>

‹‹የትግላችን መቋጫ የሙሉ መብታችን መከበር ብቻ ነው!›› ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

የወንድሞችን መፈታት አስመልክቶ ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

ማክሰኞ መስከረም 4/2008

የመግለጫው ሙሉ ቃል በጽሁፍ፡-

‹‹የትግላችን መቋጫ የሙሉ መብታችን መከበር ብቻ ነው!››

‹‹ታሳሪዎቹም ተፈቺዎቹም ጀግኖቻችን ናቸው!››

ማክሰኞ መስከረም 4/2008

የኢትዮጵያ መንግስት ያለምንም ወንጀል ከ7 እስከ 22 ዓመት በግፍ ከፈረደባቸው ወንድሞች መካከል 6ቱን እንደሚለቅ ከቀናት በፊት አስታውቆ የነበረ ቢሆንም ገና ዛሬ አራቱን ብቻ (ኡታዝ ያሲን ኑሩን፣ ወንድም ሷቢር ይርጉን፣ ጋዜጠኛ አቡበከር ዓለሙን እና ገጣሚ ሙኒር ሑሴንን) ከእስር መልቀቁን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከቀሪዎቹ ሁለት ታሳሪዎች አንዱ የሆነው ኡስታዝ ባህሩ እና ሌላ ስሙ ያልተጠቀሰ ታሳሪ ጉዳይ እስካሁን አልታወቀም፡፡ ከቀናት በፊትም በኮፈሌ መንግስት ራሱ ባስነሳው ግርግር በእስር አጉሮ ሲያጉላላቸው ከከረሙት የኮፈሌ ጀግኖቻችን ውስጥ 20 የሚሆኑትን ከአዲሱ ዓመት ጋር በማያያዝ እንዲለቀቁ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን 6ቱ ወንድሞች ይፈታሉ ተብሎ በዜና የተነገረው ከቀናት በፊት ቢሆንም 4ቱ የተፈቱት ግን ገና ዛሬ ነው። እነዚህ ወንድሞች ከሌሎቹ የትግል አጋሮቻቸው ተነጥለው ይለቀቃሉ የተባሉበትን ምክንያት ሲያሻው ፈራጅ ሲያሻው ፈቺ ከሆነው መንግስት ውጭ የሚያውቀው አካል የለም። በአንድ በኩል ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የወንድሞቻችን መፈታት የትግላችን ፍሬ ነውና የተሰማንን ደስታ እየገለጽን በሌላ ጎኑ ደግሞ ለአራት አመታት በዘለቀው ትግላችን የመንግስትን ተለዋዋጭ ባህሪና ትግሉን ለማኮላሸት ያደረገውን ከንቱ ጥረት ስናይ መንግስት አዲሱን ዓመት ተገን አድርጎ አዲስ የማደናገሪያ የፖለቲካ ጨዋታ ይዞ ብቅ ማለቱን እንገነዘባለን። ከዚህ አንፃር እና ከተያያዝነው ትግል አኳያ የተወሰኑ ነጥቦችን በጥንቃቄ ማየት አስፈላጊ ይሆናል።

