>

ህወሀት ቢዳከምም ቶሎ እጅ አይሰጥም መርዙንም በቀላሉ የሚተፋ ድርጅት አይደለም

 

መሳይ መኮንን

ህወሀት አድብቷል። አንገቱን የሰበረ መስሏል። ሆደ ቡቡ ሆኗል። መሪዎቹ በየምክንያቱ ያለቅሳሉ። ”እንዲህ መሆናችንን አናውቅም ነበር—ለካንስ በድለናችኋል” ይላሉ በየዕረፍት ሰዓቱ። በኢሳት እጅ የገባው ግርድፍ መረጃ ላይ እንደተመለከተው፡ ህወሀት በመከላከያ ሰራዊቱ የአዛዥነት ቁልፍ ቦታዎችን ሊያካፍል ተሰማምቷል። በደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ የሃላፊነት ወንበሮችን ለመልቀቅ ቃል ገብቷል። በርስትነት ይዞአቸው የቆያቸውንና በሌሎች በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ወሳኝ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን ለአባል ፓርቲዎች በኮታ ሊያከፋፍል ፍቃደኝነቱን አሳይቷል።

ህወሀት አዜብ መስፍንን ለእርድ እንዳቀረባትም ተሰምቷል። አባይ ጸሀዬን ወንጀል ካለበት በህግ ልትጠይቁት ትችላላችሁ ብሎ አሳልፎ ሊሰጥ መስማማቱ ይነገራል። ጄነራሉቹ ገንዘብ የሚዘርፉበትን ሜቴክ የተሰኘውን የደም ተቋም ከፈለጋችሁ እንዲመረመር ማድረግ ትችላላችሁ ብሏል። የወልቃይት ጉዳይ ተነስቶ ”የመሬት ረሃብ ውስጥ” እንደነበረ አመኗል። የመስፋፋት ህልሙን ለማሳካት በመሬት ዘረፋ ውስጥ መግባቱ ከብአዴን ሲነገረው አልተቃወመም። ኦህዴድም እስከዶቃ ማሰሪያው ነግሮታል። በጥቅሉ እየተካሄደ ባለው የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ህወሀት እጅ የሰጠ መስሎ ቀርቧል። ተደፍሯል። የማይነካ የሚመስለው ድንበሩ ተጥሷል። አጥሩ ተነቅንቋል።

እንደሰማነው ሃይለማርያምም ወግ ደርሶት ”ከዚህ በኋላ አልቀጥልም” ብሏል። ህውሀት ከኦህዴድና ብአዴን የመጣበትን ጭነት ለመሸከም የሃይለማርያምን ትከሻ መተማመን አልቻለም። የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለአማራና ኦሮሞ መስጠት ለህወሀት በራስ ላይ ሞትን የመጋበዝ ያህል አስፈርቶታል። በተለይ መሬት ላይ ካሉት የህወሀት ደጋፊዎችና አክራሪ አባላቱ ”ሁሉንም አስረከባችሁ–በደምና አጥንት የተገኘውን ቦታ አጨብጭባችሁ ሰጣችሁ” የሚለው እንደእቶን እሳት የሚያስፈራው ተቃውሞን የሚመክትበት አቅም የለውም። ቤተመንግስቱን ሃይለማርያም ይዞት እንዲቆይ እስከመጨረሻው ሊሟሟት ወስኗል። ከዚህ በኋላ የህወሀትን ሰው ከዚያ ቤተመንግስት ማስቀመጥ ቀለብ ከሚሰፍርሉት እነአሜሪካ ጭምር ውግዘት ስለሚገጥመው የትግራይ ተወላጅን ጠቅላይ ሚኒስትር ለማድረግ የሚሞክር አይመስልም። ሃይለማርያም የምሩን በቅቶት ከሆነና እስከመጨረሻው በአቋሙ ከጸና ለህወሀት እጅግ በጣም አጣብቂኝ ነው።

