>
11:39 am - Wednesday December 1, 2021

አሜሪካ፡ የሰብአዊያን የመጨረሻ ታላቅ ተስፋ ከኢ -ሰብያዉያን ኪሳራ ማዳን ፣[ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ]

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

Hope2

ከናዚ ጀርመን ሰው ልጅ እልቂት የተረፉት እና የኖቤል ተሸላሚ የነበሩት ኤሊ ዊሰል በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ኢፍትሐዊነትን ለመከላከል የማንችልበት እና አቅመቢስ የምንሆንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፣ ሆኖም ግን ኢፍትሐዊነትን የምንቃወምበት ጊዜ በምንም ዓይነት ሁኔታ እና በምንም ዓይነት መንገድ በፍጹም ማጣት የለብንም፡፡“

እኔ ደግሞ እንዲህ የሚል አባባል እጨምርበታለሁ፣ ”በቢሮ ተወሽቀው የሚገኙትን የፖለቲካ አስመሳይ እብዶችን እና ምንም ዓይነት ሀሳብ ማመንጨት የማይችሉ እርባና ቢስ የሀሳብ ድሁር ፖለቲከኞችን የምንቃወምበት ጊዜ በምንም ዓይነት መልከኩ እና በምንም ዓይነት መንገድ በፍጹም ማጣት የለብንም፡፡“

የሬፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ትሩምፕ ባለፈው ሳምንት “በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪክ የሚገኙ የሙስሊሙን ማህበረሰብ የመረጃ ቁጥጥርን ፍጹም በሆነ መልኩ አካትቶ የሚይዝ የመረጃ ቋት ስርዓት በመንደፍ ተግባራዊ አደርጋለሁ“  ብሎ ነበር፡፡

ዶናልድ ትሩምፕ ይህንን ብቻም አይደለም የተናገረው፡፡ እንዲህ በማለትም ሀሳቡን የበለጠ አጠናክሮታል፣ “የመረጃ ቋቱ ከሚነግረን በላይ አልፎ በመሄድ የተለያዩ የቁጥጥር ስርዓቶች መኖር አለባቸው፡፡ በአሜሪካ የሚገኙትን ሙስሊሞች ለመከታተል እና ለመቆጣጠር እንዲቻል በርካታ ስርዓቶች ሊኖሩን ይገባል፡፡“

ትሩምፕ ከዚህም በተጨማሪ “የሚቻል ከሆነም በተወሰኑ መስጊዶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ምርመራ ማካሄድ እና ሊዘጉ የሚችሉትን መስጊዶችንም በጥንቃቄ ማሰብ“ ተገቢ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ይፈልጋል፡፡

አደገኛ የሆነ የሞራል ኪሳራ?

ሌላው የሬፐብሊካን ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ ቤን ካንሰር በዩኤስ አሜሪካ ሕገ መንግስት መሰረት አሜሪካውያን ሙስሊሞችን ቀጥተኛ በሆነ መልኩ አዕምሯቸው እና ልቦቻቸው የሚያስቧቸውን ሳይቀር ልቅም አድርጎ ማንበብ እንደሚችል አስረግጦ ተናግሯል (የዲስኩር ቱሪናፋ አሰምቷል ልበለው)፡፡

ካርሰን የአሜሪካንን ሀገር የመሰረቱ አባቶቻችን የሙስሊም ፕሬዚዳንት በመኖሩ ጉዳይ ላይ እምነት የላቸውም፣ ወይም ደግሞ የሙስሊም ፕሬዚዳንት ስልጣን መያዝ እንዲችል የሚያድርግ ሁኔታን አያጸድቁም ብሏል፡፡ እንዲህ በማለትም የሀሳቡን ዳህራ ለህዝብ ይፋ አድርጓል፣ “ከእስላም ጋር ተያያዥነት ያላቸውን እምነቶች ከሚያራምድ ማናቸውም ሰው ጋር ከፍተኛ የሆነ ችግር አለኝ፡፡“

(ወንድም ቤን የአሜሪካ መስራች አባቶች ጥቁር ፕሬዚዳንት ማመናቸውን በሚመለከት ምን እያሰበ እንዳለ ግልጽ ቢያደርግልን የሚገርመኝ ይሆናል!)

ካርሰን በአሜሪካ የሚገኙ ሙስሊሞች ሻሪያን እና ከእርሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሁሉንም ሕጎች በማስወገድ ለአሜሪካ እሴቶች እና ሕገ መንግስት ተገዥ እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡

አንደው ለነገሩ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ሕገ መንግስት ውስጥ “በአንድ ቢሮ ውስጥ ስልጣን ለመያዝ ወይም ደግሞ በህዝብ ዘንድ ታማኝነትን ለማግኘት በምንም ዓይነት መልኩ ኃይማኖት በመስፈርትነት የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም“ (አንቀጽ VI) የሚል ቋንቋ የለምን?

“በአሜሪካ-ርሰራውያን ምድር” ዘንድ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ እንደማይሰራ እገምታለሁ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ካርሰር እንዲህ ብሏል፣ “በርካታ ጽንፈኝነት በሚካሄድባቸው በማናቸውም ቦታዎች እና ተቋማት ላይ ማለትም በመስጊድ፣ በቤተክርስቲያን፣ በትምህርት ቤት በመገበያያ ማዕከሎች ላይ ክትትል ማድረግ ይኖርብናል፡፡“ በማንኛውንም ነገር እና ሰው ላይ ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ነው!

ድንቄም ቁጥጥር! ጉድ እኮ ነው!

ቁጥጥሩ እንዲህ በሰውም በዕቃውም ላይ ተጠናክሮ ሲቀጥል በጠብመንጃ ሽያጭ ላይ ግን ምንም ዓይነት ቁጥጥር የለም! እንዲያውም በአሸባሪ ስም ዝርዝር ውስጥ ላሉትም ቢሆን እንኳ የጦር መሳሪያ መሸጡ ላይ ቁጥጥሩ ሊደረግ አይገባም ምክንቱም አስፈላጊ ባልሆነ መልኩ በሰዎች ላይ የጦር መሳሪያ ግዥ ክልከላ መጣልን የማይደግፈው የሁለተኛው ሕገ መንግስት ማሻሻያ ዋና ደጋፊ ነኝ፡፡ የተሻለ የሕግ የበላይነት ሊኖር ይገባል፡፡

ድርብ የሞራል ኪሳራ?

