>

የአባዱላ መልቀቂያ በህውሓት ተቀባይነት አገኘ (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

የአባዱላ መልቀቂያ በህውሓት ተቀባይነት ማግኘቱን የነገረን ሪፓርተር ጋዜጣ የአገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለማሳየት የታዋቂ ሰዎችን አስተያየት ይዞ ወጥቷል። አስተያየታቸው ከማረከኝ ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።

– የቀድሞ የንግድ ምክርቤት ፕሬዝዳንት አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ እንዲህ ይላሉ፣
” ሁኔታው ያስፈራል። ችግሩ ከፍተኛ ነው። …ችግሩ አሁን አይደለም የጀመረው። ብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች በአንድም ወይም በሌላ ምክንያት ቅያሜ አላቸው። …አገሪቷ ከገባችበት ችግር ለመውጣት የጥምረት ወይም የሕብረት መንግስት ያስፈልጋል።”

  • ፀሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት እንዲህ ይላሉ፣
    ” በእኔ እድሜ ዘመን ውስጥ እንደ አሁኑ የከፋ ጊዜ አላየሁም። ሶስት መንግስት አሳልፌያለሁ።ቀድሞ የነበሩት ችግሮች በፓርቲዎች ወይም በመንግስት የተፈጠሩ ናቸው። የአሁኑን የከፋ የሚያደርገው በሕዝቡ መካከል የተፈጠረ መሆኑ ነው። …አገሪቱ ወደዚህ ችግር የገባችበት ዋነኛ ምክንያት ሕገ መንግስቱ ለኢትዬጲያዊነት ቦታ የማይሰጥ መሆኑ ነው። ሕገ መንግስቱ ብሔር ብሔረሰቦች በሚል በብሔር ስሜት ላይ የተዋቀረ ነው። ይኼ ኢትዬጲያዊነትን ሸርሽሯል።…”

 –   ፊልም ተዋናይ ያሬድ ሹመቴ እንዲህ ይላል፣
” ያለንበት ዘመን የታሪክ እጥፋት ነው። አንድ የታሪክ ምዕራፍ ወደ ሌላ ሊቀየር ሲል ያለው እጥፋት ላይ ያለን ሆኖ ይሰማኛል። ከአፄ ሀይለስላሴ ወደ ደርግ የመጣንበት እጥፋት  አለ። በደርግ ከጄኔራሎቹ ወደ መንግስቱ ኃይለማርያም የመጣንበት እጥፋት አለ። እጥፋቱ የመንግስት መቀየር ብቻ ሳይሆን የታሪክ መልክ መቀየርም ነው።…አገሪቱ ወደዚህ ችግር የገባችበት ምክንያት የመጀመሪያው የኢትዬጲያን ህዝብ ሕዝቦች ብሎ ያመጣው ህገ መንግስቱ ነው። የኢትዬጲያ ሕዝብን ሕዝቦች ካሉ በኃላ የተለያዩ ማንነት እንዳላቸውና በማንነታቸው ውስጥ ልዩነታቸው እንዲሰፋ ተደርጓል። ያልነበረ ታርጋ ተለጥፎባቸዋል።”

  • የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ዬሴፍ ሙሉጌታ ባባ እንዲህ ይሉናል፣
    ” አሁን በተጨባጭ እየሆነ ያለውን ስመለከተው <<ኦሮማይ>> እንድል አስገድዶኛል። ዳግም ወደ እርስ በራስ ጦርነት እንዳንገባ ስጋት አለኝ።”
  • የኢትዬጲያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መግለጫ፣
    ”  በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ የሉት ግጭቶች የኢትዬጲያን ህልውናና የሕዝብን አንድነት አደጋ ላይ እየጣሉ በመሆኑ መንግስት አገራዊ ቁስሎችን የማዳንና ዕርቅን የማውረድ ሐላፊነት አለበት። የመንግስት አካላት ማንኛውንም ልዩነት በውይይት እና በድርድር በኘፍታት፣ የውይይት መድረክ እንዳይዘጋ አስፈላጊውን መስዋዕት በመክፈል አገሪቱን ከውድቀት ፣ ሕዝብንም ለሞት እና ከስደት የመታደግ ከባድ ሞራላዊና መንግስታዊ ኃላፊነት አለባቸው።… የሐይማኖት መሪዎች ያለምንም አድልዎ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ እናቀርባለን።”
Filed in: Amharic