>
4:13 am - Friday February 3, 2023

አዲስ ዓመት ያለ ተስፋ!? የኦባንግ ሜቶ መልዕክት!

ለመላው የኢትዮጵያ ሃይማኖት መሪዎችና ምዕመናን !

የተወደዳችሁ የአገራችን የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የየእምነቱ ምዕመናን፡-
Obang-O-Metho - from Obang facebookይህንን መልዕክት የምጽፍላችሁ ወንድማችሁ ይህንን ጥሪ የማቀርብላችሁ እንደ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር ለእናንተ ሃሳቤን ለማቅረብና እንደ እምነቴ ደግሞ በጌታችን የሱስ ክርስቶስ ባለኝ እምነትም ጭምር ነው። ይህንን ስል ሌሎች እንደ እኔ ዓይነት እምነት የሌላችሁን የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች ያገለልኩ መስሎ እንዲሰማችሁ ወይም ከእኔ ጋር ተመሳሳይ እምነት በሌላችሁ ላይ ጫና ለማድረስ በጭራሽ ምኞቴ እንዳልሆነ አስቀድማችሁ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። የራሴን መግለጼ እንደ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር እና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ማንነቴን አሳውቄ ሃሳቤንም በዚያው መልኩ እንድትረዱልኝ ከማድረግ አኳያ ነው።

ኢትዮጵያ በምንላት አገራችን ሁላችንም የተለያየ ሃይማኖት እንከተላለን፤ እንደየ እምነታችንም የአምልኮ ሥርዓታችንን እንፈጽማለን። አገራችን ለዚህ ዓይነቱ ልዩነት አንዳችም ሳታጓድልብን ሁላችንም ታስተናግዳለች። የምንከተለው እምነት የፈጣሪን ኃያልነት ያስተምራል፤ ሰላምን፣ እኩልነትን፣ ፍቅርን፣ መከባበርን፣ ወዘተ ያስተምራል። ይህንን አለመከተልና በጥፋት ጎዳና መጓዝ ለጊዜው ምቾትንና ድሎትን የሚፈጥር ቢመስልም የምናምነው እምነት እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የሚያመጣውን አስከፊም ነገር አብሮ ያስተምራል። ስለዚህ ለአምላክ የምንሰጠው አምልኮ እንዲሁም ለሌሎች ያለን አክብሮትና እንክብካቤ (ጠላት ብለን ለምንቆጥራቸውም ጭምር) በእያንዳንዱ የምንከተለው ሃይማኖት ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ ተገልጾዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕይወትን ምረጥ” በማለት እንዲህ ሲል ይመክራል፤ “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ” (ዘዳግም 30፡19) ዋናው ሃሳብ በምንኖርበት ዘመን የምናደርገው ማናቸውም ነገር ከእኛ አልፎ ለዘርና ለትውልድ ይተርፋል፤ መልካምም ቢሆን መጥፎ!

http://www.goolgule.com/a-new-year-without-hope-obangs-mes…/

አገራችን ወዳለችበት ሁኔታ ስንመለስ በምንወዳት አገራችን በእርግጥ ሕይወት አለ? ሰዎችስ በእርግጥ እየኖሩ ነው ማለት ይቻላል? የዚህ ምላሽ ለጥቂቶችና “ደልቶናል” ለሚሉ መልሱ “አዎ” ሊሆን ይችላል። ከአገራቸው እየተሰደዱ መድረሻቸውን በውል ሳያውቁ ለሚሄዱ ግን መልሱ “አዎ” አይደለም። በአገራቸው እየኖሩ በልቶ ማደር ተዓምር ለሆነባቸው፤ በአገራቸው ያጡትን ህይወት ለማግኘት ህይወታቸውን ለባህር አውሬና ለበረሃ ዘራፊ ለሚሰጡ፣ በየአረብ አገሩ ቀባሪ አጥተው በየቦታው ከውሻ ያነሰ ሞት ለሚሞቱ፣ አእምሯቸውን ስተው በበረሃው የአረብ አገር ቀኑን ሙሉ ለሚንከራተቱና አገራቸው የሚልካቸውም ሆነ እዚያ የሚያሳክማቸው ላጡ፣ ኢትዮጵያም የእኛ ናት ስለዚህ ሃሳባችንን በነጻነት በመግለጽ እንኖራለን በማለታቸው ብቻ “አሸባሪ” ተብለው ከቤተሰባቸው ለተነጠሉትና አዲሱን ዓመት በእስር ቤት በመማቀቅ ለሚያሳልፉ፣ ለሌሎችም እዚህ ላይ ጠቅሼ ለማልጨርሳቸው ነገር ግን ሕይወታቸው በስቃይ፣ በመከራ፣ በፍርሃት፣ በግፍ ለሚያሳልፉ ሁሉ የዚህ ጥያቄ መልስ እንዴት “አዎ” ሊሆን ይችላል? ተስፋ ሳይኖር አዲስ ዓመት ምን ይረባል? እንዴትስ አዲስ ዓመት ተብሎ ሊከበር ይችላል?

