>
5:13 pm - Saturday April 18, 6499

አልሰሙም አልታረሙም (መስፍን ማሞ ተሰማ - ሲድኒ አውስትራሊያ)

እነሆ ራሳቸው በጠሩዋቸው ጉባዔዎችና ኮንፍረንሶች ላይ ሁሉ በተደጋጋሚ ተነግረዋል አልሰሙም ፤ ተመክረዋልም አልታረሙም። እኒህም የኢትዮጵያ ገዢዎች የኢህአዴጋውያን አዛዦች የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ህወሃታውያን ናቸው። ማስረጃ ቢባል ማርሻል መለስ ከመራው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጉባዔ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ የዘለቁት መሰል ጉባዔዎች ዋቢዎቻችን ናቸው(1)። እነሆም ህወሃታውያኑ በወጣትነት ዘመናቸው በሽፍትነትና ዘረኝነት እንደታበዩ ገድለው ዘርፈውና አጥፍተው በጎልማሳነታቸው ምኒልክ  ቤተመንግሥትን በጠመንጃ ማረኩ። እነሆም በስተርጅና ዘመናቸው ባልገነቡት ቤተመንግሥት እየፏለሉ ከሽፍትነት የድውይ አስተሳሰባቸው፤ ከድኩም ባህሪያቸው፤ ከመሃይምነታቸው፤ ከመሰሪ ተፈጥሯቸው፤ ከናዚስት ዕምነታቸው ይታረሙና ይፀዱ ዘንድ ግን ከቶም አልተቻላቸውም።

እነሆም በኢትዮጵያ መንበር ላይ ተኮፍሰው ቤተ መንግሥት ከትመው ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው ከሆነ የአንድ ትውልድ ዘመን ሩብ ምዕተ ዓመት ጨርሰው የሁለተኛውን ትውልድ ዘመን ጀምረዋል። እነሆም በእኒህ ዘመናት በቂም በቀለኝነታቸውና ናዚስትነታቸው የቀደመውን ትውልድ/አዛውንቱን መቀመቅ ከትተው ከሀገር አባርረውና አጥፍተው፤ በእነርሱው ዘመነ ፍዳ የተፈጠረውንም ትውልድ እየበሉት ይገኛሉ። ዋይታና ሀዘን፤ ሞትና እስር፤ ስደትና ተስፋ ቢስነት የዘመናቸው መለያ የአገዛዛቸው መታወቂያ ሆነዋል። ከጎንደር እስከ ሲዳሞ ከኢሊባቦር እስከ ሀረርጌ ኢትዮጵያ በናዚስት ህወሃታውያን ነፍስ ጠባቂ በአጋዚ ጉግ ማንጉግ አኬል ዳማ ሆናለች – የደም መሬት።

በየትኛውም ሀገር ላይ የሰፈነ አገዛዝ በገዛ ፈቃዱ የሀገሩን አካል እንዳለቀ ሸሚዝ አያስፈልገኝም ብሎ በክፋት በበቀልና በድውይ ዓላማ አሳልፎ የሰጠ እንደ ህወሃት ያለ ‘መንግሥት’ የለም። አሰብና የሱዳን አዋሳኝ የጎንደር ለም መሬት ምስክርነት ይቆማሉ። ታሪክን ደጋግሞ ያዋረደ፤ የሰማዕታትን ባንዲራ ጨርቅ በማለት ያንኳሰሰና የተሳለቀ በሀገሩ ማንነት ላይ የሚመፃደቅና የሚያፍር መሪር ጥላቻም የሰፈነበት ሆኖም ቀደምቶቹ ባቆዩት ‘ሀገር’ መንበር ላይ ተቀምጦ ሥልጣኑን የሙጥኝ ያለ ‘መንግሥት’ እንደ ህወሃት ያለ በዚህች ምድር ተፈጥሮ አያውቅም።

ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ሀገር ከቆመ መንግሥት ከሰፈነ ወዲህ በዓለም ታሪክ እንደ ህወሃት መራሹ በገዛ ሀገሩ ህዘብ ላይ ቂመኛና መሰሪ የሀገር ገዢ ኖሮ አያውቅም። እንደ ህወሃትም ያለ ለይቅርታና ለሰላም የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ልብ የሌለው የአንድ ብሄረሰብ አባለት የክፉ ሰዎች ክምችት በዓለም ሀገራት ‘መንግሥታት’ ታሪክ ውስጥ ታይቶ አያውቅም። እንደ ትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ያለ ከጳጳስ እስከ ዘማሪ ከጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ካድሬ ከጄኔራል እስከ ተራ ወታደር ከኢንቨስተር እስከ ተላላኪ በአንድ አነስተኛ ብሄረሰብ እርኩሳን የተሞላ እና አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብን የሚያተራምስ ‘አዚመኛ’ የዘር ድርጅት ዓለም ከዚህ ቀደም አይታ አታውቅም። አቡነ ጳውሎስና አቡነ ማቲያስ ማርሻል መለስ፤ ጋራዚያኒ ደብረፅዮንና የጫካው
ጄኔራል ሳሞራ ኢንቨስተር ‘ኤፈርትና’ የአላሙዲን ሜድሮክ ምሥክራችን ናቸው።

ራሱ ‘እገዛዋለሁ’ የሚለውን ህዝብ ለመበቀል የማይታክተው ህወሃት ነገ ‘የሶማሌ ክልል’ን እንደሚለቀውና ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ማዕቀፍ ውጪ አሳልፎ ሊሰጥ እንደሚችል አብዲ ኢሌ በሚመራው የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል በኩል እያሳየና እያስፈራራም ይገኛል። የአጋዚ ክንፍ የሆነው የሶማሌው ልዩ ሃይል በ2009/2010 ዓ/ም ብቻ ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በተለይም ኦሮሞዎችን ከሀገሬ ውጡ ብሎ መለመላቸውን ሲያባርር በሺህ የሚቆጠሩትን ደግሞ ጨፍጭፏል። ከተከዜ መለስ ባለው የኢትዮጵያ ምድር ሁሉ የሚገኘውን አማራ በረቀቀው ሠይጣናዊ መንገዱና በግላጭም እየፈጀና እያስፈጀ የሥልጣን ዘመኑን ሶስተኛውን አስር ሊጠጣ ደርዙ ላይ ይገኛል። በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚካሄደው መተላለቅ በነ ሶሪያም ያልታየ ክስተት በህወሃት ዘመነ አገዛዝ ብቻ በምድረ ኢትዮጵያ የተከሰተ ነው። ይህ ሁሉ ኢሰብዓዊነት የሚተገበረው በዴሞክራሲና በፌዴራላዊ አስተዳደር እመራለሁ በሚለውና ራሱንም ‘ልማታዊ መንግሥት’ ብሎ በሰየመው የሃያ አንደኛው ዘመን የኢትዮጵያ ጉድ የህወሃት አገዛዝ ሥር ነው። እንዲህ ያለ መዓተኛ መንግሥት በየትኛውም ዓለም ሀገር ላይ ከህወሃት በቀር አልታየም።

ራሱ እመራዋለሁ ቆሜለታለሁም የሚለውን ህዝብ በጎራ ከፋፍሎ እሳትና ጭድ ናቸው በማለት የሚፈርጅ
መንግሥት/አገዛዝ በየትኛውም ዓለም ታሪከ መንግሥት ከህወሃት በፊት ተፈጥሮ አያውቅም። በኦሮሞና አማራ ህዝብ አንድነት ላይ ከናዚስቶቹ አርኪቴክት መለስ ዜናዊ ጀምሮ የሰጡዋቸው አስተያየቶችና ሌሎች ህወሃታውያንም (ለምሳሌ ጌታቸው ረዳ፤ ስዩም መስፍን፤ ስብሃት ነጋ፤ አቡይ ፀሀዬ) የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ዋቢዎቻችን ናቸው። እንቆቅልሹም እኒህ ናዚስቶች በአደባባይ ባደረጉት የዘር ማጋጨትና ማጥፋት ፕሮፓጋንዳዎች ከሥልጣን ወርደው መቀመቅ መግባት ሲኖርባቸው በኒሻን ላይ ኒሻን በሹመት ላይ ሹመት አጨብጭቦ እየሰጠ ህወሃት በመከረኛው ህዝብ ላይ ይሾማቸዋል። በጥቅምትና ህዳር 2010 ዓ/ም
በመቀሌው የናዚስት ህወሃት ጉባዔ ማግሥት የፈላጭ ቆራጭነቱን መቀመጫዎች ከተሸለሙት አንዱ ጌታቸው ረዳ አዲሱን ሥልጣን እነደ ጨበጠ ስለ ‘አያ ጅቦ’ ታሪክ እየተረተ በመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አላግጧል። ግብዝነቱ አሳውሮት እንጂ የአያ ጅቦን ታሪክ ራሱን በመስተዋት እያየ ቢናገር ኖሮ ምላሹን ያገኝ ነበር። አይን አላቸው አያዩም ማለትም ህወሃትና ህወሃታውያን ናቸውና።

