>

ወደ ገናናው ታሪካችን እንመለስ ሲባል .... (ፋሲል የኔአለም)

ወደ ገናናው ታሪካችን እንመለስ ሲባል ….
ፋሲል የኔአለም
ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ታሪኳ እንመልሳት ሲባል ወደ ስኬት ታሪኳ እንጅ ወደ ውድቀት ታሪኳ እንመልሳት ማለት አይደለም። ማንኛውም አገር የስኬትና የውድቀት ታሪክ እንዳለው ሁሉ ኢትዮጵያም የስኬትና የውደቀት ታሪክ አላት። የፋርሱ የጂኦግራፊ ሊቅ ማኒ በ5ኛው ክፍለ ዘመን   ከነበሩት አራት ታላላቅ ሃያላን መንግስታት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች መስክሯል።  ኢትዮጵያ ከደቡብ አረቢያ እስከ ደቡብ ግብጽ የሚደርስ ግዛት የነበራት፤  የአክሱም ሃውልትን፣ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የፋሲል ግንብን፣ የገዳን የእኩልነት ስርዓት ( ከግሪኮች ባልነተናነሰ) ያቆመች ፤ ጤፍንና ቡናን አላምዳ ለአለም ያበረከተች አገር ናት። ነብዩ ሙሃመድ “ ኢትዮጵያ የፍትህ አገር ናት”  ብለው እውቅና የሰጡዋት  የፍትህ ታሪክ ያላት አገር ናት። ኢትዮጵያ አውሮፓውያናንን ሲያማልል የነበረው “የፕሬስተር ጆን ኦፍ ዘ ኤንድስ” ታሪክ ባለቤት ፤  ነጭን ድል በማድረግ የአፍሪካ የነጻነትና የአልገዛም ባይነት ተምሳሌት ናት። ለጥቁር ህዝብ የነጻነት ትግል ፈር የቀደደች፣ እነ ማርክስ ጋርቬይ “ ኢትዮጵያ” ብለው የትግል መዝሙር ያዘመሩላት ብቸኛዋ የጥቁሮች አገር ኢትዮጵያ ናት።
  ወደ ገናናው ታሪካችን እንመለስ ሲባል ወደ ዘመነ መሳፍንት የውድቀት ታሪካችን እንመለስ ማለት አይደለም። ታሪክን አለማወቅ ላያስነውር ይችላል፤ ታሪክን ሳያውቁ ስለታሪክ መናገር ግን ከነውርም በላይ ነውር ነው። ኢትዮጵያ ገናና ታሪክ እንደሌላትና ታሪኳ ሁሉ የውደቅት ታሪክ እንደሆነ በድፍረት የሚጽፉ የዚህ ዘመን ጉዶች፣ ለሃፍረታቸው መሸፈኛ የሚሆን ትንሽ  ቅጠል ማጣታቸው ያሳዝናል። አባቱን የማያውቅ ሰው ስለአባቱ በድፍረት ሊናገር እንደማይችለው ሁሉ፣ ታሪክን የማያውቅ ሰውም ስለታሪክ በድፍረት ሊናገር አይችልም። ታሪክ አልባ ትውልድ ወደፊት አይራመድም፤  በውሃ ላይ እንደሚበቅል ተክል ስር አልባ ሆኖ እድሜ ልኩን እንደተንሳፈፈ ይኖራል እንጅ።  ሌሎች አገሮች ዱቄት እያቦኩ አዲስ ታሪክ ለመጋገር በሚኳትኑበት በዚህ ዘመን፣ የተጋገረ ታሪክ ባለቤት የሆኑት የእኛ ዘመን ልጆች፣ እንጀራውን መብላት ሲሳናቸው ከማየት በላይ የሚያሳፍርም የሚያሳዝንም ሌላ ነገር የለም።
ሁላችንም የሚያኮራ ታሪክ አለን።  አይናችን ገልጠን ማየት ከቻልን በየቤቱና በየሰፈሩ ተጽፎ እናገኘዋለን። አይናችንን ገልጠን መፈለግ ስላልቻልን ወይም ስለሰነፍን ብቻ ፣ “የሚያኮራ ታሪክ የለኝም” እያልን በማላዘን፣  ስንፍናችንን “ በታሪክ አልቦነት ለመሸፈን መሞከር፣ አያቶቻችን አርፈው እንዳይተኙ ማድረግ ማድረግ ብቻ ሳይሆን“ እኛ አቅቶናልና ከመቃብር ወጥታችሁ እንደገና ታሪክ ስሩልን” ብሎ እንደመጠየቅ የሚቆጠር አሳፋሪ ተግባር ነው።  ችግራችን ከስንፍናና ከአላዋቂነት ጋር እንጅ ከታሪክ ልቦነት ጋር የሚዛመድ አይደለም።   አብይ አህመድ ወደ ገናናው ታሪካችን እንመለስ ሲል “ ገናና ታሪክ የለንም ” ብለህ የምትከራከር ከሆነ፣ ያወቅህ መስሎህ የማታውቅ፣ የጠለቅህ መስሎህ የምትንሳፈፍ፣  ወደ ሁዋላ አይተህ ወደ ፊት መንዳት የማትችል፣ ማንነትክን መቀበል የከበደህና ከማንነት ቀውስ ያልወጣህ ሰው መሆንክን ማወቅ ይኖርብሃል። የማንነት ቀውስ መነሻው ታሪክ አልቦነት ነው። ከዚህ ቀውስ የምትድነውም ታሪክን በሃቅ መመርመር ስትችል ነው። ታሪክን ያማታውቅ ከሆነ፣ ከቻልክ በፍጥነት መርምረህ ከገናና ታሪካችን ጋር የሚደመር ታሪክ ለመስራት ሞክር ፣ ካልቻልክ  ደግሞ “አመልክን በጉያህ” እንዲሉ ዝም በል።
እኛ ታሪካችንን  የተቀበልን ኢትዮጵያውያን፣  ከውድቀት ታሪካችን እየተማርን ገናና ታሪካችን ለመመለስ እንታገላለን እንጅ ከታሪካችን በማፈግፈግ ማንነታችንን አንክድም አሳፋሪ ታሪክም አንጽፍም።
Filed in: Amharic