በዚህ አላቆመም፡፡ የሶርያውያንን ስደተኞች ከውሾች እኩል አድርጎ ቆጠራቸው፡፡

ካርሰር እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ለምሳሌ ታውቃላችሁ፣ በጎረቤቶቻችሁ አካባቢ አንድ የሚሮጥ የአበደ ውሻ የሚኖር ከሆነ ስለዚያ ውሻ ጥሩ ነገር ለማድረግ አታስቡም፣ እንዲያውም ልጆቻችሁን ሁሉ ከመንገዱ አካባቢ በእጅጉ እንዲርቁ ታደርጋላችሁ፡፡ ይህ ማለት በማንኛውም እሳቤ ማንኛውንም ውሻ የተባለን ፍጡር ሁሉ ትጠላላችሁ ማለት ነውን?“

ካርሰር የተመሳስሎውን ድምጸት የበለጠ ጎላ አድርጎ ለማሳየት በማሰብ ያበዱ ውሾችን ሰብአዊ ፍጡር ከሆነው ሰው ጋር በማነጻጸር የሶርያን ስደተኞች እና ጽንፈኛ አክራሪ ሙስሊሞችን በአንድ በኩል በማስቀመጥ ያበዱ እና ያላበዱ ውሾችን በሌላኛው ጎን ጫፍ በማስቀመጥ የሰውን ልጅ ስብዕና ወደ እንስሳነት ያውም ወደ አበደ ውሻነት ዝቅ በማድረግ ለማነጻጸር ሞክሯል፡፡ (የማይነጻጸሩ ነገሮችን ማነጻጸር?)

ካርሰን እንዲህ ብሏል፣ “በተመሳሳይ መልኩ እኛም በእርግጠኝነት የትኞቹ ሰዎች ያበዱ ውሾች እንደሆኑ ለይቶ ማውጣት የሚያስችል ስርዓት በመንደፍ በስራ ላይ ማዋል አለብን፡፡ እነማን ናቸው በአስመሳይነት ሾልከው የሚገቡ እና በአስመሳይነት ደህና መስለው ቆይተው እኛን ሊያጠፉን የሚችሉ? ያንን ነገር እንዴት መከላከል እንደምንችል እስከምናውቅ ድረስ ልጆቻችንን ያበደ ውሻ ባለበት ሁኔታ አውጥተን በጎረቤቶቻችን አካባቢ እንዲንቀሳቀሱ የመፍቀድ ያህል ሞኝነት የበዛበት ድርጊት ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ችግር ያለባቸውን ወይም ባበደ ውሻ ተመሳስሎነት የቀረቡትን ጽንፈኛ አክራሪዎች ለይተን የምናወጣበት ተገቢ የሆነ ስርዓት እስካላዘጋጀን ድረስ ዝም ብለን የምንቀበላቸው ከሆነ አሁንም የለየልን ሞኞች ነን፡፡“

የካርሰን  አባባል እንግዳ በሆነ እና ባልተለመደ መልኩ “ያበዱ ውሾች እና እንግሊዞች” በሚል ርዕስ የተዘጋጁትን የኖኢል ኮዋርድን እንዲህ የሚሉትን ባለሁለት መስመር ሙዚቃ አስታወሰኝ፡ “ነጮች ሰዎች የሳር ጎጆዎቻቸውን በሚለቁበት ጊዜ ነዋሪዎቹ (በቅኝ አገዛዝ ስር ስላሉት ነው የሚጠቅሰው) ቅሬታዎቻቸውን ያሰሙ ነበር /ምክንያቱም ግልጽ በሆነ መልኩ በእርግጠኝነት አዕምሮ በሽተኞች ናቸው!“

በእርግጠኝነት ወንድም ቤን የአዕምሮ በሽተኛ ነውን?

የሶርያ ስደተኞች ውሾች አይደሉም፡፡ እነሱም በአምላክ አምሳል፣ በአላህ አምሳል የተፈጠሩ እንደ እኛ ሁሉ ሰዎች ናቸው፡፡

የወንድም ቤን ካርሰር ቃላት በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ እንዳይመለስ ሆኖ ተቀብሮ የሚገኘውን የአፍሪካ የቅኝ ግዛት አስከፊ ትውስታ እንደገና ህይወት ዘርቶ የማምጣት ያህል ሆነው ይሰማሉ፡፡

በቅኝ ተገዧዋ አፍሪካ ጊዜ በህዝብ መጠቀሚያ ቦታዎች ላይ ሁሉ “ለአውሮፓውያን ብቻ” እና “ለአፍሪካውያን እና ለውሾች ያልተፈቀደ” የሚሉ ማስታወቂያዎችን እና ምልክቶችን በየቦታው ተሰቅለው ማየት የተለመደ ነበር፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ግማሽ ዓመታት በቆዳቸው ቀለም ምክንያት አፍሪካ አሜሪካውያን አይፈለጉም ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ አይሁዶችም በኃይማኖታቸው ምክንያት አይፈለጉም ነበር፡፡

ያ ጠቅላላ አግላይ መልዕክት እንዲህ በሚሉ ምልክቶቹ ላይ እየተደረገ አፍሪካ አሜሪካውያን እንዲያውቁት ይደረግ ነበር፣ “ለባሮች አይፈቀድም፡፡ ለአይሁዶች አይፈቀድም፡፡ ለውሾች አይፈቀድም፡፡”

አፍሪካ አሜሪካውያን ሰዎች እንጅ ውሾች አይደሉም፡፡ አይሁዶች ሰዎች እንጅ ውሾች አይደሉም፡፡ ሶርያውያን ሰዎች እንጅ ውሾች አይደሉም፡፡

ውጤታማ እና ስኬታማ በሆኑ አፍሪካ አሜሪካውያን ዜጎች ላይ እንደዚህ ያሉ ልብን የሚያቆስሉ ቃላትን መስማት በቀላሉ አዕምሮዬን ይበጠብጡታል፣ የማድረግ ኃይሌን እንዲነጥፍም ያደርጉታል፡፡

ሆኖም ግን ፍርሀትን እና ጥላቻን እየገመዱ ያሉት ትሩምፕ እና ካርሰን ብቻ አይደሉም፡፡

የሬፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንቶች ቴድ ክሩዝ እና ጀብ ቡሽ ከዚህም በተጨማሪ ለክርስትና እምነት ተከታይ ሶርያውያን ብቻ የአሜሪካ ጥገኝነቱ እንዲፈቀድ በማለት ቡድኑን ተቀላቅለዋል፡፡