እነሆም እንመሰክራለን። እንደ ህወሃት ያለ ቀማኛ ሀገር ገዢ በየትም ዓለም ተፈጥሮ አያወቅም። ከ400 በላይ ንፁሀንን በአሰቃቂ ሁኔታ ፈጅቶ መሬታቸውን ለህንድ ካርቱሪ ሆዳምና ለደም መጣጩ ቱጃር አላሙዲ ‘በዲናር’ የሸጠውና የፍጅቱንም ትዕዛዝ የሰጠው ናዚስቱ ማርሻል የህወሃት መሪ መለስ ዜናዊ ራሱ ነው። ለናዚስቱ መለስ ተግባር ጋምቤላ ዛሬም ህያው ምሥክር ነውና። የአዲስ አበባን ህዝብ ለመበቀል ነባር ሰፈሮቹን በልማት ካባ ያለ ካሳ እየዘረፈና መኖሪያ ቤቶችን በቡልዶዘር እየደረመሰ አእላፎቹን ነዋሪዎች የላስቲክ መኖሪያ ውስጥ የከተተው በቀለኛው ናዚስት ህወሃት ራሱ ነው። እነሆም በክፋትና በጭካኔ እጅግ የተካነው ህወሃት በዘረጋቸው አያሌ የግፍና የሰቆቃ እስር ቤቶች ውስጥ ያለ ፍትህ የሚማቅቁትን እስረኞች መኖሪዎች በእሳት እያጋየ ‘ሊያመልጡ ሲሉ’ በሚል ጭምብል ከደጅ ጠብቆ በጥይት ሲፈጅ የኖረ እንደ ህወሃት አይነት በላዔ ሰብ አገዛዝ በየትኛውም የዓለም ዳርቻ አልታየም። ከመሃል አገር በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ከሰሜን ደግሞ ጎንደር ደብረ ታቦር እስር ቤቶች ህያው ምሥክር ናቸው።

እነሆ በደም ስራቸው ውስጥ ዘር የማጥፋት ሴሎች የሚርመሰመሱባቸው ብቸኛ ስብስቦች በዚህ ዘመን ቢኖሩ ህወሃት ያቀፋቸው ዘር አጥፊዎች ህወሃታውያን ብቻ ናቸው። የቀደሙና አልያም የተቀሰፉትን ህወሃታውያን ትተን በዚህ ዘመንና ወቅት 2 የህወሃት ራስ ሆኖ መቀሌ ላይ በህዳር 2010 ዓ/ም የተመረጠው ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ሰብዕና ብቻውን መሉዕ ማስረጃችን ይሆናልና። ናዚስቱ ደብረፅዮን በ2009 ዓ/ም በፌስ ቡክ ገፁ ላይ “አይደለም ሰላሳ ሚሊዮን አማራን ሙሉ አፍሪካን ለመደምሰስ የሚችል መከላከያ ሠራዊት አለን” ሲል ጄኖሳይዳዊ አዋጅ ፅፏል። ህግና ሥርዓት ባለበት ሀገር ቢሆን ኖሮ አይደለም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መቀጠልና የናዚስት ፓርቲ መሪ ሆኖ መመረጥ ቀርቶ እንዲህ ያለ የዘር ዕልቂት (ጄኖሳይድ) መልዕክት ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለው ወንጀል በሆነ ነበር። ምክትል ጠ/ሚኒስርነትም ሆነ ‘የክል ፐሬዚዳንትነት’ ሹመትና ሽልማት የሚሰጠው ግን ህወሃት በሚመራት ኢትዮጵያ ብቻ ነው። እንዲህ ያሉ የጄኖሳይድ ነጋሪት ጎሳሚዎች
መንግትሥትና ህግ የሆኑባት ብቸና ሀገር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ብቻ ናትና።

