>

የአገር ጠንቆች እነማን ናቸዉ? የአዲስ ዘመን አጀንዳ

                                                               በታዬ ደንደኣ

አዲስ ዘመን ጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ የአገር ጠንቆችን ይዞ ማዝገም ለህዝብ እና ለመንግስት አደገኛ መሆኑን ገልፇል። ይህ በጣም ትክክል ነዉ። ችግሩ “የአገር ጠንቅ ማነዉ?” የሚለዉ ነዉ። “የአገር ጠንቅ” ለሚለዉ ሀረግ መስፈርት መቀመጥ አለበት። ያ ካልሆነ ራሱ የአገር ጠንቅ የሆነ ሰዉ ወይም ተቋም በተግባር የአገር አለኝታ የሆነዉን ሰዉ በአገር ጠንቅነት ሊፈርጀዉ ይችላል።
አንደሚገባኝ የአገር ጠንቅ ማለት የሀገርን ጥቅም የሚፃረር ተግባር የሚፈፅም አካል ነዉ። ለምሳሌ ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ብሎ የአገርን እና የህዝብን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ወይም ለራስ ጥቅም ብሎ አድር-ባይ መሆን። በዝህ ረገድ በጥቂት ዓመታት ዉስጥ ብቻ ከ29 ቢሊየን ዶላር በላይ ዘርፎ ከአገር ያወጡ ወገኖች የአገር ጠንቆች ናቸዉ። በሀገሪቱ ወስጥ በኮንትሮባንድ ንግድ ተሰማርተዉ መንግስትን ገቢ የሚያሳጡ እና ህጋዊ ነጋዴዉን ከገበያ ውጪ የሚያደርጉ ወገኖችም የአገር ወዳጆች አይደሉም። በሙስና አሻጥር ተገንብቶ ሳያልቅ መፍረስ የሚጀምር መንገድ የሚያስገነቡ በለስልጣናት የሀገር ጠንቆች ናቸዉ። ለስኳር ፈብሪካ ግንባታ የተመደበዉን ገንዘብ ከመብላታቸዉም በላይ ዜጎች እየተቸገሩ እጅግ በጣም ብዙ ስኳር ለኬንያ የሚልኩ ወገኖች የአገር ጠንቆች ናቸዉ። የራሳቸዉን ዘራኛ ፍላጎት ለማሟላት በብሔሮች፣ በሓይማኖቶች እና በቤተሰቦች መሀከል ጥላቻና ግጭት እንድፈጠር “እሳት እና ጭድ” እያሉ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ወገኖች በተጨባጭ የአገር ጠንቆች ናቸዉ። በሥልጣን ለመቆየት ወይም ህገ-ወጥ ንግድ ለማካሄድ በህዝቦች መካከል ጦርነት ቀስቅሰዉ በዜጎች ህይወት፣ ንብረት እና ጤና ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ የፖለቲካ እና የመከላከያ ኃላፊዎች የአገር ጠንቆች ናቸዉ። ዜጓችን መጠበቅ ሲገባቸዉ ዜጎችን በእርሻ ማሳቸዉ ላይ የገደሉ የመከላከያ አባላት የአገር ጠንቆች ናቸዉ። ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን እርዳታ እንዳናሰባስብ SMS የከለከሉ የቴሌ ኃላፊዎች እዉነት የአገር ጠንቆች ናቸዉ። በሀገሪቱ እኩልነት፣ ነፃነት እና ፍትህ እንዳይኖር ያደረጉ ወገኖች ፈፅሞ የአገር ወዳጅ ሊሆኑ አይችሉም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ምንም አቋም እና መርህ የሌለዉ ባለጊዜ ጌታዉ የጠላዉን እየጠላ የወደደዉን እየወደደ የሚኖር አድርባይ ጋዜጣም የአገር ጠንቅ ነዉ። አዉነትን ሳይሆን የጌታዉን ፍላጎት ብቻ የሚፅፍ እና የሚናገር ሚዲያ እንዴት የአገር ወዳጅ ሊሆን ይችላል? ከዝህ አንፃር አዲስ ዘመን ራሱን እና ጌቶቹን ደጋግሞ ማየት አለበት። በንጉሱ ዘመን ማንን ክቦ ማንን ሲንድ ነበር? በደርግ ጊዜስ ማንን መርቆ ማንን ሲራገም ነበር? ኢህአዴግ ሲመጣ ደግሞ “አስገንጣይ ወንበዴ” ሲባል የነበረዉ ተወዶ “የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ጀግና” ሲባል የነበረዉ “ገዳይ አምባገነን” ተብሎ ተጠላ። ይህ አድርባይነት መቼም የአገር ልማታ ሊሆን አይችልም። አዲስ ዘመን ጣቶቹን ወደ ሌሎች ከመቀሰሩ በፊት ራሱን በደንብ መመልከት ይኖርበታል።ያለበለዝያ የአገር ጠንቆች የአገር ወዳጆችን በጠንቅነት እየፈረጁ በህደት አገርን እና ህዝብን ሊያጠፉ ይችላሉ። እነሶሪያ ላሉበት መከራ የበቁት “የአገር ወዳጆች እኛ ብቻ ነን!” በሚሉ በተግባር ደግሞ የአገር ጠንቅ በሆኑ ወገኖች ነዉ። ለጥፋታቸዉ ሌሎችን የሚከሱ ማለት ነዉ።
የችግሮች ሁሉ መነሻ ፍረጃ ነዉ። መፈራረጅ ራሱ የአገር ጠንቅ ነዉ። “የአገር ጠበቃ እኔ ብቻ ነኝ” ማለት በሽታ ነዉ። ዜጎች የተለያዬ አመለካከት እና ፍላጎት ሊኖራቸዉ ይችላል። አመለካከታቸዉ ደግሞ ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በዘፈቀደ ለአገራቸዉ ጠላት ወይም ጠንቅ ሊባሉ አይገባም። አንድ ዜጋ ሌላዉን ዜጋ የአገር ጠላት ወይም ጠንቅ ለማለት ምንም የሞራል መሠረት የለዉም። መነሻችን “ሁላችንም ለአገራችን በአቅማችን እናስባለን” የሚል መሆን አለበት። መሠረታችን ይህ ከሆነ በተግባር ደግሞ ግልፅ መስፈርቶችን በመጠቀም ማን የተሻለ ለአገር የሚጠቅም አጀንዳ እንዳለዉ ማየት እንችላለን። ጎጂ አመለካከቶችንም ማስተካከል የሚከብድ አይሆንም።
ከ 60 አመታት በፊት ኢትዮጵያ ለኮሪያ እርዳታ ሰጥታ ነበር ይባላል። ለማንኛዉ ያኔ ኮሪያ ምንም ስላልነበራት ኢትዮጵያ እጅግ ትበልጣታለች። ዛሬ ግን ከአለም ሀብታም አገሮች አንዷ ኮሪያ ሆናለች። ይህ በተአምር ሳይሆን ዜጎቿ ተማምነዉ በእዉነት ለሀገራቸዉ በመስራታቸዉ የተከሰተ ነዉ። እኛ ሁሌ እየተፈራራጅን በለንበት እየረገጥን ነዉ። በአንዳንድ መስኮች ደግሞ ወደኀላ ተንሸራተናል። የትምህርት ጥራት ወድቋል። ቅንነት እና መተማመን ጠፍቷል። የአገር ፍቅር እጅግ ተዳክሟል። ይህ ሊቆጨን ይገባል። በእዉነት ስለእዉነት መነጋገር ይኖርብናል። የተለመደዉን ከንቱ ዉዳሴ እና ከንቱ እርግማን መደጋገም አያዋጣም። አዲስ ዘመን እና ጓደኞቹ ቢታረሙ መልካም ነዉ እንላለን።

Filed in: Amharic