>
5:30 pm - Tuesday November 1, 0292

«ያ» ትውልድ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ጸረ ኢትዮጵያ ሴራ ሲጋለጥ [ ክፍል ፩] (አቻምየለህ ታምሩ)

 

ኢትዮጵያ ወደ በለጠ ስልጣኔ፣ ዲሞክራራሲ፣ የፓርቲ ፖለቲካ አደረጃጀትና ልማት እያደረገችው የነበረውን ግስጋሴ ባጭር ያስቀረውና የገታው «ያ» ትውልድ ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ ነው። «ያ» ትውልድ እየተባለ የሚሞካሸው ደም የተጠማ ትውልድ፤ ብልህ አያቶቻችን ወደፊት እያዩ የፈጠሯትን ሰፊ አገር ወደ ኋላ እያየ በማጥበብ አፈረሳት።

በአፍ ነጠቅ ዲስኩር ኮምኒስት ሆኖ በጥላቻ የሰከረው፤በስልጣን ጥማት አብዶ፣ በአስተሳሰብ ቆርቁዞና በስታሊናዊ ፍልስፍና መርዘኛ የጥፋት ሰይፍ በኢትዮጵያ ላይ የመዘዘው «ያ» ትውልድ በዘመኑ ያጠፋው አንሶት ዛሬም አዲሱን ትውልድ ለሌላ ውድቀትና የእልቂት መዓት ሊያዘጋጅ የበቀል ሰይፉን ከሰገባው በመምዘዝ ሰልፉን በድጋሜ እያስተካከለ ይገኛል።

ያ ትውልድ በኢትዮጵያ ላይ ከመዘዘው አንዱና ዋነኛው የበቀል ሰይፍ መካከል ዋለልኝ መኮንን የሚባል ጥራዝ ነጠቅ ‹‹ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት!›› በሚል ያሰራጨው ስታሊናዊ ድንቁርናው ነው። በእግጥ ግን ከአርባ ሁለት አመታት በፊት የነበረችዋ ኢትዮጵያ በሁሉም አባቶቻችን ተጋድሎ ከወራሪ ቅኝ ገዢ ወራሪ ነጻ ሆና «የብሔር፣ ብሔረሰቦች» ህብር የነበረችዋ ውብ አገርና የሚሰፋ ድንኳን እየሰራች የነበረች፤ ከኤርትራ እስከ ቦረና ከጅግጅጋ እስከ ጋምቤላ ህበረ ብሔሮቿን እየሰበሰበች፣ በግብርና ስራ እየዘመነች፤ በኢንዱስትሪ እየጎለበተች፤ በየሞያው አስፈላጊውን የሰው ኃይል በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት እያሰለጠነች በመጓዝ ላይ የነበረች ባቡር ነበረች።

የዚህ ምስክር ያልሞተ ማስረጃችን ደግሞ ከታች የታተሙት ሁለት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ናቸው። የመጀመሪያው በ1958 ዓ.ም. ሴኔጋል ዳካር ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የመጀመሪያው የጥቁር ህዝቦች የኪነጥበት ፌስቲቫል ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ የኪነት ልዑካን ህብረ ዝማሬ ስብስብ ነው። ይህ የኪነጥበብ ልዑካን ቡድን የተመራው በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲሆን ልዑኩ ዳካር ሴኔጋል ካቀረባቸው የኢትዮጵያ ህብረ ትርዒት ትዕይንቶች መካከል በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣በጉራጌኛ፣ በአማርኛ፣ በአገውኛ፣ ወዘተ ቋንቋዎች የተሰናዱ የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜዎችና ጥዑመ ዜማዎች ይገኙበታል። አርባ ሁለት አመት ሙሉ በ «ያ» ትውልድ ስለ «ኢትዮጵያ የብሔር፣ ብሔረሰብ እስር ቤትነት» የተባለውና በቅንብሩ ላይ እንደሚታየው በዚያ ዘመን የነበረው እውነታ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነው። የዚህ ልዩነት መነሻና መድረሻው «ያ» ትውልድ የፈጠረው የፈጠራ ታሪክና የሀጢዓት ክስ ነው።

የኢትዮጵያ ቴያትር ቤቶች የኢትዮጵያ መንግስት ደመወዝ እየከፈላቸው የኢትዮጵያን ባህሎች በሙሉ አጥንተውና ህብረ አልባሳቱን በሚገባ ለብሰው ወራት የፈጀ ዝጅግታቸውን ከጨረሱ በኋላ ነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኪነጥበብ ልዑክ የኢትዮጵያን ባህል ለአለም ሊያሳይ በንጉሠ ነገሥቱ እየተመራ በየ አመቱ ወደ ሌላ አገር ሲጓዝ የነበረው። ይህ ነበር እውነተኛ ታሪካችን።