ክሩዝ በእርግጠኝነት እንዲህ በማለት አውጇል፣ “የሽብር ድርጊትን በመፈጸሙ ረገድ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትርጉም ያለው አደጋ የለም፡፡“

የሬፐብሊካውያን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪዎች ማርኮ ሩቢዮ፣ ራን ፓውል እና ሌሎችም እንደዚሁ በዋናነት ተመሳሳይ መልዕክትን በማስተላለፉ አስተሳሰብ ላይ የተዘፈቁ ናቸው፡፡ በአሜሪካ ለሶርያውያን ስደተኞች የሚሆን ቦታ የለም፡፡

የሬፐብሊካውያን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ ክሪስ ክሪስቲ “በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ በስደተኝነት ሊፈቀድላቸው የማይገቡት እድሜአቸው ከአምስት ዓመታ በታች የሆኑት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት ብቻ አይደሉም፣ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ያለው አስተዳዳር እንድንቀበላቸው የሚጠይቁንን ሰዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመመርመር የሚያስችል የብቃት አቅም ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የአሜሪካውያንን ደህንነት እና ጸጥታ ማስጠበቅ መቻል አለብን” ብላለች፡፡

ኦባማ ጭካኔ የተሞላበትን የክርስቲንን የፖለቲካ ስብዕና እንዲህ በማለት አቅልሎ ለማቅረብ ሞክሯል፣ “በመጀመሪያ ደረጃ በእነርሱ የምርጫ ቅስቀሳ ክርክር ላይ ፕሬሱ ጠንካራ ሆኖብናል በማለት ሲጨነቁ ነበር፣ አሁን ደግሞ ስለሶስት ዓመት እድሜ ህጻናት መጨነቅ ይዘዋል፡፡ እኔ ይኸ ጉዳይ ብዙም ትርጉም የሚሰጠኝ ነገር አይደለም፡፡“

ሶስት እጥፍ፣ አራት እጥፍ የሞራል ስብዕና ዝቅጠት?

“በሰው ልጅ ልቦች ውስጥ ምን ዓይነት ሰይጣን ተጣብቶ እንዳለ ማን ያውቃል?”

“ጨለማው ያውቀዋል::”

በአሁኑ ጊዜ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ፍርሀት እና ጥላቻን የሚያሰራጩት ብሄራዊ እና አስመሳይ ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡

በእስልምና እምነት እና በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ጥላቻን የሚያራግቡ ጥቂት መንግስታዊ ፖለቲከኞች አሉ፡፡

የሬፐብሊካን የኦክላሆማ ግዛት ሴናተር የሆነው እስልምናን በማስመልከት እንዲህ ብሏል፣ “እስልምና ከሀገራችን ውስጥ መወገድ ያለበት ካንሰር ነው፡፡“ ሴናተሩ በአጠቃላይ የእስልምናን ዋና ተግባር በማስመልከት ሀሳቡን በማጠናከር እንዲህ ብሏል፣ “የምዕራባውያንን ስልጣኔ ከውስጥ ማውደም“

ይኸ አነጋገር በሰሜን ናይጀሪያ የሚንቀሳቀሰው እና ቦኮ ሀራም እየተባለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን ወይም ደግሞ አይኤስአይኤል/አይኤስአይኤስ (ISIL/ISIS) የሚባለው ጽንፈኛ ቡድን ክርስትና መውደም አለበት እንደሚለው እና የኃይማኖት ጦረኞች ደግሞ እስልምና መውደም አለበት ከሚሉት ጋር አንድ ዓይነት አይደለምን?

ሆኖም ግን በእርግጥ የሬፐብሊካን ፖለቲከኞች እና አስመሳይ ፖለቲከኞች ብቻ አይደሉም እስልምናን እና ሙስሊምን ጥላሸት በመቀባት ላይ የሚገኙት፡፡

ፌዘኞች እና ዲሞክራትስ (በእርግጠኝነት እራሴን ደገምኩን?) በተጨማሪ የሞራል ኪሳራውን ዕኩይ ምግባር ተቀላቅለዋል፡፡

ታዋቂው አስቂኝ ተዋንያኑ/ኮሜዲያኑ (?) እና አሮጌ ባህልን በመገዳደር የሚታወቀው ቢል ማኸር አሜሪካውያንን በማስመልከት እንዲህ ብሎ ነበር፣ “አሜሪካውያን ለበርካታ ሙስሊሞች ሶርያውያን ስደተኞችን ጨምሮ ለአሜሪካውያን እሴቶች እንግዳ ለሆኑ ነገሮች ዕውቅና ለመስጠት አይፈልጉም፡፡“ እንዲህ የሚል ሀሳብ ጨምሯል፣ “ይኸ ሀሳብ ከሞላ ጎደል ሁላችንም የምንጋራቸው እሴቶች ሁሉም ኃይማኖቶች አንድ ዓይነት ናቸው የሚለው ሞኝነት ነው፣ እናም ይህንን ጉዳይ ሞኝነት ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡“

ደህና! በቢል ማኸር ቀልዶች ላይ ተዝናንቻለሁ፣ ሆኖም ግን እርሱ በሞኝነት ሀሳብ ውስጥ የተሞላ ነው፡፡

ሆኖም ግን ጥቂት ዴሞክራቶች አይቀልዱም፡፡ የሞራል ኪሳራን እያስፋፉ ይገኛሉ፡፡

የቀድሞው የዴሞክራቶች ዕጩ ፕሬዚዳንት ተወዳዳሪ የነበሩት ጄኔራል ዌስሌይ ክላርክ የአሜሪካንን እሴቶች የማይካፈሉትን ለጽንፈኛ ሙስሊሞች ማሰልጠኛ ካምፖች ናቸው የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ክላርክ እንዲህ ብለዋል፣ “እነዚህ (የሙስሊም) ህዝቦች ጽንፈኛ ከሆኑ እና ዩናይትድ ስቴትን የማይደግፉ ከሆኑ  እንደ መርህ ሲታይ ለዩናይትድ ስቴት ታማኝ አይደሉም፡፡ ግጭቱ በሚኖርበት ጊዜ ጤናማ ከሆነው ማህበረሰብ የመነጠል የእነርሱም መብት እና የእኛም መብት እና ግዴታ ነው፡፡“

“የማግለያ ማዕከሎች” ጽንፈኛ ለሆኑ ሙስሊሞች የተጠናከሩ የእስር ቤት ቴክኒኮች ናቸውን?

