>

አስቸኳይ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አስፈላጊነቱ እንዲሁም ጠቀሜታው!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

አስቸኳይ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አስፈላጊነቱ እንዲሁም ጠቀሜታው!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ጽሑፉ ውስጥ ለተነሡ ጥያቄዎች ለየራሳቹህ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት ሳትችሉ ለነ ዐቢይ ድጋፍ እየሰጣቹህ ከሆነ ያላቹህት በዕውቀት ላይ ከተመሠረተ ምክንያታዊነት ይልቅ በባዶ ስሜት በመነዳት ከባድ አደጋ ላይ  የሚጥል ስሕተት እየፈጸምን እንዳለን አውቀን እንድንጠነቀቅ አስቀድሜ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
ወደ ጽሑፉ፦
ሰኔ 24,2010ዓ.ም. ባሕር ዳር ላይ በተደረገው ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ጀግናዋ እኅታችን እማዋይሽ ዓለሙ በቀጥታ ስርጭት ንግግሯ የሽግግር መንግሥት ሕዝባዊ ጥያቄን በማንሣቷ አገዛዙ ደንብሯል!!! ይህ ጥያቄ እንዳይጋገብ ለማድረግና ለማዳፈንም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የወያኔ/ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ  ከአምስት ወራት በፊት በርካታ ቀናት የወሰደ ዝግ ስብሰባ አድርጎ ለለውጥ የቆረጡ መሆናቸውን ገልጸው የኢትዮጵያን ሕዝብ “ለጠፋው ጥፋት ሁሉ ይቅርታ!” ብለው መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ መቸና የትቦታ “የይቅርታ ጥያቄያቹህን ተቀብየ ይቅርታ አድርጌላቹሀለሁና በሥልጣን ላይ ቀጥሉ!” ብሎ እናዳላቸው አይታወቅም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ “ሕዝቡ ይቅርታ አድርጎልን ሁለተኛ ዕድል ሰጥቶናል!” እያሉ በድርቅና የ “ዐይናቹህን ጨፍኑ ላታልላቹህ!” ጨዋታውን ተያይዘውት ቆይተዋል፡፡
ዐቢይ ከተሾመ በኋላም ይሄ ሰሞኑን ካለፈው ሳምንት ወዲህ ጀምሮ በየሥፍራው “ለዐቢይ የድጋፍ ሰልፍ!” እየተባለ የሚደረገው ሰልፍ ከመደረጉ በፊትም ዐቢይ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እንዳደረገላቸውና ሁለተኛ ዕድል እንደሰጣቸው አድርጎ ሲናገር በተደጋጋሚ ተደምጧል፡፡ መቸና የት? ለሚለው ጥያቄ ግን መልስ የለም፡፡
ማምታታት 1
 “ሕዝቡ ይቅርታ አድርጎልን ቀጥሉ ብሎናል!” 
እነኝህ ሰዎች እየተደረገ ካለው ሰልፍ በኋላ ይሄንን ብለው ቢሆን እንኳ ምንም እንኳን ሰልፉ እየተደረገ ያለው በተናጠል ዐቢይ እየወሰደው ነው ለሚባለው “የለውጥ እርምጃ ድጋፍ ለመስጠት!” ተብሎ ቢሆንም “ዐቢይ ማለት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ነውና ለሱ የሚሰጥ ድጋፍ የእኛ ማለት ነው!” በሚል ስሌት “ሕዝቡ ይቅርታ አድርጎልን ቀጥሉ ብሎናል!” ቢሉ ለማምታታቱ በተመቻቸው ነበረ፡፡ እነሱ ግን ይሄንን እያሉ ሕዝብን ማደናቆር የተያያዙት አሁን እየተደረገ ካለው ሰልፍ በፊት ነው፡፡
 ማምታታት 2
“”ተለውጫለሁ መለወጤን እመኑና አብራቹህኝ ዝለቁ!”” 
