>

ወጣት ሳሙኤል አወቀ ተገደለ

Samuel Aweqe

ነገረ ኢትዮጵያ

የሰማያዊ ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ዞን ፀኃፊና በ2007 ዓ.ም ምርጫ የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪ የነበረው ወጣት ሳሙኤል አወቀ ተገደለ፡፡ ወጣት ሳሙኤል አወቀ ትናንት ሰኔ 8/2007 ዓ.ም ምሽት ላይ ወደ ቤቱ እየገባ በነበረበት ወቅት በሁለት ግለሰቦች ከፍተኛ ድብዳባ ከተፈፀመበት በኋላ ሆስፒታል ውስጥ ነፍሱ አልፋለች፡፡

ወጣት ሳሙኤል ከቀድሞው አንድነት ጀምሮ ሲታገል የቆየ ሲሆን የሰማያዊ ፓርቲ መስራች አባል ነው፡፡ በአካባቢው የሚፈፀሙ በደሎችን ለሚዲያ በማጋለጥ ሲያበርክተው ከነበረው ሚና ባሻገር በፓርቲው በነበረው ጠንካራ እንቅስቃሴ ምክንያት በተደጋጋሚ እስርና ድብደባ ተፈፅሞበታል፡፡

ወጣት ሳሙኤል ኣወቀ ከቀናት በፊት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ የለጠፈውን ቀጥሎ ያንብቡት

እናስርሃለን፣ እንገድልሃለን! – የገዥዎቻችን የሥራና የመግባቢያ ቋንቋ

ሳሙኤል አወቀ

ሀገሬ፣ ታሪክ፣ ሐይማኖት፣ ባሕልና ሸማግሌዎች አሏት፡፡ ነገር ግን ምነው ትንፍሽ የሚል ጠፋ? በየቀበሌው ጠያቂ የሌለው ጥቃቅን ንጉስ ነግሶብናል:: በደል እና ግፍ ራሳቸው እየፈፀሙ ለራሳቸው እንድንሰግድ የሚያደርግሥርዓት ተበጅቷል:: የቀበሌ ካድሬ የፍርድ ቤት ውሳኔ እንኳን አይገዛውም:: አላምንበትም አልተማከርሁበትም ይላል:: ወደየት ይደረሳል? ለማንስ ይነገራል? ከተመደበለት የቀበሌ ኮሚኒቲ ፖሊስ ጋር አብሮ ያስራል፡፡ ይገርፋል፡፡ ይደበድባል፡፡ ሲፈልግ የሀሠት ምሰክር አደራጅቶ እሰር ቤት ያሰወረውራል፡፡ የህዝብ ሮሮ ለነሱ ሙዚቃ ሆኗል፡፡ ሀይ ባይ፣ ገላጋይ፣ ገሳጭ አሥታራቂ ሽማግሌዎች እና የኃይማኖት መሪዎች በዓለማዊ ሕይወት ሕዝባቸውን ረስተዋል፡፡

ማተቤ፣ ኃይማኖቴና ክብሬ ያሉ በአውሬ ተግባር ግፍ ተፈፅሞባቸው፣ ቶርች ተደርገው ወኀኒ ተዘግቶባቸዋል፡፡ የፖለቲካና የነፃነት፣ የፍትሕ የእኩልነት፣ ጥያቄ ያነሱ ኢትዮጵያውያን እንዳለሰው ተደርገው ወሕኒ ወርደዋል፡፡ ተሰደዋል፡፡ ተገድለዋል፡፡ አካላቸው ጎድሏል፡፡ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን እንዲሁ ተመሳሳይ ግፍ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አገራቸው አላስኖራቸው ብላ በስደት የበረሃ አወሬ የባሕር ዓሣ ቀለብ መሆናቸው ሳያንስ በፈላ ውሃ ተገሽረዋል፡፡ ከፎቅ ተወርውረዋል፡፡ የወሲብ ንግድ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በጅምላ ታፍነው አንገታቸውን ሲቀሉ አይተናል፡፡

ብሔራዊ ውርደት በዓለም የታሪክ መዝገብ ተፅፎብናል፡፡ በሙሰናና በብልሹ አሰተዳደር ታንቀናል፡፡ የከተማ ክፉ ችጋር ጠብሶናል፡፡ ወጣቶች ሥራአጥ ተደርገዋል፡፡ እህቶቻችን ጎዳና ላይ ናቸው፡፡ ስንቱ ጉድ ይፃፋል? ትላንት ኢህአፓ እንዲህ ተደረጉ ቀይ ሽብር ታውጆ ትውልድ እና እውቀት አለቀ ብለን በታሪካችን እያዘንን ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን ግን እጅግ የከፋ እና የአስተሳሰብ እድገት የተቀጨበት ነው! እናም ሽማግሌዎች እና የኃይማኖት አባቶች ከወዴት ናችሁ? ሀገሬ ኢትዮጵያ እርቅ ያስፈልጋታል? የኢትጵያዊያን የሰቆቃ እና የጣር ጬኸታችንን እያቃሰተ ነው:: የግፍ ፅዋው ሞልቶ ገንፍሏል:: አስርሃለሁ፣ ትገደላለህ፣ ትታፈናለህ፣ ትባረረላህ የገዥዎቻችን የሥራና የመግባቢያ ቋንቋ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Filed in: Amharic