ስለዚህ በዚህ አዲስ ብለን በምንጠራው ዓመት ሕዝባችን ተስፋ ይፈልጋል፤ አሻግሮ ማየት ይሻል፤ ይህንን የማድረግ ዋንኛው ኃላፊነት የወደቀው በሃይማኖት መሪዎች ነውና በየቤተእምነቱ ወደ ፈጣሪ ከልብ የሆነ ጸሎት ከማድረግ በተጨማሪ ይህንን መልዕክት ላስተላልፍላችሁ እወዳለሁ።

ለየሃይማኖቱ መሪዎች፡-
በአገራችን ኢትዮጵያ ላመኑበት እምነት የቆሙ፣ በጽናት ከመቆማቸው የተነሳ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ፣ ከሰው ሕግ እና ከጊዜያዊ የግል ጥቅም ይልቅ በፈሪሃ እግዚአብሔር ለፈጣሪ ሕግና ሥርዓት የተገዙና ምሳሌ ትተውልን ያለፉ የሃይማኖት አባቶች አሉን። ከ“እኔ ምናገባኝ” አስተሳሰብ ያለፉ፤ ከአገዛዝ ጋር የሚያጣላቸው መስሎ ሲሰማቸው “እኔ የሃይማኖት ሰው ነኝ እንጂ ፖለቲከኛ አይደለሁም” በማለት በምቾታቸው ውስጥ ያልተደበቁ፤ በምድር ኑሯቸው የሚፈልጉትን ሁሉ በማድረግ ደልቷቸው እየኖሩ ለእውነትና ለፍትሕ መቆም ሲጠየቁ “አገራችን በሰማይ ናት” በማለት ማስተባበያ የማይሰጡ ተምሳሌቶች አሉን።

አቡነ ጴጥሮስ
የቅኝ ግዛትና ሌላውን የበታች የማድረግ እርኩስ መንፈስ የተጠናወታቸው ምዕራባውያን ጣሊያንን ለኢትዮጵያ መድበው ገዢ ሲያደርጉ ጣሊያኖች ያላሰቡት ነበር የገጠማቸው። ሕዝቡ ለእነርሱ እንዲገዛ በቤ/ክ በኩል ለማድረግ የወጠኑት አቡነ ጴጥሮስ ጋር ሲደርስ ከሽፏል። ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ምዕመኑን “እንደንጉሡ አጎንብሱ” በማለት የጣሊያንን አገዛዝ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው በማለት ሕዝቡን ማስገዛት ፈጽሞ የማይዋጥላቸው ስለነበር በመትረየስ ተደበደቡ። ይህንን ቃል ኪዳን አሰምተው፤ ጽናታቸውን ይፋ አድርገው፤ ሃሰትን በስሙ ጠርተው፤ ጭካኔን ኮንነው፤ የሕዝባቸውን ባርነት ከማየት በሕይወት አለመኖርን መርጠው አለፉ፤ “እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። … እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ” ነበር ያሉት። ታሪክን መዘከር ብቻ ሳይሆን ይህ ዓይነቱን አገዛዝን በፊት ለፊት የሚጋፈጥና ለሕዝቡ በመስዋዕትነት ተስፋን የሚፈነጥቅ “ጴጥሮሳዊነት” እጅግ ግዙፍ ምሳሌያችን ሊሆን ይገባል።

የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ
አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንደ ሃይማኖት የሚከተለው አገዛዝ ለዓመታት አፍኖ የቆየውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ተገቢ በሆነ ሁኔታ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል በማለት በቤተ እምነቱ የተመረጡት መፍትሔ አፈላላጊዎች የደረሰባቸው በዘመናችን ላመኑበት መቆም ምን እንደሚያመጣ የታየበት ነው። ከወጣት እስከ አዛውንት በመሆን የተሰባሰቡበት መፍትሔ አፈላላጊዎች ስማቸው በብዙ ጠልሽቷል፤ እጅግ ብዙም ተብለዋል። “ጂሐዳዊ ሐረካት”፣ “አክራሪ፣ ጽንፈኛ”፣ “እስላማዊ መንግሥት መስራቾች”፣ ወዘተ ተብለው ለበርካታ ጊዜያት አለፍርድ ሲንገላቱ ቆይተው በአሁኑ ጊዜ እስከ 22ዓመት በሚደርስ እስራት ስቃይ እየተቀበሉ ነው። በግድ እንዲያምኑና እንዲፈርሙ ሲደረጉ እምቢ በማለታቸው ስለተቀበሉ ስቃይ ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር፤ “… ማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ስነልቦናዊ እና አካላዊ ስቃይ ይደርስብናል። ከአስራ አራት ሰዓታት በላይ ያለ እረፍት ቀጥ ብለን እንድንቆም በማድረግ፣ ጀርባችን እስኪላጥ ራቁታችንን በሽቦ በመግረፍ፣ በሰንሰለት በማሰር እና አይናችንን በጨርቅ በመሸፈን የውስጥ እግራችን እስከሚላጥ ገልብጦ በመግረፍ ቀንና ማታ አሰቃቂ በሆነ ምርመራ እና በድብደባ ብዛት እንቅልፍ በመንሳት፣ ፂማችንን በመንጨትና እንድንላጭ በማስገደድ፣ ከአቅም በላይ የሆነ ስፖርት በግድ በማሰራት፣ ብልት በመግረፍ፣ “ልጅህን እንገድለዋለን! ሚስትህን አስረን በፊትህ ቶርች እናደርጋታለን! ብልትህ ላይ የውሃ ሃይላንድ በማንጠልጠል መሀን እናደርግሀለን!” እያሉ በማስፈራራት ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ስቃይ አድርሰውብናል።… በክረምት ቀርቶ በበጋ እንኳ ቅዝቃዜው በማይቻለው “ሳይቤሪያ” ተብሎ በሚጠራው ጨለማ ክፍል አጉረውናል። መቋቋም የሚያዳግተውን የማሰቃያ ስልታቸውን በመጠቀም ያላሰብነውንና ያልሰራነውን ‹እመኑ! ተናገሩ! ፈርሙ!› ብለው አስገድደውናል”። ግፍን እና ሃሰትን አንቀበልም፤ ይልቁንም በስሙ በመጥራት እናወግወዘዋለን፤ እስከ ህይወትም መስዋዕትነት በመክፈል እናልፋለን በማለት በዚህም ዘመን ላለነውም ሆነ ለመጪዎቹ ተስፋን ፈንጥቀው በህይወታቸው ምሳሌ በመሆን ትምህርት ሰጥተውናል።

