>

እነሆ ኦህዴድም ከፈጣሪው ትዕዛዝ አፈነገጠ። ህወሃትም ኦህዴድን በመፍጠሩ ተፀፀተ።(በዳዊት መክብብ)

ፀጉር ቤት እያለሁ አጀንዳው ተነሳ… ስለወቅቱ የኦሮሚያ አብዮት፡፡ በቤቱ ውስጥ ያለነው ሁላችንም ወደ አጀንዳው ዘለን ገባን፡፡ ከያቅጣጫው አድናቆት ጎረፈ፣ ለክልሉ አስተዳደር አባላት፡፡ አንድ በአንድ ስማቸው እየተጠራ ተሞካሹ፡፡

• `አቶ ለማ` ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነው፣ የቁርጥ ቀን ልጅ፡፡
• `ዶ/ር አብይ` የአንበሳ ልብ ከምርጥ ጭንቅላት ጋር የታደለ፡፡
• `አቶ አባዱላ` ሁለት ዘመን ላይ የቆመ ዲፕሎማቲክ ሰው፡፡
• `ኦህዴድ` የህወሃት ስጋት፣ የመጪው የኢትዮጵያ ተስፋ፡፡

ታዲያ፣ ከመካከላችን አንዱ ድንገት ፊቱ ተቀያየረ… ቁጣ ቁጣ ይለው ጀመር፡፡ እኔ እንኳ ማንነቱን አላውቀውም፣ እዚያ ሰፈር ቀበሌ ውስጥ እንደሚሰራ ነገሩኝ፡፡ የግንባሩ ላይ ደም ስር እየተገታተረ፣

“ይሄ ህዝብ `ወረተኛ` ነው… ጩኸት ይወዳል…… ደሞ እነዚህ ሰዎች መሩን ማለት ከአህያ ጋር ታሰርን ማለት ነው…” ምናምን እያለ ለፈለፈ፡፡ ሁላችንም አፍጥጠን አየነው፡፡ ወዲያው ተነስቶ ውልቅ ብሎ ሄደ፡፡

“ይሄ ሰውዬ ጆሮ ጠቢ ነው… እንዳያስባለን” ተባባልን፡፡ ወዲያው ግን ልጁን ረስተነው ቀድመን ወደጀመርነው ጨዋታ ቀጠልን፡፡

“ስሙኝማ አንድ ነገር ልንገራችሁ” አለ አንዷለም፡፡ ሁላችንም ጆሯችንን ቀሰርን… ከዚያ አፈጠጥንበት፡፡

“ህወሃቶች ከለማ የበለጠ ዶክተሩን እንደሚፈሩት ታውቃላችሁ አይደል!?”
በግርታ አየነው፣ “ለምን?” በሚል አስተያየት፡፡ አንዷለም ግን ቀጠለ…

“… ከኦህዴድ ጀርባ ትልቅ ድርሻ ያለው፣ ዋናው የለውጡ ምንጭ አብይ ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ ህወሃቶች ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ አስቡት እስኪ ከፊት ያለው ለማ መገርሳ ላይ ምንም ጥቃት ሳይሰነዘር ዶ/ር አብይ ላይ ስንት ጊዜ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተደረገበት… ባለፈው እንኳን ንግግሩን ቀይረው “ምርጫችን መጠፋፋት ነው” አለ ሲሉ የድርጅታቸው ፔጅ ላይ ለጠፉ… ወደ ሃረር ሲሄድ ግድያ ሙከራ ተደረገበት ተባለ… የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሆኖ ብዙ ለውጥ ካመጣበት ቢሮ በተሃድሶ ስም ቀነሱት… ከኢንሳም ተባርሮ ረጅም ጊዜ ያለምደባ አስቀርተውታል… በዚያ ላይ የሀሳቡ ጠንሳሽና መስራች እንዲሁም ዋና ዳይሬክተር ሆኖ የሰራበትን የኢንሳ መስሪያ ቤት ላይ በውክልና ሰራ እንጂ ኢንሳን መርቶ አያውቅም ተባለ… ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሳይቀር ዜና ሲዘግብ ሁሌም `አብይ አህመድ የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል` ይላል እንጂ መስራችና ዋና ዳይሬክተር እንደነበረ ተሳስቶ እንኳ ዘግቦ አያውቅም…”

“የፍቅሬ ስንታየሁን ፅሁፍ አንብባችሁታል?” ብሎ ጠየቀን፡፡

ሁላችንም አላነበብነውም፡፡ በሞባይሉ ከኢንተርኔት ላይ ፈለገና አወጣው፡፡ ከብበነው ማንበብ ጀመርን፡፡ ፀሀፊው፣ አብይ ኢንሳ ስለመስራቱና እዚያ ሳለ ስለገጠሙት ፈተናዎች፣ በሰራተኞች መወደዱና ሰዎች እያወቁት መምጣታቸው ህወሃቶች እንዳልወደዱለት ካተተ በኋላ ፅሁፉን እንዲህ ሲል ይቋጫል…