እንደሚታወቀው የእንቅስቃሴያችን ዋና መገለጫ በህዝቡ እና በወከላቸው መሪዎቹ መካከል ያለው ፅኑ ትስስር እና መተማመን ነው። ይህን የትግላችንን ፅኑ ገመድ በቻለው መንገድ ሁሉ ለመበጠስ እና ይህ አልሳካ ሲልም ትስስሩን ለማላላት መንግስት ብዙ ሲጥር ቆይቷል። መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት በሚዲያዎቹ መሪዎቻችንን ከማብጠልጠል አንስቶ የድራማ ዶክመንታሪዎችን በማዘጋጀት ህዝቡ በመሪዎቹ ላይ እምነት እንዳይኖረው ለማድረግ ሞክሯል። ለአንድ ህዝባዊ አላማ አንድ ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን የኮሚቴውን አባላት ግማሾቹን በቁም እስር በማዋል፣ ግማሾቹን ደግሞ አሳድዶ በማሰር ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ ሲያሰቃይ የቆየው መንግስት አሁን ላይ የተወሰኑትን ወንድሞች ከፖለቲካዊ ፍርድ ማግስት ነጥሎ የመፍታቱ አላማ የእንቅስቃሴውን ውብ ህዝባዊ ድጋፍ የመሸርሸር የተለመደ አባዜ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከዚህ በፊትም ሲከተለው የነበረው የትግሉን አቅጣጫ እና የህዝብን አስተሳሰብ የማስለወጥ ሙከራ አካል መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህ በፊት በተወሰኑት የኮሚቴው አባላት ላይ አሳድዶ በማሰር አሰቃቂና የሆነ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅም ቆይቷል። ያሰራቸውን እና በተመሳሳይ ጉዳይ የከሰሳቸውን የኮሚቴውን አባላት ደግሞ የተወሰኑትን መልሶ ሲፈታ፣ ቀሪዎቹን ደግሞ ‹‹ጥፋተኛ›› ብሏል። ለአንድ አይነት ጉዳይ አንድ አይነት ህዝባዊ አደራ ይዘው የተነሱትን ወንድሞች በዚህ መልክ የመከፋፈሉ አላማ በኮሚቴው አባላት መካከል የሃሳብ እና የቁርጠኝነት ልዩነት እንዳለ ህዝቡ እንዲያስብ ለማድረግ የተቀመረ መንግስታዊ ሴራ ነው። እናም ዛሬም እንደ ትላንቱ አንዱን ኮሚቴ ከሌላው የምናወዳድርበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለን እንገልጻለን፤ በትግሉ ምክንያት የታሰረ አንድ ሰው እንኳን እስካለ ድረስ ሁሉም እንደታሰረ ይቆጠራልና። ይልቁኑም ሃይማኖታችን በተደፈረበት፣ መንግስታዊ አምባገነንነት በሰፈነበት በዚህ ቁርጥ ጊዜ ይህንን ታላቅ ህዝባዊ አደራ ተሸክመው የሰው ልጅ ችሎ ያልፈዋል ተብሎ በማይታሰበው የስቃይ እቶን ላይ እራሳቸውን መስዋዕት ያረጉልንን ወንድሞቻችንን ሳናወዳድር ሁሉንም በክብር ሰገነት ላይ ለማስቀመጥ አናቅማማም።

መንግስት ከህዝብ በሚሰበሰብ ግብር ተቋቁመው ህዝብን በሚያጠቁ የመገናኛ አውታሮቹ አማካኝነት የወንድሞችን መፈታት አስመልክቶ የፖለቲካ ጨዋታ ለመጫወት እንዳሰበ መገመት ከባድ ባይሆንም የወንድሞቻችን ፍርድ ፖለቲካዊ የመሆኑን ያክል የተፈቱበትም መንገድም ፖለቲካዊ እንጂ ሌላ አለመሆኑን ሂደቱን የተከታተሉ ሁሉ የሚገነዘቡት ሃቅ ነው። ለዚያም ነው በመሠል የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ከመግባት ተቆጥበን ፊታችንን ወደትግሉ ልናዞር የሚገባው፡፡

ከምንም በላይ ትኩረት የምንሰጠው የትግላችንን ዋና መሰረት እና ግባችንን ነው። መንግስት የቀረቡለትን ቀላል የህዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ አሻፈረኝ በማለቱና በወሰደው የእብሪት እርምጃ የትግሉ አላማ ከመብት መጠየቅ ወደ መብት የማስከበር እና ብሄራዊ ጭቆናን የመታገል ዓላማ ከተሸጋገረ ቆይቷል። ትግሉ ሲፀነስ ጀምሮ መንግስት ግለሰቦችን በማሰር፣ በማስፈራራት እና በመግደል ትግሉን ለማስቆም ሞክሯል። በመላ አገሪቱ ሙስሊሞችን ወደ እስር ቤት ቢያግዝም፣ በገርባ፣ አሳሳ፣ ኮፈሌ እና ሃረር ንፁሃንን ቢገድልም ትግሉ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ህዝባዊነትን እየተላበሰና አዳዲስ ስልቶችን እያስተዋወቀ ከተነሳንለት አላማ ዝንፍ እንደማይል አረጋግጧል። ትግሉ ለተወሰነ ጊዜ ከነበረበት የመቀዛቀዝ ስሜት ወጥቶ በመላው የሃገሪቷ ክፍል ሰፋፊ ህዝባዊ የመታገያ እና የማታገያ ስልቶችን እያስተዋወቀ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የመንግስት የተወሰኑትን ወንድሞች መልቀቅ የትግላችን ውጤት መሆኑን መካድ አይቻልምና አላህን እናመሰግናለን።

