>

ከኢህአዳግ ተሃድሶ ወፍ መሆን በስንት ጠዓሙ?! (ስዩም ተሾመ)

በነገራችሁ ላይ ኢህአዴጎች “የተሃድሶ ስልጠና” ሲሉ ወደ አዕምሮዬ ቀድማ የምትመጣው አንዲት #ወፍ ናት፡፡ የዚህችን ወፍ ውለታ መቼም፥ እንዴትም አድርጌ መክፈል አልችልም፡፡ በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለአንድ ወር ያህል የሰው ልጅን አካል በዱላ ከመቀጥቀጥ ሌላ የማያውቁት የፌደራል ፖሊሶች “የተሃድሶ ስልጠና አሰልጣኞች” ሆነው ከመምጣት በላይ አዕምሮን አስገድዶ የሚደፍር (rape of mind) ከቶ የት አለ? ታዲያ እኔ’ማ “አዕምሮዬን ለማንም ጋጥ-ወጥ አሳልፌ አልሰጥም” ብዬ “ስልጠና” ከምንወስድበት “ዛፍ” ላይ በአጋጣሚ ቤቷን የምትሰራ ወፍ ተመለከትኩ፡፡ ለአንድ ወር ሙሉ የዚህችን ወፍ ትጋት ሳደንቅ፣ በተፈጥሮ ውበት ስመሰጥ ከረምኳ፡፡ ከተመስጦዬ የምነቃው በአሰልጣኝነት የተቀመጠው የፌዴራል ፖሊስ “ስዩም…በዚህ ላይ ምን ትላለህ?” ሲለኝ ብቻ ነው፡፡ ከዛ ከጎኔ ያለውን ልጅ “ስለ ምን እያወራችሁ ነበር?” ስለው በአንድ ቃል ጫፍ ያስዘኛል፡፡ ከዛ… “ተርርርርር…” ስልበት “አይ በቃ ገብቶሃል!” ይለኛል፡፡ እኔም ወደ ወፌ ተመልሼ እመሰጣለሁ፡፡ ፖሊሱ “በዚህ ላይ ምን ትላለህ?” ብሎ ሲጠይቀኝ የማውቀውንና የማስበውን እንጂ እሱ የሚያስበውንና የተናገረውን አይደለም፡፡ ስለዚህ እሱ በስልጠናው ላይ የተናገረውን ሆነ ከሞጁሉ የሚነበበውን ነገር በጭራሽ አልሰማም፥ አልሰማሁም!!! አሰልጣኙ ከሚናገረውና ከሚያነበው ውስጥ አንድ ስንኝ ወስጄ ሳሰላስል አዕምሮዬ ላይ የተፀዳዱብኝ ይመስለኛል፡፡ የኢህአዴግ የአስተሳሰብ ጥንባት ከሚከረፋህ አዕምሮህን ቆልፈህ ትቀመጣለህ፡፡ እንደ ህወሃት/ኢህአዴግ በስርቆት ሳይሆን በሥራ የተካነችውን ወፍ መመልከት በስንት ጣዕሙ? አዕምሮህን ታድለህ፣ በዛ ላይ የወፏን ትጋትና የተፈጥሮን ውበት ታደንቃለህ፡፡ በኢህአዴግ ተሃድሶ ግን አይን ያወጣ ውሸት፥ ክህደትና ሌብነትን ትማራለህ፡፡ በአስተሳሰብ ጥንባት ያጠንቡሃል፡፡ ውርደታቸው ሳያንስ ያወርድኋል!! ባዶነታቸው ሳያንስ ባዶ ሊያደርጉህ ይጥራሉ፡፡ ድፍረታቸው ሳያንስ ይደፍሩሃል፣ ሳያስፈቅዱ አዕምሮህን አስገድደው ይደፍሩሃል፡፡ ወፍ… ወፍ መሆን ጥሩ ነው! አዕምሮህን ከድፍረት ያድንልሃል!!! ከኢህአዳግ ተሃድሶ ወፍ መሆን በስንት ጠዓሙ! እናንተ ባለጌዎች…እኛ ወፎች!!    

እነ ዶ/ር መረራ ጉዲናም ተሃድሶ ወሰዱ አሉን። ያው ዶ/ር ደግሞ ከራሱ ጋር እየተሞገተ ይመስላል። ለብቻው፡፡ “እናንት አፍ እንጂ ጆሮ አልባዎች” እያላቸው ይሆን?
Filed in: Amharic