>

የእስክንድር፤አንዷለምና አበበ ጉዳይ (ወንድወሰን ተክሉ)

**የህወሃት በማሰቃየት ተደሳችነቱ
 እስክንድርን ጨምሮ 746የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ብሎ መግለጫ ሲሰጥ ማንቁርቱን ስንቆ የያዘውን ዘርፈ ብዙ አስጨናቂ የህዝብን እጅ ከአንገቱ ላይ ለማስለቀቅ ካለው የጭንቅ ፍላጎቱ የመነጨ እውነተኛ እርምጃ እንደሆነ እናያለን፡፡
ሆኖም ከታነቀበት ለማምለጥ እለቃለሁ ሲል እውነተኛ ውስጣዊ ማንነቱና ስብእናው ደግሞ የለም «እነዚህን ለቀህ በምን ልንደሰት ነው» ብሎ ሲሞግተው «ይፈታሉ» ብሎ መግለጫ በሰጠበት ወቅት የተደሰቱትን እና ይበልጥም ለመደሰት ያቆበቆቡትን ደስታ በመንጠቅና ብሎም በደስታቸው ምትክ ንዴትን በመስጠት እራሱን ሊያስደስትና ሊያዝናና እፈታለሁ ያላቸውን ወገኖቻችንን የአግ7 አባልነታችሁን ፈርሙና ብሎ እርፍ፡፡
ይታያችሁ፡ እነዚህ ሰዎች ካላቸው ግለ ድርጅታዊ፤ሙያዊና ህይወታዊ አቋም የተነሳ የአግ7 አባል ሊሆኑ የማይችሉ መሆናቸውን ወያኔ ከእኔና ከእናንተ ይበልጥ አጥርታ የምታውቀው እውነታ ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች አባል ያልሆኑበትን ድርጅት አባል እንደሆኑ አድርገው እንዲፈርሙና እንዲወጡ የተፈለገበት ዋና አላማ ወገኖቻችን በእርግጥም የቀረበላቸውን ያለማንገራገር (ገና ለገና እንፈታለን በሚል ማለት ነው) ፈርመው ይፈታሉ ተብሎ ታምኖበት ሳይሆን በመጀመሪያ ይፈታሉ መግለጫው እየተደሰቱ ያሉትን ወገኖቻቸውን ደስታ በመንጠቅ የራሱን ደስታ ለማግኘት እንደሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡
የህወሃታዊያን የደስታና የእርካታ ምንጭ እኔና እናንተን የሚያስደስትና የሚያረካ የመደሰቻ መንገድ ሳይሆን እኔና እናንተን የሚያስደነግጥና የሚያሳዝን ማንኛውም ክስተት እነሱን የሚያዝናና እና የሚያስደስት መሆኑ ነው፡፡
እስክንድር፣አንዷለምና አበበ ቀሰቶ በምንም አይነት ተአምር ለመፈታት ሲሉ ያልሆኑትን ነን ብለው እንደማይፈርሙ ከእኔና ከእናንተ የበለጠ ወያኔ ታውቃለች፡፡
እናም ይህንን ጠንቅቃ እያወቀች ወገኖቻችን ሊፈርሙ ቀርቶ ሊያስቡ የማይችሉትን ጉዳይ ፈርሙና ውጡ ማለት ትርጓሜው ምንድነው?
1ኛ- እነዚህን ወገኖቻችንን ለመፍታት አልፈለገም፡፡ ግን ደግሞ ማንቁርቱን ባነቀው ህዝባዊ አመጽና ዓለም አቀፍ ተጽእኖ እጅግ ተጨንቆ መላቀቅ ይፈልጋል፡፡
እናም፤ ካስጨነቀው ማነቆ ለመላቀቅ የእፈታለሁ አዋጁን በማሰማት ፈቃደኝነቱን በማሰማት «እነሆ ይፈቱ ዘንድ ተስማምቼ ወስኜያለሁ» ሲለን በሌላ በኩል ደግሞ እንዲፈቱ ባለመፈለጉ የማያስፈታ ቅድመ ሁኔታን በማቅረብ እንዳይፈቱ ማገድን ተያያዘው፡፡
2ኛ-እኔ ይፈቱ በማለት ውስኜ እነሱ ግን ፈርመው መፈታት ስላልፈለጉ እምቢ ብለውኛልና እኔን ለቀቅ አድርጉ በማለት ያስጨነቀውን ህዝባዊ እጅ ለማስለቀቅም ይመኛል፡፡
3ኛ- እጅግ አስጨንቆት ማድረግ የማይፈልገውን ተግባራት እንዲያደርግ ያስገደደውን ህዝባዊውን እጅ በንዴት መበቀል፡፡
«እንድፈታላቸው የተጨነኩበትን ሰዎች እፈታለሁ ብዬ በማስደሰት ደግሞም እንዳይፈቱ በማድረግ ደስታቸውን ወደ ንዴትና ሀዘን መለወጥ » በማለት በዚህ ስሜቱ እኛንም ሆነ በእስረኞቹ ሞራልና ስሜት ላይ መሳለቅን ነው እንጂ ህወሃት የተያያዘው ከማንኛችንም በላይ እነእስክንድር አባል ያልሆኑበትን አግ7 ድርጅት አባልነትን ተቀብለው እንደማይፈርሙ አሳምሮና ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ሁሉም ነገር ምክንያት አለው፡፡ ያለምክንያት የሚደረግ ድርጊት የለም፡፡
ለእነ እስክንድር የቀረበው የአግ7 አባልነት ፊርማ ፎርም አላማውና ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ በእርስዎ በኩል?
የእነዚህ እፉኝት ልጆች አስተሳሰብ እንደ እኔና እንደእናንተ አይደለም፡፡
ለእኛ የደስታ ምንጭ ለእነሱ የሀዘንና ንዴት ምንጭ ነው፤የእነሱ የደስታ ምንጭ ለእኛ የሀዘንና ንዴት ምንጭ ነውና እኛ እንደምናስበው ያስባሉ ብለን ለሰከንድም አንጠብቅ፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ህወሃት እጅግ እያንገሸገሻትና እጅግም እየመረራት አይደለም እነ እስክንድርን ከእስር መፍታት የአራት ኪሎውንም የምንሊክ ቤተ መንግስትን ደም እምባ እያለቀሰች ጥላ ትጠፋለች፡፡
በውዴታዋ ሳይሆን በግዴታ እነ እስክንድርን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ትፈታለች፡፡
የሚያስፈታውም ጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው!!
በዚሁ አጋጣሚ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአምስት ቀን የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ እንደታወጀ እንድታውቁና እናንተም ላላወቀ እንድታሳውቁ አደራ እላለሁ፡፡
Filed in: Amharic