ወያኔ/ኢሕአዴግ ፈልጎት የነበረው በከፍተኛ ደረጃ በተቀናበረ ሴራና አሻጥር ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በመሥራት የሕዝቡን አእምሮ አጥበው (brainwash) ሲያበቁ “”ተለውጫለሁ መለወጤን እመኑና ተደምራቹህኝ ቀጣይ ጊዜያትን “መጭው ጊዜ ከኢሕአዴግ ጋር ብሩህ ነው!” እያላቹህ አብራቹህኝ ዝለቁ!”” ብሎ ነገሩን አድበስብሶ የገጠመውን ችግር በማለፍ ከአጣብቂኝ መውጣት ነበር፡፡
በዚህ ሒሳብም የለውጥ አንቃሳቃሽ ተብለው የተመደቡት ዐቢይ፣ ለማ፣ ገዱ፣ ደመቀና ቡድናቸው ሕዝብን ይወሰውስልናል፣ ያግባባልናል፣ ያሳምንልናል ያሉትን የቃላት ጋጋታ የቻሉትን ያህል አዝንመዋል ውጤትም ለማግኘት አስችሏቸዋል፡፡
ዐቢይ ከዚህም አልፎ ልክ ወያኔ በመለስ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለን ዲሞክራሲ፣ ለውጥና ስኬት ያመጣ እያስመሰለ ገንዘብ ለሎቢዎች (ለአግባቢዎች) እየከፈለ በዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛዎች ላይ ያስዘግብ እንደነበረው ሁሉ ከእነኝህ የብዙኃን መገናኛዎች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት (ኮንታክት) አሁንም በመጠቀም ዐቢይም ከወሬ በስተቀር ገና ምኑንም ሳይይዘውና አንዱንም ነገር ሳይከውን በውጥን ደረጃ እንኳ የሚገለጽ ነገር ሳይኖረው በምዕራባውያን የብዙኃን መገናኛዎች ላይ “ሁለተኛው ማንዴላ! ፣ ብልሁ መሪ!” ምንትስ የሚሉ የውዳሴ ቃላትን ለራሱ እያስዘገበ ዓለማቀፋዊ እውቅናና ተቀባይነት እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገለት ይገኛል፡፡
እናም እንደምታዩት ወያኔ/ኢሕአዴግ በተለያየ ድራማ (ትውንተ ሁነት) ሕዝብን አወናብዶ አታሎ ከዚህ ከገጠመው አጣብቂኝ ለመውጣት ለአእምሮ የሚከብዱ፣ ለማመን የሚያስቸግሩ፣ ጥርጣሬ እንዳይኖር ለማድረግ የሚያስችሉ ድርጊቶችን እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ጥረቱም ሠምሮለት ሕዝቡ የድራማው መሪ ተዋናይ ከሆነው ከዐቢይ ጋር እንዲጣበቅ ማድረግ ችሏል፡፡ መሪ ተዋናዩ ዐቢይም “መደመር!” በሚለው ፈሊጡ በርካቶችን “ተደምረናል!” ማሰኘት ችሎ ነበረ፡፡
ይሁን እንጅ ምንም እንኳ ዐቢይ “ተደመሩ!” ሲል የለውጥ አሥተዳደር የተባለውን “የአዲሱ ኢሕአዴግ ደጋፊ ሁኑ!” ማለቱ ቢሆንም “ተደምረናል!” ከሚሉቱ የሚበዙቱ ግን “ተደምረናል!” ሲሉ ዐቢይ በድራማው ላይ የተሰጠውን የፀረ ሕወሓት ገጸ ባሕርይ ቃለ ተውኔትና ድርጊት እውነት መስሏቸው ዐቢይን በግል “ግፋበት እንደግፍሃለን!” ማለቱ ነው እንጅ “የኢሕአዴግ ደጋፊ ሆኛለሁ!” ማለቱ እንዳልሆነ በግልጽ ከሚያሳዩትና ከሚያንጸባርቁት ድርጊቶች መረዳት ይቻላል፡፡
ሁኔታውን በሌላ አገለጽ ስንገልጸው የነዐቢይ ወይም የወያኔ/ኢሕአዴግ ዓላማና ሩጫ ጠራርጎ ሊወስዳቸው የመጣውን አቢዮት በኃይል ለመቀልበስ ተያይዘውት በነበረው መንገድ መግፋቱ ሀገሪቱን በሰው ልጅ ደም ጎርፍ ሊያጥለቀልቃትና መጨረሻ ላይም እነሱም በሰው ልጅ የደም ጎርፍ ሊወሰዱ እንደሚችሉ ስለተረዱ ኢሕአዴግን በሁለት የተለያየ አቋም ከፍለው አንደኛውን የለውጥ አቀንቃኝ ሌላኛውን የለውጥ ተቃዋሚ አድርገው የለውጥ አቀንቃኙ የሕዝብ አመኔታንና ተቀባይነትን እንዲያገኝ በለውጥ ተቃዋሚው እንደጠላት እንዲታይና ለማጥፋት የሚፈልግ መስሎ እንዲተውን፤ የለውጥ አቀንቃኙም የለውጥ ተቃዋሚውን ጠላት አድርጎ እንዲተውን በማድረግ በዚህም መሠረት ወያኔ ዐቢይን ልግደለው ቢል በየትኛውም ቦታ በየትኛውም ሰዓት ያውም በጥይት ሳይሆን ጥቃት ተፈጽሞበት ሳይሆን በራሱ አጋጣሚ እንደሞተ አስመስለው መግደል የሚችልበት ዕድል እያለው በአደባባይ ቦንብ አፈንድቶ ለመግደል የፈለጉ እስከማስመሰል ደርሰው እየተወኑ ይገኛሉ፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ነገር የእነሱ ተውኔት እውነት እንዲመስል ለማድረግና ሕዝብን ለማሳመን ሲባል ምንም የሚያውቁ ዜጎች አካል መጉደሉ ሕይዎት መቀጠፉ ነው፡፡
