>

ዘላለም ስንት ነው? (ግርማ ሰይፉ ማሩ)

አውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሰርዓት ሲኖር ተጠቃሚ የሚሆኑት ለዚህ ሲሉ ክቡር ህየይወታቸውን ለመሰዋዕትነት ያዘጋጁትና ይህንን መራራ ፅዋ በክብር የከፈሉት ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁንም የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ ሰርዓት መሰፈን ደስ የሚያሰኘው የተጠቃሚ ምርጫ ለመሰዋዕትነት በመዘጋጀት እና በመክፈል አድልዖ ያለማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነት ሰርዓት የሚጠቀሙትም እነዚህን መሰረታዊ የሰው ልጅ መብቶችን ለማስከበር በሚደረግ ትግል ወቅት እራሳቸውን በፍርሃት ውስጥ ያኖሩትን ብሎም እራሳቸው ጨቋኞቹን ጭምር መሆኑ ነው፡፡ ለመሰዋዕትነት እራሳቸውን ያዘጋጁ ዜጎች ለምን እንዲህ ሆነ ብለው የሚቆጩበት ጊዜ የላቸውም፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት በሌለበት በመንግሰት የሚመራ ቁሳዊ ዕድገት አስተማማኝ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ የተገለፀ ሀቅ ነው፡፡ በሀገራችን ዕድገት አለ የለም ክርክር ጉንጭ አልፋ ከሆነም ቆይቶዋል፡፡ በሀገራችን ቁሳዊ ዕድገት እንዳለ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ የዚህ ዕድገት ተቋዳሾችም ጥቂቶች እንደሆኑ ማመን የግድ ይላል፡፡ እነዚህ ደልቃቆች ውኃ ስለማይጠጡ የውሃ ችግር ችግራቸው አይደለም፤ መብራት ቢጠፋ ጄኔሬተር ያስነሳሉ፣ ሞባይልም ቢሆን ባለ ሳተላይት ይኖራቸዋል (እነዚህ ብዙ አይደሉም)፣ ሌላም ሌላም ልንዘረዝር እንችላለን፡፡ እነዚህ ኪሳቸውን በገንዘብ ሞልተው፤ ነፃነታቸውን በፍርሃት በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ያደረጉ ሰዎች ሌሎች በሚከፍሉት መስዋዕትነት ነፃ የሚወጡ ናቸው፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ገፊ የሆነው ምክንያት የሆነው ግን እነዚህ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያሉ ሰዎች ፍርሃትን አበደባባይ ሲሰብኩት መስማቴ ነው፡፡

ይህ ቀን እስኪያልፍ ድረስ ተዉኝ ልኑርበት እየተባለ በድፍረት መፎከር ተጀምሮዋል፡፡ ድሮ በድብቅ ይፈራል ሲባል ነው የምናውቀው አሁን በድፍረት ስለ ፍርሃት የሚወራበት ዘመን ደረስናል፡፡ ይህን የሰማሁት ባለቤቴ ክሊኒክ ወረፋ ሆና ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ድንገት እግር ጥሎኝ አልፎ አልፎ ጎራ ከምልበት “መዝናኛ” ቤት እንደተቀመጥኩ ነው፡፡ መቁሰያ ቢባል ይሻላል፡፡ አንድ ወደ ጎልምሳና የተጠጋ የሰላሣ ሰምንት ዓመት ሰው ስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የማውቀው

ብሎ እንዲህ ብሎ ፎከረ፤

“ፈሪና ተራራ ዘላለም ይኖራል፤

ብርሌና ደፋር ቶሎ ይሰበራል፡፡

ስለዚህ ተዉኝ ልኑርበት ብሎ የሱን ፍርሃት እንደ ተራራ ሲያገዝፈው፡፡ ለነፃነታቸው ቀናዔ የሆኑትን እና በተፈጥሮ ያገኙትን ነፃነት አናሰነካም የሚሉትን ደግሞ ከተራ ድፍረትና ብርሌ ጋር አነፃፅሮ ለፍርሃቱ ማወራረጃ ውሲኪውን ተጎነጨበትም፡፡ ይኼኔ ነው የቆሰልኩት እና ይህን ለመክተብ ማሰታወሻ የያዝኩት፡፡

