(የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም፤ ታሪኩ ደሳለኝ )
ተሜ የመከራህ ልክ ልክ የለውም!
“ከዛሬ ጀምሮ ተመስገንን መጠየቅ አይቻለም” የዝዋይ እስር ቤት አዛዦች፡፡
ለወገብህ ማሳረፊያ ፍራሽ የሌለበት፤ ለህምም ማስታገሻ ኪኒን ማግኘት የማይቻልበት፤ ለሀምሳ ሰው በሰሩት የእስር ክፍላቸው ውስጥ ሦስት መቶኛ አደርገው ከ 15 ቀናት በፊት ሲወረውሩህ ይሁን ብልህ ተቀብለኸዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ከላይ የመጣ ትዛዝ ነው በሚል ምክኒያት በቤተሰብም በወዳጅም እንዳትጠየቅ ሲከለክሉህ ይሁን ብለህ እንደተቀበልከውም እርግጠኛ ነን፡፡
ዛሬ ፆሎተ ሐሙስ ነው አምላካችን ለቀራኒዮ እንግልት እራሱን አሳልፎ የሰጠበት ቀን፡፡ ተሜ ከባሰው ህምምህ አኳያ፣ ከለህብት ክፍል፣ ከከፋው ጥላቻቸው እና ጥላቻቸውን ከሚተረጉሙበት መንግድ አንፃር ለመጨራሻው ለቀራኔዮ መድረሻህ እያዘጋጁህ ይሆን እንዴ? ቢሆንስ ተሜ አንተ ላመንክበት አለማ እስካሁን መከራውን በፀጋ እንደተቀበልከው ሞትህምንም ቢሆን ለሀገርህ ነውና ሰቀህ ትቀበለዋልህ እንጂ አታፈገፍግም፡፡ በፊትስ ለሀገሬ ጎዞዬ እስከ ቀራኒዮ ድረስ ነው ብለህን የለም እንዴ፡፡ አሁን በዐል ነው፡፡ ቤተሰብ የሚሰበሰብበት፣ የሄደው ሚመለስበት እኛ ቤት ግን ሰው ጎሏል ያውም ተሜ….. ምን ጎደለ? ምን ላደርግ? ባትለን እንኳን እናታችን ላንተ እንዳይጎድልብህ የቋጠረችልህን ስንቅ መስጠት አልቻልንም፡፡ ስንቴ አደራ እንብላ?… ለኛ በዐል አይደለም እናታችን የያዘችውን ፆምም አትፈታም፡፡ እንደ ሌሎቹ ቤት ቤታችን አይደምቅም፡፡ ድሮስ ህማማቱ የመከራ እንጂ መቼ የደስታ ሆኖ ያውቃል? ጊዜዎቹ በዝምታ ቢያልፉም ከቶም እንዳናዝን የሚደርገን እየከፍልክ ያለህው ዋጋ ለሀገር መሆኑን ማወቃችን ብቻ ነው፡፡ ተሜ!… አንተ ግን ከኛ በላይ ብርቱ ነህ፡፡ ያውም የብርቱ ብርቱ!!!