>

ወ/ሮ ፈትለወርቅ ለድርጅቱ አቶ ዓለም ገብረዋህድ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ተሰማ (በወንድወሰን ተክሉ)

የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አስካል የሆነው የህወሃት ድርጅት በመቀሌ እያካሄደ ካለው ዝግ ስብሰባ ትናንት ከሃላፊነት ካነሳቸው አቶ ዓባይ ወልዱ ምትክ ሁለት ሰዎችን መምረጡን ኢሳት ዘግባል።

የህወሃት ሊ/መንበርና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት በነበሩት አቶ ዓባይ ወልዱ ምትክ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር የድርጅቱ ሊ/መ ተደርገው ሲመረጡ አቶ ዓለም ገብረዋህድ ደግሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ኢሳት ዘግባል።
በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ስር እየተካሄደ ያለው የህወሃት ድርጅታዊ ግምገማና ስብሰባ ላይ አዳዲስ ውሳኔዎች እየተላለፉ ሲሆን ስብሰባውን ረግጠው በመውጣትና ተመልሰው በመግባት ዛቻ እንደሰነዘሩ የተወራላቸውን ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴነትና ከኤፈርት ሊ/ነት እንዳነሳም መግለጻችን ይታወሳል።

በከፍተኛ ጥበቃና ወታደራዊ ጥበቃ ስር እየተካሄደ ያለው የህወሃት አመራር ስብሰሰባ ድርጅቱ ካለው ዘጠኝ ፖሊት ቢሮ አባላት መካከል አራቱን ያሰናበተ ሲሆን አንደኛው ብቻ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለተ.መ.ድ ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በመመረጣቸው ከፖሊት ቢሮው መልቀቃቸው ተገልጾ በእነዚህ ምትክ አምስት አዳዲስ አባላትን ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ድርጅቱ አቶ ጎበዛይ ወ/አረጋይና ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ የተባሉትን ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንደሚያባርር ተገልጾ ዶ/ር ዓዲስ ባሌማ እና ሌላው አቶ ገብረዋህድ ማስጠነቀቂያ እንደደረሳቸው ተገልጻል።

ህወሃት በከፍተኛ ውስጣዊ ንቅዘት፣ሙስና እና ውስጣዊ መበስበስ የፊጢኝ ተይዞ ወደፊት መራመድ ተስኖታል እየተባለ በሚተችበት ሰዓት ድርጅቱ ለሳምንታት የዘለቀ ዝግ ስብሰባን አንዴ በመቀሌ ሌላ ግዜ ደግሞ በአዲስ አበባ ሲካሄድ እንደቆየ ይታወቃል።
ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ተንታኞች ድርጅቱ በተፈጥሮዓዊ የእድገት መጨረሻ ላይ ያለ በማለት ይገልጹና በዚህ ደረጃ ላይ ያለ ማንኛውም ሃይል የፈለገውን ያህል ሹም ሽር ቢያደርግ ብርታትና ጥንካሬውን ተጎናጽፎ ተጠናክሮ መውጣት የሚቻለው አይደለም ይላሉ።

የመቀሌው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ዝግ ስብሰባ ያልተጠናቀቀ ሲሆን በድርጅታዊ ሂስና ግለሂስ እያደረገ እንዳለ እየተነገረ ነው።

Filed in: Amharic