>
2:37 pm - Sunday September 19, 2021

ክላሽና መስቀል [ኤፍሬም እሸቴ]

Klash and Cross. Epherm Esheteበፌስቡክ መንደር መነጋገሪያ ሆኖ የዋለ አንድ ፎቶግራፍ ሁለት ካህናት እርበርሳቸው እጅ እየተነሣሡ መስቀል ሲሰላለሙ (ሲሳለሙ) ያሳያል። ፎቶውን መነጋገሪያ ያደረገው አንዱ ካህን ሌላውን መስቀል ስላሳለመው ሳይሆን (የተለመደ ሥርዓት በመሆኑ) ከቀሳውስቱ አንዱ ከመስቀሉ ጋር ክላሽ ያነገበ መሆኑ ነው። ፎቶውን ያነሣው የፎቶው ባለቤት የፎቶውን ሥፍራ፣ እና አጠቃላይ ዐውዱን አልነገረንም። የፎቶው ባለቤት ስለ ፎቶው ዝርዝር ማብራሪያ ጽፎ ነገር ግን በፌስቡክ እንደተለመደው የውሰት-ውሰት/የተውሶ ተውሶ/ እኔ ጋር ያደረሰው ሰው ፎቶውን እንጂ መግለጫውን አልወሰደውም ይሆናል። ግማሽ ጥሎ ግማሽ አንጠልጥሎ መሔድ ሁሌም የሚያበሳጭ የኢትዮጵያውያን ጠባይ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም። አንዱ የጻፈውን ሌላው ገልብጦ ሲለጥፍ ከየት እንዳገኘው እንኳን ለመናገር ትንሽ አክብሮት አይሰጥም። የአእምሮ ባለቤትነት ጽንሰ ሐሳብ የሌለበት ልማድ ነው ያለን። ምናልባት አልለመድነው ይሆናል እንጂ በጥንታዊው ትምህርት ቤት አንዱ የሌላውን ሐሳብ ሰርቆ በራሱ ስም መጠቀም ጸያፍ እንደሆነ መምህራን ይናገራሉ። ተረት እንኳን «አለ እገሌ፣ አለች አሉ እገሌ» የምንለው አለ ነገር አይደለም።

ሰውየው በደንብ ያልተማረ ነበር አሉ። ምናልባት ሰነፍ ይሆናል፤ ምናልባትም የሚፈልገው ድረስ እንዲማር ሁኔታው አልተመቸም ይሆናል። ደግሞ ሊቅ መባሏንም ይፈልጋት ኖሯል። እናም ራቅ ካለ አገር ሄዶ ከቤተ ክርስቲያን ከሊቃውንቱ ጋር ተገኘ አሉ። ከዚያም ቅኔ ለእንግዳ መስጠት ባህል ነውና እንግዳው ሊቅ ቅኔ እንዲቀኝ ዕድሉ ሲሰጠው ልብሱን አሳምሮ ወደ አደባባዩ ወጣ አሉ። ከዚያም ግሩም ቅኔ አቀረበ አሉ። ነገር ግን ቅኔዋ የርሱ ሳትሆን የመምህሩ ነበረች። ማንም የሚያውቅበት አልመሰለውና ደረጃውን የጠበቀ ዝርፊያ (ፕላጂያሪዝም) ፈጽሞ አስጨብጭቦ ወረደ አሉ።ይሁንና በዚያ የሚገኙ ጎምቱ ሊቅ የቅኔው ባለቤት ማን እንደሆነ ስለሚያውቁ እንዲህ አሉት አሉ። «ቅኔያቸውስ ደርሶናል፣ ለመሆኑ የኔታ ደኅና ናቸው?» ሲሉ ቅኔዋ የርሱ እንዳልሆነች ነገሩት አሉ።

ወደ ርዕሳችን እንመለስ። በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት መሠረት አንድ ካህን ሌላውን ካሳለመ በኋላ ራሱም መልሶ የሌላውን ካህን መስቀል ይሳለማል። (ማለትም፡- ካህን ቁጥር አንድ ካህን ቁጥር ሁለትን ያሳልማል፤ ከዚያ ካህን ሁለት መልሶ ካህን አንድን ያሳልማል)። ካህን ካህንን ሲያሳልም «ሲመተ እዴሁ ለአቡነ ጴጥሮስ» (የአባታችን የጴጥሮስ የእጁ ሹመት) እያለ ነው። የሚሳለመው ካህንም በበኩሉ “እግዚአብሔር ይሥምከ ውስተ ዘለዓለም መንግሥቱ” (“እግዚአብሔር በዘላለም መንግሥቱ ይሹምህ”) ብሎ ይመልስለታል። (ለምንጩ ቅዳሴ ሓዋርያት መጨረሻው ላይ ተመልከት)። አሳላሚው ካህን መስቀሉን በሁለት እጆቹ በአክብሮት ይዞ ዝቅ በማድረግ እንጂ ሌላውን ምእመን እንደሚያሳልመው ዓይነት አይደለም።