የእንዲህ ዓይነት ጥቃቱና የእርስበርስ መዘላለፍ መወጋገዙ ዋነኛ ዓላማ ዐቢይንና ቡድኑን በወያኔ የሚጠላ አስመስሎ በማቅረብ ሕዝቡ ዐቢይንና ቡድኑን እንዲያምነው፣ እንዲቀበለው፣ የዐቢይ ደጋፊ ተከታይ እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ ሕዝቡ “ከዐቢይ ጋር ወደፊት!” ካለላቸው ኢሕአዴግ በሥልጣን ይቀጥላል ማለት ነውና፡፡ ኢሕአዴግ ቀጠለ ማለት ደግሞ ወያኔ ከቅስፈት ከጥፋት ከውድቀት ተረፈ ማለት ነውና መጨረሻ ላይ ይሄንን ውጤት ማምጣት ነው የተፈለገው፡፡
ነገር ግን በለውጥ አቀንቃኙ ቡድን የሚሠራው የማታለልና የማግባባት ሥራ የማይሳካ ከሆነ የለውጥ ተቃዋሚ ተደርጎ የተቀመጠው ክፍል እንደገና የበላይነትን አግኝቶ የተመለሰ በማስመሰል ወደነበሩበት በኃይል እርምጃ ሕዝብን ዝም አሰኝቶ ለመግዛት ጥረት ወደሚያደርጉበት ሁኔታ መመለስ የሚችሉበትን አማራጭ ክፍት አድርገው ነው እንደምንም ብለው ሕዝብን በማወናበድ፣ በማጭበርበር፣ በማታለል፣ አቢዮቱን ቀልብሰው ዕድሜያቸውን የማራዘም ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት፡፡
በርካታ ወገኖች ይሄ ነገር ድራማ (ትውንተ ኩነት) መሆኑን ለማመን በእጅጉ ተቸግረዋል፡፡ ወያኔ ደርግን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስወግዞ ድጋፍ ለማግኘት ሲል የገዛ ወገኑን የሃውዜንን ሕዝብ ሆን ብሎ በአሻጥር ለእሱ የሚሠሩ ከሐዲ የደርግ የጦር መሪዎችን አዝዞ ያስጨፈጨፈ አረመኔ የጥፋት ኃይል መሆኑን የማያውቁ የዋሃን የመስቀል አደባባዩን የቦምብ ፍንዳታ እየጠቀሱ “ይሄ እንዴት ማስመሰል ሊሆን ይችላል?” ይላሉ፡፡ የነ ዐቢይን ቡድን ንግግሮችንም እየጠቀሱ “አሁን ይሄ ትወና ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የፊልም አክተርን (የምትርኢት ተዋናይን) ወይም የተውኔት ተዋናይን አያውቁም መሰለኝ፡፡ የትወናንና የተዋናይን ምንነት ካወቁ የነ ዐቢይ ቡድን ትወና ትወናነትን መረዳት አይከብዳቸውም፡፡
ቆይ ስታስቡት እነኝህ ለወያኔ ጥቅም ሲሉ በገዛ ወገናቸው ላይ አረመኔያዊ ግፍ ሲፈጽሙ የኖሩ፣ ሲፈጁ የኖሩ፣ ሥነልቡናቸው የተሰለበ፣ ሰብእናቸው የረከሰ የብአዴንና የኦሕዴድ ባለሥልጣናት ወያኔ የትም ሳይሔድ አብሯቸው እያለ “የቀን ጅብ፣ ቁማርተኛ፣ ድኩማን፣ የለውጥ እንቅፋት፣ ፀረ ዲሞክራሲዎች…..!” እያሉ እንደ አምላክ የሚያዩዋቸውን ጌቶቻቸውን ለመዝለፍ የሚደፍሩ፣ ለመቃወም የሚያስችል ወኔ የሞራል (የቅስም) ብቃትና ጥንካሬ የሚኖራቸው ይመስላቹሀል???
እንዲሁም ደግሞ ወያኔን ለሥልጣን ያበቃው የትግሬ ሕዝብ ብቻ ባይሆንም ወያኔ ግን “ከመቶ ሽህ በላይ የትግራይ ሕዝብን አስፈጅቸ መራራ ትግል አድርጌ ነው ሥልጣን የጨበጥኩት በካርድ አሳልፌ አልሰጥም!” በማለት “ሥልጣን ወይም ሞት!” የሚል የጸና አቋም እንዳለው ያረጋገጠው ወያኔ ሲያስመስል እንጅ እንዲህ በቀላሉ ሥልጣን አሳልፎ ሰጥቶ አጨብጭቦ የሚቀመጥ ይመስላቹሀል ወይ የዋሃን ወገኖቸ???
ወያኔ “ወዶና ፈቅዶ፣ በለውጥ አምኖ ሥልጣኑን ለአጋሮቹ አሳልፎ ሰጠ!” ተብሎ ቢሆን እንኳ ለማመን አይከብድም ነበረ፡፡ እየተባለ ያለው ግን “ወያኔ አቅቶት በለውጥ አቀንቃኞች ተሸንፎ ሳይወድ በግዱ ተገፍቶ ሥልጣኑን እንዲያጣ ተደረገ!” የሚለውን አባባል መሬት ላይ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ይሄንን እንድናምን የሚጋብዙ ናቸው ወይ ወገኖቸ??? ኧረ ተው ኧረ ተው አትጃጃሉ አቢዮቱን ውኃ በላው???
