርሃን ፍጥነት አገር ማንነቷ÷ ያጸኗት አዕማድ ተነቃቅለው በፈረሱባት÷ ነባር መልካም ታሪኳ፣ ብሔራዊ ተቋማቷና ቅርሶቿ÷ መንፈሳዊና ባህላዊ ዕሤቶቿ ተሸርሽረው እያለቁ ባሉባት አገር፤ የተፈጥሮ ሀብቷና አንዳንድ ቅን ዜጎች ያፈሩት ሀብትና ንብረት በአገዛዙ ሰዎችና (በኦህዴድ/ብአዴን) እና አገራችንን ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ባበቃው ወያኔ ሕወሓትበጠራራ ፀሐይ በሚዘረፍባት አገር፤ ዘረኛነት ባመጣው ጦስ በጦርነት÷ በጅምላ ጭፍጨፋ÷ በረሃብ÷ በመፈናቀልና በስደት ሕዝብ በሚያልቅበት አገር፤ ተወዳዳሪ በሌለው በኑሮ ውድነት ጨንገር ቁም ስቅሉን የሚያይ ሕዝብ ባለበት አገር፤ እንዲህ ዓይነት ግፍና በደል በሚፈጸምበት ሕዝብ ስም ከጠቀሰናቸውና ከሌሎችም አገራት የሚመጣው ብድርና እርዳታ ከአገር በሚሸሽበትና ለጥቂቶች ጥቅም በሚውልበት አገር ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የሚባሉት ተቋማት ምን እያደረጉ ነው? ብድር የሚሰጡት ለማን ነው? ምን ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችንስ ነው የሚያስቀምጡት?

የሕዝባችሁን ሰብአዊ መብትና ነፃነት ገፋችኋል ነውቅድመ ሁኔታው? ገንዘቡን ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ወደ ውጭ አሽሽታችኋል፣ ለግል ጥቅማችሁ አውላችኋል ነው?ሕዝባችሁን ለመጨፍጨፍ ለድሮንና ለመሣሪያ መግዣ አውላችኋል? አስፈላጊውን ቅደም ዝግጅት ሳታደርጉ ሕዝባችሁን በጠላትነት ፈርጃችሁ ከቤት ንብረቱ አፈናቀላችሁ ዐውላላ ሜዳ ላይ ጥላችሁታል÷ አገር አልባ አድርጋችሁታል ነው?ከሕግና ሥርዓት ውጭ ከዐቅም በላይ የሆነ ግብርና ቀረጥ ጥላችሁበታል በግለሰብ የባንክ ሂሳብ እንደፈለጋችሁ ታዙበታላችሁ÷ የባንክ ግብይት ምስጢራዊነት አይጠበቅም÷ ባንኮች አገዛዙ ባደራጃቸው ማጅራት መቺዎች ይዘረፋሉ ነው ቅድመ ሁኔታው? በምግብ ሸቀጦች ላይ ግብር እየጣላችሁ ሕዝብ በጠኔ እንዲያልቅ እያደረጋችሁ ነው ወዘተ. በዚህም የ‹‹ወርቅ ዕንቊላል›› የሚጥለውን ሕዝብ በየትኛውም መስክ በነፃነት ተንቀሳቅሶ እንዳይሠራ ካደረጋችሁት በኋላ፣ ምርትም አገልግሎትም በሌለበት ሁናቴ የግብርም ሆነ በመሠረታዊ አገልግሎቶች (ውኃ፣ ኤሌክትሪክ ወዘተ.) ላይ ዦሮን ጭው የሚያደርግ ከሕግና ሥርዓት ውጭ ክፍያ ቆልላችሁ ነገ ተነገ ወዲያ መክፈል ሲያቅተው፣ መግቢያ መውጫ ስታሳጡትና ወደ ጠርዝ ስትገፉት ከቊጥጥር ውጭ በሚፈጸመው ዓመፃ(አሁንም አብዛኛው አቅቶታል) በአገር እና በቀጣናው ላይ የሚመጣውን ከፍተኛ ቀውስ አስባችሁታል ወይ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች አይደሉም በነዚህ የምዕራብ ተቋማት የተቀመጠው፡፡ ባንፃሩም በተለያዩ የሥራ መስኮች ጠባይን ለማረም/ለማስተካከል የሚጣሉ ቅጣቶችን (ከሕግና ሥርዓት ውጭ የሕግ አስከባሪ አካላት የሚላቸውን ‹ወሮበሎች›ተጠቅሞ ‹ሆን ብሎ› በጉልበት ቅጣት የሚጥል) እንደ ግብር መደበኛ የገቢ አርእስት አድርጎ የወሰደ አገዛዝን የውንብድና ተግባር የሚያርም ቅድመ ሁኔታ አለ ወይ? ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ መልሱ የለም ነው፡፡ ምክንያቱም የነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ዓላማ ሕዝብና አገር ተጠቃሚ እንዲሆን አይደለምና፡፡