እርጉዝ ለእርግዝና በመጠኑም ቢሆን የመቀራረቡን ያህል በተመሳሳይ መልኩ መለያየትም ለማግለያ ካምፖች የቀረበ ነው፡፡ የማግለያ ማዕከሎች ወዲያውኑ የማግለያ ካምፖች እስር ቤቶች ይሆናሉ፡፡

በአሜሪካ ጽንፈኞችን እና ታማኝ ያልሆኑ ሙስሊሞችን ከጀግናዎች እና ታማኝ ከሆኑት መካከል እንዴት አድርገን ነው መለየት የምንችለው?

የተቀደሱ የአሜሪካ እሴቶችን ለመጠበቅ ሲባል ግዙፍ የምርመራ ተቋም ማቋቋም እና መመስረት አለብን?

እያንዳንዱ አሜሪካዊ ሙስሊም ለእውነተኛ ለተቀደሱት የአሜሪካ እሴቶች ታማኝ መሆኑን ለማወቅ ወይም ታማኝ ያለመሆኑን ለመገንዘብ ሲባል ግዙፍ ከሆነው የምርመራ ተቋም እያስቀረብን ምርመራውን በማከናወን ታማኝ ያልሆኑትን ወደ ማግለያ ካምፖች ማጋዝ ይኖርብናልን?

በእርግጠኝነት የማግለያ ካምፖችን መጠቀም የጀመርነው የጃፓን ንጉሳዊ አገዛዝ የፒርል ወደብን እ.ኤ.አ በ1942 ማጥቃት በጀመረበት ወቅት ነው፡፡

እነዚህን ካምፖች “እውነተኞቹን” አሜሪካውያን ከጃፓን ዝርያ ካላቸው አሜሪካውያን በመለየት ለመጠበቅ ሲባል እንደገና “አመላካች ካምፖች” (በተለመደው አጠራር ሳይሆን ደግ በሆነ እና በመልካም ስያሜ የማቆያ ካምፖች) በማለት እንጠራዋለን፡፡

ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት በዌስት ኮስት የሚኖሩ አሜሪካ ጃፓናውያን ላይ የብዙሀን እልቂት እንዲፈጸምባቸው ትዕዛዝ ሰጡ፣ ምክንያቱም እነዚህ ዜጎች በሙሉ ታማኝነት የሌላቸው እና ከዚህም ባሸገር ለጃፓን ንጉስ በሚስጥር ጽኑ ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው የሚል እምነት ስለነበራቸው ነበር፡፡

ከ110,000 በላይ የሚሆኑ በዌስት ኮስት የሚኖሩ አሜሪካ ጃፓናውያን ዜጎች ከሚኖሩበት አካባቢ በኃይል እንዲፈናቀሉ እና በካምፕ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ አንዳቸውም ላይ ቢሆን ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው አልነበረም! አንድም!

እ.ኤ.አ በ1944 የዩኤስ አሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሳፋሪ በሆነው የኮሬማትሱ እና የዩናይትድ ስቴትስ የብዙሀን ድምጽ የአሜሪካ ጃፓናውያን ዝርያ ባላቸው ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንዲህ በማለት ሕጋዊ አድርጎታል፡

የህዝቦቹን ቁጥር እና ያላቸውን ኃይል በእርግጠኝነት እና በፍጥነት ማረጋገጥ እስካልተቻለ እና እነዚያ ህዝቦች ታማኝነት የሌላቸው መሆናቸው እስካልታወቀ ድረስ ያንን በወታደራዊ ባለስልጣናት እና በኮንግረሱ የተሰጠውን ዳኝነት መሰረተቢስ ነው በማለት ውደቅ ልናደርገው አንችልም፡፡ ጦርነቱን የሚያካሂዱት የመንግስት ክፍሎች በጣም ወሳኝ በሆነ ሰዓት እነዚህንሰዎች ግልጽ በሆነ መልኩ ለመለየት እና ለማግለል የማይቻልበት ሁኔታ ስለሚፈጠር እና ሀገራዊ አደጋን ለመከላከል እናደህንነትን ለመጠበቅ ሲባል እንደዚያ ዓይነቱ ፈጣን እና በቂ የሆነ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ከግንዛቤ በማስገባትእርምጃው ተገቢ አይደለም የሚል እምነት ሊኖረን አይችልም፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ኃይል በተቀላቀለበት የሀሳብ ድምጸት የጃፓን ዝርያ ባላቸው አሜሪካውያን ላይ የተወሰደውን እርምጃ ጀስቲስ ዳኛ ኦዎን ጀ. ሮበርት እንዲህ በማለት ተቃውመውታል፣ አውግዘውታልም፡

እነዚህን የጃፓን ዝርያ ያላቸውን ዜጎች በወታደራዊው ፕሮግራም መሰረት ለማጋዝ እና በእስር ቤት እንዲታሰሩ በማድረግ ነጻነትን ለመቀዳጀት ብዙ ነገር ተብሏል፡፡  ሆኖም ግን የሕግ የበላይነትን ባገናዘበ መልኩ ይህንን ስርዓት ዘላቂነት እንዲኖረው እና ነጻነትን መቀዳጀት እዲቻል ከማድረግ ይልቅ ሕጉን እራሱን እንዲታወቅ ማድረግ የበለጠ ድምጸት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም ግን ወታደራዊ ትዕዛዝ ሕገ መንግስታዊ ባይሆንም ከወታደራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዘለለ አይሆንም፡፡ በዚያም ጊዜ ቢሆን እንኳ ተተኪው ወታደራዊ አዛዥ ሙሉ በሙሉ ሊጥሰው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን አንድ ጊዜ የሚቀርብ የፍርድ ሀሳብ እንደዚህ ያለውን ትዕዛዝ ከሕገ መንግስቱ ጋር በማያያዝ በሚያገናዝብበት ጊዜ ወይም ደግሞ ሕገ መንግስቱ እራሱ በዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የሚጥለውን ገደብ በመመልከት ፍርድ ቤቱ ምንጊዜም ቢሆን በወንጀል ማጣራት ተግባራት ላይ የጠራ እና በአመክንዮ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ስለሚያስተላልፍ የአሜሪካ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ሕጉ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ከዚህአንጻር ለአስቸኳይ ሁኔታ በሚል ወታደራዊ መሳሪያ ተጭኖ አንድን ነገር ለማድረግ ሲባል ለወታደራዊ ባለስልጣንየሚቀርብ የመርህ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ጄኔራል ክላርክ ይንን የተጫነውን የጦር መሳሪያ ወደ አሜሪካ ሙስሊሞች እንዲያነጣጥር እና እልቂት እንዲፈጠር ይፈልጋልን?

