>
10:40 pm - Thursday May 19, 2022

“ከኢህአዴግ አዲስ ነገር አይጠበቅም” (አቶ አስራት አብርሃም)

የቀድሞ የአረና አባል አስራት አብርሃም በቅርቡ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ እንደተቀላቀለ ታውቋል፡፡ በአጠቃላይ በሃገራዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ  ከሎሚ መጽሔት ጋዜጠኛ ቶማስ ኣያሌው ጋር ያደረገው ቆይታ

“ከአቶ መለስ በኋላ የሚወሰዱት እርምጃዎች ታስቦባቸው የሚደረጉ አይመስሉኝም”

“ከኢህአዴግ አዲስ ነገር አይጠበቅም”
አቶ አስራት አብርሃም

ሎሚ፡- በዚህ ሠሞን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህን መቀላቀልን የሚገልፅ መረጃ አይቼ ነበር፤ ይህ ነገር ከምን ደረሰ?

አስራት፡- ከአንድነት ፓርቲ ጋር የቆየ ግንኙነት ነው ያለኝ፤ በመድረክ ውስጥ አብረን ሠርተናል፡፡ በ2005 ዓም ከአረና ፓርቲ ከለቀኩኝም በኋላ በየጊዜው በተለያዩ ጉዳዮች እንገናኛለን፡፡ በአንድነት ጽ/ቤት በሚዘጋጁ ተለያዩ ዝግጅቶች ላይ እንግዳ ሆኘ ተጋብዤ ፅሁፍ ያቀረብኩበት ወቅትም ነበር፡፡ ከአረና በኋላ በፓርቲ ፖለቲካ ለመግባት ሳስብ ቀድሞ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው “አንድነት” ነው፡፡ ይህን ቀረቤታዬን የተረዱ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮችም ለምን እኛ ጋር ተቀላቅለህ አትታገልም የሚል ጥያቄ ያቀርቡልኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ፓርቲው የተለያየ የውህደት እንቅስቃሴዎችን ያደርግ ስለነበር፣ ውጤቱን ለማየት በሚል እስካሁን ለመግባት አልቻልኩም፡፡ አሁን ግን በቅርቡ በይፋ ፓርቲውን ለመቀላቀል ችያለሁ። 
ሎሚ፡- እንግዲህ አንድነትን ስትቀላቀል ሁለተኛ ፓርቲህ ነው የሚሆነው ለመሆኑ እንደው ለአንባቢዎች ይረዳ ዘንድ ከአረና ፓርቲ የለቀቅክበት ምክንያት ምንድነው?
አስራት፡- በወቅቱ ከአረና የወጣሁት እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ በወቅቱ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ ከነበረው ጉዕሽ ገብረፃዲቅ ከሚባል የአመራር አባል ጋር ነው የወጣነው። የወጣንበትን ምክንያትም በሚመለከት በወቀቱ በጋዜጣ መግለጫ አውጥተናል፡፡ ወደዛ ነገር በድጋሚ መመለስ ብዙም አስፈላጊ ባይሆንም ለጥያቄህ ምላሽ ለመስጠት ያህል በፖለቲካዊ አካሄድ ላይ በተለይ በውህደትና በመድረክ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ፣ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መጠነኛ ልዩነት ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሂደት እየተገነዘብነው የመጣን የአባታዊነት መልክ ያለው ተፅዕና ወጣቶች ላይ ይደረግ ነበር። እኔ በፓርቲው ውስጥ መስራችም፣ ከፍተኛ አመራርም ስለነበርኩ ከሌሎች ወጣቶች አንፃር የተሻለ ነጻነት ነበረኝና ይሄ በአባላት ዘንድ አለ ይባል የነበረውን ችግር ብዙም አይገባኝም ነበር። አሁን ሆኜ ሳስበው በአንዳንድ ጎዳዮች ላይም ራሴ የችግሩ አካል የነበርኩ ይመስለኛል። ስርዓቱን አምርሬ የታገልኩትን ያህል በራሳችን ፓርቲ ውስጥ የነበሩ መጥፎ አሰራሮችና ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ባህሎች በመታገል በእኩል ደካማ የነበርኩ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። ከመጀመርያው ጀምሮ ነገሮች ሲበላሹ በፅናት የማስተካከል እርምጃ ብወስድ ኖሮ በዚህ መልኩም ላንለያይ እንችል ነበር፤ የሆኖ ሆኖ ከፓርቲው ራሳችን አገለልን። የፖለቲካ ጥርስህን የነቀልክበት ፓርቲ በዚህ መልኩ ስትሰናበተው በጣም ነው የሚያንገበግበው። ነገር ግን ጭቆናን፣ ፊውዳላዊ አስራርንና ባህልን እታገላለሁ ብሎ የመጣን ሰው የዚያ አይነት ዝንባሌ እንዳለ ሲገነዘብ መበርገጉ አይቀርም። ያም ሆኖ ስርዓቱን በትክክል በሚታገሉ ኃይሎች ላይ ጠጠር እንኳ ላለመወርወር ባለኝ አቋም መሰረት ከወጣሁም በኋላ እንደ ግለሰብም እንደ ደጋፊም ሆኜ ከዓረና ጋር እየሰራሁ ነው የቆየሁት፡፡ በየጊዜው በተለያዩ አገጣሚዎች እየተገናኘን እንነጋገራለን፡፡ በእውነቱ ከአረና ወጣሁ የሚያስብል ነገር አልነበረም፡፡ ከፓርቲው ወጥቻለሁ ወይስ አልወጣሁም የሚለው ነገር ለእኔም ግልፅ ሳይሆንልኝ ነው የቆየው። አሁን ወደ አንድነት ስገባ ነው በትክክል ከአረና መውጣቴን የተረዳሁት ማለት ይቻላል።

