>

ፍትህ በመጠየቋ በሃርነት ትግራይ ለእስር ሰቆቃ የተዳረገችው ንግስት ይርጋ ማናት? (አብቹ ወርቅነህ)

ወጣት ንግስት ይርጋ ተፈራ የቤት ስሟ ይርገዱ ነው። 
ንግስት የተወለደችው ሰሜን ጎንደር አርማጭሆ ወረዳ ሲሆን፥ እድሜዋ ወደ 24 ዓመት ይጠጋል። ንግስት ይርጋ ነዋሪነቷን አባቷ በሚገኙበት ጎንደር ከተማ በማድረግ፣ በሱቅ ስራ ተሰማርታ፣ ትምህርቷን እና ስራዋን ጎን ለጎን እያስኬደች፥ ሳንጃ ከተማ የሚኖሩ እናቷን የምትረዳ፣ ከእድሜዋ በላይ ስሟ ከፍ ብሎ የሚጠራ፣ በጓደኞቿ የተወደደች መልከ መልካም ወጣትና ትጉህ ሰራተኛ እንደሆነች በቅርብ የሚያውቋት ይመሰክሩላታል።
ሳትወድ በግድ ወደ ማንነት ትግል ከመግባቷ በፊት፥ ሳቅ ጨዋታ ወዳጅ፣ ዘመናዊነት የሚያጠቃት፥ ለወዳጆቿ ማር ለጠላቶቿ ነብር የሆነች የአርማጭሆ ልጅ እንደሆነችም ብዙዎች ይናገራሉ፥
ንግስት ይርጋ ወደ ትግል ለመግባት የተገደደችበት ምክንያት፥ የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ ባልደረባ የሆነው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በወያኔ አፋኝ ቡድን የተቃጣበትን የኃይል እርምጃ በኃይል ለመመከት ያደረገውን ራስን የመከላከል እርምጃ ተከትሎ፥ በዘረኛው የወያኔ መንግስት የተወሰደውን ህገ ወጥ አፈና እና የግድያ ሙከራ በማውገዝ ጎንደር ላይ በፈነዳው ሕዝባዊ ቁጣ መሆኑ ይታወቃል።
ወጣት ንግስት ይርጋ ተፈራ የታሰረችው በከሳሾቿ እንደሚባለው የሽብር ወንጀል ሰርታ ወይም በመንግስት ተቋማትና በህዝብ ንብረት ላይ ውድመት አድርሳ ሳይሆን ጎንደር ላይ ድንገት የፈነዳው የአማራ ሕዝብ እንብኝተኝነት ያስደነበረው የወያኔ አገዛዝ፥
ጎንደር ላይ የፈነዳው የአማራ ሕዝብ ተጋድሎ ዙፋኑን ሳይገለብጥ እንደማይቆም ከፍተኛ ስጋት ስለገባው ለትግሉ አይን የሆኑ የአማራ ወጣቶችን በማሰርና በመግደል ህዝቡን በማሸማቀቅ ትግሉን ለማክሰም በማሰብ በወሰደው የጭካኔ እርምጃ ነው።

ለምሳሌ በንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች ተዘርዝረዋል፥ የሽብርተኝነት ወንጄል ክሱን ሲዘረዝር፥ ከጎንደር እስከ መተማ ባደረጉት እንቅስቃሴ፥ 10 እና 95 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት፥ ከባህርዳር እስከ ጎጃም አካባቢ ሌላ ወደ 96 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ጥፋት አድርሰዋል በማለት ጠቅላላ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በማውደም የሚል ክስ ተዘርዝሮባቸዋል።