እንግዲህ የሳላሣ ስምንት ዓመት ጎልማሳው በከተሜነት ዕድሜው ስሌት በአስራ ሁለት ዓመቱ ሰለፈሪነት ገብቶት እሰከ ዛሬ ለሃያ ስድስት ዓመት አብዛኛውን ደግሞ በኢህአደግ የአገዛዝ ዘመን አንገቱን ደፍቶ እየኖረ ነው፡፡ ለዘላለምም ከነፍርሃቱ ይኖራል፡፡ ፍርሃትም ተራራም ዘላለም ሊኖሩ ይችላሉ ይህ ወንድማችን ግን ከአሁን በኋላ ስንት ሊኖር ብሎ ነው የፍርሃት ፉከራ የሚያወርደው? የሚል ጥያቄ ጫረብኝ፡፡ ዘላለም ለእንዲህ ዓይነት ፈረዎች ስንት ነው? ሰዎች በምድር ላይ በፍርሃት ተውጠው በተጎለቱበት አይደለም ዘላለማዊ የሚሆኑት፡፡ ብዙ ቁም ነገር የሰሩ ጀግኖች የሚዘከሩት በሰሩት ቁም ነገር ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ጆኔፍ ኬኔዲ፤ ወዘተ ከሀገራቸው አልፈው እኛ እንደመደበኛ እውቀት የምናውቃቸው ሰዎች በለጋ ዕድሜያቸው ይህችን አለም ተሰናብተዋል ነገር ግን ለዘላለም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ በላይ ዘለቀ ስቅላት ሲፈረድበት አርባ ዓመት ያልሞላው ጎልማሳ ነበር እንቢኝ ውርደት ብሎ የሞትን ፅዋ ተጎነጨ ነገር ግን በላይ ዘለቀ “የበላይ ናት እሷስ” እየተባለ በዘፈን ይወደሳል፣ ቅኔ ይቀኙለታል፡፡ ዘላለም ስንት ነው ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡ በፍርሃት አንገት ደፍቶ በቁም ሞቶ እድሜ መቁጠር? ወይስ በድፍረት አንገት ቀና አድርጎ መኖር?

ተማም አባቡልጎ የሚባል የህግ አማካሪኛ ጠበቃ መቼም የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ በአንድ አጋጣሚ በፍርድ ቤት ቅጥር ጊቢ ሆነን ስንጫወት እንዲህ አለኝ “እሰር ቤት ስለ መግባት እና ሰለመገደል ማሰብ የእኛ ስራ መሆን የለበትም፡፡ የእኛ ተግባር መሆን ያለበት በድፍረት፣ በስርዓት፣ በነፃነት አንገት ቀና አድርጎ መኖር ነው አለኝ፡፡” እውነቱን ነው አሳሪና ገዳዮች እንዴት፣ መቼ እና በምን ሁኔታ እንደሚያደርጉት ያስቡበት እንጂ እኛ ምን በወጣን ሰለ እሰርና ሞት እናስባለን፡፡ በተቃራኒው ግን ፈሪ ሁልጊዜ በትክክል መፍራቱን እያረጋገጠ መኖር አለበት፤ ያለበለዚያ ሰው መሆኑ በሚፈጥርበት የነፃነት ስሜት ተነሳስቶ ደፋር ሆኖ ገዢዎችን እንዳያሰቀይም መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ ፍርሃቱን በትክክል መፍራቱን ማረጋገጥ የፈሪ ሃላፊነት ነው፡፡ ያለበለዚያም እንዴት ዘላለም ይኖራል፡፡ ድንገት ድፍረት ይመጣና እንደ ብርሌ መሰበር ይመጣል፡፡ አንባቢዎች ፍረዱኝ ፈሪ ነው ወይስ ከፍርሃት ውጭ ያለ በሰጋት የሚኖር?