“…አቶ አብይ ኢንሳ የሚባለውን የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከምንም ተነስቶ አቋቋመው፡፡ ተቋሙ በደንብ መሰረት እስኪይዝም ጠበቁት፡፡ በኋላም ከሱ በኩል ተቋሙ ጠንካራ የመረጃና የቴክኖሎጂ ስራ የሚሰራ መሆን አለበት በሚል፣ ከህወሓት ሰዎች በኩል ደግሞ የለም የስለላ ተቋም እናድርገው የሚለውን የውዝግብ ነጥብ ተከትሎ ጊዜ ጠብቀው አባረሩትና ህወሐቶች እራሳቸው ለስለላ ሲሉ ተቆጣጠሩት፡፡”

በተመሳሳይ `የሚኒስትሩ ትጋትና የህወሐት በቀለኛነት` በሚል ርዕስ፣ (መንገሻ መ.) የተባለ ሰው የፃፈውን አውጥቶ አስነበበን፡፡ ፅሁፉ፣ አብይ አህመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር እያለ ስለሰራው ይገልፃል፤

“…በአንድ ዓመት ሳይሆን በ10 ዓመት እንዲህ ያለ ተቋም መገንባት ስለመቻሉ ተጠራጠርኩኝ፡፡ የቀየሩት የተቋሙ ቅርጽ፣ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሰሩት የልህቀት ማዕከልነት ስራ፣ ለብዙ ጊዜ ሳይሳካ ቆይቶ እሳቸው ከመጡ በኋላ አሳማኝ ጥናት በማቅረብ ያቋቋሟቸው የባዮ ቴከኖሎጂና የስፔስ ሳይንስ ሁለት ግዙፍ ተቋማትን ጨምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ የሰሯቸው ስራዎች የሰውዬውን ፍጥረት በብዙው ተጠራጠርኩት፡፡” ይላል መንገሻ፡፡

አንዷለም ንግግሩን ቀጠለ፣

“እንደዚህ ከሰራ በኋላ ግን በተሃድሶ ስም ተቀንሶ ነበር… ደስ የሚለው እሱ በሄደበት ለውጥ አያጣውም… የክልሉን አስተዳደር ከተቀላቀለ በኋላ ኦህዴድ በጣም ተቀየረ፡፡ ኦህዴድን ለማዳከም መፍትሄው ዶክተሩን መምታት ወይም በህዝብ እንዲጠላ ማድረግና ከዚያ ማስወጣት እንደሆነ ስለገባው ህወሃት አብይ ላይ እየዘመተበት ነው…”

አንዷለም ንግግሩን ጨርሶ ሲያየን ሁላችንም ተገርመን ነበር፡፡ እኔም ከዚያ በኋላ ስለ ዶ/ር አብይ የተነገረውን ለማረጋገጥ ሞከርኩ፣ ከሞላ ጎደል ሁሉም እውነት ሆኖ አገኘሁት፡፡

አምና፣ ጨፌ ኦሮሚያ ስብሰባ አድርጎ ከሸሚዛቸው ስር የህወሃት ማልያን የለበሱትን የኦህዴድ አባላት እነ ሙክተር ከድርንና እነ አስቴር ማሞን ኦህዴድ ከድርጅቱ ሲያሰናብት ህወሃት ዝም ማለቱ ዋጋ እንዳስከፈለው ዘግይቶ የገባው ይመስለኛል፡፡ ከምንም በላይ ደሞ ዶክተር አብይን ከፌደራል ቢሮ ሲቀንሰው ወደ ክልሉ አስተዳደር እንደሚሄድ አለማሰቡ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ጠፍጦፎ የሰራው ኦህዴድ መቼም ሊከዳው እንደማይችልና “ዘላለሙን ቢንፈራገጥ ከመላላጥ አያመልጥም” የሚለው እብሪቱ አሁን ለህወሃት የእግር እሳት ሆኖበታል፡፡

ኦህዴድ አሁን በክልሉ የሌሎችን ጣልቃ ገብነት አስቀርቶ የፌደራል አስተዳደር ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር አጋር እየፈለገ ነው፡፡ አንድነቱንም ሊያፀና ወደ ባህርዳር ተጉዞ ከገዱ አንዳርጋቸው አስተዳደር ጋር ምክክር አድርጓል፡፡ ህወሃት ባንፃሩ ካጥቂነት ወደ ተከላካይነት እየተሸጋገረ ሲሆን ኦህዴድ በሄደበት መንገድ ተከትሎ አጋር ፍለጋ በጎንደር በኩል ገዱ አንዳርጋቸውን አግኝቶ ወቀሳ ቢጤ አቅርቧል፤

“…ከኦሮሞ ጋር ለምን ግንኙነት መሰረታችሁ? አላማው ምን ነበር? ምንስ ታስቦ ነው? አሁንም ብታስረዱን…”

ይሄን ያሉት ደሞ፣ መድፍ ሲያጓራ ደንገጥ የማይሉትና በወዛጋቢ ንግግራቸው የሚታወቁት ታጋይ አቦይ ስብሃት መሆናቸው ህወሃት ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ እነሆ ኦህዴድ ከፈጣሪው ትዕዛዝ አፈንግጧል፡፡ ህወሃትም ኦህዴድን በመፍጠሩ እየተፀፀተ ነው።

 

Filed in: Amharic