>

ስንት ዋጋ በከፈሉ አዲስአቤዎች ቁስል ላይ እንጨት አትስደዱ? እጃችሁንም አፋችሁንም ሰብስቡ!!! (እየሩሳሌም ተስፋው)

ስንት ዋጋ በከፈሉ አዲስአቤዎች ቁስል ላይ እንጨት አትስደዱ? እጃችሁንም አፋችሁንም ሰብስቡ!!!

እየሩሳሌም ተስፋው

የአዲስ አበባን ህዝብ የድል አጥቢያ አርበኛ አርጎ መሳል ተገቢ አይደለም በ97 ግንባሩን ለጥይት አሳልፎ የሰጠውን እንተወውና የ 97 ድብት ባለቀቀው ሰዓት አዲስአበቤዎች በሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲ አማካኝነት አዲስአበባን ጨምሮ በተለያዪ ክ/ሀገሮች በመገኘት ህዝቡን ሲያነቃቁ ነበር ከነዚህም በጥቂቱ
* 2005 ዓም አዲስ አበባ ላይ ፀረ ሽብር አዋጁ እና የተለያዪ አፋኝ አዋጆች እንዲሰረዙ
ሁሉም የመንግስት ሌቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ
የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች እና የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ
የኑሮ ውድነቱ እንዲስተካከል እና ሌሎች አጀንዳዎችን አንስተው ከ ስምንት አመት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ብዙ ህዝብ የተገኘበት ሰላማዊ ሰልፍ አካሄደዋል
* ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆችን በቦታው በመገኘት የደረሰባቸውን በደል በኢሳት ቴሌቭዥን አማካኝነት ለህዝብ እንዲደርስ በማድረጋቸው ኃላፊዎቹ ለፍርድ ቀርበዋል
* ለሱዳን የተሸጠውን የጎንደር መሬትን በመቃወም በጎንደር ተገኝተው ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሰልፍ ቢያደርጉም የጎንደር ህዝብ እንደጠበቁት ተቃውሞውን ሳይቀላቀላቸው እነሱ ግን ጥያቄአቸውን አቅርበው ተመልሰዋል
* የአዲስአበባ ዙሪያ ማስተር ፕላን ምክንያት በማድረግ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ግድያ በመቃወም አዲስአበባ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል
* የ2007 ምርጫ ምህዳሩ ይስፋ በማለት የአዳር ሰልፍ ጠርተው የኢህአፓ ዘመን የተመለሰ በሚመስል መልኩ እራሳቸውን ለሞት አሳልፈው በመስጠት በተለያየ መንገድ ህዝቡን ቀስቅሰው የሰልፉ እለት በጣም በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበው ወደ እስርቤት ተልከዋል
* ከሳውዲ አረቢያ በግፍ እዲወጡ ለተደረጉት የኢትዮጵያውያን ድምፅ ለማሰማት የሳውዲአረቢያ ኢንባሲ ፊት ለፊት የተቀጠቀጡትስ
* ቫቲካን ላቆመችው የሞሶሎኒ ሀውልት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ሲወጡ 6ኪሎ ላይ የተቀጠቀጡትስ ?
* በታላቁ ሩጫ በላይም ተቃውሞአቸውን በማሰማታቸው ለእስር እና ለፖሊስ ቆመጥ የተዳረጉትስ?
* ብሔር የለኝም ብሔሬ ኢትዮጵያዊነት ነው እያለ የሚያቀነቅነው ላመነበት ግንባሩን ለጥይት አሳልፎ የሚሰጠው ከቄሮ ከፋኖ እና ዘርማ እንቅስቃሴ በፊት ሲንቀሳቀስ ለነበረው ይህ ለውጥ እንዲመጣ አሻራውን ለጣለው ለሸገር ልጅ ዛሬ ሲዛበቱበት ማየት ያሳዝናል
* ይህ ለውጥ እንዲመጣ (ገና ብዙ ቢቀረንም) ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከፍሏል ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ ብሎ እሚያስተዛዝብ ክሬዲት ለመውሰድ መሻማት አስፈላጊ አይደለም።
ተጨማሪ ሀሳብ ከሰዋሰው ዮሀንስ

ስለ አዲስ አቤዎችማ :

“ማን ያውራ ?የነበረ:

ማን ይናገር? የቀበረ “ ይላሉ አበው ሲተርቱ! (ሰዋሰው ዮሀንስ)

ምንም እንኩዋን ከአገር ከለቀቅን የአንድ ጎልማሳ ዘመንን ያህል ብናስቆጥርም: አዲስ አቤዎችማ: በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ዛር የፈለቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ: ባለፈው 43 ዓመታት: የዓመፅ ጥሪ ባደረጉ ወቅት ሁሉ: የዓመፅ ጥይት መለማመጃና ማሙዋሻ: ቤተ ሙከራ እንደነበሩ: ባለፈው በነበረውና አሁንም ባለው ግፈኛ ሥርዓት ደጋፊዎችና ተቃዋሚ ድርጅቶች እርባና ቢስ ሁሉ ከንቱ አጀንዳ በርካታ ትውልድ  እስከዛሬ ድረስ የገበረች ታላቅ የኢትዮጵያ ከተማ ቢኖር አዲስ አበባ መሆንዋን ብናረጅም ሕያው ምስክሮች ነንና በዛ ሕዝብ ቁስል ላይ ከቶ ማንም አፉን እንዳያላቅቅ አደራ?
አዎ !  “አዲሳቤዎችን “ በዘመን አመጣሹ  ልክፍት ከንቱ የብሔረሰብ ካርቶን  ውስጥ አስገብቶ: “ ከእኛ ብሔረሰብ ይህን ያህል ሕዝብ ተሰውቶአል“ የሚል  ስታትስቲካዊ መርጃ የሚያቀርብ:  “ የአዲስአቤ ቅይጥ ብሔረሰብ ነዋሪዎች  ነፃ አውጪ“  ድርጅት አለመኖሩ: አጀንዳውን የሚያስጮህለት እንዳይኖረው አደረገው እንጂ:
ያለፉት 27 ዓመታትስ ከአዲስ አበባ ተገፍቶ በባሕርና በበረሐ ያለቀውስ መስዋዕትነት ወዴት ወዴት?“
በየእስርቤቱ የማቀቀውስ? በየስደት አገሩ ስደተኛ ጣቢያስ የሚንገላታውስ?  ከስራው ተፈናቅሎ ለማኝ የሆነውስ? እረ ስንቱ ይነገራል?
አዲስ አበቤዎች ጠበውም መጥበብ: አብጠውም መፈንዳት ስለማይፈልጉ: አንገታቸውን ቀብረው: የነበራቸው እድር: እቁብና: የቤት ዕምነት  ወዘተ ባሕላዊ እሴቶቻቸው ያስገኙላቸው ሕብረት እንኩዋን ሳይቀር : እንደ ካርታ ተፐውዞ: በገዛ ምድራቸው  “መጤ“  እሰከመባል የተገፋስ ሕዝብ አለ ወይ?
ነካክታችሁ  ስንት ዋጋ በከፈሉ አዲስአቤዎች ቁስል ላይ እንጨት አትስደዱ? እጃችሁንም አፋችሁንም ሰብስቡ!
እስከ ዛሬ ለመጣው በጎ ጅምር: የድል አጥቢያ አርበኛ ለመሆን : ይሄኛው ብሔረሰብ: ሐይማኖት: ጎሳ: የፖለቲካ ድርጅት ወዘተ. አለያም ግለሰብ ብቻውን ዋጋ እንደከፈለ አድርጋችሁ : በትውልድ ሕይወት ቁማር ለመጫወት የምትፈልጉ ሁሉ !እጃችሁንም አፋችሁንም ከአዲስአቤዎችም ከኢትዮጵያ ሕዝብ መከራና ቁስል ላይ አንሱ!
እስከ ዛሬ ድረስ ለደረሰው ግፍና መከራ ከማንም በላይ ዋጋ የሚከፍሉት: ሕፃናትና ሴቶች: የድሐው ልጅና አጋዥ የሌለው: ሕዝብ ነውና: ጥቂት ሠላም የሚመስል ነገር ሲፈነጥቅ: መርዝ በመዝራት ትውልድ አትበክሉ?
እስከዛሬ ስለ ጨነገፈው በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሲባል የኢትዮጵያን እናቶች የዘመናት የሰቆቃ ድምፅ በመወከል
የትውልድ እናት ሰዋስው ነኝ
ከሰሜን ዋልታ
Filed in: Amharic