ሎሚ፡- ላንተ በብሔር ፖለቲካ ላይ የሚያራምዱ ፓርቲዎች ዙሪያ ምን አይነት አመለካከት አለህ?

አስራት፡- በመጀመሪያ አንድ ነገር ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ አረና የክልል ፓርቲ ነበር ብዬ ነው የማስበው፡፡ የብሔር ፓርቲ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ትግራይ ውስጥ ከአራት በላይ ብሔሮች አሉ፡፡ ትግርኛ ተናጋሪው ብሄረሰብ አለ፣ የኢሮብ ብሄረሰብ አለ፡፡ የኩናማ ብሔረሰብ አለ፣ እንደዚሁም የተወሰኑ አማርኛ፣ ኦሮምኛ የሚናገሩ ብሄረሰቦች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲው በክልሉ የሚገኙ ህዝቦች ሁሉ የሚወከል ህዝባዊ ፓርቲ ለማድረግ በፕሮግራም ደረጃ ግንዛቤ ነበር፡፡ ስለዚህ እኔ የብሔር ፓርቲ ነው የምለው አንድን ብሔር ብቻ መሠረት አድርጐ የተቋቋመ ሲሆን ነው፡፡ ዋናው ነገር እኔ ስለ ብሔር ፓርቲ ያለኝ እምነት አንደኛ በብሔርም መደራጀት መብታቸው መሆኑን እቀበላለሁ፤ ሁለተኛ ለኢትዮጵያ አንድነት እስከቆሙ ድረስ ችግር የለውም ብዬ ነው የማስበው፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት መቆም አለባቸው፣ ገዢው ፓርቲ ከሚያራምደውን ፖለቲካ የራቀ ፖለቲካ ማራመድ አለባቸው፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚራምደው የዘር ፖለቲካ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ ያለሁበት፣ ብሔረሰብ ተጨቁኗልና ያ ብሔረሰብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር እኩል መብቱን ላስጠብቅለት ነው የምታገለው የሚል ሀሣብ ያለው ቢመጣ ለእኔ ችግር የለውም፡፡

ሎሚ፡- ከአረና ከወጣህ በኋላ የየትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ሣትሆን ቆይተሃል፡፡ ያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የመገምገሚያ ጊዜህ ነበር?