ለበርካታ ዓመታት በተለያያዩ ብዙ አጋጣሚዎች እምነት የማይጣልባቸውን የጃፓን ዝርያ ያላቸውን አሜሪካውያን የቡድን አባላት በካሊፎርኒያ በጣም ሩቅ ከሆነ በረሀማ አካባቢ ላይ የተዘጋጀውን “የማንዛናር እስር ሰፈራ” ማዕከልን ጎብኝቻለሁ፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጀፓን አሜሪካዊነት ዜግነት ያላቸው እና ሌሎች የውጭ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው የሚታሰሩበት የነበረው ያ ቦታ በአሁኑ ጊዜ ታሪካዊ ቦታ ሆኖ ይገኛል፡፡

ሁልጊዜ ወደ ማንዛናር በምሄድበት ጊዜ ፋሲሊቲዎች ካሉበት በስተምዕራብ በኩል በመቆም በዘር ልዩነት፣ የአንድን ሰው ንብረት ከሕግ አግባብ ውጭ ለእራስ ማድረግ፣ አንድ ሰው የአናሳ ብሄረሰብ ቡድን አባል በመሆኑ እና በአንድ ሰው ግላዊ አስተሳሰብ ያለምንም ማስረጃ እምነት የሌለው እና ታማኝነት ያልሆነ በሚል ምክንያት የሚደርስበትን ውርደት እና ሊመጣ የሚችለውን ነገር በምዕናብ አሰላስላለሁ፡፡

እንዴት ኃይልን በመጠቀም እየገፈተሩ፣ እያዳፉ ወደ መኪናዎች፣ አውቶብሶች፣ የጭነት መኪኖች እና ባቡሮች እያስገቡ በማጨቅ ምንም ነገር በማይታይበት አውላላ የበረሀ ካምፕ ውስጥ ያስገቧቸው እንደነበር በምናብ ስቃኘው በጣም አድርጌ እገረማለሁ፡፡

እያንዳንዱ ግለሰብ እና ቤተሰብ ወደ ማንዛናር እና ወደሌሎች ካምፖች ከዋሽንግተን፣ ከአሪጎን፣ ከካሊፎርኒያ እና ከአሪዞና ፋሲሊቲዎች በወታደራዊ ጥበቃ ከተላከ በኋላ የመለያ ቁጥር ይሰጠዋል፡፡ (የመለያ ቁጥሮች በንቅሳት ይደረጋሉ አላልኩም፡፡ እንደዚያ ዓይነቱ ድርጊት የሚፈጸመው በአውስችዝ-ቢርከናው፣ በቡቸንዋልድ፣ በዳቻው፣ በትሬብሊንካ እና በሌሎች ቦታዎች ነበር፡፡)

ለእኔ በማንዛናር ቦታ አካባቢ መዘዋወር ሁልጊዜ የጭንቀት ክስተት ነው፡፡

ሆኖም ግን የማንዛናርን የመኪና ማቆሚያ ቦታ በለቀቅሁ ጊዜ ጭንቅላቴን በማወዛወዝ ተጻራሪ በሆነ መልኩ የተጻፉትን እና እንዲህ የሚሉትን ቃላት በምልክቱ ላይ ተጽፈው ስመልከት እስቃለሁ፡  “ማንዛናር የጦር ማግለያ ሰፈር ማዕከል“

በምንም ዓይነት መንገድ ምንም ዓይነት ወንጀል ያልሰሩ አሜሪካውያን ዜጎችን “ማግለያ ማዕከል?”

ወደ “ማግለያ ማዕከሉ” የሚላክ ማናቸውም ሰው ቢሆን የወንጀል ድርጊት ፈጽመሀል ተብሎ ክስ ተመስርቶበት አያውቅም፡፡

ሁሉም ወደዚያ ቦታ በኃይል ተይዘው የሚጋዙት ሁሉ ምንም ዓይነት ወንጀል ያልሰሩ ንጹሀን ዜጎች ናቸው፡፡

ጆርጅ ኦርዌል “የፖለቲካ ቋንቋ…ነጩን ውሸት የጠራ እውነት አስመስሎ የሚያቀርብ እና ስሙ በገዳይነት ያደፈውን የተከበረ አድርጎ የሚያቀርብ፣ ምንም ዓይነት መሰረት የሌለውን ጠንካራ መሰረት ያለው አስመስሎ የሚያቀርብ ሊጨበጥ ሊዳሰስ የማይችል ባዶ ነፋስን መጨበጥ አድርጎ የሚያቀርብ ነው፡፡“

በኦዌንስ ሸለቆ መካከል በጦር መሳሪያ የታጀበ ማማ ማቆም በእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ “የማግለያ ማዕከል” የማይዘገን ጉም ማለት ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ “ለጽንፈኛ ሙስሊሞች” ዘመናዊ ማንዛናር ለማዘጋጀት እያሰቡ ነውን?

ምናልባትም እንደ “አቡ ዛር የሰላም ጊዜ ማግለያ ማዕከል” ሁሉ ማናዛርን እንደገና ለመክፈት አስበው ነውን?

