>

የቅማንት ካርድ - የህወሀት የመስፋፋት ፖሊሲ ፕላን ቢ መሆኑ ይሆን???  (ፋሲል የኔአለም)

የቅማንት ካርድ – የህወሀት የመስፋፋት ፖሊሲ ፕላን ቢ መሆኑ ይሆን???

ፋሲል የኔአለም

ህወሃት ከበረከት በመቀጠል ሊጫወትበት ያሰበው ካርድ ቅማንት ነው።  ቅማንት ከኢትዮጵያ ነባር ነገዶች  አንዱ ነው፤ ምንም እንኳ ባህሉና ቁንቋው በታሪክ ጉዞ የተዋጠ ቢሆንም፣ ያለውም ቢሆን ይከበርልኝ ማለቱ ክፋት የለውም። ክፋቱ ጥያቄውን ከሚያቀርቡት መካከል የተወሰኑት ቅማንቶች አለመሆናቸው ነው፣ ወይም በመካከላቸው በህወሃት የሚነዱ ሰዎች መኖራቸው ነው።  የጎንደር ከተማ አስተዳደር በቅማንት ስም የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ የከለከለበት ምክንያት ከጥያቄው ጀርባ ህወሃት እንዳለበት ስላወቀ እንደሆነ አስባለሁ። ህወሃት የቅማንትን ጉዳይ የሚያነሳው  የመስፋፋት ፖሊሲው   አካል ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣  የገዱን አስተዳደር  አዳክሞ ብአዴንን መልሶ በእጁ ለማስገባት በማሰብም ነው።  እቅድ “ለ” ሊባል ይችላል።
የህወሃትን እቅድ የተረዱት ብአዴኖች፣ የጥያቄውን ተገቢነት አይተው ለህወሃትም ተጨማሪ ምክንያት ላለመስጠት በሚል  የተወሰኑ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በቅማንት ስር እንዲተዳደሩ ፈቅደዋል። ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ቅማንቶች በብዛት ባሉበት ቦታ ፣ በቅማንት የሚመራ አስተዳደር  ተቋቁሟል ። ይህ ውሳኔ ግን ህወሃቶችን  አላረካቸውም። የእነሱ ፍላጎት እስከ መተማ ያለው መሬት በቅማንት  ስር እንዲሆን ማስደረግ ነው ። ይህን ማስደረግ ከቻሉ ቅማንት የሚመራው አስተዳደር በቀጥታ ከሱዳን ጋር የሚገናኝ ይሆናል፤  ከዚያም ህወሃቶች ቅማንት  ከአማራ ክልል ወጥቶ  ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ጥያቄ እንዲነሳ ግፊት ያደርጋሉ።   ይህን ማሳካት ከቻሉም ትግራይ በመተማ በኩል ከሱዳን ጋር የሚያገናኘውን ሰፊ መሬት ያገኛል። ይህ እስኪሆን ደግሞ ቅማንት በሚመራው መሬት ላይ የፈለጉትን መሳሪያ እያስገቡ ክልሉን ሰላም ይነሱታል። ያዳክሙታል። በአዲሱ የቅማንት ወሰን፣ ቅማንት በቀጥታ ከሱዳን ጋር የሚገናኝበት እድል የለውም። ቅማንት ደሴት ሆኗል። ብአዴኖች የህወሃትን እቅድ ለማክሸፍ ቢችሉም ህወሃት አሁንም እያነከሰ አቧራ ከማስነሳት አልቦዘነም።
በአጠቃላይ ለአገራችን ሁነኛው መፍትሄ፣ ዶ/ር አብይ ያነሱት የአስተዳደር ወሰን ጽንሰ ሃሳብ ቢሆንም፣  ያ እውን እስኪሆን ድረስ ቅማንቶች የህወሃት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ መሳሰቡ ተገቢ ነው።
Filed in: Amharic