>
7:18 am - Friday October 22, 2021

ህዝብ የለም....ቢኖርም ህዝብነትን ተሰልቧል ! (አሌክስ አብርሃም)

ሴትዮዋ በሰፈሩ የታወቁ ተናጋሪ ናቸው አሉ …እና ጎረቤቱ ሁሉ ልኩን ስለሚነግሩት ጠልቷቸዋል ! አንድ ሌሊት ታዲያ ቤታቸው ሌባ ይገባና ያለ የሌለ ሃብታቸውን ዘርፎ ይሄዳል በሌሊት ወጥተው ኡኡ ይላሉ ተዘረፍኩ ድረሱልኝ ነብሴን እንኳን አድኑኝ እያሉ ጮኁ ጎረቤቱ ግን ባልሰማ ድምፁን አጥፍቶ ጭጭ አለ ! ምናልባትም የታባቷ እያለ ይሆናል ! በቀጣዩ ቀን ሁሉም ጎረቤት ኧረ አልሰማንም እያለ ያው በተለመደችው አስመሳይነት ከንፈሩን መጠጠ ! ሴትዮዋ የዋዛ አይደሉም በቀጣዩ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት በራቸው ላይ ቆሙና ‹‹ኡኡ እሳት እሳት ተቃጠልን›› ብለው ጮሁ …ጎረቤቱ ባንድ እግር ጫማ በግልገል ሱሪ እና በወዘተ ከዳር እስከዳር እንደፌንጣ እየዘለለ ወጣና …የታለ እሳቱ … የታለ ጭሱ ማለት ጀመረ ….እና እማማ ግርርርርም ብሏቸው ምን አሉ ??????
‹‹ትላንትም የጮህኩበት ድምፅ ይሄው ነበር ››

ከላይ ያለችው መግቢያ ከሆነ ሰው የሰማኋት ነች ! ምናልባት ባለቤት ካላት እንጃ ከሌላትም የህዝብ ለህዝብ ብለን ወደዋናው ጉዳያችን እንግባ !!

የአገራችን ፖለቲካ ለብዙሃኑ ግራ አጋቢ ነው ! መንግስት አለ ተቃዋሚ አለ ! በጣም የሚገርመው ሁለቱም እንሞትለታለን እንፈለጥለታለን የሚሉት ህዝብ ግን የለም !! እንዴት ህዝብ የለም …ብሎ ቱግ የሚል ይኖራል ያው ወይ ደጋፊ ነው ወይ ተቃዋሚ ነው …አሁንም ህዝብ የለም !!

ቆይ ግን ህዝቡ የት ሄደ ካልን መልሱ የትም አልሄደ …ህዝቡ ያው ምድሩ ላይ መሬቱ ላይ እያረሰ …እየነገደ… እየተጋባ …እየተዋለደ …እና እየሞተ በአካል አለ ግን በስነልቦና ነፃ የመሆን ወኔውን ተሰልቧል ! ማን ሰለበው …ፖለቲከኞቹ !!ዛሬ አይደለም ይሄ ስልቢያ የተጀመረው …ህዝብን ሰልቦ ሰላቢ ርእዮት የመጎለት አባዜ ቢገባን ዋናው ፖለቲካ ጠል ግን ፖለቲካ ጯሂ አገር የመፍጠራችን ምክንያት ይመስለኛል ! ይሄውልህ ነፃነትን እንዴት እንደተቀማን …

ለምሳሌ በቀላሉ ህዝብ በማን ይገለፃል በማን ይወከላል …በጥበብ ሰዎች !!… ህዝቡ ዘፈን ሰማም አልሰማም …በዘፋኞች ባህሉ ወጉ እምነቱና ማንነቱ ይገለፃል ቁጣውና ትህትናው ….ህዝቡ አነበበም አላነበበም በደራሲዎች ታሪኩ እውነቱ ውሸቱ ህልሙ ፍቅሩ ጥላቻው መከፋቱ ይገለፃል ህዝቡ ስእል ገባውም አልገባውም በሰአሊያን ቀለም ለብሶ ቀለም ጎርሶ የህዝብ ትንፋሽ ሸራ ላይ ይገለጣል …. እንግዲህ ይሄ ሁሉ የጥበብ ሰው ከፖለቲከኞቹ የበለጠ ህዝብን ይወክላል ስል ማጋነን አይደለም ! ግን የሚያሳዝነው በመንግስትም ይሁን በተቀዋሚ በኩል የጥበብ ሰዎች የሚጫንባቸው የባርነት ቀንበር ለፖለቲካ ተፈለጥን ተቆረጥን ከሚሉት በላይ ከባድ ነው !