ምዕራባውያኑ ለፈጠሩት ኢፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት አገሮችን ደካማ አድርጎ ለባርነት በማመቻቸት ሀብታቸውን ለመዝረፍ እና ባጠቃላይ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሥርዓታቸውን እነሱ በሚፈልጉት አቅጣጫ ቅርፅ ለማስያዝ መሣሪያ ሆኖ ማገልገል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እኛን ጨምሮ (የእኛ የከፋው አገዛዞቹ ዘረኛ ፋሺስቶች መሆናቸው ሳያንስ በሕዝብ ጥላቻ የሰከሩና አገር ለማፍረስ ሌት ተቀን እየሠሩ መሆናቸው) የአፍሪቃ አገሮች አገዛዞች አሳዳሪዎቻቸው ምዕራባውያኑ ሲሆኑ፣ ሥልጣን ላይ የመቆየት ዋስትና እስከተሰጣቸው ድረስ ሕዝብን ለባርነት÷ አገርን ለቅኝ ግዛትና ለውርደት አሳልፈው ለመስጠት የማያንገራግሩ ናቸው፡፡ በቅርብ ዓመታት የፈረንሳይ መንግሥት በምዕራብ አፍሪቃ አገሮች ያሳየው ዓይን ያወጣ ከቀድሞ የቀጠለ የቅኝ ግዛት ተግባር ለምዕራባውያኑ ፍላጎት ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በቅርቡ ኢትዮጵያን በሚመለከት እ.አ.አ. ጁላይ 2025 ባወጣው ዘገባ IMF COUNTRY REPORT 25/188 ለአገዛዙ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ብድር ለመልቀቅ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች አገራችንና ሕዝባችን የሚገኙበትን በተወሰነ መልኩ እላይ የጠቀስኋቸውን እጅግ አስከፊ ገጽታዎች አንዱንም ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ የጸጥታ ችግርን በስሱ ቢያነሳም፣ አገዛዙ እገዛዋለሁ የሚለውን ሕዝብ በማንነቱ ምክንያት የዘር ማጥፋትና ጅምላ ጭፍጨፋ እየፈጸመ መሆኑ ሚዛን የሚደፋ ብድሩን የሚያስከለክል ቅድመ ሁኔታ ሆኖ አልቀረበም፡፡ በመሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ የታየው ቅጥ ያጣ ጭማሪ፣ በቀላጤ በየጊዜው የሚያሻቅበው ሕገ ወጥ የግብር ጭማሪ፣ የጥቁር ገበያውን የውጭ ምንዛሬ ንግድ ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ተቆጣጥረውት ሳለ፣ ‹በሕጋዊ መልኩም› የውጭ ምንዛሬ ግብይት እንዲሠሩ የፈቀዱላቸው ኪዮስኮችም ከአገዛዙ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ሆነው ሳለ፣ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሬ ጋር የተያያዘውን ችግር የፈጠረው አገዛዙ ሆኖ ሳለ፣ የብር የመግዛትን ዐቅም ዋጋ አሳጥቶ ተራ ወረቀት ያደረገው አገዛዙ ሆኖ ሳለ፣ ባጠቃላይ ኢትዮጵያውያን በለየለት የድህነት ዐዘቅት ውስጥ ከሰው በታች እንዲኖሩ ያደረገና አንድ ሐሙስ በቀረው አገዛዝ (ያመከናቸውንና በሕይወት ልምድ ያለዘቡና፣ ካገር ፍቅር የተራቆቱ ‹ኩታራዎችን› ሰብስየነሱን ፍላጎት ስለፈጸመ ብቻ) የተጠቀሱትን ርምጃዎች እንዲወስድ የተደረገው በነሱ ምክረ ሃሳብ (ሬኮመንዴሽን) መሆኑ ከሪፖርቱ መረዳት ይቻላል፡፡ በዜጎች መከራና ስቃይ ፋሺስታዊ የሆነን የጐሠኞች አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም መሞከር በምድርም ሆነ በሰማይ ይቅር የማይሉት ወንጀልና ኀጢአት ነው፡፡ ተቋማቱ ይህንን እያደረጉ ነው፡፡

በነገራችን ላይ አገዛዙ በአገራችንና በሕዝቧ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግዙፍ ወንጀሎች ከእነዚህ ተቋማት የብድር አሰጣጥ ፖሊሲና ቅድመ ሁኔታዎች ጋር በማያያዝ በጥቂቱ ለማንሳት የሞከርሁት በእንቅርት ላይ ዦሮ ደግፍ ስለሆኑብን እንጂ የኛን የቤት ሥራ እነሱ እንዲሠሩልን አይደለም፡፡ እንዲሠሩልንም አይጠበቅም፡፡ ከዓላማቸውም ጋር በእጅጉ ተቃራኒ ነው፡፡በቊስላችን ላይ እንጨት አትስደዱብን ለማለት እንጂ፡፡ ዱርዬ የሆነው አገዛ በናንተ እገዛ ጭምር መከራችንን እንዲያራዝም ከማድረጋችሁና በድህነታችን ላይ መክበሩ ሳያንስ እናንም የድህነት ጌቶች መሆናችሁን አቁሙ ለማለት ነው፡፡ ድንበር የዘለለው ወንጀልና ርኵሰት በምድርም ሆነ በሰማይ እውነተኛ ፍርድ የሚያገኝበት ጊዜ ሳይመጣ አይቀርም፡፡ ወገኔ በስንፍና ‹ሬሳ› ሆነህ ከቀጠህ የዘራኽውን ማጨድህ የማይቀር ነው፡፡ ‹ነፃ አውጪ› አትጠብቅ፡፡ ራሱን ነፃ አላወጣምና፡፡ አንተንና አገሩን ከወሬ በስተቀር በተግባር መነሻውና መድረሻው አላደረገምና፡፡ ክፋትህን ሳትተው ለይስሙላ የምታደርገው ጸሎት አንዳች ግዳጅ አይፈጽምምና፡፡

Filed in: Amharic