ወያኔም ይሄንን የምንጠረጥር ሰዎች ልንኖር እንደምንችል ጠፍቶት እንዳይመስላቹህ የለውጥ ቡድን ብሎ የመደባቸውን የነዐቢይ ቡድን ተቃዋሚ፣ ተቃራኒ፣ ተፃራሪ ሆኖ መተወንን የመረጠው፡፡ ነገር ግን እነ ዐቢይን ተቃውሞ፣ ተፃርሮ፣ ጠላቶቹ አስመስሎ ካልቀረበ በስተቀር ሕዝቡን እነ ዐቢይን እንዲያምን፣ እንዲቀበል፣ እንዲደግፍ፣ እንዲከተል፣ እንዲቀበል አድርጎ በነዐቢይ በኩል ኢሕአዴግን እንዲቀበል ማድረጊያው መንገድ ይሄ ብቻ ስለሆነበት፣ የለውጡ ተቃዋሚ ሆኖ መተወኑ ሰሞኑን በየቦታው እየቀሰቀሰው እንዳለው ግጭትና ተመሳሳይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ነጻነት ስለሚሰጠው፣ እንዲሁም ሕዝቡ ነጻነት ተሰምቶት ስር ነቀል ለውጥ እንዳይጠይቅ በየቦታው በሚፈጽሙት ነገር ፈርቶ ተሸማቆ ተቆጥቦ እነሱ በቃኙት አቅጣጫ ብቻ እንዲጓዝ ለማድረግ ዕድል ስለሚሰጣቸው ስለሚጠቅማቸው ነው ወያኔ ካለው ጉልበትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አኳያ አሁን አቅመቢስ ሆኖ ሥልጣን ያስረከበ መስሎ መታየቱ ሊያስጠረጥር መቻሉ ሳያሳስበው ሥልጣኑን የተነጠቀና በግጭት ፈጣሪነት ብቻ የተገደበ የለውጥ ተቃዋሚ መስሎ መተወንን የመረጠበት ምክንያት፡፡
እነ ዐቢይም “ጠጉረ ልውጦችን ተጠንቀቁ!” እያሉ መግለጫ በመስጠት ከማፌዝ በስተቀር ለዚህ በሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ላለው ከዘር ማጥፋት ቀጥሎ ሁለተኛው የዓለማችን ትልቁ የእርስበርስ የዘር ግጭት የመቀስቀስ ወንጀልን በቀስቃሾቹ የወያኔ ባለሥልጣናት ላይ አቅም እንኳ ቢያንሰው የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እገዛ በመጠየቅ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ሲችሉ እነ ዐቢይ ይሄንን ማድረግ የማይፈልጉት ለዚህ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ጭራሽ የሱዳንንም ጦር በመጠቀም ወገናችንን እያስፈጁ ይገኛሉ፡፡ እስኪ ይታያቹህ! ወገንን በባዕዳን የማስፈጀት ክፋት እንዴት ሊገለጽ ይችላል? አሁን እነኝህ እውን ኢትዮጵያውያን ናቸው??? ምነው በደላቸውን በእጅጉ እያከፉ ይቅር ለመባባል እንዳይመች ባያደርጉት???
እናም የተውኔቱ ፍልሚያ በዚህ መልኩ ቀጥሎ እንደምታዩት በተደለሉ፣ በተታለሉ፣ በተጃጃሉ ልኂቃንና ፖለቲከኞችም እገዛ ጭምር ሕዝብን ለማታለል የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበላቸው ባለበት ሁኔታ እሑድ ሰኔ 24,2010ዓ.ም. ባሕር ዳር በተደረገው ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ልበሙሉ ጀግናዋ ታጋይ እማዋይሽ ዓለሙ ወሳኝ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ አነሣችና እነ ዐቢይ ሲገነቡት የሰነበቱትን ሕዝብን ወትውቶ በማሳመን የኢሕአዴግ ተከታይ ደጋፊ አድርጎ ኢሕአዴግን የማስቀጠል ሥራ ንዳ ከአፈር ደባለቀችው፡፡ የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በዚህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተስተጋባ ጥያቄና ድንገተኛ መብረቃዊ ምት ተደናግጠው በጀርባቸው ላይ ቀዝቃዛ ላብ ወርዶባቸዋል፡፡
ከዚህ ቅጽበት ጀምሮም ተቃዋሚ እንደሆኑ የሚያስመስሉ የወያኔ ቅጥረኞች የጌቶቻቸውን ድንጋጤ ለማስታገስ ምንም ዓይነት ተጨባጭነት በሌለውና አመክንዮአዊ ማብራሪያ ጨርሶ ባልያዘ መልኩ በአሁኑ ሰዓት የሽግግር መንግሥት ለሀገራችን እንደማይጠቅም፣ ሀገሪቱን ሊያፈርሳት እንደሚችል፣ ለአማራ ሕዝብ የማይጠቅምና የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን የማይመልስ እንደሆነ፣ ጥያቄው የሕዝብ ጥያቄ እንዳልሆነ፤ ዋናው ነገር ኢሕአዴግ ራሱን ማስተካከሉ መሆኑን፣ ሥልጣን ከኢሕአዴግ ከወጣ ሀገሪቱ የምትፈርስ መሆኑን ወዘተረፈ. ተጨባጭነት የሌላቸውና ለማስፈራራት የሞከሩ ሐሳቦችን በማኅበራዊው የብዙኃን መገናኛው ፈጥነው በማራገብ ሕዝቡ ጥያቄውን እንዳይገፋበት የማድረግ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ይህ ጥያቄ የሕዝብ ጥያቄ ለመሆኑ ማረጋገጫው ጀግናዋ እኅታችን እማዋይሽ ጥያቄውን ስታነሣ ሕዝቡ ለሌሎቹ ካሰማው የድጋፍ ድምፅ እጅግ በላቀ አስገምጋሚ ከፍተኛ የድጋፍ ድምፅ ማሰማቱና ጥያቄውን ደግማ እንድታነሣው ማድረጉ ጥያቄው የሕዝብ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እርግጥ ነው ሕዝቡ የፈለገው ስር ነቀል ለውጥ ነው፡፡ ይሁንና የተለያዩ ሥጋቶች ስላሉና ሽግግሩን ሰላማዊ ለማድረግ የሽግግር መንግሥትን ለመቀበል ስለተገደደ ነው ጽኑ ፍላጎቱ ስር ነቀል ለውጥ ቢሆንም የሽግግር መንግሥትን እየጠየቀ ያለው፡፡
የሽግግር መንግሥት አመሠራረት  በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች እያንዳንዳቸው ያላቸውን ብዛት መሠረት በማድረግ ተመጣጣኝ ወይም ተገቢ ውክልና ተሰጥቷቸው የሚመሠረት ዋናው በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ የሚመሠረተው መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ መዳረሻ አሻጋሪ ጊዜያዊ ወይም መቆያ ሒደቱን አመቻች አሳላጭ የመንግሥት ዓይነት ነው፡፡
