>

የአዳም ዘመንና ራዕይ [አለማየሁ ገላጋይ]

ደራሲ አዳም ረታ ከሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን የተለየ ስነ-ስጽሑፋዊ ብሒል አለው፡፡ ፀጋዬ “የሕዝቡ ሙቀት ካልሞቀህ፤ በሕዝቡ ሕዝባዊነት ውስጥ ካልታቀፍክ የእሱን ሕይወት አትተረጉምም፡፡ ደራሲ መሞት የሚጀምረው ከሕዝቦች አካል ውጭ ከተለየ በኋላ ነው” ይላል፡፡ አዳም ደግሞ የደራሲን ከአገር መሰደድ እንደ ደራሲው ትንሣኤ ሙታን ያየዋል፡፡ “ተራራኮ ራቅ ስትል ነው የሚታየው” የሚል እምነት አለው፡፡ “ተራራን ተራራው ላይ ሆኖ አጥርቶ ያየ ማነው?”

ፀጋዬ በስተመጨረሻ በስደት አሜሪካ ኒውዮርክ ሳለ መጻፍ ተስኖት እንደነበር ራሱ ይናገራል፡፡ አዳም ረታ ደግሞ ባለው የስነ-ጽሑፍ ብሂል እየተመራ፤ አገሩን ከአገሩ ራቅ ብሎ እያስተዋለ በመጻፍ ላይ ነው፡፡ እርግጥ “ተራራው” ላይ ሆኖም ስለ “ተራራው” ሲጽፍ እንደነበር አንዘነጋውም፡፡ “ማህሌት” እና “አባደፋር” ላይ ያቀረባቸው አጫጭር ልቦለዶቹ የተጻፉት እንደዚያ ነው፡፡ “አለንጋና ምስር” ላይም እዚሁ አገር ውስጥ እያለ ያቀረባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ሰሞኑን ገበያ ላይ የዋለው ስድስተኛ መጽሐፉ ግን ሙሉ በሙሉ የተጻፈው “ከተራራው” ባሻገር ሆኖ አገሩንና ሕዝቡን ከሩቅ እያስተዋለ ነው፡፡ ሆላንድ እና ካናዳ ውሰጥ ሆኖ ከ1983 እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ፡፡

Ywesdal menged yemetal menged- Adam Retaየአዳም ረታ ስድስተኛ መጽሐፍ እንደተለመደው እንግዳ ርዕስ ይዞ ነው የመጣው፡፡ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ይሰኛል፡፡ ያልተለመዱ ርዕሶች አንዱ የአዳም መለያ እየሆነ ነው፡፡ የመጀመሪያው የአጫጭር ልቦለድ መድብሉ በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አርታዒዎች ተቀይሮ “ማህሌት” ተባለ እንጂ አዳም የሰጠው ርዕስ እንዲሁ እንግዳነት ነበረው፡፡ “ሥዕል በቁርጥራጭ ጨርቆች ላይ” የሚል፡፡ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” የጥቅሉ ድርሰት መጠቅለያ ርዕስ ሆነ እንጂ መጽሐፉ ውስጥ ያለ ተቀናቃኝ የሚያስተዳድረው የራሱ ግዛት አለው፡፡ ከአጠቃላዩ 456 ገጾች ውስጥ 71 ያህሉ ገጾች የዚህ ርዕስ ሉአላዊ መስተዳድር ሆኖ ተመድቧል፡፡

“ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ርዕሱ ተፈልቅቆ የወጣው ከነባር ትውፊት ነው፡፡ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ/ አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ” ትውፊቱ ለደበበ ሠይፉ መነሻ ሆኖት ባለ ሁለት ቅንጥ ግጥም አስፍሮበታል፡፡
“ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ እግር ሄደ እንጂ ልብ አይሰደድ”