ህወሀት ልመና ላይ ነው። ”ህይወታችንም፡ ቀብራችንም አንድ ላይ ይሁን” እያለ በመማጸን ላይ ነው። ከህዝብ የመጣው ማዕበል ሁላችንንም ይውጠናል፡ የሚተርፍ የለም እያለ ማስፈራራቱን ተያይዞታል። ኦህዴድና ብአዴን በያዙት አቋም ስለመቀጠላቸው እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም እስከአሁን ባለው የስብሰባው ሂደት ለህወሀት ፊት አልሰጡትም። በተከላካይነት መስመር ላይ ገትረውት የ26 ዓመት የተጠራቀመ ሂሳብ እያወራረዱ መሆናቸው ይነገራል። በለማ የሚመራው የኦህዴድ ቡድን ለዘመናት በህወሀት የተደረበለትን የ’ጠባብነት’ ካባ አውልቆ ለደብረጺዮን አልብሶታል። ”ጠባቦችስ እናንተ ናችሁ” ብሏል ኦህዴድ። ብአዴን እያነከሰም ቢሆን የህወሀትን ክራንች ሊያስጥል ምልክት አሳይቷል። ገዱ ብቻውን አይደለም። እንደሚባለው ዶ/ር አምባቸው መኮንን፡ ተስፋዬ ጌታቸው አብረውት እየተጋፈጡ ነው። አቶ ብናልፍ አንዱዓለምና አቶ ይናገር ደሴ በአፋቸው ከህወሀት፡ በልባቸው ደግሞ ከገዱ ጋ መሆናቸውን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። አቶ ዓለምነው መኮንን፡ ካሳ ተ/ብርሃንና ከበደ ጫኔ እስከመቃብር ድረስ ከህወሀት ጎን ላይለዩ ወስነዋል ይባላል። ደመቀ መኮንን አለየለትም። እንደልማዱ ከነፈሰው ጋር ይነፍሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህን በውጥረትና በጭንቀት የተከበበውን ስብሰባ የድምጽ ብልጫ ይፈታዋል ብሎ የሚጠብቅ ካለ የዋህ ነው። እጅ ተቆጥሮ የበዛው አሸናፊ፡ ያነሰው ተሸናፊ ሆነው የሚወጡበት ስብሰባ አይደለም። አንዳንዶች 36ቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሚሰጡት ድምጽ የዚህ ስብሰባ አሸናፊው ይወሰናል የሚል አስተያየት ሲሰጡ አያለሁ። በዚያ ስሌት ከሄድን ህወሀት አሸናፊ ሆኖ መውጣቱ የሚያጠራጥር አይደለም። ህወሀት የራሱን ዘጠኝ ድምጾች፡ የደኢህዴንን ዘጠኝ ጨምሮበት ከብአዴን በትንሹ የእነዓለምነውን ሶስት አክሎቦት ከኦህዴድ የሚንሸራተቱ ሁለት ድምጾችን አግኝቶ ከ20 በላይ አስቆጥሮ ሊያጠናቅቅ ይችላል። የሚሆነውም ይሄው ነው። ነገር ግን አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚናፍቀው ለውጥ ከኢህአዴግ ስብሰባ የሚጠበቅ አይደለም። የእነለማ አሸናፊነት የሚገኘው ከጀርባቸው ከተሰለፈው ህዝብ ሃይል እንጂ ከኢህአዴግ ጽ/ቤት አይሆንም። የእነለማ ጉልበት የህዝብ ዕምቢተኝነት ነው። የእነገዱ አቅም የተቀጣጠለው አብዮት ነው። ህወሀት ይህቺን ዕውነት ያውቃታል። የህዝብን ልብ የካድሬ ድምጽ በማከማቸት የሚያገኘው እንዳልሆነ አይጠፋውም።

አሁንም ጥያቄዎች ይነሳሉ። ህወሀት በመከላከያውና በደህንነት መስሪያ ቤቱ ያለውን የዘመናት የበላይነት አጥቶ በስልጣን ለአንዲት ቀን መቆየት ይችላል ወይ? የኢትዮጵያ ህዝብ ምንድን ነው የሚፈልገው? ከሞያሌ እስከ ሁመራ፡ ከጎዴ እስከ አሶሳ የኢትዮጵያ ህዝብ እያነሳ ያለው ጥያቄ ምንድን ነው? የለማ መገርሳ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የቄሮዎች ምኞት ነውን? የመከላከያ ሰራዊት ዕዞች የአማራ ተወላጆች በኮታ መከፋፈላቸው ለአማራው ፋኖ ምን ሊረባ? የጌታቸው አሰፋ መስሪያ ቤት ለሌላው ኢትዮጵያዊ ክፍት መሆኑ ፋይዳው ምንድ ነው? የአዜብ መስፍን ቃሊቲ መውረድም ሆነ የአባይ ጸሀዬ የቃመውን ስኳር ማስተፋት ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሚሰጠው የለውጥ እርካታ ጋ ምን አገናኘው?