በብሔረሰቦችና ጎሳዎች ውክልና የሚመሠረትበት ምክንያት የሚገለልና ሳይወከል የሚቀር እንዳይኖር ሁሉም እንዲወከል ለማድረግ ሲባል ነው እንጅ በዲሞክራሲያዊ (በመስፍነ ሕዝባዊ) መንገድ በሕዝብ ተመርጦ የሚመሠረተው መንግሥት የጎሳ ፖለቲካን (እምነተ አሥተዳደርን) እንዲከተል ለማድረግ አይደለም፡፡ የሽግግር መንግሥት ይሄንን የመወሰን ሥልጣን የለውምና፡፡
እዚህ ላይ ግን ማለት ወደ ሽግግር መንግሥት ከገባን ወያኔ ከ13 ዓመታት በፊት ባደረገውና ከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመበት ብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ አኀዞች ጥቅም ላይ መዋላቸው አይቀርምና ይህ አኀዝ ለሽግግር መንግሥት ምሥረታ ፍጆታ ከመዋሉ በፊት የግድ ትክክለኛው የቆጠራ ግኝት ይፋ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ወያኔ የአማራን የሕዝብ ተወካዮች ውክልናና የፖለቲካ የመደራደር አቅም ለመቀነስ በማሰብ በዚያ ቆጠራ ሆን ተብሎ የአማራ ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጎ የተቀነሰው ቁጥር በኦሮሞና በትግሬ ቁጥር ላይ እንዲጨመር ተደርጓልና፡፡
በሽግግር መንግሥት ወቅት የቀውስ የግጭት ያለመረጋጋት መንስኤ የሆነው የአገዛዙ ሕገመንግሥት ከአገልግሎት ውጭ ይደረግና ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) የሆነው የሀገሪቱ ነባራዊው ምኅዳር (status quo) ሀገሪቱን ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥና ቀውስ የዳረጋት የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ሀገሪቱን ከመቆጣጠሩና ይሄንን ሁሉ ፖለቲካዊ ቀውስ ከመፍጠሩ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ይደረግና ያሉ ችግሮችን ለአለመግባባት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ሁሉ በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን የሚይዘው መንግሥት እንዲፈታቸው የቤት ሥራው ይሰጠዋል፡፡
ይሄም ማለት ይሄ አሁን ያለው ራሱን አገዛዙን ብቻ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ታስቦ የተሸነሸነው ብሔረሰብንና ቋንቋን መሠረት ያደረገው ኢፍትሐዊና ኢዲሞክራሲያዊ (ኢመስፍነ ሕዝባዊ) የክልል አሸናሸን ወይም የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) የክልል አሥተዳደር ይሻርና ወደ ደርግ ዘመኑ የክፍላተ ሀገር የግዛት አሥተዳደር ይመለስና በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሥልጣን ይዞ የሀገሪቱ የግዛት አሥተዳደር ምን መምሰል እንዳለበት እስኪወስን ድረስ ድረስ የሽግግር መንግሥቱ ሀገሪቱን የሚያሥተዳድርበት ቻርተር (ጊዜያዊ ሕግ) ቀርጾ እያሥተዳደረ በመቆየት ሽግግሩን ሰላማዊ ማድረግ ነው የሽግግር መንግሥት ሚናና ኃላፊነት፡፡ የሽግግር መንግሥት ዋነኛ ተግባርና ጠቀሜታ ይሄው ነው፡፡ በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን የሚይዘው መንግሥትም ሕገ መንግሥት ቀርጾ የሀገሪቱን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓትን መርጦ ሥራላይ በማዋል የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ይንቀሳቀሳል፡፡
እርግጥ ነው ወያኔ በዘረጋው ችግር የተሞላ የጎሳ ፌዴራሊዝም ተጠቅመናል ብለው የሚያስቡ አካላት ለምሳሌ የትግሬ፣ የኦሮሞና የሱማሌ ልኂቃን ወደፊት በኢትዮጵያ ሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት አሁን በኢፍትሐዊነት ያገኙትን ጥቅም “እናጣለን!” ብለው በእጅጉ ስለሚሠጉና የመገንጠል ፍላጎትም ስላላቸው የሽግግር መንግሥትን ምሥረታና ሒደቱን ፈጽሞ አይፈልጉም፡፡ ከፈለጉም አሁን ያለው የክልል ግዛት ባለበት ሁኔታ ነው የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚፈልጉት፡፡ ይህ አሁን ያለው ቋንቋንና ብሔረሰብን መሠረት ያደረገው ኢፍትሐዊና ኢዲሞክራሲያዊ የክልል ግዛት አከላለልና የቀውስ ምንጭ የሆነው ሕገመንግሥት ካልተሻረና ባለበት ከቀጠለማ የሽግግር መንግሥት ወይም የመንግሥት ለውጥስ ለምን አስፈለገ ታዲያ??? በዚህ ሕገመንግሥትና አገዛዝ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችን ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት አይደለም ወይ የሽግግር መንግሥት ያስፈለገው??? እነኝህ አካላት የሀገሪቱ ችግሮች በፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ እንቅስቃሴ ለምን ያሳስባቸዋል??? በራስ መተማመኑና እውነት ካላቸው የሽግግር መንግሥቱ ነገሮች በዚህ አገዛዝ ከተፈጠሩ ችግሮች አስቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ የመመለሱን ሒደት ለምን ይጠሉታል???
