>
5:18 pm - Sunday June 15, 3760

ወደ ኀላ እንጓዝ ...ትላንትን እንደዛሬ ሳስታውሰው.... [ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል]

Eskindir Nega, Serkalem, Nafkotእነእስክንድር ነጋ በፌዴራሉ ከፍተኛ ” ፍ/ቤት” የተወሰነባቸው ፍርድ “አግባብ አይደለም” ሲሉ፣ ለጠቅላይ “ፍርድ ቤት”ይግባኝ ብለው፣ ጠቅላዩም፣ ነገሩን በግዜ ቀጠሮ ሲጎትተው ከርሞ ለመጨረሻ ግዜ የተቀጠረበት ዕለት። ሚያዚያ 26/2004 ሀሙስ። ይህች ቀን ታሪክ የሚሰራበት አልያም ታሪክ ራሱን የሚደግምበት።

የጠቅላይ ፍ/ቤት በር የተከፈተው ጠዋት 2፡30ላይ ነው። ብዙ ባለጉዳዮች በግቢው ውስጥ ወዲህ ወዲያ ይላሉ። ሁሉም አንድ ነገር ይሻሉ -ፍትህ!ፍትህ! …(ፍትህ የምትለዋ ቃላት በ3ፊደል ሲፃፍ መቅለሉ)

እኔና ጓደኞቼ 3ኛ ወንጀል ችሎት በር ላይ እንገኛለን። ወደዚህ ችሎት ብዙ ሰው በመምጣት ላይ ነው። የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ እነማን እንደመጡ፣ማን ከማን ጋር እንደተጨባበጠ በዓይነ ቁራኛ የሚከታተሉ “ጠጉረ-ልውጦችም ” አብረውን ናቸው።

“ዛሬስ ምን ይወሰን ይሆን?”
“ዛሬም ፋይሉን መርምረን አልጨረስንም ነው የሚሉት…”
“መወሰን አቅቷቸው እኮ አይደለም ትዕዛዝ እስከሚቀበሉ ነው”…አብረውኝ የነበሩት ጓደኞቼ ናቸው የራሳቸውን ግምት የሚያስቀምጡት….

3፡15 አካባቢ….አንድ ነጭ ሚኒባስ ችሎቱ በር አካባቢ መጥቶ ቆመ። ከ2እና 3 ደቂቃ ባልበለጠ ግዜ በሩ ተከፈተ። በውስጡ የተጠቀጠቁት ፖሊሶች መሳሪያቸውን እንዳነገቱ ወረዱ።
መጨረሻ ላይ ሁለት ሰዎች በአንድ ካቴና የታሰሩ ወረዱ። አንዱዓለም አራጌና እስክንድር ነጋ ነበሩ። የእስክንድር አንድ እጅ፣ከአንዱዓለም አንድ እጅ ጋር በብረት ተጠፍሯል። ባልታሰረው እጃቸው፣ ችሎቱ በር ላይ ለቆምነው ሰላምታ አቀረቡልን።

በአፈሙዝ የተከበቡት አንዱዓለምና እስክንድር ችሎት ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ። ከትንሽ ደቂቃ በኋላ የችሎቱ ታዳሚም መግባት ጀመረ። ችሎቱ ከመጥበቡ የተነሳ ከ20ሰው በላይ የመያዝ አቅም የሌለው ነበር። ብዙዎች መቀመጫ አጥተው በር ላይ ለመቆም ተገድደዋል። እኔና ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን በአንድ ወንበር ላይ ለሁለት ተቀምጠናል። (ወሴ ሁለታችንም አርበ- ጠባብ መሆናችን ሳይጠቅመን አልቀረም)

ብዙም ሳይቆይ”ዳኞች”ተሰየሙ።

“ምን ይሉ ይሆን?”…የልብ ትርታዬ ፍጥነቱን ጨመረ።ድው፣ ድው፣ድ ው.. ..ያንተ ያለህ!
የመሀል ዳኛው እንዲህ ሲሉ ጀመሩ፦
“እንግዲህ የሚወሰነውን መቀበል አለባችሁ።ፋይሉን መርምረን ጨርሰናል።ውሳኔውን እናሰማለን”.. . ፊት ለፊታቸው የተቀመጠውን ውሃ ጎንጨት እያደረጉ ንባባቸውን ቀጠሉ።

ስሜቴ ተደበላልቋል።አንዴ እንደመደንገጥ፣አንዴ እንደመናደድ፣ስንቱን አስተናገድኩ….
“ማርያምዬ..ምን ልላት እንደነበር ሳላውቀው፣ቅዱስ ገብርኤል…ለእሱም ምንም አላልኩም፣የሰፈሬ ታቦት ቅዱስ ጊዮርጊስ….መልዓክቶቹ ተሰባስበው”ምን እንታዘዝ?”ቢሉኝ? መልሴ ምንም ነበር።

አሰልቺ ንባብ። በሀሰት የተሞላ ዶሴ። ስቀለው ስቀለው የበዛበት። ጆሮዬን ለ”ዳኛው”ንባብ፣ ዓይኔን እስክንድር ላይ ተክያለሁ። አልፎ አልፎ ዓይን ለዓይን ግጥም እንላለን። በአውራ ጣቴ “አይዞህ” የሚል ምልክት አሳየዋለሁ። አፀፌታውን ፈገግ በማለት ይገልፃል።
” 7ኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ ከግንቦት 7 ዓመራሮች በተሰጠው ተልዕኮ…” ዓቃቤ ህጉ በክስ መዝገቡ ያላነሳውን “ደጋጎቹ ዳኞች” ጨመሩበት። ….ማጠቃለያውንም የተፈረደበት 18 ዓመት እንደማይበዛበት በመግለፅ ንግግራቸውን ረገጥ አድርገው “ይፅናበት” ሲሉ ደመደሙ።
እንግዲህ እንዲህ ጨክኖ ሲመጣና ቁርጣችንን ስናውቀው፣ ሲረብሸኝ የነበረው ስሜቴ ብን ብሎ ጠፋ። ልቤ ደፈረ፣እንደውም ፀብ ሁሉ አማረው።
ሳላስበው ችሎቱ ውስጥ” እስክንድር ጀግና ነህ ” ጮክ ብዬ ተናገርኩ። እረ በዚም አልበቃኝ…”ዛሬ አንተ አሸንፈሃል፣የኔ ጀግና ብትሞትም አይቆጨኝ” ደገምኩ …
“ዝም በይ፣ውጭ”…የሚለኝን ፌዴራል ፖሊስ ለግዜው ከምንም አልቆጠርኩትም። ፈሪ ከደፈረ ማለት እንደኔ ነው….

ይህች ዕለት ሁልግዜም በውስጤ ትኖራለች…የነበረው ነገር ሁሉ እንደትላንት ይታየኛል። ይሄ ውሳኔ ከተሰጠ 3ዓመት ሊሞላው 4ቀናት ቀርተውታል።
የሀገራችን ህግ በቀል ነው።…የጠላከውን የምትበቀልበት። ይሁና!!
ድል አላግባብ በግፍ እስር ቤት ለተወረወሩ ንፁሃን ወገኖቻችን!!…
የዚህችን ቀን ማን እንዳነሳኝ ባላውቅም ክሊፖን (ፎቶዋን) እለቃታለሁ።

Filed in: Amharic