>

ህወሀቶች የዘሩት የጥላቻ ፍሬ አንድ በአንድ እየተመነገለ ሲወገድ እንደማየት ምን የሚያስደስት ነገር አለ? (መሳይ መኮንን)

ሁለት ተቃራኒ ስሜቶች ከወዲህና ወዲያ እያላጉኝ ነው።  ደስታና ሀዘን፡ ፍቅርና ጥላቻ፡ ተስፋና ጽልመት፡ ብርሃንና ጨለማ፡ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት። ከሀዋሳ የወገን ጥቃት በቀን ጨለማ ሲጋርደኝ፡ ከቤተመንግስት የብርሃን ወጋገን እየታየኝ ይመልሰኛል። ከወልቂጤ የሰቆቃ ድምጽ በጆሮዬ ያቃጭልና ከአራት ኪሎ በሚስተጋባ የፍቅር መልዕክት እረጋጋለሁ። ከህወሀት መንደር የቀን ጅቦች በጽልመት የተሞላ የዕብሪትና የትዕቢት ጩሀት ሲያደነቁረኝ፡ ከሰባተኛው ንጉስ በሚሰማ የተስፋ ቃል እጽናናለሁ። መከራ ነው። የአንድ አፈር አፈሮች፡ የአንድ ማህጸን ልጆች ቃዬልና አቤል፡ ሴጣንና መላዕክ ሆነው ነፍሴን አስጨነቋት። ህወሀትና ዶ/ር አብይ።
በከፍያለው ተፈራ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት፡ የእነአበበ ካሴ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚያም የእስር ቤት ሰቆቃ፡ የወላይታ ወንድሞችና እህቶች ዘግናኝ ግድያ፡ የጉጂና ጌዲኦ ወገኖች መከራ፡ የአርጎባዎች ሞት፡ የአማራዎች ስቃይ በአንድ ጎን ሆነው ውስጤን በሀዘን እየናጡት አለሁ። በሌላ ጎን በዶ/ር አብይ በኩል የምሰማው፡ የሚደረገው፡ እያመጣ ያለው የአንድነት መንፈስ፡ ሰማይ ምድሩን እየተቆጣጠረ ያለው ኢትዮጵያዊ ስሜት ልቤን በደስታ እያሞቀው፡ ነገዬን በተስፋ እያበራው ነው። በህወሀቶች የማያባራ ተንኮልና ሴራ አንድ ጎኔ ሲጎዳ፡ በዶ/ር አብይ የተስፋ መንገድ ሌላኛው ጎኔ ይጠገናል። ነፍሴ በእርግጥም ተጨንቃለች።
አዎን! ሀሳቤ ተበታትኗል። ከዚያ አዳራሽ የተሰማውን ፈዋሽ መልዕክት ደግሜ ደጋግሜ አዳመጥኩት። በጆሮ እየተንቆረቆረ ከልብ ጓዳ ገብቶ፡ አእምሮን ፈተሾና በርብሮ ነገን በተስፋ እንድንጠብቅ የሚያደርግ እጹብ ድንቅ ንግግር። ንግግር ብቻ አይደለም። መሬት ወርዶ በተግባር ሊመነዝር የመቻል አቅም ያለው ራዕይ። በዚህን የምጥ ወቅት፡ ኢትዮጵያ ለፈተና በቀረበችበት ዘመን፡ የዶ/ር አብይ ዓይነት ልበ ሙሉ፡ ቅንና የወገን ተቆርቋሪ መሪ ማግኘት መታደል ነው። ሁኔታዎች ስሜታዊ ያደርጋሉ። በእኔ ትውልድ ይቅርና በልጆቼ ዘመን ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ ነገሮች ሆነው እያየን ስሜት ቢገዛን፡ ስሜት ቢያሸንፈን ሃጢያቱ ምንድን ነው?