የሀገራችን ሁኔታ ጉራማይሌ መሆኑን ማሳያው ይህን የፍርሃት ቀረርቶ የሰማሁት ሚያዚያ 26/2006 ካደረግነው ሰልፍ በተመለስን ሶስት ቀን ሳይሞላው መሆኑ ነው፡፡ ፍርሃትን እንቢ ብለው “እመነኝ አልፈራም” ሲሉ የነበሩ ወጣቶች ድምፅ በተለይ የወጣት ሀብታሙ አያሌው ድምፅ ጆሮዬ ላይ እያቃጨለ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ “መብትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም”፣ “ማዕከላዊ ይዘጋ፣ ማዕከላዊ ጓንታናሞ”፣ ወዘተ. የሚሉ መፈክሮች በሰማሁበት ጆሮ መሆኑ ነው፡፡ “አንገድለም ግደሉን” እየተባለ በአደባባይ ሲፈክር ከነበረ ብዙ ሺ ህዝብ በተለየ በአንድ “መዝናኛ” በተባለች ጠባብ ክፍል ውስጥ የፍርሃት ፉከራ ምን የሚሉት እነደሆነ ለእኔ ግልፅ አይደለም፡፡ ፍረዱኝ የቱ ነው ለመኖር ጣዕም የሚሰጠው? ተዉኝ ልኑርበት ብሎ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሆኖ ቀንና ምሽት ሳይለዩ በአልኮል ውስጥ፣ ግራና ቀኝ ያለን ሁሉ እየፈሩና እየተጠራጠሩ የእነ ማቱሳላህ ዕድሜ ቢገኝ እንኳን ዘላለም መኖርን ያስመኛል?

የዚህ ፅሁፍ ዋና ዓለማው ፈሪን መውቀስ አይደለም ይልቁንም ፍርሃትን ስለመፍራት እንድንወያይ እና ከዚህም የሚገኘውን የተሻለ የዘላለም ትርጉም የሚገኝበትን መንገድ መሻት ነው፡፡ በድፍረት ውስጥ ስለ አለ የነፃነት ጣዕምን ሰዎች እንዲያጣጥሙት ማሳየት ያለብኝ ስለመሰለኝ ነው፡፡ ድፍረት ሲባል በፍፁም ከጀብደኝነት ጋር ተገናኝቶ አላስፈላጊ ትርጉም እንዲሰጠው አልፈልግም፡፡ ውሃ ዋና የማይችል ሰው፣ ደፋር ነኝ ብሎ ቢዋኝ እንደሚሰምጥ ማወቅ አለበት፡፡ ሁሉም እርግጠኛ መሆን ያለበት ፈንጂ ላይ የመረማመድ ድፍረት እየሰበኩ አይደለም፡፡ ተፈጥሮዋዊ መብታችንን ላለማስናካት የሚያስፈልገውን ወኔ በአሰፈላጊ ጊዜ መጠቀም ይኖርብናል የሚል ሃሳቤን ለማጋራት ነው፡፡ እንደዚህም ሆኖ ግን መፍራትም፣ ከፍርሃት ጋር ተዋዶ መኖርም ምርጫ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ምርጫ እናከብራለን የምንል ከሆነ ደግሞ የተሳሳተ ምርጫም ቢሆን ምርጫውን ማክበር የግድ ይላል፡፡ ሰው ከሆነ ግን ምርጫው ልክ እንዳልሆነ ሲረዳ ምርጫውን ያስተካክላል፡፡ ሰው የመሆን ጥቅሙ ይህ ነው፡፡ ነፃነት ለእኔ ከእግዜር የተሰጠኝ መክሊት እንጂ በማንም የተቸርኩት አይደለም፡፡ ይህን መክሊቴን ቀብሬ መኖር አብዝቼ መጠቀም የእኔ ድርሻ ነው፡፡ በተሰጠን መክሊት ልክ እንጠየቃለን፡፡

ከላይ ሰለ ሚያዚያ 26 ሰልፍ ካነሳሁ አይቀር ሁለት ትዝብቶኝ ማሰፈር ይገባኛል ብዬ አመንኩ፡፡ በሰልፉ ላይ ሆኜ የታዘብኩት አንድ የወታደሮችን መኖሪያ የሚጠብቅ ዘብ ያሳየውን የተለየ ባህሪ ነው፡፡ ጠብ መንጃውን የታጠቀው ዘብ መቼ እንደሚተኩስ እና እንደሚገድል አይታወቅም ወይ? ለህውቀት እንዲረዳኝ መሳሪያ የያዘ ወታደር በፈለገ ሰዓት መሳሪያውን የመጠቀም መብት አለው ወይ? ይህን ጥያቄ እንዳነሳ የገፋፋኝ በወታደሮች መኖሪያ ቅጥር ጊቢ መግቢያ ላይ በስሜት የተነሱ ሰዎችን ከመግቢያው በር እንዲርቁ እየተከላከልን እያለ አንድ መሣሪያ የታጠቀ ዘብ ጠጋ ብሎን “አልሄድም ነው የሚሉት!!” ብሎ መሳሪያውን ከቃታው ላይ ሲያደርግ ተመልክቼ እንዴት አንደዘገነነኝ ማሰረዳት ስለምቸገር ነው፡፡