ወደ ፎቶው ጉዳይ ስንመለስ፡- መነጋገሪያ የሆነው እና «ሰላማዊውን በመስቀሌ፣ አሸባሪውን በክላሼ» የሚል የሚመስለውን ፎቶ የሚያይ ሰው ጫፉ እንደ ጦር የሾለ ረዥም የብረት አንካሴ ይዞ “በሰላም ከመጣህ «እባርከከ» በጸብ ከመጣህ «እዘብጠከ»” ያለውን ባህታዊ ሊያስታውስ ይችላል። «ሰይፍ ዘክልዔ አፉሁ፣ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ» ማለት ይኼንን ይሆን? ታጣቂ ካህን ስናይ በጦረኝነት ስሙ ስለማይታማው ካህን እነሆ አንድ ሥነቃል ማስታወስ ግድ ይለናል።

«የተማሪ ወዳጅ ቢቀር ምናባቱ፣

ዱላ ሲያነሱበት ይላል “ባዛኝቱ”።» እየተባለ በሴቶቹ ተተርቷል። ይሁን እንጂ የቁርጡ ቀን ሲመጣ ካህኑ መስቀሉንና ታቦቱን፣ ጠመንጃና ጦሩን ይዞ «ወንዶቹ» ከዋሉበት ቦታ ውሏል።

‹‹ደህና ሁኚ ድጓ ደህና ሁኚ ቅኔ፣

ጀግኖች ከዋሉበት መዋሌ ነው እኔ›› እያለ ለአገሩ ደሙን ለማፍሰስ መውጣቱም ይታወቃል።

የሆነው ሆኖ ካህን እና ጠመንጃ አብረው አይሄዱም። የካህን ጠመንጃው መስቀሉ እና ትምህርቱ ነው። መስቀሉ ከማንኛውም መሣሪያ የበለጠ የትኛውንም ምሽግ መናድ ይችላል። ጣሊያን የፈራው የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስን ቃል እና ውግዘት እንጂ ምድራዊ መሣሪያቸውን አልነበረም። እንኳን ሕዝባችን ምድራችን ራሱ ለጣሊያን እንዳትገዛ መገዘታቸውን መቼም አንዘነጋውም። እንኳን ሰው ግዑዝ ፍጥረት እንኳን ለካህን ቃል ይታዘዛልና የኢትዮጵያ ምድር የፋሺስቱ ጣሊያን መኖሪያ ሳይሆን መቀበሪያው ሆናለች። በርግጥ የካህን ቃሉ ሥራ የሚሠራው ክህነቱ እንደ አቡነ ሚካኤል ዘጎሬ (በጣሊያን የተገደሉ) እና እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት ዘኢትዮጵያ ያለ ሲሆን ነው። መለካዊነትን በምትጠየፍ ቤተ ክርስቲያን ተቀምጠው መለካውያን የሆኑ (ፈቃደ ንጉሥ ፈጻሚዎች) ግን ከነአቡነ ጴጥሮስ ሊመደቡ አይችሉም።

በዚህ አንድ ፎቶግራፍ መነሻነት እና ቀስቃሽነት በዘመናችን የሰፈነውን የመስቀል እና ክላሽ ያላቻ ጋብቻ በተመለከተ ብዙ ልንልበት እንችላለን። የኛ ካህናት (በተለይም ቤሳቤስቲን ሳይጠብቅ ለማተቡ የሚያገለግለው) ገበሬ ካህን፤ ሲያርስ ውሎ፣ በሬዎቹን ፈትቶ ወደ ከሰዓት ቅዳሴ እንደሚገባ፣ አሐዱ ብሎ ቀድሶ ምሥጢራትን እንደሚፈጽም እናውቃለን። በሌላው ሕይወቱ ከሌላው የዘመኑ ገበሬ በምንም አይለይም። ቤተሰቡን ያለ እርጥባን የሚያስተዳድር ጎበዝ ገበሬ ነው። ከሰው እርጥባን ስለማይጠብቅም ለኅሊናውና ለክሩ ኗሪ ነው። ደሞዝተኝነት ሲመጣ ለክርና ማተብ መኖር መቅጠኗን አይተናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የ«መስቀልና ክላሽን» መፋቀር በዚህ ጎበዝ ካህን ሕይወት ብቻ የምንመዝነው ከሆነ ለውይይት አይመችም። ሁላም እንደሚያውቀው፤ ዋልድባ ሳይቀር በምንኩስና ስም ገብተው ትግል/ስለላ ሲያካሒዱ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ሥልጣኑን ይዘዋል። ክህነቱን ትተው ትግል ገብተው የነበሩ ተጋዳላዮች ካሸነፉ በኋላ ወደ ቤተ ክህነቱ ተመልሰው ሥልጣኑን ተቆናጠዋል። ይህ ምስቅልቅ መስመር ካላገኘ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ እና የዓለሙ ዓላማ ይመሳቀላል። መስቀል እና ነፍጥ ሊዋሐዱ ባይችሉም በዚህ ዘመን ግን ከመቀላቀላቸው የተነሣ የመስለቁ እና የክላሹ ባለቤት አንድ ወደመሆን መጥቷል። ሁለቱን እስካልለየን ድረስ የቤተ ክርስቲያናችን የጠራ የወንጌል ዓላማ ከሚፈለግበት ሳይደርስ መቅረቱ ሳይታለም የተፈታ ነው። መስቀሉና ክላሹ ይለይ። መስቀሉ ወደ መቅዱስ ክላሹ ወደ ካምፑ ይመለስ።

Filed in: Amharic