አሁን ደግሞ ከአስመራ መልካም ዜና ሰማን። የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የዛሬው መልዕክት ስለትልቋ ኢትዮጵያ ዳግም እንዳስብ አድርጎኛል። ትልቋን ኢትዮጵያ ያለኤርትራ ማሰብ አልቻልኩም። ምንም እንኳን ኤርትራ ነጻ ሀገር መሆኗን ባውቅም፡ አንድ ቀን አንድ እንሆናለን የሚል ህልም እንዳረገዝኩ አለሁ። ኤርትራ በነበረኝ የሶስት ሳምንት ቆይታ የተረዳሁት መለያየታችን ሁለታችንንም እንደጎዳን ነው። ከምጽዋ የቀይ ባህር ዳርቻ ተንጣሎ የሚታየው ፍርስራሽ የአጼ ሃይለስላሴ ቤተመንግስት፡ ከአስመራ መሃል ማርያም ቤተክርስቲያን የቆመው ”ለኢትዮጵያ አንድነት የወደቁ አርበኞች” ሀውልት፡ በቃኘው ሻለቃ ጎልቶ የሚታየው የኢትዮጵያ ልጆች አሻራ፡ በአስመራ ወመዘክር በክብር የተቀመጡ የኢትዮጵያ ነገስታትን ታሪኮች የያዙ መጽሀፍት፡ በተለያዩ የኤርትራ በረሃ አከባቢዎች ወዳድቀው የሚታዩ የጦርነት ዘመን ቅሪቶች፡ ጋራና ሸንተረሩ ላይ ተቀበርው የቀሩ የኢትዮጵያ ልጆችን ታሪክ የሚነግሩ የሚመስሉት ቦታዎች፡ አዎን…… በኤርትራ ትልቋን ኢትዮጵያ አይቻታለሁ።
መልካም ጉርብትና ወደ አንድነቱ የሚያመጣ በመሆኑ የዛሬው የአስመራ ምላሽ ቀኔን ያማረ እንዲሆን አድርጎታል። በእርግጥ ህወሀቶች በየቀኑ ወደ መቃብር የሚወስዳቸው መንገድ ላይ በፍጥነት እንዲጓዙ የሚያደርጋቸው ክስተት እየሆነ ነው። እነስብሃት በህይወት እያሉ ከአስመራ እንዲህ መልካም ዜና መስማት አስገራሚ ነው። ህወሀቶች የዘሩት የጥላቻ ፍሬ አንድ በአንድ እየተመነገለ ሲወገድ እንደማየት ምን የሚያስደስት ነገር አለ?
መጥፎዎቹ ጊዜያዊ ናቸው። ኢትዮጵያ ላይ ያንዣበቡት ስጋቶች እንደጉም ተነው የሚጠፉ እንደሚሆኑ አምናለሁ። ጥላቻ በፍቅር የሚሸነፍበት፡ ጨለማ ለብርሃን ቦታውን የሚለቅበት፡ ጽልመት ጥፍቶ ብሩህ ተስፋ የሚደምቅበት፡ የሀዘን እንጉርጉሮ በደስታ ሲቃ የሚለወጥበት ጊዜ ሩቅ  አይሆንም።
ዶ/ር አብይ ከህወሀት የሚመጣባቸውን ፈተና በህዝባቸው ባገኙት መጠነ ሰፊ ድጋፍ እየታገዙ በአሸናፊነት ጎዳና ላይ መውጣታቸው የጊዜ ጉዳይ እንጂ የማይቀር ነው። እንዲህ ከዳር እስከዳር፡ ዘርና ቀለም፡ ሃይማኖትና ቋንቋ ያልገደበው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ያገኘ መሪ በመሆን በታሪክ የሚሰፍሩ የመጀመሪያው ሰው ያደርጋቸዋል። ይህ ሲባል ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም። ፈተናዎች እየበዙ መምጣታቸው ይጠበቃል። ከህወሀት ከሚመጣው ብርቱ መሰናክል በተጓዳኝ ሌሎች ወገኖችም የሚወረውሩት የጥፋት ሰይፍ እንደሚኖር ምልክቶችን እያየን ነው።
ዶ/ር አብይ ከህወሀት መንጋጋ የሚያስጥል ህዝብ ከጎናቸው እንዳለ ያውቃሉ የሚል እምነት አለኝ። ይህን ህዝብ ይዘው ማድረግ የሚፈልጉትን ከማድረግ የሚያግዳቸው ሃይል ሊኖር አይችልም። አሁን ከምንጊዜውም በላይ እርግጠኛ መሆን አለባቸው። ህዝብ የእሳቸው ነው። ሞልቶ የተትረፈረፈ ፍቅር የሰጣቸው ህዝብ ከእሳቸው ብዙ ይጠብቃል። ሁሉንም ነገሮች በአንድ ጊዜ እንዲያደርጉ ባይጠበቅም የመጣው የለውጥ ንፋስ ከወዴት እንደሚያደርሰን ፍንጩን ማየቱ ወሳኝ ነገር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ለውጡ ኢህአዴግ የሚባል የግዑዛን ስብስብን ሜካፕ ቀብቶ በሌላ ቅርጽና መልክ ሊያስቀጥል የማይችል እንደሚሆን እምነት የሚሰጥ እርምጃዎችን ከወዲሁ መውሰድ ያለባቸው ይመስለኛል። የእሳቸው የለውጥ ጉዞ መዳረሻው ሁሉም የኢትዮጵያ ሃይሎች የሚሳተፉበት የሽግግር ስርዓት እንዲተከል ማድረግ ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ።