እነኝህ አካላት ሊረዱት የሚገባ ዐቢይ ቁምነገር ቢኖር የሀገሪቱ ችግር በፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ መንገድ የመፈታቱን ይሄንን ሒደት ወደዱም ጠሉ የግድ መቀበል ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ ተያይዞም ሌላ መረዳት ያለባቸው ቁምነገር ይህ አሁን ሥራ ላይ ያለው ፍጹም ኢፍትሐዊና ኢዲሞክራሲያዊ የጎሳ ፌዴራሊዝም የአገልግሎት ከጠበቃው አንባገነን አገዛዝ ጋር ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ነው፡፡
የዚህ የጎሳ ፌዴራሊዝም ኢፍትሐዊነትና ኢዲሞክራሲያዊነት ዋነኛ መገለጫው አንዲት ሀገር የምትተዳደረው በጎሳ ፌዴራሊዝም ከሆነ በሀገሪቱ ያሉ ጎሳና ብሔረሰቦች በሙሉ የራሴ የሚሉት የራስ ገዝ ክልልና መንግሥት እንዲሰጣቸው የፌዴራሊዝም (የራስገዛዊነት) የመንግሥት ሥርዓት መርሕ የሚያስገድድ ሆኖ እያለ የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ግን በሀገሪቱ ካሉት ከ82 ጎሳዎችና ብሔረሰቦች ለአምስቱ ብቻ ማለትም ለትግሬ፣ ለኦሮሞ፣ ለአፋር፣ ለሶማሌና ለሐረሪ ብቻ የራስ ገዝ ክልልና መንግሥት ሲሰጥ ለሌሎቹ ግን የፌዴራል (የራስገዝ) መንግሥት ሥርዓት በሚያዘው መልኩ ይሄንን የራስገዝ ክልል መንግሥት አለመስጠቱ ነው፡፡
እርግጥ ነው በሥያሜ ደረጃ የአማራ ክልል ተብሎ ይጠቀሳል፡፡ ይሁን እንጅ የአማራ ክልል ሕገመንግሥት እንደነ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የሶማሌና የሐረሪ ክልሎች ሕገመንግሥቶች የአማራን ክልል በክልሉ የሚኖሩ ጎሳዎችና ብሔረሰቦች ሁሉ ነው ይላል እንጅ የአማራ ሕዝብ ክልል ነው አይልም፡፡
በተመሳሳይም የጋምቤላን፣ የቤንሻንጉል ጉምዝን፣ የደቡብን ክልሎች የወሰድን እንደሆነ ሕገመንግሥታቸው ክልሎቹ በውስጡ ያሉት ጎሳና ብሔረሰቦችን እየዘረዘረ የነዚያ ጎሳዎች የጋራ ክልል እንደሆነ ይናገራል እንጅ የፌዴራል (የራስ ገዝ) መንግሥት ሥርዓት በሚያዘው መልኩ ለእያንዳንዳቸው ለየራሳቸው ለእያንዳንዳቸው የክልል አሥተዳደርና የመንግሥት ሥልጣን አልሰጠም፡፡
እንግዲህ የወያኔ/ኢሕአዴግ የፌደራል መንግሥት ሥርዓት እንዲህ ዓይነት ፈጦ የሚታይ ኢፍትሐዊነትና ኢዴሞክራሲያዊነት ችግሮች አሉበት፡፡ ሲጀመርም የተሰባጠረ የጎሳና የብሔረሰብ አሰፋፈር ባላት ሀገር የጎሳ ፌዴራሊዝም ሥርዓትን ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ ማሰቡ በራሱ የለየለት እብደት ነው፡፡
“አይ እብደት አይደለም መፈጸም አለበት!” ከተባለ ግን ሥርዓቱ በትክክል ይተግበርና የትግራይ ክልል የሚባለውም ራሱ ከአራት ተከፍሎ የኢሮብ ክልል፣ የሳሆ ክልል፣ የኩናማ ክልል፣ የትግሬ ክልልና የክልል መንግሥት አሥተዳደር ተብሎ መከፈል አለበት፡፡ ሌላውም እንደዚያው፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው የፌዴራል የመንግሥት ሥርዓት በትክክል ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ተተግብሯል ወይም ሥራላይ ውሏል ማለት የሚቻለው፡፡
ይሁንና ይሄንንም ቢሆን ተግባራዊ አደርጋለሁ ማለት ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰማንያ ሁለቱንም ብሔረሰቦችና ጎሳዎች በመሬት የይገባኛል ሽሚያ የድንበር ግጭት ለዘለዓለም እየተፋጁ እንዲኖሩ ማድረግ ነውና፡፡ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች እንዲህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ እንዳይገቡ ማድረጊያ መድኃኒቱ መላ ሀገሪቱን የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ማድረግ ብቻና ብቻ ነው፡፡
እናም የጎሳ ፌዴራሊዝምን ሙጥኝ የምትሉ አንባገነን የትግሬ የኦሮሞ የሱማሌ ልኂቃን ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ካላቹህ ከዚህ ጠንቀኛ ኢፍትሐዊና ኢዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባቹህ ውጡ!!! ተለዩ!!! ጣሉና ለሁሉም ወደምትሆን ወደምትጠቅም ኢትዮጵያ፣ ሁሉንም እኩል ወደምታስተናግድ ኢትዮጵያ የሚወስደንን የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ደግፉ፣ ጠይቁም???