በእርግጠኝነት “39ኛውን ዓመታዊ የማናዛናርን የቅዱስ ኃይማኖት ጉዞ” የተሳተፉት 1,500 ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አይስማሙም፡፡

ሚስጥራዊ ቃላትን በመጠቀም የፍርሀት አራጋቢዎች እና ሁሉንም ሙስሊሞች ጥላሸት የሚቀቡ የፖለቲከኞች የስም ዝርዝር ከጊዜ ወደ ጊዜ እጨመረ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡

የእስልምና ጥላቻን በመዝራት እና ፍርሀት በማራገብ ለሶርያውያን ስደተኞች መስብክ የዕለት ከዕለት ፋሽን እየሆነ መጥቷል፡፡

በርካታ የሆኑ በአሜሪካ እና በመላው ዓለም የሚኖሩ ሙስሊሞች የጽንፈኛ እስልምና እምነት ተከታዮች ድብቅ የሚስጥር ባልደረቦች ናቸው በማለት የሀሰት መረጃን እየሰበሰቡ የሚያሳዩ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡

እነዚህ ሰዎች የሙስሊም “የሻሪያን ሕግ” ተፈጻሚ በማድረግ ሁሉንም የምዕራቡን ዓለም ስልጣኔ ዶግ አመድ በማድረግ “ከእስልምና እምነት ተከታዩ ዓለም” ለማጥፋት ይፈልጋሉ ይላሉ፡፡ በካሊፌቶች አገዛዝ፣ የነብዩ መሀመድ ተተኪ አድርጎ እራሱን በሚሰይም እና በእስልምና ዓለም አቀፍ ሕግ በመመራት መኖርን ይመርጣሉ ይላሉ፡፡

ይኸ ዓይነት ስለሙስሊሞች የሚነገረው የድድብና ንግግር ብዙ አሜሪካውያን ጥቁሮች ከነጮች የበለጠ ዘረኞች፣ ሂስፓኒኮች ወይም ደግሞ አብዛኞቹ ነጭ አሜሪካውያን በተለይም ደግሞ ወጣቶች ድብቅ ዘረኞች ናቸው ከሚለው ጽንፈኛ አመለካከት ጋር ብዙም የተለዬ አይደለም፡፡

አስደንጋጩ ነገር እንደዚህ ዓይነቶቹ የድድብና አስተሳሰቦች ለምን እንደሚባሉ በእርግጠኝነት የክርክር ተግዳሮት የማይቀርብባቸው የመሆኑ ጉዳይ እና በሸፍጥ የተሞሉ ሀሰት መሆናቸውን ማጋለጥ ያለመቻሉ እንዲሁም የፍርሀት ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ የእስምልና ጥላቻ፣ የውጭ ኃይሎችን መፍራት፣ ሀሜት ማሰራጨት እና የመሳሰሉት ሁኔታ ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ በአሜሪካ ሕዝብ ጨዋነት፣ ፍትሀዊ አመላካከት እና ተፈጥሯዊ መልካምነት ላይ ፍጹም የሆነ አዎንታዊ እምነት አለኝ፡፡

በስሜታዊነት በተሞሉ አምባገነኖች የሚራገቡትን እና ፍቅር እና ሰላም የተሞላባቸውን ታላላቆቹን የአሜሪካንን እሴቶች ለማውደም እየተሸረበ ያለበትን ሁኔታ ፊት ለፊት የምንቃወምበት ጊዜው አሁን ነው፡፡

የምችል ብሆን ኖሮ ስለቤን ካርሰን መጥፎ መግለጫዎች እና አረመኒያዊ ኢሰብአዊ ድርጊቱ በአሁኑ ጊዜ ሌላ ቀን ለመኖር እየተጋሉ ላሉት ለእያንዳንዳቸው የሶርያ ስደተኞች እኔ በግሌ ይቅርታ ብጠይቃቸው እወድ ነበር፡፡

ለእያንዳንዳቸው ሶርያውያን አሜሪካኖች እንደዚህ አይደሉም በማለት ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡ አሜሪካኖች በጥላቻ የተሞሉ አይደሉም፣ አሜሪካኖች ጎጂዎች አይደሉም፣ አሜሪካኖች በቀልተኞች አይደሉም፣ አሜካኖች አዋራጆች አይደሉም፣ አሜሪካኖች ክብርን የሚነኩ አይደሉም፣ አሜሪካኖች መጥፎዎች አይደሉም፣ አሜሪካኖች ጨካኞች አይደሉም፡፡

አሜሪካኖች በመሬት ላይ የወደቀን፣ ዕድሉ የጠመመውን፣ በባህር ውስጥ የሰመጠውን፣ በተስቢስነት አዘቅት ውስጥ የሚማቅቀውን፣ የተራበውን፣ ተስፋየለሹን፣ ተከላካይ የለሹን እና ኃይል የለሹን ወንድ፣ ሴት፣ ልጅ የሚመቱ ባለመሆናቸው ላይ እምነት እንዳለኝ ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡

አሜሪካኖች እንደዚያ አይደሉም፡፡ ለእኔ የአሜሪካውያን ባህሪያት በነጻነት፣ በክብር፣ በለጋሽነት፣ በወንድማማችነት መንፈስ፣ በእኩልነት፣ በእርዳታ ሰጭነት፣ በጓዳዊነት፣ በመግባባት፣ በእርግጠኝነት፣ በስልጡንነት፣ በጋራነት እና በአብሮነት መንፈስ ላይ የሚሽከረከሩ እና በጽናት የሚተገብሩ ህዝቦች ናቸው፡፡

በአሜሪካ የነጻነት ሀውልት በመዳብ እና በብረት ቅልቅል ጠንካራ መሰረት ላይ ተጽፈው የሚገኙትን እና የአሜሪካውያንን መንፈስ በትክክል የሚገልጹትን እንዲህ የሚሉትን ሀረጎች እና ቃላት እንዲህ አቀርባለሁ፡

መድከምህን፣ መቸገርህን ንገረኝ፣

አካልህ ሁሉ ነጻ አየር እንዲተነፍሱ፣

በስቃይ ላይ ሆነው የሚወራጩትን፣

እነዚህን መጠለያ የለሾች እና የተበሳጩትን ወደእኔ ላካቸው፣

ለእነዚህ ሁሉ ወገኖች ከወርቃማው በር ላይ ቆሜ ፋኑሴን አበራላቸዋለሁ፡፡

እነዚህ ቃላት እ.ኤ.አ በ1883 በአሜሪካዊው አይሁድ ገጣሚ በኢማ ላዛሩስ በኒዮርክ ከተማ በግዙፉ ሀውልት ተጽፈው ከተቀመጡት የተወሰዱ ናቸው፡፡

ማህተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “በሰው ልጆች ሰብአዊነት ላይ እምነት ማጣት የለብህም፡፡ ሰብአዊነት ውቅያኖስ ነው፣ የውቅያኖሱ ጥቂት የውኃ ጠብታዎች ቆሻሻ ቢሆኑ ውቅያኖሱ በሙሉ ቆሻሻ ሊሆን አይችልም፡፡“ እኔም እንደዚሁ በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ እምነት ማጣት የለብንም እላለሁ፡፡