አንዳንድ ጥቃቅን የሚመስሉ ግን ደግሞ ፍጥነታቸውን ከመጎተት ባለፈ የማደናቀፍ አቅም ሊኖራቸው የሚችሉ እንቅፋቶችን ማስወገድም ጊዜ የሚሰጡት ሊሆን አይገባም። አዲስ ወይን በአዲስ ብርጭቆ እንጂ በአሮጌ ማቅረቢያ ከሆነ ለውጡን ብልጭልጭ ያደርገዋል። እነሽፈራው ሽጉጤ፡ ሲራጅ ፈርጌሳ፡ ወርቅነህ ገበየሁ፡ ተሾመ ቶጋ የመሳሰሉ አሮጌ ብርጭቆዎችን ይዘው አዲስ ወይን ማቅረብ ጣዕሙን ከማጥፋት ባለፈ ወደ መርዛማ ወይን ሊቀየር የመቻል እድል አለውና ዶ/ር አብይ እነዚህን የህወሀት ቫይረስ ተሸካሚዎችን በአስቸኳይ ከአጠገባቸው ማሰውገድ ይኖርባቸዋል።
 ሹመት ሲሰጡም አዲስ አስተሳሰብ፡ አዲስ ፊት ላይ ቢያተኩሩ ህዝብ የጣለባቸው አመኔታ አሁን ካለው በእጥፍ መጨመሩ አይቀርም። የብሄራዊ ባንክ ገዢ በመሆን የህወሀትን የዘረፋ ድርጊት ሲተባበሩ የከረሙትን ሰው መሾም ተገቢ ውሳኔ አይመስልም። ሌሎችም ከዚህ አንጻር የሚጠቀሱ በእንከንና ወንጀል የተሞሉ ግለሰቦች ከፊታችን ዞር እንዲያደርጉ እንጂ መልሰው በሌላ ማለያ እንዲጫወቱ ባያደርጉ ለውጡን ይበልጥ ያፈጥነዋል የሚል እምነት አለኝ።
የቅዳሜው ስለፍ በመላው ኢትዮጵያ መደረግ ይገባዋል። ታዲያ ዓላማው ላይ መጠነኛ ማሻሻል ቢደረግ ጥሩ ነው። ዶ/ር አብይን ከመደገፍ ባሻገር በቀጣይ እንዲሆኑ የምንፈልጋቸውን የምንጠይቅበት መድረክ ሊሆንም ይገባል። የሚሰጠን መሪ ካገኘን የምንፈልገውን መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ከምንም በላይ ለህወሀት ግልጽ መልዕክት የሚተላለፍበት፡ የለውጡን ሂደት ለመቀልበስ ሙከራ እንኳን የሚያደርግ ከሆነ ህዝባዊ ቁጣው ሞቱን አጉል ሊያደርገው እንደሚችል በደማቁ የሚነገረው ትዕይንት መሆን ይኖርበታል።
በአንዳንድ ሰዎች ላይ መጠነኛ ቅሬታ አለኝ። የዶ/ር አብይን የመደመር ስሌት በቅጡ ሳይረዱ የመጨፍለቅ ዓይነት መስመር ይዘው የሚጋልቡ እንዳሉ ታዝቤአለሁ። እሳቸው ስለሀሳብ ነጻነት፡ ዲሞክራሲ አውርተው ለዚያ መቆማቸውን በመግለጽ እንደመር ሲሉ ከዚህ መልዕክት ባፈነገጠ የሀሳብ ልዩነት ሲያዩ ተረባርበው ሲጨፈልቁና ሲደፍቁ የሚታዩ ሰዎች እየበረከቱ ነው። ዶ/ር አብይ እንደመር ሲሉ እንደፋብሪካ ሳሙና አንድ ቅርጽና መልክ ይኑረን፡ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንያዝ፡ አንድ ቃል እንናገር እያሉ አይደለም። ከኢትዮጵያ እንገንጠል የሚሉና፡ እስከየመን የኢትዮጵያ ግዛት ነው ብለው አቋም የሚይዙ በሁለት ጽንፍ ያሉ ሃይሎች ሀሳባቸው የሚሰተናገድበት ስርዓተ መንግስት እንዲመጣ ተግተው የሚሰሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመደመርን ስሌት በሀሳብ ልዩነት ውስጥ አክብረው መሆኑ ልንረዳ ይገባል።
በተረፈ ህወሀቶች የሚያዋጣቸው ምርጫ ተሰጥቶአቸዋል። የማርያም መንገድ አግኝተዋል። የወንድ በር ተከፍቶላቸዋል። ይህ ዕድል እንዲያመልጣቸው ባያደርጉ ለእነሱ ይጠቅማቸዋል። ዶ/ር አብይ ለእነሱም መውጪያ በር ሊሆኗቸው በተገባ ነበር። ከአጉል አወዳደቅ የሚያተርፋቸው ጥሩ አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙ ቢቀሩ የሚጎዱት እነሱና እነሱ ብቻ ናቸው።
መልካም ቀን
Filed in: Amharic