ለምሣሌ መዝገብ ቤት ያለ ሰራተኛ ማህተም ሳይፈቀድ እንደማያደርገው፣ ገንዘብ ቤት ያለ ገንዘብ ያዥ ሳይታዘዝ እንደማይከፍለው ሁሉ ጠመንጃ የያዘ ወታደር ሆነ ፖሊስ ተራ ግርግር ተፈጠረ ብሎ መተኮስ፣ ሲተኩስም አንገት ላይ ተኩሶ መገድል ይችላል ወይ? ለወታደርና ፖሊስ አሰገዳጅ የሚባሉ ሁኔታዎች እንዳሉ እረዳለሁ፡፡ የሰለፉ ዕለት የተመለከትኩት የዘብ ሰሜት እጅግ ያስደነገጠኝ ነገር ሰለሆነ ነው፡፡ እግረ መንገዱን በሲግናል በኩል ስናልፍ አንድ አንድ ሰልፈኞች ያሳዩት ያልተገባ ድርጊት በግሌ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብኛል፡፡ በህንፃ ላይ ሆነው የድጋፍ እንዲሁም የሰድብም ምልክቶች ይተላለፉ ነበር እነዚህን ሁሉ በትዕግሰት እና በፍቅር መመለስ ነበረባቸው፡፡ “መከላከያ የኛ!!” የሚል መፈክር መኖር ነበረበት በእርግጥም መከላከያ የእኛ ነው፡፡ ጥቂቶች መጠቀሚያ ስላደረጉት የእኛ መሆኑን መካድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያማዝናል፡፡ ኢህአዴግ ለስልጣን እየቀረበ ሲመጣ “የጭቁን መኮንኖች እና ጭቁን ወታደሮች” ማህበር መመስረቱ የማይረሳ ነው፡፡ በመጨረሻው ግን ሁሉንም መበተን ነበር የወሰነው፡፡ ኢህዴግ የደርግን መንግሰት ካስወገደ በኋላ ከሰራቸው ትልቅ ሰህተቶች አንዱ የኢትዮጵያን መከላከያ ሀይል የደርግ ሰራዊት ብሎ መበተኑ ነው፡፡ ይህ የማይታረም ስህተት ከአሁን በኋላ መደገም ያለበት አይደለም፡፡ ከሌላው ሰህተት መማር መቻል ይኖርብናል፡፡

በመጨረሻም “ማዕከላዊ ይፍረስ፣ ጓንታናሞ ነው!!” ሲባል የነበረውን የሚያዚያ 26 መፈክር ድጋሚ ብቻዬን ማለት አማራኝ፡፡ ምክንያቱም “ዞን 9” በመባል የሚታወቁትን ወጣት ጦማሪዎች በፍርድ ቤት ቀርበው ግርፋትና ድብደባ ደርሶብናል ብለው አቤት ማለታቸውን ሰምቼ ነው፡፡ የፀረ ሽብር ህግ ለመርማሪዎች ከገደብ በላይ በሚስጥር የመመርመር እና መረጃ የመሰብሰብ ስልጣን የሰጣቸው (የወሰዱት) መረጃን በበቂ አሰባሰበው ወንጀለኛ ለመያዝ ነው ቢባልም ይህን ከመጠቀምና መረጃ ለፍርድ ቤት ከማቅረብ ይልቅ የመረጡት መንገድ በአሰራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የሚሰራበትን የግፍ ምርመራ ዘዴ ነው፡፡ተጠርጣሪን አጣርተው መያዝ ሲገባቸው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ ተጠርጣሪንም ቤተሰብንም ማንገላታት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው መንግሰት በተደራጀ መልክ መረጃ አሰባሰበው ክስ መመስረት እንደማይችል፤ ይልቁንም በጉልበት በመጠቀም ማሰፈራራትን መምረጡን ነው፡፡ ተፈጥሮዋዊ ነፃነታቸውን በህውቀታቸውና በልምዳቸው መሰረት ህዝብ እንዲያውቅ ሲተጉ ከነበረ ወጣቶችና በባንኮኒ ውስጥ ተዉኝ ልኑርበት ከሚለው ማን ክብር አለው? ምርጫው የግል ነው፡፡

ቸር ይግጠመን!!!!

girmaseifu.blogspot.com

Filed in: Amharic