አስራት፡- ከአረና ከወጣሁ አንድ አመት ሆኖኛል፡፡ ነገር ግን አንድ ተስፋ የማደርገው ነገር ነበር ይህም የአረና ጉባኤ ስለ ፓርቲዎች ውህደት የሚወሰነውን ውሳኔ ነበር፡፡ በትክክልም እኔ በምፈልገው መልኩ ከመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር እንዲዋሃድ ካልሆነም ከሌላ ፓርቲ ጋር ተዋህዶ ሃገራዊ ፓርቲ ጋር እንዲዋሃድ ብሎ ጉባኤው ወስነዋል፡፡ ያ ውህደት በቶሎ ይሳካል፡ እኔም እገባለሁ ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ረጅም ጊዜ የቆየሁም አልመሰለኝም፡፡ የሚጠና ነገርም አልነበረም፤ ሲጀመርም፣ ውህደት እንዲፈፅሙ ከሆነ የእኔ ፍላጐት አንድነትና አረና የተወሃደበት ፓርቲ እንደምገባ ይታወቅ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማንን ነው የምታጠናው፤ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ያሉት፤ አቋማቸውም በፖለቲካው ለቀዬ ሰው በደንብ የሚታወቅ ነው፡፡ ለማጥናት ሣይሆን ጊዜ የፈጀሁት ስጠብቅ ነው፡፡ እንደነገርኩህ ከአረና ጋር ተቆራርጬ ነበር ማት አይቻልም፤ የአካሄድ ልዩነት ቢፈጠርም ለትግል ነበር የመጣነውና እናመሰግናለን ብለን ነው የተለየናቸው፡፡ አብረን ታግለናል፤ ወደፊትም አብረን የምንታገልበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል፣ አልተቀያየምንም፡፡ እኛ ወደዚህ ወደ ፖለቲካው የመጣነው ልንታገል ነው፤ ሌላ አላማ እስከሌለን ልንታገል እስከመጣን ድረስ ትግሉ እራሱ ሊያጣላን አይችልም፡፡ እንዴት እንታገል? እንዴት ትግሉ ውጤታማ ይሁን? የሚለው ነገር ሊያለያየን ይችላል እንጂ በጠብ፣ በክፋት እንድትተያይ የሚያደርግህ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ እኔ ፖለቲካን በአጠቃላይ ብተወው የሚቀርብኝ ነገር ትግሉ ብቻ ነው፡፡ እንደማንኛውም ሰው አንገቴን ደፍቼ ልጆቼን ማሳደግ እችላለሁ፤ አንገት መድፋትም ላይጠበቅብኝ ይችላል። ከስርዓቱ ጋር በሀገር ጉዳይ እንጂ ግላዊ ጠብ የለኝም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመሳተፍ ስፈልግ ዋናው ነገር አሁን ካለው ስርዓት የተሻለ እናመጣ ይሆናል፤ ለእኛ ባይሆንም፣ ለልጆቻችን የተሻለ ነገር እናቆይላቸው ብለን በማሰብ ነው፡፡ በእኛ ሀገር ወደ ፖለቲካው ስመጣ ብዙ ችግር ሊኖር እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ በተለይ በትግራይ አካባቢ ሆነህ ስርዓቱን ስትታገል፣ በሁለት መልኩ ነው የምትመታው፡፡ ያ ሁሉ ታሣቢ አድርገን ነው አረና ወደ መመስረቱ የገባነው፡፡ በዚህ እምነትና ስሜት ነው ወደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ የገባሁት፡፡ በእርግጥ የስርዓቱን አደገኛነት በደንብ እረዳው ነበር ለማለት አልደፍርም፤ ወደ ፖለቲካው ሙሉ ለሙሉ ከገባሁ በኋላ ነው ነገሮች በደንብ እየገቡኝ የሄዱት።

ሎሚ፡- አሁን በሃገሪቱ ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችን አሰላለፍ እንዴት ትመለከተዋለህ?