በሽግግር መንግሥት ምሥረታው ላይ ኢሕአዴግ ከመሥራቾቹ አንዱ ሆኖ ስለሚካተት በዐቢይ ፍቅር ያበዳቹህ፣ የተለከፋቹህ፣ የተጃጃላቹህ ልኂቃን ዐቢይ ይጠቅመናል ብላቹህ ካሰባቹህ ለሽግግሩ መንግሥት ሊቀሥልጣናትነት ወይም ሊቀመንበርነት (ፕሬዘዳንትነት) እጩ አድርጋቹህ ልታቀርቡትና ልትመርጡት ትችላላቹህ፡፡ በዚያም በሉ በዚህ ግን ስር ነቀል ለውጡ ቢቀር የሽግግር መንግሥት ግን የግድ መመሥረት ይኖርበታል፡፡ ይሄንን ካላደረግን በስተቀር የወያኔን ሸፍጥ፣ ሸር፣ ሴራ፣ አሻጥር መቋቋምና በኢፍትሐዊነትና በሕገወጥነት ብቻውን ተቆጣጥሮ ከያዘው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) ወያኔን ማስወጣትና ተጠያቂ ማድረግ ፈጽሞ አይቻልም!
ዐቢይ እስከአሁን ስንት ነገር ሲወሸክት በሕገወጥነትና በኢፍትሐዊነት መንገድ ተመሥርተው እየተንቀሳቀሱ ስላሉት ስለ ኤፈርትና ስለ ፋና፣ ዋልታ፣ ድምፀ ወያኔ ሕገወጥ የወያኔ ድርጅቶች አንድም ነገር ትንፍሽ ማለት የማይፈልገው ወያኔ/ኢሕአዴግ በእነኝህ ሕገወጥ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ባለመፈለጉና ዐቢይም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ነገር እንዳይናገር ስለታዘዘ ነው፡፡
ዐቢይ በተደጋጋሚ “የትግራይ ሕዝብ ምንም የተጠቀመው ነገር የለም! ችግር ላይ ያለና መደገፍ ያለበት ሕዝብ ነው! ትግራይ ሔዳቹህ ብታዩ ምንም ነገር የለም! ፣ ለምቷል ተገንብቷል የሚባለው ነገር ሁሉ ውሸት ነው! …..” እያለ በኤፈርት በርካታ ግዙፍ ግዙፍ ካምፓኒዮች (ድርጅቶች) እና በወያኔ ባለሥልጣናት የተናጠል ዝርፊያ የሀገር ካዝና እየተራቆተ የፈሰሰባትንና ኢፍትሐዊ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የተገነባችውን ትግራይ ምንም እንደማናውቅ ዓይኑን ያጥፋውና ዓይኑን በጨው አጥቦ ሸምጥጦ እየካደ ምንም እንደሌላት አድርጎ እያስተባበለና ጭራሽም ከዚህ በላይም መገደፍ ያለባቸው መሆኑን ፈርጠም ብሎ እየተናገረ ያለበት ምክንያት ዐቢይ እያስመሰለ እየተወነ እንዳለው ሁሉ ትክክለኛ የለውጥ ሰው መስሎ የታያቸው ሰዎች በሕገወጡ ኤፈርትና በእነ ፋና ዋልታ ድምፀ ወያኔ ሕገወጥ የብዙኃን መገናኛዎቹ ላይ ርምጃ እንዲወስድ እንዳይጠይቁ ለመከላከል ቢጠይቁትም የሚወስደው ርምጃ እንደማይኖር ለማስገንዘብ ነው፡፡ እርምጃ መውሰዱ ቀርቶ የፈለገ ነገር ብታደርጉት ሕገወጥነታቸውን እንኳ አይናገርም፡፡
ዐቢይ የወያኔ ቅጥረኛና የወያኔ ድረሰት መሪ ተዋናይ መሆኑን ማወቅ ከፈለጋቹህ ሕዝብን አነጋግራለሁ ብሎ በሚቀርብበት ጊዜ በሕገወጦቹ ኤፈርትና የብዙኃን መገናኛዎቹ ላይ ምን እርምጃ ሊወስድ እንዳሰበ ጠይቁትና የሚለውን ስሙት፡፡ በተለይም አሜሪካ ያላቹህ ወገኖች ዐቢይ ሊመጣላቹህ በዝግጅት ላይ ነውና ተዘጋጅታቹህ ጠብቁት፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይሄንን ጥያቄ አይመልስም ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ መልስ ሰጥቶ ለማለፍ ጥረት ያደርጋል እንጅ ለማስመሰል እንኳ “ልወስደው ያሰብኩት እርምጃ አለ ምን እንደሆነ ግን አሁን አልነግራቹህም!” ብሎ አታሎ ለማለፍ አይሞክርም፡፡
እናም እባካቹህ ወገኖቸ በተለይም በደመነፍስ እየተነዳህ ያለኸው ልኂቁ ክፍል ተላላ አትሁኑ??? ዝምብላቹህ አትነዱ??? መርሕ አልባ የስሜት ጉዞን በእውር ድምብስ አትጓዙ??? በእርምጃቹህ ፊደል የመቁጠራቹህ፣ የመመማራቹህ፣ የማወቃቹህ ታዋስኦ ይገለጥ፣ ይታይ፣ ይነበብ??? ጠይቁ መርምሩ ሞግቱ??? በየዋህነትና በይሉኝታ አትጠለፉ??? ሕዝብ በእናንተ እየተሰናከለ እየተሸወደ ነው፡፡ ለዚህ ኪሳራና ሕዝባዊ አቢዮት መቀልበስ ኃላፊነቱን የምትወስዱ መሆናቹህ ሊያሳስባቹህ ይገባል!!!