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የወንድሞቻችን መፈታት የትግላችን ተጨማሪ ጥያቄ እንጂ ዋነኛ ጥያቄያችን አለመሆኑን ሁሌም ማስታወስ ይገባል። የትግላችን ማጠንጠኛ መንግስት የጀመረው ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ብሄራዊ ጭቆና ነው፡፡ የትግላችን ግብም ይህንን ጭቆና ማራገፍ እና መብታችንን በዘላቂነት ማስከበር መቻል ነው። እስራትን እና ድብደባን ያስተናገደው፣ ደም የፈሰሰለት እና አጥንት የተከሰከሰለት ትግላችን ሃይማኖታዊ ጭቆናን ታግሎ የማሸነፍ ታላቅ ተልዕኮ እንጂ በዚህ መሃል በተፈጠሩ ክስተቶች በመዳከር የሚያባክነው ጊዜ እና ጉልበት አይኖርም። መንግስት ከሙስሊሙ ጋር የተጋባውን እልህ የማለዘብ እውነተኛ ፍላጎት ካለው በመላ አገሪቱ ያለምንም ወንጀል ያጎራቸውን ሙስሊሞችን በሙሉ ፈትቶ፣ የህዝቦችን የማመን፣ ያመኑበትን የመተግበር እና የማስተማር ነፃነት እንደማይዳፈር ማረጋገጥ የሚያስችለውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በተለያዩ መደለያዎች የትግሉን አቅጣጫ ለማስለወጥ መሞከር ከከንቱ ድካም የዘለለ አይደለም።

በተለያየ ጊዜ እና ሁኔታ መንግስት ያቀደለትን ሴራ እየመከተ የቀጠለው ትግላችን አሁንም መንግስት በአዲስ አመት ይዞት ብቅ ያለውን አዲስ ሴራ ለመመከት ትግላችንን ከመቼውም በላይ አጠናክረን በመቀጠል ምላሽ እንሰጣለን። ለዚህ ሂደት ደግሞ መስዋዕትነት የከፈሉ እና እየከፈሉ ያሉ ጀግኖቻችን ዋና የትግል ፋኖዎቻችን ናቸው። አሁን ላይ መንግስት የተወሰኑትን ወንድሞች መፍታቱ በየጊዜው የሚወስዳቸው የማደናገሪያ ፖለቲካዊ ድራማዎች አካል መሆኑን ተገንዝበን አሁን ለትግበራ የቀረቡ እና ወደፊትም በስፋት የምንተገብራቸውን ህዝባዊ ስራዎች በትጋት እና በንቃት በመፈፀም ትግሉን አጠናክረን ለመቀጠል ቁርጠኝነት ልናዳብር ይገባል። በመሆኑም ከዚህ ውጭ በሆነ አካሄድ መንግስት ያዘጋጃቸውን የ‹‹ይቅርታ›› እና ተያያዥ የመከፋፈያ አጀንዳዎች ርእስ በማድረግ አላስፈላጊ ክፍፍል እና ጭቅጭቅ ውስጥ ከመግባት ሁላችንም በመቆጠብ፣ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ደስታ እና ከዓላማ የሚያዘናጋ ፈንጠዝያ በመቆጠብ ወደትግላችን ብቻ እናተኩር ዘንድ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡ የትግሉ ታሳሪዎች በሙሉ መስዋእትነት ባስፈለገ ጊዜ አንዳችም ሳይሳሱ ውድ መስዋእትነት የከፈሉ መሆናቸውን እውቅና በመስጠትም ታሳሪዎችም ተፈቺዎችም ለእኛ ምንጊዜም ጀግኖች መሆናቸውን በመረዳት ከአላስፈላጊ አጀንዳዎች በመራቅ ለጀግኖቻችን ያለንን ክብር እንገልጻለን፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ከረጅም ስቃይ በኋላ የተፈታችሁት ውድ ጀግኖቻችን፣ እንዲሁም የእስር ጊዜያችሁን ጨርሳችሁ በአመክሮ መፈታት እየቻላችሁ በተለመደው መንግስታዊ የ‹‹ይቅርታ›› ድራማ ከእስር እንድትወጡ ለተደረጋችሁ የኮፈሌ ጀግኖቻችን ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ! የከፈላችሁትን መስዋዕትነት አላህ ይቀበላችሁ!›› እያልን ሙስሊሙ ማህበረሰብም ለእነዚህ ጀግኖች ሁሉን አቀፍ ድጋፉን እንዲቸራቸው በአላህ ስም እንጠይቃለን።

ታሳሪዎቹም ተፈቺዎቹም ጀግኖቻችን ናቸው!

የትግላችንን ህዝባዊነት አያሰፋንና እያጎለበትን በአላህ ፈቃድ ከድል ደጃፎች እንደርሳለን።

ድምጻችን ይሰማል! አላሁ አክበር!

የመግለጫው ፒዲኤፍ ቅጂ ሊንክ፡-

http://goo.gl/dc4RPE

Filed in: Amharic