አዎን! ህወሀት ተደፍሯል። ቆሌው ተገፏል። በገዛ ባሪያዎቹ ክብሩን አጥቷል። ምርጫ የለውም። በመከላከያው ውስጥ የያዘውን የበላይነት መቀነሱ አይቀርም። በደህንነት መስሪያ ቤቱ የሙጥኝ ብሎ የያዛቸውን ቦታዎች መልቀቁ የሚጠበቅ ነው። ጥርቅም አድርጎ የዘጋውን የወልቃይት ጥያቄ ለድርድር ሊያቀርበውም ይችላል። በመሬት ረሃብ ያግበሰበሳቸውን የአማራ መሬቶች ላይ ውይይት ለማድረግ የሚያመነታ አይደለም። የተለያዩ ጥገናዊ ለውጦች ማድረጉ የስብሰባውን መጠናቀቅ ተከትሎ የሚታዩ ይሆናሉ። ቅዝምዝሟ እስክታልፍ ዕብሪቱን ሊተነፍስ፡ ጥጋቡን ሊቆጣጠረው ይሞክራል። ግን ህወሀት መቼም አይታመንም። ህውሀትን ማመን ቀብሮ ነው። ደግሞም እስረኛ ሊፈታ ይችላል። እንደ አይን ብሌን የምንሳሳላቸውን እነ መረራ ጉዲናን፡ እስክንድር ነጋን፡ በቀለ ገርባን፡ ዓንዱዓለም ዓራጌንና ሌሎችንም ሊለቃቸው ይችላል። ምርጫ የለውም። እንደውም የስብሰባው ማጠናቀቂያ ላይ የማጀቢያ እርምጃ ሊያደርገው እንደሚችል መጠርጠሩ አይከፋም።

ህወሀት ቢዳከምም በቀላሉ አይሞትም። ቢደፈርም ቶሎ እጅ አይሰጥም። መርዙን በቀላሉ የሚተፋ ድርጅት አይደለም። ኦህዴዶችንና ብአዴኖችን ” እስከመቃብር አትለዩኝ” የሚለው ልመናው ከአንጀት አይደለም። እነለማ ከስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ከሚያቃጭለው የህወሀት የለቅሶና ልመና ድምጽ ይልቅ ከውጭ ለሚስተጋባው፡ ከአድማስ አድማስ በአንድነት ለደመቀው የህዝባቸው የለውጥ ጩሀት ጆሮአቸው ቅርብ መሆን አለበት። የህወሀት ለቅሶ የአዞ ዕምባ ነው። ልመናው ዳገቱን እስኪወጣው ነው።

እነለማ ለህውሀት ለቅሶ ልባቸው ራርቶ፡ ልመናው አንጀታቸውን በሀዘኔታ ሞልቶት፡ ተሰፍሮ በሚሰጣቸው፡ ተለክቶ በሚታደላቸው የመከላከያና የደህንነት ወንበሮች ተማርከው ስብሰባውን በስምምነት የሚያጠናቅቁ ከሆነ ፖለቲካዊ ሞታቸውን እዚያው ከስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ጨልጠው ይወጣሉ እንጂ የህዝብ ትግል አይቆምም። በህወሀት ጊዜያዊ እጅ መስጠት ተዘናግተው፡ ከህወሀት ጋር ለመቀጠል ከተስማሙ ”መቃብራቸውም ከህወሀት” ጋር ሆኖ በታሪክ ሲወቀሱ ይኖራሉ እንጂ የቄሮዎችና የፋኖዎች ንቅናቄ ለአፍታም የሚገታ አይሆንም። እነለማ ቀሪ ዘመናቸውን በጀግንነት እየተወደሱ፡ ውለታቸው በሺ እየተመነዘረ እየተከፈላቸው፡ ከትውልድ ትውልድ የሚሻገር ታሪክ ትተው እንዲያልፉ ይጠበቃሉ። ዕድሉ በእጃቸው ነው። ጊዜ የለም። በጣም ረፍዷል።

Filed in: Amharic