>

ሞታችንን ግማሽ መንገድ ሂደን ለመቀበል ዝግጁ ነን

ሞታችን ግማሽ መንገድ ሂደን ለመቀበል ዝግጁ ነን 

እንደ መቅድም፥

በትግሉ የእድሜ ስሌት ምራቅ ዋጥ ያደረግን ነን ብለን እናምናለን እና ለጦራችን እና ለህዝባችን ብቻ ስንል ብዙዉን ነገር በዉስጣችን እንይዘዋለን። 

የአፈና ትዕዛዙ በሚዲያ ስለሆነ ምላሹም በሚዲያ ይሁን ከሚል የተሰጠ ምላሽ

 

ፋኖ ጌራወርቅ ወርቁ ዳኝው

እኛ የነፃነት እና የፍትህ ሃይሎች ነን፤ ስልተ መንገዳችንም ሰብዓዊነት ያልሸሸዉ ወታደርነት ነዉ። የፍትህ ዋጋ ዉድ መሆኑንም እንረዳለን፤ ዘርዓ ያዕቆብ በበኩር ልጃቸዉ ላይ ሞት የፈረዱበት፣ ጌታዉ አካለ ወልድ የብዕራቸዉን ሽልማት በሂዎት ለሌሉት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሰጡበት፣ ንጉስ ሚካኤል የምግቡን ገበታ በአዳራሹ በር ያስቀደመጡበት፣ ተድላ ጓሉ የላይኛዉን ሰፈር ለቀጥቃጮች ሰጥተዉ ታችኛዉን የመረጡበት፣ ምክናያቱ፥ ለፍትህ ሲባል እንደሆነ ጠንቅቀን እናዉቃለን። ስለሆነም በከንቱዎች የሚመዘዝን ሰይፍ ፈፅሞ አንፈራም፤ የምንፈራዉ ከከንቱዎች ወገን ሆነን ህዝባችን ካለቀሰ እና ጦራችን ተነጥሎ ከተበላብን ብቻ ነዉ፤ ያኔ ፈራሹ ገላችን ብቻ ሳይሆን ህያዊት ነፍሳችን ማቃሰቷ የማይቀር ይሆናል። 

እኛ ያልነዉ፦ በወርዳችን እና በቁመታችን ልክ እንሰፋ፥ ለአንድነት ቅድሚያ እንስጥ ነዉ፤ እኛ ያልነዉ የነበሩ የአንድነት ጉባኤዎች ይገምገሙ እና የችግሩን ትንተና ሰርተን መፍትሄ እንፈልግ ነዉ፤ እኛ የጠየቅነዉ ስለ አንድነቱ የሚወሰነዉም ሆነ አንድነቱ የሚፈርሰዉ በሁለት ግለሰቦች ነዉ፥ በሁለት ግለሰቦች ችግር ምክናያት ጦራችን እና ህዝባችን ተለይቶ አይመታብን፥ ለህዝባችንም የመለያያ ድንበር አይበጅለት የሚለዉን ነዉ፤ እኛ ያልነዉ ፕሮግራም ይኑረን፣ አላማችን እንወቅ፣ የሁኔታ ትንተና እንስራ፣ የሚያስማማ ርዮት ዓለም እንቅረፅ፣ ስትራቴጅክ ሰነድ የተባለዉ መነሻ ታሪክ የአክሱም ስልጣኔ አይሁን ነዉ፤ እኛ የጠየቅነዉ ከጓድ መሪዉ እስከ ክፍለ ጦር አመራር ያለዉ፣ በእየ ጊዜዉ እየተገማገመ እና አደረጃጀቱን እየፈተሸ ወይንም ሪፎርም እየሰራ ስለ እዉነት ለነፃነት እና ለፍትህ እየተዋደቀ፣ አንድ አመት ከሰባት ወር ሙሉ  በጫካ ስልጣን የሚጣላዉ የዕዝ አመራር አደረጃጀቱን ይፈትሽ እና በጦሩ ፊት ምክርቤቱን ይፋ አድርጎ ሪፎርም ይስራ ነዉ፤ እኛ ያልነዉ የትምህርት ጉዳይ መፍትሄ ይበጅለት፣ ትግሉ ሃያ አመት ቢጠይቅ ሃያ አመት ሙሉ ትምህርት ቤት ልንዘጋ ይቻለናል ወይ የሚለዉን ነዉ።….ወዘተ 

እንግዲህ ይሄን ማለት ወንጀል ከሆነ? እንሰቀል፤ የእኛ መሰቀል የህዝባችን ስቃይ እና የጦራችን አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል የሚያቆስመዉ ከሆነም ይግባኝ ማለትን አንፈልግም። ፍትህን ግን ለአንድ አመት ከሰባት ወር ሪፎርም ካልሰሩ የስልጣን ጥመኞች እና ስለስማቸዉ ከማይጨነቁ ስም ሰጥቶ ገፊዎች አንጠይቅም፤ ሁሉን የሚያዉቀዉ ጦራችን ጉዳያችን ይመልከተዉ እና ብይን ይስጥ፤ ህዝባችንም ይታዘብ፤ እኛም ሞታችን ግማሽ መንገድ ሂደን እንቀበል። 

የግርጌ ማስታወሻ፦ ከላይ የተነሱ ሃሳቦችን በሙሉ በዉስጥ አንስተን ያልተመለሱ ናቸዉ፤ ወደ ሚዲያ የመጡት፥ የአፈና ትዕዛዙ በሚዲያ ስለሆነ ምላሹም በሚዲያ ይሁን ከሚል ነዉ።

Filed in: Amharic