አስራት፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሰላለፍ አዲስ ነገር የለውም፡፡ ብዙ የተለየ አሰላለፍ አለ ብዬም አላስብም፡፡ ሁልጊዜ ግን በፖለቲካችን ውስጥ ሶስት አይነት አሰላለፍ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ አንደኛው በብሔር የተደራሁ ከኢህአዴግ ጋር በአካሄድ፣ በአላማም፣ በብዙ ነገር ልዩነት የሌላቸው፣ ነገር ግን በስልጣን ጥያቄ ብቻ ከኢህአዴግ ጋር የተለየ የዘር ፖለቲካ ብቻ የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ “የግራ ፖለቲከኞች ልንላቸው እንችላለን”። ሁለተኛው አሰላለፍ ከእኛ ሃገር ነባራዊው ሁኔታ በመነሳት በተለምዶው “ቀኝ አክራሪ” እየተባሉ የሚጠሩት ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲና ለፍትህ ሳይሆን “የወያኔ ስርዓት” ስልጣናችንን ቀማን በሚል ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወይም ታሪካዊ የስልጣን ባለቤትነትን አንስተው የተነጠቅነውን ስልጣን ማስመለስ አለብን የሚል አጀንዳ ከዴሞክራሲ ጥያቄ ባሻገር ይሄ የሚያሰባስባቸው ኃይሎች በዚህ ክፍል ሊመደቡ ይችላሉ። አሁን አሁን በዚህ የሚመደቡ ኃይሎች አንድም አቋማቸው እያረሙ ወደ መሀል የሚመጡበት አንድም ጥግ እየያዙ እየደከሙ የሚሄዱበት ዕድል ነው ያለው።
“በእኔ በኩል ፖለቲካው መዘመን አለበት ብዬ አስባለሁ፤ ሲጀመር ይሄ ሃገር ለሁላችንም እኩል መሆን አለበት፡፡ ኢህአዴግ እኔ ብቻ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊ እኔ ብቻ ነኝ የሚመለከተኝ” ይላል በራሱ መንገድ፡፡ በዛ በኩል ያለው ደግሞ እኛ ብቻ ነን ኢትዮጵያዊያን እኛ ነን መሠየም የምንችለው፡፡ እውነተኛ ኢትዮጵያዊም የሆነም ያልሆነም መሠየም ያለብን እኛ ብቻ ነን የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ፖለቲካው በርዕዮተ አለምና በጋራ እሴቶች እንጂ በማይታወቁ፣ በማይተነተኑና በማይመረመሩ መናፍስት መመራት የለበትም። ፖለቲካው መዘመን አለበት ሲባል ብዙህነትን የተቀበለ ኢትዮጵያዊነት ማበልፀግ፤ በመርህ፣ በግልፅነት፣ ፊት ለፊት በሚደረግ ዘመናዊ የፖለቲካ ባህል እየጎለበተ የሚሄድ የሰለጠነ ፖለቲካዊ ስርዓት መፍጠር ማለት ነው። አባቶቻችን መምሰል ባለብን ነገሮች ብቻ ነው መምሰል የምንችለው፤ ከዚያ ውጪ እኛ ተሽለን ነው መገኘት ያለብን። ዘመኑም እንደዚያ እንድንሆን ያስገድደናል። ለዚህ ነው እነዚህ የግራ አክራሪም፣ የቀኝ አክራሪም ከመዘመን ውጭ ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ሶስተኛው አሰላለፍ መጠናከር አለበት ብዬ የማስበው ሁሉን የሚያቅፍ መካከለኛ ፖለቲካ፣ ማራመድ የሚችል /ቀኝም፣ ግራም/ ሣይሆን ጫፍና ጫፍ ያሉትን የሚያስታርቅ ጥግ የያዘውን ፖለቲካ ወደ መሃል እንዲመጣ የሚያደርግ ፖለቲካ የሚያዳብር፣ ያልተሰባሰበው ኃይል የሚያሠባስብ ነው፡፡ ይሄኛው አሰላፍ ጠንክሮ አልወጣም፤ ፖለቲካው በተለመደው መንገድ ነው እየሄደ ያለው በተመሳሳይ መንገድ ደግሞ ስትሄድ 23 አመት በሙሉ በዛ መንገድ ተኪዶ ለውጥ አልመጣም፡፡ በዚህ ጫፍ በያዘ መንገድ ተኪዶ ለውጥ ቢመጣም ሀገር በሚያፈርስ መንገድ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው ስርዓት ሆነ ብሎ ሁለቱም ኃይሎች በራሳቸው ፅንፍ እንዲሄዱ እያደረገ ነው ያለው። “ኦሮሚያ አካባቢ የሚሠራውን ማየት ትችላለህ” ኢህአዴግ ሌላኛው ፅንፍ ከፍ ሲል፣ ያኛውን ፅንፍ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ስርዓቱ በሁለቱ ፅንፎች መሃል መኖር ያስፈልጋል፡፡ እኔ ደግሞ እያልኩ ያለሁት የሁለቱ ፅንፎች ሃሣብ እንዲቀራረብ፣ እንዲታረቅ በማድረግ የተለየ ፖለቲካ ማራመድ ያስፈልጋል፡፡ በዛ ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ ስለዚህ ይሄ መካከለኛ አስተሳሰብ ያለውን ፖለቲካዊ አካሄድ ማምጣት ያስፈልጋል ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሎሚ፡- ተቃዋሚዎች ካልተዋሃዱ ለውጥ ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለህ ታምናለህ?