«ኢትዮጵያን የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት» አደረጓት ተብለው ለአርባ ሁለት አመት ያህል የሀጢዓት ክስ የወረደባቸው ንጉሰ ነገስት ኢትዮጵያ «የብሔር፣ ብሄረሰቦች» አገር መሆኗል ለማሳየት በየአመቱ «የብሔር ብሔረሰቦችን» የባህል ልዑክ መርተው የአገራቸውን ህብረ ቀለምነት ለማሳየት አለማቀፍ ትዕይንቶች በሚታዩበት ዋና ከተማ ሁሉ ሲገኙ ነበር። ታሪካችን ሲፈተሽ፤ ዶሴው ሲወጣ፤ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳው ሲመረመር የሚታየው የነጠረ እውነት ይኸው ነው። ያ ትውልድ ግን በዚህ ፈንታ ሀጢያት ፈጥሮ ያቺን ማደግ ያላቆመች ትልቅ አገር በዱልዱም ቢላዋ ገዝግዞ፣ ገዝግዞ ዛሬ ላለችበት የመስቀለኛ መንገድ ደረጃ አበቃት።

ያ ትውልድ በጻፈው የሐጢዓት ክስ የኢትዮጵያ ብዝሃነት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ያልነበረ፤ በመለስ ዜናዊ ዘመን ግን ከደደቢት ተስቦ እንዳዲስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተከሰተ አዲስ የፈጠራ ታሪክ ተደረተ። ሆኖም ግን በተንቀሳቃሽ ምስሉም እንደሚታየው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴዋ ኢትዮጵያ ላለም የተዋወቀችው ከነ ብዝሀነቷ ህበረ ብሔራዊት አገር ሆና ነበር።

ሁለተኛው ያልሞተ ማስረጃ ደግሞ «ኦሮምኛ እንዳይነገር ተከልክሎ ነበር» በተባለበት ዘመን እ.ኤ.አ. በ1930 ዓ.ም. ዳኛው፣ ተከሳሹም፣ ፖሊሱም ኦሮሞዎች ሆነው ተከሳሽ ቋንቋውን እየተናገረ በቋንቋው ፍትህ ፊት ቀርቦ በቋንቋው ሲዳኝ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ነው። ልብ በሉ! ኦሮምኛ እንዳይነገር ተከልክሎ ነበር በተባለበት በዚያ ዘመን፤ ያውም ቋንቋው በኦፊሴል የስራ ቋንቋ ባልሆነበት ሁኔታ ህብረ ብሔራዊ ዜጎችን ስታስተናግድ የኖረችዋ ኢትዮጵያ ከዛሬ 80 ዓመታት በፊት ፍርድ ቤቶቿ በኦሮምኛ ቋንቋም ችሎት ያስችሉ ነበር። የምንኖርበት ዘመን የማይዋሽበት ዘመን ሆነና ከሀዲዎች የሸረቡት ሴራ በማያወላዳ ማስረጃ እንዲህ እየተጋለጠ ነው።

ወደፊት በሚወጡ ጽሁፌች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፓርላማ ውስጥ ኦሮምኛ ይነገር እንደነበር፤ ኦሮምኛ ይናገሩ የነበሩ እንደራሴዎች ለእንደራሴዎች ምክር ቤቱ ጉዳያቸውን በኦሮምኛ ያሰሙ እንደነበር፤ ኦሮምኛ የማይሰማው ፓርላመንቴሪያን ደግሞ እየተተረጎመ ይቀርብለት እንደነበር ከነ ማስረጃው ይዤ እቀርባለሁ። ከዚህ በተጨማሪ የሌለ ታሪክ እየጻፈና እያስጻፈ፣ ቂም በቀልን እየሰበከ፤ በሰላም ይኖር የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፉ አውሬ ያደረገውን የታሪክ ቅሌት መታሰቢያ ለሆነው «ያ» ትውልድ የፈጠረው የፖለቲካ ታሪክ የኃጢዓት ክስ እንጂ በዘመናዊ መልክ የተቋቋመችው ኢትዮጵያ ለሁሉም ሕዝቧ የነጻነትና የእኩልነት ማኅደር እንጂ የማንም እስርቤት እንዳልነበረች፤ ጨቋኝም ሆነ ተጨቋኝ ብሔረሰብ ደረጃ ታይቶባት የማያውቅ፤ይልቁንም ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ቤተሰብ የሆነና ከማንም የአፍሪቃ ሕዝብ በላይ የሥነ ልቡና ኩራትና ከማን አንሼነት መንፈስ ለማዳበር የበቃ ታላቅ ህዝብ እንደነበር የተመዘገቡና የማያወላዱ ማስረጃዎችን በማጣቀስ ለሰፊው ህዝብ እናቀርባለን!

Filed in: Amharic