የሚያሳዝነው ይሄን ሁሉ መንገድ መጥተንም ያንን ሁሉ የጥበብ ሰው ጠብ ላማይል የፖለቲካ እንቶፈንቶ ገብረንም አሁንም ይሄ አፈና ብሶበት መቀጠሉ ነው ! ከደርግ

ከደርግ እንጀምር ….ገብረ ክርስቶስ ደስታን እናስታውስ አገሬ እንዳለ ወገኔ እንዳለ የአገሩን እፍኝ አፈር እንደናፈቀ በባእድ ምድር የቀረ ታላቅ ገጣሚ ታላቅ ሰአሊ ነበር …በስንክሳር ፖለቲካ የተንገበገበላትን አገር እንደናፈቀ ቀረ …እስቲ ከዚህ በታች ያለውን ግጥሙን ተመልከቱ አገሬ ከሚል ግጥሙ ላይ የተቀነጨበ ነው …ታውቁታላችሁ ግን አንብቡት …የት ድረስ አገር በህሊና ዙፋን ላይ እንደምትቀመጥ …

አገሬ ሃብት ነው፤
ጎመኑ ስብ ጮማ፣ ቆሎ ክትፎ ስጋ፣
ድርቆሹ ፍትፍት ነው፣ ቃሪያው ሙክት ሠንጋ፣
ጠጁ ነው ወለላ፣
ከኮኛክ ያስንቃል የመንደሩ ጠላ።
እህሉ ጣእም አለው እንጀራው ያጠግባል፣
ከቢራ ከሻምፓኝ ውሃው ይጣፍጣል፣
በዓሉ ይደምቃል፣
ሙዚቃው ያረካል፣
ጭፈራው ዘፈኑ ችግርን ያስረሳል።
እዚያ ዘመድ አለ፣
ሁሉም የናት ልጅ ነው፣
ሁሉም ያባት ልጅ ነው፣
ጠላትም አንዳንዴ ይመጣል መቃብር፣
ባለጋራም ቸር ነው “ያገር ልጅ ሲቸገር” ፤
ገነት ነው አገሬ ….

አለና መቃብር ነስተን ቁንጥር አፈር ከልክለን አስቀረነው ….እነማን ‹‹ፖለቲከኞቹ›› እኛ ሁሉም የእናት ልጆች እኛ ሁሉም የአባት ልጆች የተባልነው …ህዝብ …በጥቂት ፖለቲከኞች ምክንያት እንዲህ በስቃይ በናፍቆት የሚጮህ የምድረበዳ ድምፅ ያልሰማነው …ለምን ነበር …ህዝብነትን በፖለቲካ ተሰለብና …ከላይ ወይ ደጋፊ ወይ ተቃዋሚ እንጅ ህዝብ የለም ብየ ነበር …ይሄው ! ገብሬ ህዝብ ስለነበር የለህም ተባለ !! ህዝብን ህዝብ የሚያደርገው ወይ መደገፉ ወይ መቃወሙ እንጅ አገሩ ምድሩ ላይ መፈጠሩ አይደለም አለና ፖቲካው !

ሰላቢ ፖለቲካችን ከዛ ምን ተማረች …ምንም !! ሰይፏን በዓሉ ግርማ ላይ መዘዘች …በአሉ ህዝብ ሁኖ ያየውን ፃፈ (ደግሞ ያለው አልቀረም ሻእቢያ ደርግን ጣለችው) በዓሉ ህዝብ ነበረ …ህዝብነትን ተከለከለ ሰው ሰው እንዳለ ሞተ …ተገደለ እንጅ ሞትማ ወግ ነው ! ሰው ሰው ህዝብ ህዝብ አለ እሱም እንደገብረ ክርስቶስ ….እስቲ ይችን የበዓሉን ግጥም እናብብና ህዝብነት እንዴት ነውር እንደተደረገብን እንታዘብ ….