አስራት፡- እዚህ ላይ ሁለት ነገር ነው ያለው፣ በነገራችን ላይ ውህደት አንደኛ በፕሮግራም፣ በአላማ፣ በሰው ስብጥርም መቀራረብ አለብህ፡፡ እኔ ውህደት ብቸኛው መንገድ ነው ብዬ አላስብም፡፡ እንዳልኩት ሁለት አማራጭ ነው ያለው፡፡ አንደኛ ተቀራራቢ ሃሣብ ያላቸውን ፓርቲዎችን ማዋሃድ፤ እነዚህን በማዋሃድ ጠንካራ ተቃዋሚ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ውድድሩ በኢህአዴግና በአንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ መሀል እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄም የማይቻል ከሆነ ደግሞ የተወሰኑ እውነተኛ የሆኑ ፓርቲዎች ግንባር ወይም ቅንጅት በመፍጠር ማጠናከር ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ሊወዳደር የሚችል ኃይል ለመፍጠር ሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው እንዳልኩት ፓርቲዎችን ማሠባሠብ፣ ሁለተኛ ደግሞ ከፓርቲ ውጪ ያሉ ሠዎችን በማሠባሰብ ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲ መስራት ይቻላል፡፡ በርካታ ሠዎች አሉ፤ ገና ወደ ፖለቲካው ያልተቀላቀሉ፡፡ ችግሩ ምንድነው የማን ቡድን ነው ጐልቶ የሚወጣው የሚለው ነው? በማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ስልጣን መሰረት ያደረገ የኃይል አሰላለፍ አለ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ከስልጣን ስሌት ካልወጣ ችግር ነው፡፡ ይሄ ፓርቲ መንግስት ቢሆን ስልጣን የሚይዙት እነማናቸው የሚለው ነገር ነው ስልጣኑ ሳይኖር እያበጣበጠ ያለው፡፡ ለዛ ነው ተቃውሞው ከኢህአዴግ ፍጥነት ጋር መሄድ ያልቻለው፡፡ ኢህአዴግ ብዙ ነገር ሰጥቶ ተቀብሎም እየኖረ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች አካባቢ ግን ያለው ምንድነው በጣም ኋላ ቀር የሆነ የፖለቲካ አካሄድ ነው ያለው፡፡ የተወሰኑ ኃይሎች ራሳቸው ብቻ ታግለው አሸንፈው ስልጣን ለብቻ መያዝ ይመኛሉ፡፡ ያ እንደማይቻል እንኳን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማንበብ አልቻሉም፡፡

ሎሚ፡- በ2007 ዓ.ም ምርጫ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍ ወይስ በፓርላማ ያላቸውን የመቀመጫ ቁጥር ለመጨመር ይሄደሉ ከዚህ ብለህ ትገምታለህ?

አስራት፡- በነገራችን ላይ ስለ 2007 ዓ.ም ምርጫ ሳስብ ምንም የሚታየኝ ደህና ነገር የለም፡፡ በእኔ እምነት የ2007 ዓ.ም ምርጫ በጣም ድርሰዋል፤ ከዚህ በኋላ ምን እንደሚሠራ አላውቅም። ስለዚህ እንደ እስትራቴጂ ተቃዋሚዎች እዚህ ላይ ምን ማድረግ ነው ያለባቸው ምርጫውን እንደአንድ ግብዓት መጠቀም ነው፡፡ ኢህአዴግ ወደ ትክክለኛ ምርጫ የሚያመጣበትን መንገድ መፍጠር እንጂ አስተሳሰቡን ሣይቀይር፣ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛና ነፃ ሣይሆን፣ የተለመደው አይነት የፖለቲካ ጨዋታ እንጂ የሚኖረው የተለየ ነገር አይሆንም፡፡ ከ2007 ዓ.ም ምርጫ የተለየ ነገር አትጠብቅም፤ በኢህአዴግ በእኩል ለውጥ የለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ኢህአዴግን ማስገደድ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልደረሱም። ኢህአዴግን ለምርጫ አስገድዶ፣ ምርጫ ቦርድን አስቀይሮ፣ ገለልተኛና ነፃ ምርጫ ቦርድ ተዋቅሮ፣ ነፃና እኩል ሚዲያን የመጠቀም እድል ተከብሮ፣ በፕሮግራምና በፖሊሲ ተከራክሮ ወደ ምርጫ መግባት ከተቻለ ችግር የለውም ምርጫውን በየትኛውም ጊዜ ማድረግ ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ ግን ይሄ የምርጫው ሂደትና አሰራር ተቃዋሚዎች የተሳተፉበት እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች በመጀመሪያ ከገዢው ፓርቲ ጋር በእነዚህ ጉዳች ላይ በአጠቃላይም በምርጫ ሂደቱ ላይ መደራደርና መስማማት አለባቸው፡፡ በመጀመሪያ ምርጫው ሲካሄድ ማነው ምርጫውን የሚያካሂደው? ምርጫ ቦርድ እንዴት ነው መቋቋም ያለበት ተብሎ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በኋላ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሠሩት ስራ በምርጫው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡እነዚህን ነገሮች የምታደርግበትን ተፅዕኖ ሳይፈጠር ወደ ምርጫ ቢገባ ትርጉም ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ፓርቲ ወደ ምርጫ የሚገባበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል እረዳለሁ፡፡

ሎሚ፡- አሁን ኢህአዴግ እየሄደበት ያለውን ሃገርን የመምራት መንገድ እንዴት ታየዋለህ?