አልበርት አነስታይንም እንዲህ በማለት ተቀላቅለዋል፡ “ምንጊዜም ሰብአዊነትህን ብቻ አስብ፣ ሌላውን ነገር ሁሉ እርግፍ አድርገህ ተወው፡፡“

“ኢፍትሀዊነትን ለመከላከል አቅመቢስ የምንሆንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፣ ሆኖም ግን ኢፍትሀዊነትን ለመቃወም ምንም ዓይነት ጊዜ ልናጣ አይገባም፡፡”

በሙስሊም ወገኖቻችን ዘንድ እየተፈጸመ ያለውን ኢፍትሀዊነት ለማስቆም አቅሙ የለኝም፣ ሆኖም ግን ያንን ኢፍትሀዊነት ለመቃወም አቅመቢስ ልሆን ፈጽሞ አልችልም!

እቃወማለሁ!

እቃወማለሁ፣ ሆኖም ግን በተወሰኑ ቡድኖች እና በተለዬ እምነት ላይ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ፣ ባላቸው የስራ ኃላፊነት እና ሀብት አላግባብ በመጠቀም ስም ለሚያጠለሹ፣ ስብዕናን ለሚያጠፉ፣ ለሚወነጅሉ፣ ጥላቻን ለሚያሰራጩ፣ ወጥነት አሰራርን ለሚያጠፉ እና የጠቅላይነት ስሜትን ለሚያራምዱ በጥቂት ሰይጣናዊ ምግባርን በተላበሱ ፍጡሮች የሚፈጸመውን ኋላቀር እና አረመኒያዊ ተግባራት ለመግለጽ  የምችልበት ቃላት ያጥሩኛል፡፡

ዓለም ሁሉንም አፍሪካ አሜሪካውያንን እንደ ቤን ካርሰር እና ሁሉንም ነጭ ህዝቦች እንደ ዶናልድ ትሩምፕ አድርገው የሚቆጥሩ ከሆነ በፍርሀት ድንጋጤ የምርድ ይሆናል፡፡

ማንም በአመክንዮ የሚያምን እና በእራሱ የሚተማመን አሜሪካዊ ሁሉንም አሜሪካውያንን ለበርካታ ዓመታት በሰው ልጆች ላይ እልቂት በመፈጸም እና አሸባሪነተን በማራመድ ተሳታፊ ሆኖ ከቆየው ድርጀት ከበኩ ክሉክስ ክላን የጥላቻ ድርጊቶች ጋር በመሆን ዓለም ሁሉንም አሜሪካውያንን መፈረጅ ይችላልን?

ወደ አስርት ዓመታት ገዳማ ያህል ሳምንታዊ ትችት ጸሀፊ ሆኘ በቀጠልኩባቸው ጊዚያት ሁሉ  ከጊዜ ወደ ጊዜ አሜሪካንን በከፍተኛ ደረጃ ሀሳባዊ በማድረግ፣ ስለአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ ስለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ስለካፒታሊዝም፣ ስለጀብደኝነት፣ ስለወታደራዊነት፣ ስለኮርፖራል፣ ስለኒዮሊበራሊዝም፣ ስለምሁራዊነት፣ ስለአድርባይነት፣ ስለአካባቢያዊነት፣ ስለኋላቀርነት፣ ስለጽኑ የአርበኝነት መንፈስ፣ ስለግዛት እና ስለሌሎች ነገሮች አታነሳም በሚል ተከስሻለሁ፡፡

በአሜሪካን ሕገ መንግስት ታምናለህ ትማፀናለህ ይላሉ ።አሜሪካኞች በጣም ልዩ ናቸው  ትላለህ ይላል ክሱ።

በእኔ የስራ ዓለም የአሜሪካንን ሕገ መንግስት ለመደገፍ እና ለመጠበቅ ለበርካታ ጊዚያት ይፋ የሆኑ ቃል ኪዳኖችን ፈጽሚያለሁ፡፡ ቁጥራቸውን ረስቻለሁ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለም፡፡ ግልጽ በሆነ መልኩ በዩ ኤስ አሜሪካ ሕገ መንግስት ቃለ መሀላ ፈጽሚያለሁ፡፡

በርግጥም አሜሪካኞች በጣም ልዩ ናቸው።

ሁለቱን ም ክሶች አቀበላለሁ፡፡

ለእኔ የአሜሪካ ልዩ መሆን ማለት በተጨባጭ ምን ማለት ነው?

ጥቂቶች እዲህ ይላሉ፣ “የአሜሪካ ልዩ የመሆን ሁኔታ“ በወግ አጥባቂዎች የሚራመድ ሚስጥር ነው ይላሉ፡፡

ሀሳቡ ከአሜሪካ ታሪክ ጀርባ ባርነትን ጨምሮ፣ የአሜሪካ ቋሚ ዜጎችን ለመለያየት ጂም ከሮው ሳውዝን እና የአሜሪካንን መስራች አባቶች እና ሕገ መንገስቱን ቅዱስ አድርጎ ለማቅረብ የተሰነዘረ ነው ይላሉ፡፡

ለእኔ ስለዴሞክራሲ እና ስለግል ነጻነት ልዩ በሆኑ ሀሳቦች ላይ በማህበረሰቡ የተመሰረቱ መርሆዎች ናቸው፡፡

ከዚያም በማለፍ አንድ እርምጃ ወደፊት እራመዳለሁ፡፡

አሜሪካ ለሰብአዊነት የመጨረሻ ተስፋ ናት፣ እናም በርካታ ችግሮችን ሊያስከትሉ ከሚችሉ እና በስሜት ከሚነዱ እምባገነን እና አስመሳይ ፖለቲከኞች የሞራል ኪሳራ መጠበቅ አለባት ብየ አስባለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 1/1862 የነጻነት ስምምነት አዋጁ ከመፈረሙ አንድ ወር ቀድም ብሎ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን ለኮንግረሱ መልዕክት ልከው ነበር፡፡ ስለአሜሪካ አንድነት ስለመጠበቅ ንግግር ያደርጉ ነበር፡፡ እንዲህም ብለው ነበር፣ “እንዴት እንደምትጠበቅ ዓለምም እኛም እናውቃለን፡፡“ በመቀጠልም እንዲህ ብለው ነበር፣ “ለባሮች ነጻነት በመስጠት ለነጻ ነጻነትን አረጋገጥን ማለት ነው- ለሰጠናቸው ክብር እና ምንንስ ማስጠበቅ እንዳለብን ግልጽ በማድረግ ማለት ነው፡፡ በቅድስና እንጠብቃለን ወይም ደግሞ በመሬት ላይ ያለችውን የመጨረሻዋን ነገር እናጣለን፡፡“

በምድር ላይ ያለችውን የመጨረሻዋን የተሻለች ተስፋ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አስርት ዓመታት ውስጥ ክብር ባለው ሁኔታ ልንጠብቃት እንችላለን? ስለሆነም አሜሪካ የሙስሊሙን እምነት ለሚከተለው አሜሪካዊ ምንድን ናት?