ከጎራው ዘልቄ እስኪ ልነጋገር 
ካለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር 
የኔ ውብ ከተማ 
ህንፃ መች ሆነና የድንጋይ ክምር 
የኔ ውብ ከተማ 
መንገድ መች ሆነና የድንጋይ አጥር 
የኔ ውብ ከተማ የኔ ውብ አገር 
የሰው ልጅ ልብ ነው 
የሌለው ዳርቻ የሌለው ድንበር 
ሕንፃው ምን ቢረዝም ምን ቢፀዳ ቤቱ 
መንገዱ ቢሰፋ ቢንጣለል አስፋልቱ
ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድነው ውበቱ !? አየህ በዓሉ በሁሉም መፅሃፎቹ ስለሰው ፃፈ ስለህዝብ ጮኸ በብእሩ ተነበየ ብእሩን ሰብረው ድራሹን አጠፉት ‹‹ ፖለቲከኞቹ ››

ፖለቲካችን ህዝብን ህዝብ አድርጋ የምትመለከተው ወይ ስትደግፍ ወይ ስትቃዎም ነውና በዓሉን ዋጥ ስልቅጥ አድርጋ ‹‹ይችን በላች ብለህ ፆሜን እንዳታሳድረኝ›› አለች ደሟን ከአፏ እየጠራረገች !በደመኛ አይኗ ሌላ መስዋእት እየቀላወጠች ! ፆሎቷን ሰይጣን ሰማት …በአብዮት ስም ወጣቱን ሙህሩን ጠራርጎ አጎረሳት …ያውም ‹‹አንድ ያጣላል›› እያለ ደጋግሞ !! ጭራሽ ያንኛው ትውልድ ደግሞ ነፃ ሁኖ መኖርን በአባባል አስደግፎ ነፃ ህዝብ ብሎ ነገር የለም አለን !! ወይ ተቃዎም ወይ ደግፍ አለበለዚያ ህዝብ አይደለህም ብሎ ቁጭ አለ ….((መሃል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል )) ሲል አባባል ብቻ እንዳይመስልህ !! በዓሉ ብሎም የስልሳና ሰባዎቹ ትውልድ ባከኑ ….ባከኑ ….ህዝቡ ህዝብ አጣ !!

እንቀጥል …ጥላሁን ገሰሰ ብቻውን ህዝብ ነበር …አንድ ቀን ‹‹ና እኛን ደግፍ ›› አሉና ዝፈን አሉት ጥሌ ፖለቲካ አያውቅም …የሚያውቀው አገር ነው …የሚያውቀው ህዝብ ነው …እና ህዝብን ሊገድል አገር ሊገነጥል ወንበዴ በሰሜን መጣ ሲሉት በጊዜው ሁሉም ህዝብ እንደሚያስበው ህዝብን ወክሎ ‹‹በለው ያንን ተገንጣይ ወንበዴ›› ብሎ ዘፈነ …አገሬ ብሎ እንባውን እያዘራም ዘፈነ ….ደርግ ወደቀ መንግስት ተቀየረ ….ወንበዴ ብለኸናል ብለው ያንን የጥበብ ዋርካ አንቅረው ተፉት …ጥላሁን ግን ህዝብ ነበርና ኤርትራ ተነኮሰችን ሲባል ግንባር ድረስ ሂዶ ስለአገሩ ዘፈነ !! ቂሙ ግን አልተፈታም ህዝብ ነዋ ! ታላቁ የአገሪቱ በአል (ሚሊኒየም ) ላይ እንኳን ሳይጋብዙት ቀሩ ! ከመሞቱ በፊት በጣም አዝኖ ይህንኑ ልብ በሚሰብር መንገድ ተናገረ ! አገለሉኝ !!

ቀብሩ ላይ እንኳን መስቀል አደባባይ ካራት ኪሎ ርቆ ቁራጭ ደብዳቤ ልከው እዛው ግቢያቸው ውስጥ ጥላቻቸውን እያላመጡ ከመስቀል አደባባይ የሚተመውን የህዝብ የፍቅር ጩኸት የሃዘንም እንባ ባልሰማ አለፉት ! ወይ አለፋቸው …ፍቅር እስከመቃብር በተፃፈባት ምድር ጥላቻ እስከመቃብር ነገሰ ፖለቲከኞቹ ላይ !! ሰንብቶ ግን አቶ መለስ ሞቱ እዛው አደባባይ ላይ ህዝቡ በቁራጭ ወረቀት ሳይሆን በአካል ተገኝቶ ሬሳቸውን ሸኘ…ህዝብ ህዝብነቱን ባህሉን እንጅ ፖለቲካውን የሚያላምጥ አጋሰስ አይደለምና ! ፖለቲካ እዛው ላይ ታሪክን ደገመች ለመለስ ቀብር የተገኘ የጥበብ ሰው አይኑ ላፈር አለች ! በተቃዋሚዎቿ ልሳን ! ህዝብ ብሎ ነገር የለም ወይ ደግፍ ወይ ተቃዎም !!