አስራት፡- የተለየ መንገድ የለውም፤ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ስልጣኑን ማስቀጠል ይፈልጋል፡፡ ስልጣን ለማስቀጠል ደግሞ ያሰጋሉ የሚላቸውን ኃይሎች በጠላትነት እንዲፈረጁ ማድረግ ነው፡፡ ይሄንን ስራ ደግሞ አሁንም እየቀጠለበት ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ከኢህአዴግ አዲስ ነገር አይጠበቅም፡፡ ለምንድነው አዲስ ነገር የማይጠበቀው ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣኔን ይቀማኛል የሚለውን ኃይል በሙሉ በጠላትነት የሚያይ ስርዓት ነው፡፡ ለጠላት ደግሞ ሠላማዊ መንገድ አትሰጠውም፡፡ ለጠላትህ በምርጫ ስላሸነፈህ ብቻ ስልጣን አትሰጠውም፤ ከጠላት ጋር የሚኖር ነፃ ውድድር የለም፡፡ በዚህ ልክ ነው የሚሄደው፤ ጠላት ብሎም አስቀምጧል፡፡ አንተ ደግሞ ጠላት አይደለሁም ተወዳዳሪ ነኝ ብትለው ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የተለየ አቋም እንዲይዝ የምታደርገው ይሄ አካሄድ የሚያዋጣው አለመሆኑን ሲያየው ነው፡፡ የህዝብ ተፅዕኖ ሲያርፍበትና ሌላ አማራጭ እንደሌለው ሲያውቅ ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ በተፅዕኖ በድርድር እንጂ በመልካም ፈቃድ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ እዚህ ጋር የጥቅምና የስልጣን ጥያቄ ነው ያለው፡፡ እኛ ሃገር ስልጣንና ጥቅም የተያያዙ ናቸው፡፡ ስልጣን ካለህ ተጠቃሚ ነህ፣ ስልጣን ከሌለህ ሁሉም የለህም፡፡ ኢህአዴጐች ስልጣን ብናጣ እስር ቤት ነው የምንገባው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ስለሆኑ ከእነርሱ የምትጠብቀው ምንም ተስፋም ሆነ ለውጥ የለም፡፡ ለዛም ነው የዘርና የጥላቻ ፖለቲካ እያራመደ ያለው፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎችም ወደ ዘር ፖለቲካ ገብተው እያገዙት ነው፡፡ እርሱ በድርጎ ከሚያኖራቸው ፓርቲዎች በተጨማሪ ለሚፈልገው ስራ ሣይገባቸው በእርሱ ወጥመድ ውስጥ ገብተው የሚሠሩለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ፡፡

