>
5:13 pm - Tuesday April 18, 1747

እስክንድር ነጋ ከእስር እንደወጣ ያስተላለፈው መልእክት (በዋዜማ)

ዛሬ ተጨማሪ የፖለቲካ እስረኞች በነፃ ተለቀዋል፣ እስክንድር ነጋ አንዱ ነው። ከእስር እንደወጣ ያስተላለፈው መልእክት ይህ ነው።

ምስጋናዬ ይድረሳችሁ
ክብር ለኃያሉ እግዚአብሔር፣ ለህዝብ፣ ለወዳጆቼ፡ የሙያ አጋሮቼ ለሆኑት ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፤ እንዲሀም ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ (በተለይ ለምዕራባዊያን) ይሁንና በዛሬዋ ዕለት ከትንሿ እስር ቤት ወጥቼ ትልቁን እስር ቤት ተቀላቅያለሁ፡፡ ልቦናቸውን በጭቆና ያደነደኑ አምባገነኖች እጄ ለ18 ዓመታት እንዲጠፈር ያዘጋጁት የግፍ ሠንሠለት፣ ይኸው በ6ኛው ዓመቱ በኃያሉ እግዚአብሔር ፈቃድና ፍትሕ በተራበው ህዝባችን ትግል ተበጣጥሶ ወድቋል፡፡ ይህ የተበጣጠሰ ሠንሠለት የዲሞክራሲ ትግላችን መጠናከር መገለጫ ቢሆንም፣ በሀገራችንና በህዝባችን ላይ የጠለቀው የህሊና ሠንሠለት ገና እንዳልተፈታ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አንችልም፡፡ ህዝብ ከጭቆና ነጻ እስኪወጣ ድረስ ትግላችን ይበልጥ እየተጋጋለ መሄድ ይገባዋል፡፡
የሀገራችን ፖለቲካ በአንድ በኩል ተስፋ፣ በሌላ በኩል አደጋ ይዞ መንታ መንገድ ላይ አቁሞናል፡፡ በበጎ ገጽታው፣ የህዝባችን የዲሞክራሲ ጥያቄ ጎልብቶ አምባገነናዊውን ኢሕአዴግ አንገዳግዶታል፡፡ ትግሉ እዚህ እንዲደርስ ብዙ ንጹሃን ተንገላተዋል፣ ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተርበዋል፣ ተጠምተዋል፣ ታርዘዋል፣ ተሰደዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ 
ይህን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉት ግን፣ ተስፋን አንግበው እንጂ ኢሕአዴግ ላይ ጥላቻና በቀልን ሠንቀው አይደለም፡፡ ተስፋቸው ከሁሉም በላይ የፍቅርና የመቻቻል፣ ከዚየም የፍትሕና የእኩልነት፡ ብሎም የእኩልነትና የፍትሕ የሆነውን የሠላም ሀገር ማየት ነው፡፡ ግባችን ብቻ ሳይሆን ትግላችንም የግድ እነዚህን እሴቶች ማዕከል ማድረግ አለበት፡፡ ስልቱን አበላሽተን ግቡን ማሳመር አንችልም፡፡ የብሄር ጥቃቶችና የፋብሪካ ቃጠሎዎች ለትግል ያነሳሳንን ተስፋ ያጨለሙ አደጋዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ነገ ሳይባል፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑነ መቆም አለባቸው፡፡
የሀገራችንን የፖለቲካ ጥያቄዎች በሠላማዊ መንገድና በድርድር ለመፍታት እንዲያስችል፣ ኢሕአዴግ ከሁሉም ተቃዋሚዎች ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መደራደር ይኖርበታል፡፡ በሕጋዊ መድረክ ላይ ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር ብቻ የሚደረግ ድርድር በቂ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ብዙ ትምሕርት ሊቀሰምበት የሚችል ነው፡፡ ሠላምን ለማውረድ ሁሉም አማራጮች መፈተሽ አለባቸው፡፡
ከአፄ ኃይለሥላሴ ወደ ደርግ፣ ከደርግ ወደ ኢሕአዴግ የተደረጉት ሽግግሮች በሀገራችን ላይ ከባድ ጠባሳ አሳርፈው ማለፋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በተለይ… በተለይ ታላቁ-የኢሕአዴግ ታሪካዊ ስህተት እንዳይደገም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድናደርግ ይጠበቅብናል፡፡ በሌሎች ሀገራት ያልታዩ ፈተናዎች ድሮም ሆነ ዘንድሮ አልተጋረጡብንም፡፡ እንደ ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ በርካታ ሀገራት ተመሳሳይ ፈተናዎችን በጥበብ አልፈዋቸው ዲሞክራሲያዊ ሀገራት ገንብተዋል፡፡ ጥበቡና ክሕሎቱ እኛም ጋር አለ፡፡
ከፊት ለፊታችን ብሩህ ዘመን ይጠብቀናል፡፡ ታሪክ ከእኛ ጋር ነው፡፡ እውነት ከእኛ ጋር ነው፡፡ ፍትሕ ከእኛ ጋር ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ሁሌም ቢሆን የተበዳይ መከታ የሆነው ፈጣሪ ከእኛ ጋር ነው፡፡ የድል አክሊል ይጠብቀናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው በትግላችን ጽናት፣ በአካሄዳችን መቻቻል፣ በመንፈሳችን ፍቅር፣ በአስተሳሰባችን ሚዛናዊነትና በተግባራችን ሠላምን ይዘን ወደፊት መጓዝን ነው፡፡
– ቀሪ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!
– ምስጋና በትንሿ እስር ቤት ሳለሁ ላሰባችሁኝ ሁሉ!
– ምሥጋና ለዓለም አቀፍ አጋሮቻችን!
-ምሥጋና ለዲሞክራሲ ለታገላችሁት ሁሉ!
– ጽድቅ ለሰማዕቶቻችን!
– ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለፈጣሪ!

እስክንድር ነጋ
አዲስ አበባ

ከዋዜማ ሬዲዮ

Filed in: Amharic