እሄን ጉዳይ አስተውላችሁ ፍረዱት እንግዲህ ወገኖች፥ ክሱ የተደረደረው በዚች የ24 ዓመት ወጣት በንግስት ይርጋ መሪነት እንደ ተፈጸመ ተደርጎ ነው።
ወጣት ንግስት ይርጋ እንደዚህ ከፍ ያለ ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የማድረግ አቅሟን የልምድ ማነስና የልጅነት እድሜ የሚገድባት፥ ምንም ወንጀል የሌለባት ወጣትና፥ ጎንደር በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ንቅናቄ ላይ ባደረገችው የማስተባበር ተሳትፎ በከተማው ታዋቂነትን ያተረፈች ፍትህ ፈላጊ ታዳጊ ዜጋ መሆኗን፥ በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ምስል የተሰራ “አማራ ሕዝብ አሸባሪ አይደለም” የሚል ቲሼርት ለብሳ በጎንደር አደባባይ ድምጿን ከፍ አድርጋ ፍትህ ስትጠይቅ ላስተዋለ ሰው ንጹህ ዜጋ መሆኗን ለመገመት አያቅተውም።

የታፈነችበት ሁኔታ፥

ወጣት ንግስት ይርጋ ሁሌ እንደምታደርገው አርብ መስከረም 6 ቀን 2009 ዓ.ም  ከጎንደር ከተማ ተነስታ ወደ እናቷ ቤት አርማጭሆ ሳንጃ በጉዞ ላይ እንዳለች ነበር፥
ከአባቷ የትውልድ መንደር ማሂንና ሙሴባንብ በሚባሉ ቀበሌዎች አካባቢ የሚገኙ አክስት አጎቶቿን አይታ ስታልፍ ተከታትለው ያፈኗት።
በታች አርማጭሆ ሳንጃ ከተማ ወደ ሚገኘው ቤቷ ስታመራ በመንገድ ላይ ታፍና አዲስ አበባ ተወስዳ በማዕከላዊ ከ120 ቀን የስቃይ ቆይታ በኋላ፥ ዛሬም በቃሊቲ ማጎሪያ ቤት መጠን የለሽ በደል እየተፈጸመባት፥ በሴትነቷ ጥቃት እየደረሰባት፥ ሰብዓዊ ክብሯ ተጥሶ፣ ማንነቷ መሰደቢያ ሆኖ፥ ጥፍሮቿ በጉጠት ተነቅለው፥ አማራነት ወንጀል አይደለም ባለች ግፍና መከራ ቁርስ ምሳዋ ሆኖ ፍትህ በማይገኝበት ፍርድ ቤት እየተመላለሰች አማራ ሆና ከመገኘቷና ማንነቴ ይከበር ከማለቷ በስተቀር ወንጄል እንደሌለባት ለፍርድ ቤቱ አሳውቃ፥ በሴትነቷና በማነነቷ ጥቃት እየደረሰባት መሆኑን በተደጋጋሚ አስረድታለች።

ወጣት ንግስት ይርጋ በሕዝብ ዓይን ጎልታ መታየት የጀመረችው፥ የወልቃይት ማንነት ኮሚቴዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ዓፍነው ለመውሰድ በመጡ የወያኔ ታጣቂዎችና በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የመከላከል እርምጃ ምክንያት ጎንደር ላይ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ፥ ሰልፍ በመምራትና በማስተባበር ባደረገችው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ቢሆንም፥ ቀደም ሲል ቃሊቲ  እስር ቤት ከጓደኛዋ ጋር ሰው ለመጠየቅ  ሄዳ ባየችው የወጣት አማራ እስረኞች ስቃይና  እስር ቤቱን የሞላው ኢትዮጵያዊ  ብዛት ፥ በተለይም ከገጠሪቱ ጎንደር ባልሰሩት ወንጄል ታፍነው መዳረሻቸው ሳይታወቅ ለእረጅም ጊዜ ያለጠያቂ ሲሰቃዩ ባየቻቸው ወገኖቿ ልቧ ተነክቶ ከተመለሰች ጊዜ ጀምሮ፥ በማዕከላዊ፣ በቃሊቲና በቂሊንጦ ለሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ጩኸትና የመከራ ድምጽ ምላሽ ለመስጠት የወያኔን ስርዓት በአደባባይ ለማውገዝ ቆርጣ እንደገባችበት በቅርብ የሚያዉቋት የትግል አጋሮቿ ይናገራሉ።