መጋቢ ጉዲና ቱምሣ
ለአገራቸውና ለሕዝባቸው እጅግ ብዙ አስበውና አልመው ሕልማቸውን ከግብ ሳያደርሱ በአጭር እንዲቀሩ የተደረጉት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዩን ቄስ ጉዲና ቱምሣን ይህ ያለንበት ዘመን በግድ እንድናነሳቸው ያደርገናል። ምዕራባዊ አስተሳሰብንና አመራርን በአትዮጵያ ቤ/ክ ላይ ለመጫን የፈለጉትን ኃይሎች በአንድ በኩል በመቃወምና ለኢትዮጵያ የሚሆን አገራዊ ሃሳብ በማመንጨት ለማሳመን ሲጥሩ በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥ የሚደረገው የወንጌል ስርጭት ምንነትንና ይዘት በገሃድ ያስተምሩ ነበር። ጉዲና ቱምሣ “የፍቅርና የፍትሕ ሃይማኖት” ብለው የሚጠሩት ወንጌል ምንነት ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር፤ “እኛ (ቤ/ክ) ለፍትሕ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበርና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እንመኛለን፤ እንሠራለን”። ይህንን ዓይነቱን አስተሳሰብ ለመስማት እጅግ የከበደው አገዛዝ የፍትሕ ድምጽ የነበሩትን የሃይማኖት መሪ አሠራቸው፤ አሰቃያቸው። በወቅቱ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኔሬሬ መጋቢ ጉዲናን ከእስር ለማስፈታትና ከአገር እንዲወጡ ለማስደረግ እንደሚችሉ ሃሳብ ባቀረቡ ጊዜ የቄስ ጉዲና ቱምሣ መልስ እንዲህ የሚል ነበር፤ “ቤተክርስቲያኔም ሆነ ሕዝቤ ያለው እዚህ ነው፤ እንደ እኔ ያለ የቤ/ክ መሪ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መንጋውን በትኖ እንዴት ይሸሻል? (እዚሁ) ለመቆየት ወስኛለሁ” ካሉ በኋላ በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስን ቃል ጠቀሱ “በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” ስለዚህ “በጭራሽ አላመልጥም፤ አልከዳም” በማለት “የፍቅርና የፍትሕ ሃይማኖት” ምንነትን በህይወታቸውም ጭምር በመስበክ የዛሬ 36ዓመት የተስፋን ብርሃን ፈንጥቀውልን አለፉ።

እነዚህን ለምሳሌ ያህል አነሳኋቸው እንጂ አገራችን የሃይማኖት ጀግኖችን ያፈራች ናት። ያልተዘመረላቸው፣ ያልተጻፈላቸው፣ ስማቸው የማይታወቅ፣ የተረሳ፣ ጥቂቶች አይደሉም። ጥያቄውና ሸክሙ ያለው አሁን ባላችሁት በእናንተ ላይ ነው፤ በተለይም መሪዎች፤ ምክንያቱም እናንተ የአምላክ አፍ ናችሁ፤ ጉበኞች፣ ጠባቂዎች ናችሁ (ሕዝ.33)!! ስለዚህ ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “አስተማሪዎች (መሪዎች) የሆንን የባሰውን ፍርድ እንቀበላለን” ይላል (ያዕቆብ3፡1)። በዚህ ብቻ አያቆምም፤ እንደ ሃይማኖት መሪነታችሁ የምትሰብኩትና የምትኖሩት ህይወት የማይገጣጠም ከሆነ፤ ይህንን ብናገር፤ ለፍትሕ ብቆም የሚመጣብኝን መሸከም አልችልም፤ እንደ ንጉሡ አጎንብሱ ብዬ ቀን ባልፍ ይሻላል፤ ጊዜው የልማትና የዕድገት ነው፤ ሃይማኖቴ እስካልተነካ ድረስ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አያስፈልገኝም፤ ወዘተ በሚል ማስመሰያ ራሳችሁን ደብቃችሁ ምዕመኖቻችሁንም በዚሁ የምትመሩ ከሆነ መጽሐፉ እንዲህ ይላችኋል፤ “አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው” (ያዕቆብ 1፡26)።

ለምዕመናን፤
አንድን ሃይማኖት የምትከተሉት ህይወት በዚህ አጭር የምድር ኑሮ ተወስና የምትቀር አለመሆኗን ስለምታውቁ ነው፤ ለዚህም ነው በፈሪሃ እግዚአብሔር ሃይማኖታችሁን የምጠብቁት። ይህ ሲሆን ግን እያንዳንዳችሁ ሃይማኖታችሁ ለሚያስተምረው ትምህርት በጽናት መቆም፤ ሌሎች ሲበደሉ “እኔን ምን አገባኝ” ሳይሆን የአምላክ ፍጡር በጭራሽ እንዲህ ዓይነት በደል ሊደርስበት አይገባም፤ ፍርድም የሚሰጥ ከሆነ በተገቢው መንገድ ሊበየን ይገባል በማለት ስለ እውነት፣ ስለ ሐቅ፣ ስለ ፍትሕ መናገር የምዕመን ኃላፊነት ነው! የወገናችሁ ተስፋ ማጣት ነው ከአገሩ፣ ከከተማው፣ ከቀዬው እንዲሰደድ የሚያደርገውና የወገናችሁ ስቃይና መከራ ተሰምቷችሁ ድምጽ ሁኑለት፤ ጸሎት አንዱና ወሳኙ ቢሆንም ጸሎት በገሃድ መታየት፣ በተግባር መተርጎም አለበት።