እነሆ ደግሞ እንዲህ እንመሰክራለን። ከሽፍትነት ተንደርድሮ በመሀይምነትም ተጀቡኖ ቤተ መንግሥት ከገባ በሁዋላ ሚሊየነርና ቢሊየነር የሆነ በዓለም ታሪክ እንደ ህወሃት ያለ አልተፈጠረም። እንደ ህወሃትም ያለ ‘ከሀገሩ’ የሚሰርቅ ዘራፊ ‘መንግሥት’ በዓለም ሀገራት ላይ ከዚህ ቀደም ተፈጥሮ አያውቅም። እንደ ህወሃትም ያለ በዕውቀት ያላገጠ፤ በትምህርት ማዕረግ ኳስ የተጫወተ የሚንሿሿ የጋን ዲግሪና ዶክትሬት የተሸከመ ‘መንግሥት’ በዚህች ምድር ተፈጥሮ አያውቅም። በህይወት ዘመኑ ራሱን ከቶም ያልሆነና ሆኖም የማያውቅ፤ አለማወቁንም የማያውቅ አውቃለሁ ባይ የህወሃት ፅናፅል የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚመራት ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ብቻ ናት። እሱም ሃይለማርያ ደሳለኝ ይባላል።
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የህወሃት ናት። ህወሃትን መቀየርም ሆነ ማስተካከል ንፋስን እንደ መከተል ነው። አይቻልም!! የነገይቱ ኢትዮጵያ ግን በምንም ተአምር እንደ ድርጅትም ሆነ በግለሰብ ህወሃትን ያካተተች መሆን አይኖርባትም። ኦህዴድን ብአዴንን እና ደህዴንን በተመለከተ አስቸጋሪና ትዕግሥትን ፈታኝ ሊሆን ቢችልም እንኳን ያለ አንዳች ማወላዳት የህወሃትን ፍጡራን ‘ህወሃታውያኑን’ አፅድቶና አስወግዶ ሀገራዊና ወገናዊ ሰብዕና ካላቸው ጋር መሀል መንገድ ላይ መገናኘትና የነገይቱን ኢትዮጵያ ማቆም ይቻላል። ለነገይቱ ኢትዮጵያ እንደ ድርጅትም ሆነ እንደ ግለሰብ ህወሃትን ያካተተ “እርቀ ሠላም” ግን ተግባራዊነቱና ትርጉሙ እንደ ህወሃት ‘ብሄር ብሄረሰብና ህዝብ’ ፖለቲካ መያዣና መጨበጫ የሌለው “ዩቶፒያ” ነው። ፖለቲከኞች የፖለቲካ ተንታኞችና ‘ምሁራን’ ለነገይቷ ኢትዮጵያ ሲባል “ህወሃትን ያካተተ እርቀ ሠላምና ሽግግር” ያስፈልጋል የሚለው   ዲስኩራቸውና “መፍትሄያቸው” ከዚህ ሁሉ የህወሃት የሰቆቃ፤ የምዝበራ የግፍ ዘመንና ተሞክሮ በሁዋላ ሲሰሙት ራሱ የሚያጥወለውልና ፍፁም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። የኢትዮጵያ ችግሯ ናዚስቶችና መሀይምናኑ ህወሃታውያን ብቻ ሳይሆኑ ‘ተምረዋል’ ተብለው ‘የታመነባቸው’ ምሁራኗም (በውስጥም በውጪም ያሉ) መሆናቸው ደግሞ የመጪውን ዘመን ብርሃን አደብዝዞታል። ዋ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ ሆይ! እንባሽና ፍዳሽ ማብቂያው መቼና እንዴት ይሆን?

ታህሳስ 2010 ዓ/ም (ዲሴምበር 2017)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com
(1) ዋቢ፤ አንባቢ ሆይ! ህወሃት/ኢህአዴግ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያውያን ህፀፁን ስለመነገሩና ስለመመከሩ ቀጣዮቹን
ቪዲዮዎች በትዕግስትና በጥሞና ተመልከታቸውና የራስህን ድምዳሜ አድርግ

Filed in: Amharic