ሎሚ፡- በቅርቡ የታሰሩ ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን ጉዳይ ሠምተሃል፡፡ ይሄን በሚመለከት አንዳንድ ወገኖች በስርዓት ውስጥ ያለውን ጭንቀት ይገልፃል ይላሉ፡፡ አንተ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አስራት፡- ልክ ነው፤ ስርዓቱ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የሚወስደው እርምጃ ታስቦ የሚደረግ አይመስልም፡፡ ትንሽ የመደንገጥ ነገር አለ፡፡ አሁን እነዚህ ጦማሪያን ለስርዓቱ ስጋት የሚሆን ነገር ሰርተው ሣይሆን ምሣሌ ይሆናሉ ተብሎ ነው፡፡ ወጣቶች ናቸው፤ ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ምሣሌ ይሆናሉ በሚል ነው፡፡ ራሳቸውን ከፍርሃት ማውጣታቸው ነው ወንጀል የሆነው፤ ራሱን ከፍርሃት ነፃ ያወጣ ወጣት ኢህአዴግ ማየት አይፈልግም፡፡ ራሱን ከፍርሃት ነፃ አውጥቶ የሚንቀሳቀስ ወጣት ካለ ሌላውንም ነፃ እያወጣ ስለሚሄድ ለስርዓቱ አደጋ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ማስደንገጥ አለበት፡፡ በነፃነት የሚንቀሳቀስንና ሀሳቡን ለመግለፅ የሚሞከር ሰው ካሠረ ሌላው አርፎ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ነው፡፡ ይሄ ህዝብ ደግሞ ደንግጠዋል፤ በጣም ብዙ ችግር ያየ ህዝብ ነው፤ በቀይ ሽብርም፣ ከዛ በኋላም በ1997 ዓ.ም ብዙ ግፍ የደረሰበት ህዝብ ስለሆነ ሊፈራ ይችላል፡፡ ለዚህ ዓላማ የተደረገ ነው የሚመስለኝ፡፡ በቀጣይነት ምርጫ አለ፤ ከዛ በፊት ማስደንገጥ፣ ተስፋ ማስቆረጥ አለበት፤ በፖለቲካ መሣተፍ፣ በሚዲያ መሣተፍ በአጠቃላይ ለውጥ ለሚፈልጉ ሠዎች ተስፋ እንዲቆርጡና አርፈው እንዲቀመጡ የማድረግ ስልት ይሆናል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በዚህ ሰዓት ከእኛ ይጠበቃል ብዬ የማስበው የዚህ አይነት ነገር ሲመጣ ወደ ትግሉ እየተቀላቀሉ፤ እየተተካኩ መሄድ ነው፡፡ ማሰር፣ መግደል መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ለስርዓቱ ማሣየት ያስፈልጋል፡፡

ሎሚ፡- በተለያዩ ክልሎች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የኦሮሞ ተማሪዎች ተቃውሞ አሠምተዋል፡፡ የሞቱ ሠዎች መኖራቸው ታውቋል፡፡ የዚህ አይነት ሁኔታን መንግስት በምን አይነት መልኩ ነው ማዳመጥ ያለበት? አሁን በመንግስት ታጣቂዎች የተወሰዱት እርምጃዎች መፍትሄዎች ናቸው ወይ?

አስራት፡- ሁለት ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ በመጀመሪያ የተማሪዎቹ ጥያቄን መደመጥ አለበት፡፡ በሠላማዊ መንገድ የጠየቁት በሠላማዊ መንገድ መልስ መስጠት እንጂ መግደል ተገቢ አይደለም፡፡ የሰው ህይወት ሲጠፋ በጣም ነው የሚያሳዝነው፡፡ ሃገር ተረካቢ የሚባለውን አዲሱን ትውልድ፣ በዚህ አይነት ሁኔታ ህይወቱ ሲያልፍ በጣም ቅስም የሚሰብር ነው፡፡ በቀጣይነት በሃገሪቱ ፖለቲካ ላይ ችግር የሚፈጥር ነው የሚሆነው። በዚህ ሁኔታ መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ ትክክል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የምናየው የአንድ ብሄር ጉዳይ አጀንዳ እየሆነ የተቸገርንበት ነገር አለ፡፡ የሆነ ብሔር ሲበድል እርሱ ይቃወማል፣ ሠልፍ ይወጣል፣ ሌላው ዝም ይላል። በተራው ያ ዝም ያለው ሲበደል ደግሞ እርሱም ለብቻው ይቃወማል፣ ለብቻው ተመትቶ ያርፋል፡፡ ሌላው ባለተራ ሲነካም እንደዚሁ ብቻውን ይነሣል፡፡ ምንድነው በትውልዱ መካከል መግባባት የለም ወይ ትግሉ የጋራ ማድረግ ያልተቻለው፣ ኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የማይኖረው ለምንድነው? ለምሣሌ እኔ አሁን ኦሮማያ ተብሎ ተከልሎ ያለው አካባቢ የኦሮሞ ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ የለኝም፡፡ ያ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ እንደ ማንኛውም ብሔር እያንዳንዱ ብሔር የራሱን ቋንቋ መጠቀም፣ በቋንቋው መማር፣ የራሱን አካባቢ ማስተዳደር እንዳለ ሆኖ የሌሎችን የኢትዮጵያዊያን መብት መጠበቅ አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በማንኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር መብት አለው፡፡ ኢህአዴግ ያረቀቀው ህገ መንግስትም ቢሆን ይሄንን ይላል፡፡ ከዚህ ሠዎች ተፈናቀሉ የሚለው ነገር ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያ መፈናቀል የለበትም፡፡ ትግራይ የትግርኛ ተናጋሪ ክልል ብቻ አይደለም፡፡ አማራ ክልል የሚባለው የአማርኛ ተናጋሪ ሠዎች ብቻ ክልል አይደለም፡፡ ኦሮሚያም፣ ደቡብም በዛ መልክ ነው መታየት ያለበት፡፡ የሌላ ሃገር የሌላ ምድር ይመስል የሚደረገው ትክክል አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ያሉ የኦሮሞ ገበሬዎች መፈናቀል የለባቸውም፤ መብታቸውን ያለአግባብ መወሠድ የለበትም፡፡ በዚህ ዙሪያ ሁላችንም መቃወም፣ መታገል አለብን፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ ያለ አግባብ ከቀዬው መፈናቀል የለበትም፤ አዲስ አበባ እየተስፋፋች ነው፤ የኦሮሚያን መሬት እየወሰደች ነው የሚለው አባባል ግን ችግር አለው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው መሬት ወደዚህ ሄደ ወዲያ መጣ ብለን ማውራት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ለእኔ ዘላቂነትና ትርጉም ያለው ፖለቲካም አይደለም፡፡ የአስተዳደር ለውጥ ሊደረግ ይችላል፤ ይህም እዛ የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው ወዴት መሄድ እንዳለባቸው መናገርና መወሰን ያለባቸው፡፡