የትግራይ ተወላጆችም በዚህ ውስጥ አላችሁበት፤ እናንተም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ የእስልምና፤ የፕሮቴስታንት፣ እምነት ተከታዮች ናችሁ። እንዲሁም ኢህአዴግ በሚባል ሃይማኖት ውስጥ ያላችሁ፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተጠመቃችሁና “የመለስ ራዕይ” የሚባል ድግምት በመድገም የተለከፋችሁ ሁሉ የምታምኑትን ማመን ትችላላችሁ። ሆኖም ግን ከፈጣሪ የሚበልጥ ሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ አመለካከት ወይም ራዕይ የለምና ሁላችሁም በፈጣሪ ፍርድ ወንበር ፊት በመቆም መልስ የምትሰጡበት ፍርድ መኖሩን አትዘንጉ።

ስለዚህ ኢህአዴግን እያመለካችሁ በየቤተ እምነቱ ያላችሁ መሪዎችም ሆነ ምዕመናን ሁሉ የምታነቡት የሃይማኖት መጽሐፍ ለአንዱ አምላክህ ስገድ እርሱንም አምልክ ነው እንጂ የሚለው ለድርጅት፣ ለግምባር፣ ለንቅናቄ፣ ለፓርቲ ስገድ አይልም። አምላክ በሃይማኖት አባቶችና በነቢያት የገለጸለጸልህን ፈቃድ ተከተል ነው እንጂ የሚለው “የመለስን ራዕይ” የእምነትህ መመሪያ አድርግ አይልም። ስለዚህ ወደ እምነታችሁና ወደ ፈጣሪያችሁ ተመለሱ። ቢያንስ ኅሊናችሁ የሚነግራችሁን ወቀሳ ስሙ፤ የሕዝብ እምባ ግድ ይበላችሁ።

ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ፍቅር ለራሳችሁም ሆነ ለወገናችሁ በመቆማችሁ ስቃይን፣ መከራን፣ ሰቆቃን፣ ሃዘንን፣ ወዘተ እየተቀበላችሁ ያላችሁ የሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ምዕመናን በአጠገባችሁ ላሉት የተስፋን ጮራ እየፈነጠቃችሁ፣ የመኖርን ምንነት በህይወታችሁ እያስረዳችሁ ነውና በርቱ። አምባገነንነትና ጭቆና ዘላለማዊ አይደለም፤ ፈራሽ፣ ከንቱ፣ ዛሬ ታይቶ ነገ የማይገኝ፣ ሰብዓዊ ነው እንጂ አምላካዊ አይደለምና አትፍሩት። አምላካችን እጅግ ታጋሽና እጅግ ርኅሩኅ ቢሆንም ቅን ፈራጅ፣ በፍርዱም የማያዳላ፣ መማለጃ የማይቀበል ነውና ዛሬ ገዝፈው ለመታየት የሚሞክሩትን በእብሪተኝነታቸው የሚቀጥሉና ሕዝብን እያስለቀሱ መንገሥ የሚመኙትን ሁሉ በዚህ አዲስ ዓመት በቃችሁ የሚልበት ሊሆን ይችላልና በእምነት ጽኑ። በየትኛውም እምነት ብትሆኑም የአምላካችሁ ቃል እንዲህ ይላል፤ (ኢያሱ1፡9) “በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ አይዞህ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”

ስለዚህ አሁንም ተስፋ አለ፤ አሁንም ፍትህ ይሰፍናል፤ አሁንም በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ አለን!!

በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋን የምመኝላችሁ ወንድማችሁ፤
ኦባንግ ሜቶ
_________________
ለተጨማሪ መረጃ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶን በዚህ ኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡- Obang@solidaritymovement.org

Filed in: Amharic