>
5:18 pm - Monday June 15, 8229

ኢህአዴግ ከትናንት እስከ ዛሬ (ያሬድ አማረ)

    ይህን በህብረ ዝማሬ  ያሰማው ታምራት ላይኔን አይንህን ላፈር ያለው ምን አልባትም ከአመታት በኋላ ከትግራይ ክልል ተነስትው የአዲስ አበባ ከተማ ርእሰ መስተዳደር የከተማዋ ገዢ ተደርገው የተሸሙት አቶ አርከበ እቁባይን መምጣትና ፤በወቅቱ በከተማዋ ላይ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚንቀሳቀሱበት ውቅት አንድ ለእናቱ በሆንው የአዲስ አበባ ስታዲየም ይዘመር የነበረ ህብረ ዝማሬ ነበር፡፡ በእርግጥም የአዲስ አበባ ህዝብ በወቅቱ አቶ አርከበ እቁባይ ኢህዴግና ኢህአዴጋዊ ርእዮተ አለም የሚያራምዱ መሪ እንደነበሩ ቢያውቅም ለተራማጅ አስተሳሰባችው ድጋፉን አልነፈጋቸውም፡፡ብዙውን ግዜም የሸግር ልጅ ከዘውግ የራቀና አጥንት ቆጠራ ውስጥ ሳይገባ ማንም ከየት ይምጣ ከየት  መልካም የሚሰሩትን በአደባባይ በምክንያት የሚያከብር ብሎም እኩይ የሚሰሩትንም እንደዛ የሚቀጣ በሳል መሆኑን አስረጅ ወይም ነጋሪ አያሻም፡፡እውነት ለመናግርም አቶ ታምራት ላይኔ ከአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበርሰብ ስለመጡ በአንጻሩ አቶ አርከበ እቁባይም ከትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ስለበቀሉና ስለመጡም አልነበረም ወቀሳና ሙገሳ የተቸራቸው ፡፡ህዝቡ በራሱ ሚዛን መዝኖ ቀሎ ያገኘውን አዋርዶ የተሻለ ለመስራት የቻለውን አክብሮና አመስግኖ የተቀበለው ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አርከበም ከህዝብ ልብ ሳይወጡ  ያልተጠበቁ ክስተቶች በምርጫ 97 መታየት ጀምሩ ህዝቡም በጨዋ ደንብና ስርአት አቶ አርከበ ሆይ እንወድዎታለን ባልጠራው የኢህአዴግ  ፖለቲካ ፕሮግራምና ፖሊሲ መጓዝን መርጠዋልና  በቅንጅት አይምጡብን በማለት አስተማሪ በሆነ አርጩሜ በምርጫ ቀጣቸው፡፡ እሳቸውም የቀደመ ተዝታቸውን ይዘው ወደ ጉሬያቸው ወዳሳደጋቸው እናት ድርጅታቸው ተጠቅልለው ገቡ፡፡ያ ቅቡልነትም ውሃ በላው፡፡
አቶ መለስም ነጮቹን ልብ በሚያማልል ንግግር ምርኮኛ አደረጋቸው የቀድሞዊ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር በአፍሪካ አቻ የማይገኝለት መሪ እስከ ማለት በሚደርስ ቁልምጫ አሞካሹት፡፡የነጮቹን ልብ ጠንቅቆ የተረዳው መሌ ቀድሞውንም በአርከበ ስራዎችና በህዘቡ ዘንድ እያገኘው ያለውን ቅቡልነት በመተማመን እንከን የለሽ ምርጫ እንደሚያደርግም ጭምር የመተማመኛ ቃሉን ሰጠ፡፡ ሚያዝያ 29 መስቀል አደባባይም በከፍታው ማማ ላይ ወጥቶ ምም ማጭበርበር ሳያስፈልግ ይህ ማእበል ተቃዋሚዎችን ይበላቸዋል ሲል በሀሴት ሲቃ ድምጽ ተመፃደቀ፡፡ለመለስ የሚያዝያ 30 ዋዜማ ሀሴት እንዲያደርግ እድል ቢሰጠውም ማግስቱ ግን መጪውን አመላካች አሰደንጋጭ መጪውንም የሚያመላክት ነበርና ደስታውም ሆነ ሀሴቱ ጭው ወዳለ ድንጋጢ ለመለወጥ የአንድ ቀን እደሜ እንከዋን አልነበረውም፡፡የሚያዝያ30ው ሰልፍ የምርጫውን ውጤት የወሰነ ነበርና ኢህአዴግ በመላ ሀገሪቱ አይቀጡ ቅጣት ተቀጣ፡፡ሁኔታዎች ሊታሰቡ በማይችሉ ቅፅበቶች ተለዋወጡ ከምርጫው  በኋዋላ ሀገሪቱ ወደ ለየለት አምባገነናዊ የመለስ ዜናዊ አስተዳደር መዳፍ ስር ወደቀች፡፡ እነ ቶኒ ብሌርም  ይህን አይተው ተሸውደን ነበር ሲሉ ሂሳቸውን አወረዱ፡፡