ሎሚ፡- ህወሃትና የትግራይ ህዝብ በአንተ እይታ በምን አይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

አስራት፡- ህወሃትንና የትግራይን ህዝብ መጀመሪያውኑም ያስተሳሰራቸው ችግር ነው፡፡ የጋራ ችግር ነበር፤ የጋራ ጥያቄ ነበር፤ ህዝቡ ባለፉት የተለያዩ ስርዓቶች የአስተዳደር ችግር ነበረው፡፡ በዚህ ምክንያት ተደጋግፈው ይሄ ኃይል ለስልጣን በቅቷል፡፡ የትግራይ የገበሬ ልጆችን ፈንጅ እያስረገጠ ወደ ስልጣን የመጣ ስርዓት ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ስርዓት ስልጣን ላይ ከመጣ ይህን ያል ጊዜ ቆይቶም ቢሆን የትግራይ ህዝብ የሚፈልገውን ነፃነት፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አላገኘም፡፡ ዝም ብሎ ህወሃት ትግርኛ ስለተናገረ የትግራይ ህዝብ እራሱን በራሱ እያስተዳደር ነው ማለት አንችልም፡፡ እንደዛማ ከሆነማ ኦህዴድም ኦሮምኛ በመናገሩ የኦሮሚያ ሰዎች ነው እያስተዳደረ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በራሱ በነፃ ምርጫ አወዳድሮ ያስቀመጠው መንግስት እስከሌለ ድረስ በተፅዕኖ በጠመንጃ ኃይል በስልጣን ላይ ያለ ኃይል ነው፡፡ በዚህ ላይ ከኤርትራ ጋር ከተፈጠረው የድንበር ጦርነት ጋር ተያይዞ አካባቢው የጦርነት ቀጠና ሆኗል፡፡ አካባቢው ከወደብ የራቀ ከአዲስ አበባ በከፋ ሁኔታ የሚገኝ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከውጭ የሚመጣ እቃ ከጅቡቲ ወደብ ተራግፎ ከዛ አዲስ አበባ መጥቶ 800፣ 900 ኪ.ሜ ተጉዞ ነው እዛ የሚደርሰው፡፡ ስለዚህ ትግራይ በኢኮኖሚ ለማደግና በሰላም ለመኖር የማይመች ሆኗል፡፡ ተገቢ የሆኑ አስተዳዳሪዎች የሉትም፡፡ ከዚህ አንፃር የትግራይ ህዝብና ህወሃት እንደ በፊቱ የወላጅና የልጅ ግንኙነት አላቸው ብዬ አላስብም፡፡ ለዚህም ነው አሁን አሁን ተቃዋሚዎች በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሳሉ ያሉት፡፡ እየታሰሩም እየተፈቱም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ገደልና ቋጥኝ ፈልፍሎ ሠርቶ ለመኖር የሚችል ህዝብ ነው፡፡ ህዝቡ አሁንም የሚፈልገው በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሶ ህይወቱን መምራትና ሰርቶ የሚኖረበትን ሁኔታ ነው፤ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በሰላምና በፍቅር መኖር የሚፈልግ ህዝብ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ህዝቡና ህወሃት በተመሳሳይ መንገድ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡
ሎሚ፡- ጊዜህን ሠጥተህ ለዚህ ቃለመጠይቅ ስለተባበርከኝ አመሰግናለሁ፡፡
አስራት፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Filed in: Amharic