ብቻ ምን አደከመን ዛሬ ላይ መንግስትን ስትቃዎም አገርህ ላይ ሳር ቅጠሉ እሳት ይሆንብህና መረገጫ መቀመጫ ታጣለህ …ሰንሰለት ይዘጋጅልሃል …. መንግስትን ስትደግፍ ተቃዋሚዎች መቆሚያ መቀመጫ ያሳጡሃል …ሁለቱም የህዝብ ጠላት ብለው ይፈርጁሃል … ዝም ካልክ አንድ የቀበሌ ካድሬ ቤትህ ድረስ ለግንቦት ሃያ ዝፈን …ለምንትስ ቀን ዝፈን ሊልህ ይችላል ማንንም ደግፈህ ሳይሆን በቃ ነፃ ሰው ሁነህ ህዝብ ሁነህ ልኑር በማለት እንቢ ብትል እንዲሁ ነገ መንገድህ ሁሉ አሜኬላ ….እሽ ብትል እግርህ በረገጠበት አገር ሁሉ አሜኬላ ….ፀሐፊ ዘፋኝ እየተለቃቀመ በስበብ አስባቡ ለእስርና እንግልት ሲዳረግ መንግስት ያሰረውን ተቃዋሚ ሲሸልም ተቃዋሚ ያገለለውን መንግስት ሲሸልም ህዝብነት ወዴት አለች ያስብላል !

ፖለቲከኞቹ ግራ ቀኙን ከእነርሱ ዓላማ ጋር ያልሄደውን ሁሉ ‹‹የህዝብ ጠላት›› እያሉ ቢፈርጁም ሕዝቡ ግን በ‹‹ጠላቶቹ ሙዚቃ እየተዝናና በጠላቶቹ የጥበብ ስራ እየተማረ እና እራሱን እያነፀ አለ ! ይሄ ማለት ወይ ህዝቡ ጠላቱን አያውቅም ወይም ፖለቲከኞቹ ህዝቡን አያውቁትም !…አሁንም ህዝብ የለህም እየተባለ ነው …ልኑር ቢልም ስልብ ፖለቲካ ህዝብነትን ሰልቦ ውሱን ቡድንተኝነት ሳጥን ውስጥ ያሽገዋል! !ስንቶቹ ግራ ገባቸው ስንቶቹ በቀጥታም በተዘዋዋሪም …ተሰቃዩ ተቸገሩ ሞቱ …..ያሉትም ግራ ቀኝ ላለመነካካት የተሸማቀቀ ዘፈን የተሸማቀቀ ፅሁፍ የተሸማቀቀ ስእል እየሰሩ አሉ …ፖለቲከኞች እስቲ ህዝብን ታገሉለት እንጅ አትታገሉት ! የጥበብ ሰው በነፃነት ያመነበትን ይፃፍ ይዝፈን ይሳል … የማንም ሳይሆኑ በራስ ማንነት የሚኖርበት አገር ወዴት አለ …ህዝብነት ወዴት አለ …

ሰው መሆን ብቻ የት ነው አገሩ …ናፈቀን !! ነፃነት ባይኖረን እንኳን ነፃነትን ተስፋ እንድናደርግ የሚረዳን ማነው …ነገ አንዱ ስልጣን ቢይዝ ያው ተቃዋሚሚም የተቃዋሚ ቦታውን ይይዛል …ያው እኔን ምሰሉ ማለት ይቀጥላል ….
ህዝብነትን የሰለበ ፖለቲካ ሰላቢ ነው !! ‹‹ትላንትም የጮህኩበት ድምፅ ይሄው ነበር ›› ያሉት ሴትዮ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የሚታወሱን ትላት የተቃወምናቸው ያደረጉትን ዛሬ እኛ ደግመን ካደረግነውና ትላንት ዝም ያለው ዛሬ ካጨበጨበ ….ድጋፉ እውነትን ሳይሆን ጥላቸውም ድጋፉም እውነት ተናጋሪው ላይ ነውና ….ህዝብነት ተሰልቧል !

Filed in: Amharic