>
5:26 pm - Friday September 17, 7204

አቶ በቀለ ገርባ በጠና ታመዋል፡፡ ህክምናም ተከልክዋል፡፡

ቢቢኤን

በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በቀለ ገርባ በጠና መታመማቸው ተገለጸ፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ጤንነታቸው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደማይገኝ ስለ ጉዳዩ መረጃው ደርሶናል ያሉ አካላት አስታውቀዋል፡፡ እጅግ በጣም ከመታመማቸው የተነሳም፣ ቤተሰብ ሊጎበኛቸው ወደ እስር ቤት ሲሄድ፣ ቆመው ማናገር የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ህመሙ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት አስቸኳይ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸውም ተጠቁሟል፡፡

አቶ በቀለ ገርባ በጠና መታመማቸውን ተከትሎ፣ ከእስር ቤት ወጥተው ለመታከም ለወህኒ ቤቱ አስተዳደር ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የገለጹት መረጃዎች፣ ሆኖም የእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች ውጭ ወጥተው መታከም እንደማይችሉ ነግረዋቸዋል ብለዋል-መረጃዎቹ፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ታስረው የሚገኙበትን ቂሊንጦ እስር ቤት የሚያስተዳድሩት የፖሊስ ኃላፊዎች፣ አቶ በቀለ በወህኒ ቤቱ በሚገኘው ክሊኒክ እንዲታከሙ በመግለጽ፣ ውጭ ወጥተው የተሻለ ህክምና እንዳይከታተሉ እንዳደረጓቸውም ከመረጃዎቹ ጥቆማ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በእስር ቤቱ ውስጥ የሚገኘው ክሊኒክ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ከመስጠት የዘለለ አቅም እንደሌለው የሚናገሩ ታዛቢዎች፣ እንዲህ ያለ ከባድ የጤና መታወክ ሲያጋጥም፣ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች እስረኞች ወጥተው እንዲታከሙ የመፍቀድ ግዴታ እንዳለባቸው ታዛቢዎቹ ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም በህወሓት አገዛዝ ስር በምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የእስረኞችን መብት የማክበር ስርዓት እንደሌለ ያከሉት እነዚሁ ታዛቢዎች፣ በዚህም የተነሳ በርካታ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ህክምና ተከልክለው ለዕድሜ ዘመን በሽታ መዳረጋቸውንም ታዛቢዎቹ ይገልጻሉ፡፡

በእነ ደጀኔ ጣፋ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት የኦፌኮ ተከሳሾች አንዱ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ በዋስ እንዲፈቱ ተፈቅዶላቸው የነበረ ቢሆንም፤ ውሳኔው በአንድ ጀምበር ተሽሮ በእስር ቤት እንዲቆዩ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ በአሁን ሰዓት በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት አቶ በቀለ ገርባ፣ በቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመድ እንዳይጠየቁ ከመደረግ ጀምሮ፣ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙባቸው፣ ፍርድ ቤት በቀረቡበት አጋጣሚ ሁሉ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም በእስር ቤት የሚፈጸምባቸው በደል እና ግፍ አሁንም ቀጥሎ፣ ህክምና እንዳያገኙ መከልከላቸው ተነግሯል፡፡

Filed in: Amharic