አቃቤ ሕግ “ንግስት ይርጋ ሽብርተኛ” ናት ብሎ በመዝገብ ካቀረባቸው ክሶች መካከል በዋናነት፥ 
1. በጎንደሩ ሰልፍ የቆሰሉትን ለማሳከም የለበሰችውን ልብስ አውልቃ ከ5000 ሺህ ብር በላይ ማሰባሰቧ
2. በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ፎቶ ባነር ማሰራቷ
3. የኮለኔል ደመቀ ፎቶ ያለበትን ቲሸርት በ120 ብር መግዛቷ
4. ሰልፉ በሰላም በመጠናቀቁና በአመራሯ ተስፋ በጣለባት የጎንደር ወጣት እትዬ ጣይቱ ተብላ ስለተጠራች ይላል።

ሰው መርዳት ሽብርተኛ የሚያስብለባት አገር ኢትዮጵያ፥ 

አገራችን በምትመራበት ስርዓት ምን ያህል የፍትህ መጣመም እንዳለ በንግስት ላይ ከቀረበው አሳፋሪና አስቂኝ ክስ እንዲሁም ከፍርድ ቤቱ ዉሳኔ መረዳት እንችላለን።
ወጣት ንግስት ይርጋ እንኳን ለገንዘቧ ለህይወቷ የማትሰስት፥ ለዓመነችበት ጉዳይ ራሷን የምትሰጥ ጀግና አማራ ወጣት ናት፥ ከግሮሰሪዋ ያጠራቀመቻትን ገንዘብ ለሰላማዊ ሰልፍ የሚውል እቃ በመግዛትና በተቃውሞው ምክንያት ለቆሰሉና ለተፈናቀሉ በዙሪያዋ ተሰባስበው ለተቸገሩ ወጣቶች ወጭ በማድረግና ድጋፍ በመስጠት ገንዘብ ጨርሳ በእጇ ላይ ምንም እንደ ሌለ የነገረችው በውጭ አገር የሚገኝ ዘመዷ ገንዘብ እንደላከላት ተረድተናል።

በዚች ገና የፖለቲካ ሀ ሁ በመቁጠር ላይ ያለች ጀግና ወጣትና የሀገር ተስፋ፥ አሸባሪነት ወንጄል ሆኖ የተመዘገበባት ቀልድ መሰል ክስ አማራ ሕዝብ አሸባሪ አይደለም ከሚል ጽሁፍ ጋር የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ምስል የያዘ ቲሸርት በገንዘቧ ገዝታ መልበሷ እና በተቃውሞው ላይ ባደረገችው የማስተባበር እንቅስቃሴ እቴጌ ጣይቱ የሚል ስም ስለወጣላት ቅናት ወይም ስጋት አድሮባቸው ነው የሚሉም ብዙ ናቸው።
ንግስት ይርጋ ተፈራ የታሰረችው ምንም ዓይነት ወንጄል ሰርታ አልነበረም፥ አሁንም በእስራት በስቃይ የምትገኘው ከአማራ ብሄር በመወለዷ በጠላትነት ተፈርጃ ነው።

የጎንደሯ ንግስት ይርጋ ተፈራ እውነትም ጀግና የጀግና ልጅ ናት!
ንግስት እንደ ማንኛውም የዘመኑ አንዳንድ ወጣት ፖለቲካና እሳት በእሩቅ ነው በማለት፣ አይታ እንዳላየች፣ ሰምታ እንዳልሰማች ማለፍ ስትችል፥ በእጇ የያዘችውን ገንዘቧን፣ አበባውን የልጅነት እድሜዋንና የወጣትነት ውበቷን በመሰዋት፥ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች የምትገኘው፥
ለማንነቷ ክብር፥ ለሕዝቧና ለአገሯ ነጻነት ለማምጣት በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ ባደረገችው የህልውና ተጋድሎ ነው።

የንግስት ይርጋ መስዋዕትነት በአማራ ሕዝብ የትግል ታሪክ፣ ትውልድ የማይረሳውና በማህደር የሚቀመጥ የማንነት ተጋድሎ ነው።

Filed in: Amharic