ከ97 ምርጫ በኋላ ከቀድሞ በባሰና በለየለት ሁኔታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሚናገሩት ቋንቋ እየተቧኑ መቧቀስ የተለመደ ክስተት እየሆነ መጣ የእምነት ተቋማትም አጅንዳዎች እየሰፉና ወደ አደባባይ ተቃውሞዎች እያደጉ መምጣት መንግስትም ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ዶክመንታሪ ፊልሞችን  እግር በእግር እየለቀቀ ወደ ከፍተኛ ማጥቃት መሸጋገር ያለመተማመኑ ከአንዱ ጥግ ወደሌላው ጥግ በፍጥነት እንዲዳረስ የራሱን አስተዋፅኦ አደረገ፡፡
አድፍጠው የነበሩ የዘውግ አስተሳሰብ አራማጆች ኢህአዴግ ባመቻቸላቸው የመጫወቻ ሜዳ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላቻቸው፡፡ ምድሪቱ የበረከት ምድር መሆንዋ ተረስቶ የደም ምድር ሆነች፡፡ጩኅትና ዋይታ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ከምእራብ እስከ ምስራቅ አስተጋባ ፡፡ይህ በሆነበት ቅፅበት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን በቃኝ አሉ ፡፡በጥልቅ ታድሻልሁ ያለው ኢህአዴግም ያለምንም የፖለቲካ ሪፎርም ዶ/ር አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመ፡፡እኛም ደስ አለን፡፡ደስታችን ያለምክንያት ሳይሆን ሰውየው ሰንቄአቸዋለሁ ያሉንን ጀንዳዎች ባደመጥን ግዜ፤ነፍሳችን የሻተችውን ልናገኝ ነው በሚል ተስፋ ተሞልተን ጭምር ነው ፡፡
    የኦህዴዱ አባልና የኢህአዴግ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር አብይ ከጅምሩ በተለይ የዘውጌ አስተሳሰብ ነግሶ ሰብአዊ ክብር በተሟጠጠበት፤ ስው በመንጋ እንዲያስብ የሚያስገድዱ ግፊ ምክንያቶች በተንሰራፉበት፤ የሀገሪቱ አንድነትን የሚፈታተኑ ሁነቶች በሚስተዋሉበት ፤ሰአት መምጣታቸው ያን የምንናፍቅውን እኛ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ነብርን እያልን ግን ያፈረስነውን የኢትዮጵያዊነት ቅጥር ወደ ነበረበት ክብር ለመመለስና ዳግም በማይናወጥበት መሰረት ላይ ለማኖር ብሎም  ለማነፅ የተናገሯቸው ድንቅና ውብ ቃላቶች ላለፉት 27 ዓመታት በዛ ወንበር ዙሪያ የተሰለፉም ሆነ ወንበሩ ላይ የተቀመጡ አድርገውት የማያውቁት በአንፃሩ ይህን የኢትዮጵዊነት ጣእመ ዜማ ለመስማት የምንፈልግና ለዚህ እውን መሆን ለቆምን ዜጎች ነፍሳችንን ከሰማየ ሰማያት ነጥቆ  ወደ አርያም ወሰዶ የሀሴት ምግብን የሚመግብ ነበርና ከልብ አምነን ተቀበልን፡፡ ቃል የድርጊት መሰረት ነውና ቃላቸው ወደ መሬት ወርዶ እውን የሚሆንባቸው ቀናትን መሽቶ በነጋ ቁጥር በመጠባበቅ ላይም እንገኛለን፡፡ ከምንምና ከማንም በላይ ቃል የእምነት እዳ ነው እያለ ባስተማረን፤ ኮትኩቶም ባሳደግን ማህበረሰብ ፊት የገቡትን ቃል በቶሎ ተግባራዊ እንዲደደርጉ በተለይ የሁሉ ነገሮች መቆምና ህልው ሆኖ መቀጠል የጀርባ አጥንት የሆኑት ጠንካራ ተቋማት ማቋቋምና ማዋቀር ለይደር የማይተው መሆኑ ችላ ሳይባል   በተለይ ኢህአዴግ ነው ወይስ ዶሩ ብቻ የተለወጠው የሚለው ሃሳብም እንደተጠበቀ ፤ ቃልዎን እስኪፈፅሙ ሃሳብዎን ተግባራዊ እስኪያደርጉ ግዜ ሰጥቶ ከመጠበቅና  ከማበረታታት የዘለለ አደባባይ የሚያስቆም ምክንያቱ ጎልቶ አልታየኝም፡፡
Filed in: Amharic