የአዳም መጽሐፍ ይቺን ሐሳብ በከፊል መሠረት አድርጓል፡፡ አብዛኞቹ ገጸ-ባሕሪዎች ከግቢ ወጥቶ እንደማያውቅ ውሻ ልባቸው አገራቸውን አፀድ የሚዞር ስደተኞች ናቸው፡፡ ልብ እና ቀልብ አልሰደድ ብሎ ከገዛ እግር እና አካል የተጣጣበትን ትርክት እዚሁ የአዳም መጽሐፍ ውስጥ እናገኛለን፡፡ እንደ ሎጥ ሚስት መሀላቸው ትዕዛዝ ሆኖባቸው “ወይ ሀገሬ” በሚል መገላመጥ ወደ ጨው አምድነት የተለወጡ በድን ገጸ-ባሕሪዎች “ይወስዳል መንገድ…”ን በትዝታ ዜማ ያወራርዳሉ፡፡ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ስደት ቀሰስተኛ ሞት ሆኖባቸው በሕይወት ላይ ንዴት እና ንጭንጭ ይዘረግፋሉ፡፡

“እዛም የለሁ እዚህም የለሁ በሌለሁበት የሌለሁበትን እየተመኘሁ” (ገጽ 281) የሁሉም መዝሙር ነው፡፡

ስደት የአዳም ረታና የአዲሱ መጽሐፍ ነጠላ ግብ አይደለም፡፡ ስደት የዘመን መልክ ሲረግፍ የተፈጠረ አንዱ ስንጣቂ ነው፡፡ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ውስጥ ዘመን ከረጅም እንቅልፍ ተቀስቅሶ ሲንጠራራ በውጥረቱ እንደረገፈ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ገጾች ላይ እንረዳለን፡፡ “የመንግስቱ ነዋይ ጊዜ” ላይ ዘመን የመፍረስ አደጋው ደረሰበት፡፡ “ብዙ ተኛሁ” ይላል የንዑስ ምዕራፉ ተራኪ ትንሹ ሰናይ፡፡ የሕዝቡን፣ የሀገሪቱን፣ የመሬቱን… በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ መቆየት ሲፈክር ነው፡፡

“ብዙ ተኛሁ፡፡ ከትናንት ማታ አንድ ሰዓት እስከ ዛሬ ጠዋት ሁለት ሰዓት ነው የተኛሁት፡፡ ስባንን ድገተኛ የመሰለች ነገ መሃል ተጠናቅቄ ወድቄያለሁ ደክሞኛል፡፡ ብዙ ስተኛ ይደክመኛል”፡፡ (ገጽ 1)
ሰናይ ዘመንን ወክሎ ይፈክራል፡፡ የሀበሻ ዘመን ሲባንን ድንገተኛ የመሰለች ነገ መሃል ተጠናቆ ወድቋል፡፡ ክቡር ዘበኞች ናቸው ዘመንን ከረጅም እንቅልፍ የቀሰቀሱት፡፡ እዚህ የንቃት መንጠራራት ላይ ዘመን ባለ ብዙ መልክ ጅማሮ ያደርጋል፡፡ ጥንት የነበረውን መግባባትና መከባበር ይዳስሳል፡፡ የዘመን መልኩ አለመግባባት ይሆናል፡፡ እመቤትና ሽታዬ ገበጣ ለመጫወት ወጥተው ፀብ ያተርፋሉ፡፡ የገበጣ ጠጠሮች ሲመነጫጨሩ ግን ውስጥ የሌለበት ሰናይ አፍንጫውን ይመታል፡፡ የዚያን ዘመን መልክ-አንድ!

“ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” እንደ ሥላሴዎች አንድም፤ ብዙም በሆኑ ታሪኮች ተዋቀረ ነው፡፡ ስምንት ምዕራፍ (ክፍልም) የሆኑ ታሪኮችን አቅፎ በእናት ዶሮ ብሒል ሙቀት ይሰጣቸዋል፡፡

‹የመንግስቱ ነዋይ ጊዜ› የሚለው ቀዳሚ ትርክት የዘመን መልክ ነው፡፡ ተለጣጣቂው የዘመን ስባሪ በ ‹ቢሾፍቱ ልጆች ጥላሞት› ትረካ ውስጥ ብቅ ይላል፡፡ ‹ቀዳዳ› ሌላው የዘመን እርከን ነው፡፡ ‹ፍትፍትና ደጀ ሰላም›፣ ‹ኩሳንኩስ›፣ ‹አሕዛብ ማድ ቤት በር ላይ› እንዲሁም ‹ወላንሳ ወላንሳ/መሐረቡሳ› መጽሀፉ ላቆረው የታሪክ እርከን በየራሳቸው ቢርካ ትርክት የሚያዋጡ ገባር ምእራፎች ናቸው፡፡ ምእራፎቹ ገባር የታሪክ ወንዝ ብቻ አይደሉም፡፡ የዘመን ስንጥርጣሪዎችም ናቸው፡፡ እብድ ዘመን እንደ እንቧይ ለመፍረጥ የበቀሉ ትውልዶችን ሐዲድ አድርጎ ሲገሰግስ ይስተዋላል፡፡ በጭጎጎታም አካሉ ከየመንገዱ ዳር እየጠለፈ የሚዳጫቸው እልፎች ናቸው፡፡ ቅጥ ያጣ ችግር፣ ቅጥ ያጣ ፖለቲካዊ አቋም፣ ቅጥ ያጣ ስደት፣ ቅጥ ያጣ ራስ ወዳድነት፣ ቅጥ ያጣ ሕይወት የዘመን ብዙ መልኮች ናቸው፡፡ ታሪካችን ‹‹ከእሾህ የተጠጋ ቁለቋል ሲያለቅስም ሲያስለቅስም ይኖራል›› ይሆንብናል፡፡ በ ‹‹ይወስዳ መንገድ . . . ›› ውስጥ ዘመን እንደወራጅ ውሃ ማሽቆልቆል የተፈጥሮ ግዴታው ሆኖ ቀርቧል፡፡ የአዳም መጽሀፍ አንዱን የዘመን ወንዝ የተለያየ ስምና ድልድይ አበጅተን እንደምንመላለስበት አይነት ባህሪ አለው፡፡

ከአፍንጮ በር የተነሳው ወንዝ ራስ መኮንን ሲደርስ ሌላ ስምና ድልድ እንደሚያስፈልገው ማለት ነው፡፡ እሪ በከንቱ ላይ እንደዚያው፣ አሮጌ ቄራ፣ አምባሳደር ኡራኤል፣ . . . አዳም ብዙ ስምና ድልድይ ያበጀው ለአንዱ የዘመን ወንዝ ነው፡፡ ዘመን ተንፎለፉሎ፣ ተንፎለፉሎ ያለንበት ዘመን ላይ አይቆምም፡፡ ጭልምልም ያለ የመጪው ጊዜ ሰርጥ ውስጥ ገብቶ መዳርሻችንን ተስፋ ቢስ ያደርግብናል፡፡ ‹‹ወላንሳ ወላንሳ/መሐረቡሳ›› የሚተርከው ይህን የዘመን መዳረሻ ትንቅንቅ ነው፡፡

በመንግስቱ ነዋ ጊዜ የተጀመረው ትርክት የቀይ ሽብሩን ዘመን አቆራርጦ ከስራ የመፈናቀሉን ጉልጥምት አልፎ በቀለበት መንገድ በኩል በመጪው ተዳፋትነት እዚህ አዘቅት ውስጥ ይገባል፡፡ አዘቅቱ ፍጹማዊ እንዳሆን መሰረቱን የጣለው በሚያስቀናና ለመስዋዕትነት በተዘጋጀ ፍቅር ላይ ነው፡፡ ይሄ የአዳም ረታ ምናብ ወለድ ምዕራፍ 170 ገጾችን ፈጀ ሲሆን አሁን ካለንበት ዘመን 75 አመታት ወደፊት ተሸቀንጥሮ የሚኖረውን ማሕበረሰብ በስላቅ ይቃኛል፡፡ መጪዋ ኢትዮጵያ በቁጡ፣ በጨካኝና ትዕግስቱ ባለቀ የአየር ጠባይ ዜጎችን የምታስቸንቅ ትሆናለች፡፡ ‹‹በዘረ መል ምሕንድስና›› () ትከሻ ላ የወደቀው ሕዝቡ ኑሮ ተፈጥሮ ተመንጭቆ ሳይነስን ሙጥኝ ያለ ሰው ሰራሽ ሕይወት እንዲመራ ተገዶ እናያለን፡፡ በዚህ ላይ ፖለቲካው፡፡