በምድር ላይ ያለች የተሻለች የመጨረሻዋ ተስፋ?

ለሰብአዊነት?

ምናልባትም የሙስሊም እምነትን ለሚከተሉ አሜሪካውያን መልሱ በታላቁ አፍሪካ አሜሪካዊ ገጣሚ በላንግስተን ሁግ “አሜሪካ እንደገና ለአሜሪካ ትሁን” በሚል ርዕስ  እንዲህ የሚሉ የግጥም ስንኞችን ቋጥረዋል፡

የጥንቷ አሜሪካ እንደገና ትምጣ፣

ጋራ ሸንተረሩን ሜዳውን አቋርጣ፣

ውቅያኖሱን ሰብራ ወንዙን አቆራርጣ፣

የጭቅና ምንጩን ድሪቶ ገልብጣ፣

ፍትህን ቀምራ እኩልነት መርጣ፣

የጥንቷ አሜሪካ አዲስ ሆና ትምጣ፡፡

 

ውቢቷ አሜሪካ ህልሞቿን ታሳካ፣

መብት ሳትደፈጥጥ ፍትህን ሳትነካ፣

ሰላም ሳይደፈርስ ቦምብ ሳይንካካ፣

ምድር ሳትናወጥ ሰማይ ሳይንኳኳ፣

አዝመራ እያሸተ አበባ እየፈካ፣

ዕድገትን ታስመዝግ ውቢቱ አሜራካ፡፡

 

ልዕለ ኃያሏ ቁንጮ የሀገራት፣

ለሰላም ለፍትህ የምትቆም በጽናት፣

ላለም ስልጣኔ ታላቅ ድርሻ ያላት፣

ዜጎቿ ባንድነት ዘብ የሚቆሙባት፣

መልካሟ አሜሪካ የሰው ልጆች እናት፡፡

 

ነጻ ህዝብ ይኑራት ነጻ ቤትም ታግኝ፣

ሰላም ዝናብ ይስጣት የሌለው ውርጅብኝ፡፡

 

አሜሪካ ለኔ መች እንዲህ ነበረች፣

በሾህ ባሜከላ ባጥር የታጠረች፣

አሸባሪነትን ቀፍቅፋ የያዘች፣

ቅጥረኛ ጽንፈኛን በውን ያረገዘች፣

ላምባገነን ቆማ ፍትህን የጣሰች፣

በመንታ ምላሷ ቅጥፈት ያነገሰች፣

አስመሳይነትን ፈጥራ የጸነሰች፣

እረ መላ በሉ እባካችሁ ሰዎች፣

የጥንቷ አሜሪካ ወዴት ትገኛለች?

 

ሀገሬ አሜሪካ የህልመኞች ትሁን፣

ሌት ቀን ለሚያስቧት ለማምጣት ዕድገትን፣

ፍቅር ያለበሳት ታላቅ ሀገር ትሁን፡፡

 

ነገስታት በሀሰት ሸፍጥ የማይሰሩባት፣

ሙሰኛ አምባገነን የማይጨፍሩባት፣

የሰው ልጆች መብት የማይጣሱባት፣

የጽንፈኛ ወሬ የማያሸብራት፣

የአሸባሪ ድርጊት የማይታይባት፣

የውሸት አርበኝነት ቦታ የሌለባት፣

ግን መልካም ዕድሎች የተንሰራፉባት፣

እውነት ድንኳን ተክሎ የተቀመጠባት፣

ህይወት ነጻ ሆኖ የሚቦረቅባት፣

የጥንቷ አሜሪካ ከቶ ከወዴት ናት?

የሶርያ ስደተኞችን ለመርዳት ንቁ ተሳትፎ አደርጋለሁ፡፡

እንዲያውም ከዚህም በላይ እ.ኤ.አ የ1981 የፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን የዩ ኤስ አሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ፖሊሲ መግለጫ “ተግባራዊ ማዕቀፍ” ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሶርያውያን ዜጎች ለተፈናቀሉበት ሰብአዊ ቀውስ ምላሽ ይሆን ዘንድ ተግባራዊ እንዲደረግ ሀሳብ አቀርባለሁ፡፡

ይህንን ሁሉ የማደርገው በርዕዮት ዓለም፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በፖለቲካ ትክክለኛነት ወይም ደግሞ በሌላ በምንም ዓይነት ጉዳይ ምክንያት አይደለም፡፡

ሆኖም ግን ይህንን የማደርገው ዘላለምዊ በሆነ መልኩ አንድ ጊዜ ለተነሱ ጥያቄዎች አስፈላጊ የሆነውን ምላሽ ለመስጠት በማሰብ ነው፡፡

ተርቤ በነበረበት ጊዜ ምንም የሚበላ ነገር አልሰጠኸኝም፣ ተጠምቼ በነበረበት ጊዜ ምንም የሚጠጣ ነገር አልሰጠኸኝም፡፡ እንግዳ ሆኘ በመጣሁ ግዜ አላስተናገድከኝም፡፡ ታርዠ በነበረበት ጊዜ አላለበስከኝም፡፡ ታምሜ እና ታስሬ በነበረበት ጊዜ አልጠየቅኸኝም፡፡ በእውነት እንዲህ እልሀለሁ፡ ከእነዚህ ነገሮች አንዳቸውንም ለወንድሞችህ እና ለእህቶችህ ባደረግህ ጊዜ ለእኔ እንዳደረግህ እቆጥረዋለሁ፡፡ 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!         

ህዳር 14 ቀን 2008 .

Filed in: Amharic