>

የአፋሕድ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት እዝ እና የአፋብኃ በላይ ዘለቀ እዝ የመስማሚያ ስድስት ነጥቦች-!!

የጠላትን ቅስም የሰረው የአፋሕድ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት እዝ እና የአፋብኃ በላይ ዘለቀ እዝ የመስማሚያ ስድስት ነጥቦች-!!

የጎንደር የመስማሚያ ነጥቦች ለአጠቃላይ አፋሕድ እና አፋብኃ መስማሚያ መሰረት የጠሉ የመስማሚያ ነጥቦች ናቸው!!!

ጋዜጠኛ ወንድወሰን ተክሉ

በትናንትናው እለት በጎንደር በሁለቱ አደረጃጀቶች መካከል ለወራት የዘለቀውን የጎኒዮሽ ግጭት ያስቀረ ባለ ስድስት ነጥብ የመስማሚያ ሀሳቦች ላይ ተስማምተው በመፈራረም መላውን አማራ አስደስተዋል።   ስምምነቱ እንዲህ በቀላሉ የተደረገም አልነበረም። ለግዜው ስማቸውን በማንጠቅሳቸው  ሶስት ወሳኝ ሽማግሌዎች ያለሰለሰ ትጋትና ጥረት ወንድማማቾቹ  የመስማሚያውን ሀሳብ ተቀብለው ለመፈራረም ቢበቁም በሁለቱም ዘንድ ያሉ ወይም ከሁለቱ ጀርባ ሆነው ይህ ስምምነት እንዳይፈጸም በብርቱ የጣሩ ግለሰቦች እንዳሉ መታወቅ አለበት። እነዚህ ግለሰቦች ዛሬም ሆነ ነገ ይህንን ስምምነት በመጻረር፣ በመቃረንና የስምምነቱን ይዘትና ትርጉም በማዛባት ተግባር ላይ የሚተጉ በመሆናቸውም ሁላችንም በንቃትና በቅርበት ልንከታተላቸው ይገባል።

ከሳምንታት በፊት አርበኛ ሻለቃ መከታው ማሞ እና አርበኛ ዝናቡ ልንገረው ሁለቱን የጎንደር አርበኞች ራስ አርበኛ ደረጀ በላይ እና አርበኛ ሀብቴ ወልዴን  ስማቸውን ለግዜው መጥቀስ ከማንፈልገው ሶስት ሽማግሌዎች ጋር ሆነው በማነጋገር በአስቸካይ ግጭቱን እንዲያቆሙ የሚያስችል የመጀመሪያ ዙሪ ስምምነት Preliminary Agreement እንዲስማሙ ማድረጋቸውን መግለጼ ይታወሳል። በዚህ የመጀመሪያ ዙር ስምምነት ከሁለቱም ወገን ሶስት ሶስት አባላትን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ንግግሩ እየተካሄደ ባለበት ሂደት ከአፋሕድ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት እዝ  ፋኖ ጌታ አስራደ እና ከአፋብኃ በላይ ዘላቀ እዝ ፋኖ አስቻለው ከኮሚቴው ተቀን ሰው በአዲስ እንዲተኩ ከተደረገ በኃላ  የሁለቱ ድርጅቶች ለቀናት የዘለቀ ውይይትና ድርድር ካደረጉ በኃላ ባለ ስድስት የመስማሚያ ነጥብ ላይ ተስማምተው ፊርማቸውን በማኖር በትናንትናው እለት ስምምነታቸውን ለመላው የአማራ ሕዝብ ይፋ አድርገዋል።

ስድስቱ የመስማሚያ ነጥቦች 

-፩ኛ- ድርጅታዊ ሕልውናቸውን ጠብቀው በጋራ እና በአንድነት ጠላትን መታገል

-፪ኛ- የጎንደርን ምድር ለሁለቱም ድርጅቶች  ነጻ የመንቀሳቀሻ ቀጠና ማድረግ ( ይህ የእኔ ቀጠና ነው በዚህ መንቀሳቀስ አትችልም የሚሉትን የጸብ ምክንያቶችን ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ደፍኖ ሁለቱም ድርጅቶች መንቀሳቀስ በሚችሉትና በሚፈልጉበት ቀጠና በነጻነት መንቀሳቀስ)

-፫ኛ-ዳግም አንዱ በአንዱ ላይ መግለጫ አለማውጣት

፬ኛ-  የጥቁር አስፓልት -ከባሕርዳር ጎንደር ትልቁን አውራ ጎዳን በስተቀር በሌሎች መንገዶች ላይ የቀረጥ ስብሰባን ስራ ማስቀረት ። ( ይህ አንድን አማራ በአፋሕድ እና በአፋብኃ እኩል በአንድ ግዜ ከመቀረጥ ያዳነ ስምምነት ነው)

-፭ኛ- ከሁለቱ ደጅቶች አንደኛው የመንገድ መዝጋት አዋጅ ለማወጅ ሲወስን አዋጁን ከማወጁ በፊት ለአቻው ድርጅት ቀድሞ ማሳወቅ

-፮ኛ- ከሁለቱ ድርጅቶች የተውጣጣ ባለአስር አባላት ኮሚቴ ያለው (ከአፋሕድ ፭ እና ከአፋብኃ ፭  አባላት የተውጣጡ) የጋራ ኮሚቴ መስርቶ Check and balance እየተቆጣጠሩ ጎን ለጎን እኩል በጋራ መታገል በሚሉ ስድስት ነጥቦች ላይ በመስማማት የጋራ ኮሚቴም አቋቁመዋል።

አፋሕድ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሲያደርግም ሆነ በተመሳሳይ አፋብኃም ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሲያደርግ አንደኛው ለአንደኛው ድጋፍና ሽፋን የመስጠትን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተውበት ሁለቱም ድርጅቶች በስምምነት የደመደሙትን ውይይትና መግባባትን ፈጥረዋል። 

ሁለቱ የጎንደር ድርጅቶች እናት ድርጅቶቻቸውን አፋሕድ እና አፋብኃን በተመለከተ በጎንደር የፈጠሩትን ድርጅታዊ ህልውናቸውን ጠብቆ በአንድነት ጎን ለጎን ለመታገልና ቀጥሎም በሂደት ወደ ሁለንተናዊ አንድነት ለመምጣት እኩል በጋራ እንደሚሰሩ ከስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን በመካከላቸው ለሚነሳ ማንኛውም አይነት ችግር በእነዚህ አምስት ኮሚቴዎች  አማካይነት በጋራ ለመፍታት ከስምምነት ላይ ደርሰው ውይይታቸውን በሚያስደስት ሁኔታ ደምድመዋል።
♦ ♦ ♦

ይህ በእንዲህ እንዳለ የስምምነቱ ዜና ያስደነበረው ጠላት በጀግኖቻችን ላይ መጠነ ሰፊ የከበባ ማጥቃት ስራ የከፈተ ሲሆን በአስደናቂ ተጋድሎና መስዋእትነት ከበባውን በጣጥሰው  በድል ወጥተዋል።

Filed in: Amharic