በዚያ ዘመን ፖለቲካ ገላ ላይ ጸጉር በመኖርና ባለመኖር የተመሰረተ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ጸጉር ገላቸው ላይ ያልበቀለ ‹‹መነኖች›› ጸጉር ባላቸው ‹‹ጠጋዎች›› ይጨቆናሉ፡፡ አዳም ዚህን ፖለቲካ ምንጭ ከመጽሐፍ ቅዱስ ፊሊሞች መዝዞ በንግስተ ሳባ በኩል አድርጎ እስከ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ድረስ በመዝለቅ ‹ማኒፌስቶዎችን ያጠናክራል፡፡›› እንደ ኤሪክ ቮን ዴኒኪን ያሉ ያልታወቁ በራሪ አካል ምርምር (UFOLOGY) ትክክለኛ ስም በመጥቀስ ይተቻል፡፡ አዳ ይሄን መቀመቃም መጪ ዘመን አሳምኖ ለመሳል ብዙ ለፍቷል፡፡ አቅሙን ሳይመትን ያለ ሐይሉን ተጠቅሟል፡፡ በአስፈሪው ጨለማ ዘመን ውስጥ ብቅ የሚሉ ጥርሶቻችን ጥቂት ብርሃን እንዲፈነጥቁ ማስቻሉ ደግሞ ልዩ ተሰጥኦው ነው፡፡

‹‹ጉልባን›› የተባለ የሬድዮ ጽኁፍ አቅራቢ ብዕር ስሙን ብቻ ለዘመኑ ብርቅ ከነበረው ባቄላ አልመዘዘም፡፡ ያላደነቀው ግጥምም እንዲሁ የዘመኑን ጣዕም መሰረት ያደረገ ነው፡፡
‹‹አንቺ ስንዴ ነሽ እኔ ባቄላ
ተጣጠቢና እንበላላ›› ትሰኛለች ዝነኛዋ ግጥም፡፡ በዚህ ግጥም ብንስቅም አዘቅቱ ያስፈራል፡፡ የሰው ልጅ ከእናት ተፈጥሮ ጋር ጦርነት የሚገጥምበት ‹አርማጌዶን› የአዳም መጽሀፍ መዝጊያ ምዕራፍ ነው፡፡ እንደ ብሉይ ዘፍጥረት ከሚቆጠረው ዘላለማዊ እንቅልፍ ተነስተን በአዳም ራዕይ (እንደ ዮሀንስ ራዕይ) ሕያዋን ሁሉ በሞት መለከት ስር የሚሰባሰቡበት መጪ ዘመን፡፡

በመጽሀፉ የጀርባ ጽኁፍ ምልከታዬን ላጠቃል፡፡

‹‹አዳ ረታ ታዋቂ ደራሲያን ከሆኑት ከነ ሐዲስ አለማየሁ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ጸጋዬ ገብረመድህን ጋራ መመደብ የሚችል ነው ሊባል ይችላል››

አስተያየቱ አክሊሉ ደሳለኝ በተባሉ ግለሰብ በተሰራ ጥናት ላይ የተሰጠ ነው፡፡ አዳም ዞታውን አይተን ከዚህም ፈቅና ደፈር ያለ አስተያየትም ለመስጠት የምንችልበት ዕድል ያለን ይመስለኛል፡፡

አዲስ አድማስ ጋዜጣ
2003 ዓ.ም

Filed in: Amharic