እናም መጃጃሉ ይብቃ!!! እያንዳንዳችን ወያኔ/ኢሕአዴግ ይለወጣል የሚለውን ቅዠት አውጥተን ጥለን ለድል ጫፍ ላይ ወደደረሰው ሕዝባዊ ትግላችን እንመለስ!!! የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገር ሲባል ወያኔ/ኢሕአዴግ የፈጸመብንን አረመኔያዊ ግፍና የሀገር ክሕደት ይቅር ቢል በግሌ ችግር የለብኝም ችግሩ ያለው ወያኔ/ኢሕአዴግ “ይቅር ከተባልኩ በኋላም በሥልጣን እቀጥላለሁ!” ማለቱና የሀገሪቱን ካዝና ባራቆተው ዝርፊያው የወሰደውን የሕዝብ ሀብት ኤፈርትን ጨምሮ ለሕዝብ ወይም ለመንግሥት ገቢ ማድረግ ፈጽሞ አለመፍቀዱ ነው፡፡
ሀገሪቱ ካዝናዋ ባዶ በሆነበት ሁኔታ ወያኔ ዘርፎ የወሰደውን የሕዝብ የሀገር ሀብት እንደያዘ ታማኝ የኦሕዴድ የብአዴን ወይም የደኢሕዴን አሻንጉሊቶችን ወይም ቅጥረኞቹን አስቀምጦ ሥልጣን ለቀኩ ቢል እንኳ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ለውጥ ከቶውንም ሊመጣ የማይችል መሆኑ ነው ወያኔ የዘረፈውን የሕዝብ ሀብት ኤፈርትን ጨምሮ ለሕዝብ ወይም ለመንግሥት ሳያስረክብ ሥልጣንን ለሕዝብ ማስረከብን ፈጽሞ ሳይፈቅድ 27 ዓመት ሙሉ ለፈጸመብን አረመኔያዊ ግፍና የሀገር ክሕደት ይቅር ማለታችን ትርጉም አልባና ጥቅም አልባ የሚሆነው፡፡ በዚህ ትርጉም የለሽ ይቅርታ ተጠቃሚ የሚሆነው ወያኔ ብቻ ነው፡፡
እናም እባካቹህ ወያኔ እያጭበረበረ እንደሆነ እየገባቹህ ሕዝብን ለማታለል የሚያደርጋቸውን ለውጥ የማያመጡ ነገሮች እንደትልቅ ነገር በመቁጠር “ለአሁኑ ይሄ ይበቃናል የቀረው ነገር የቀጣዩ ትውልድ የቤት ሥራ ይሁን!” ብላቹህ ሕዝቡ ይሄንን አሁን ያለውን ሁኔታ በጸጋ ተቀብሎ አርፎ እንዲቀመጥ እራሳቹህን ለወያኔ ቀጥራቹህ የምትንቀሳቀሱ አቢዮት ቀልባሾችና ቅጥረኞች፣ እንዲሁም የወያኔን ተፈጥሯዊ ዕኩይ ማንነት ወይም ሰይጣናዊ የማይቀና የማይታረም ባሕርይ ጠንቅቆ ካለመረዳት ለወያኔ “አውቀን ብንታለልለት ይሉኝታ ተሰምቶት የምሩን ይለወጥ ይሆናል!” በሚል አጉል ተስፋ አውቃቹህ እየተጃጃላቹህ ያለቹህ ወገኖች እባካቹህ ታረሙ አርፋቹህ ተቀመጡ???
እንዳንዶቻችንን ደግሞ ቅን አሳቢ ለሀገር ለሕዝብ ተቆርቋሪ መሪ አግኝተን ለዘመናት የቆየ እንዲህ ዓይነት መሪ የማግኘት ጥማታችንን የማርካት ፍላጎታችን፣ ናፍቆታችን፣ ምኞታችን፣ ገዓራችን ሐሳዊውን እንደ እውነተኛ እንድንቀበል እያስገደደንም ነውና እንጠንቀቅ!!! የውኃ ጥማት የሚረካው በውኃ እንጅ በሽንት አይደለም፡፡
በመጨረሻም ለለውጥ አቀንቃኝ ተዋንያን ለነ ዐቢይ የማስተላልፈው መልእክት ቢኖር የተሰጣቹህን ትወና አንዳንድ ግድፈት ቢኖርበትም እንደ የተዋጣለት ተዋናይ በሚገባ ተውናቹህ ውጤት በማስገንዘብ ወያኔን ማስደሰት ብትችሉም የዚህ ተውኔት መጨረሻ እናንተን በማጥፋት እንደሚጠናቀቅ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኘ ልነግራቹህ እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም የዓለማችንን ታላቅ ተውኔት እየተወነ እንደነበረ እንዲታወቅበትና ማንነቱ እንዲገለጥበት አይፈልግምና ነው፡፡
ያላቹህ አማራጭ ሁለት ነው አንደኛው ወያኔ በተውኔቱ መጨረሻ ላይ ቀረጣጥፎ እንደሚበላቹህ አውቃቹህ እራሳቹህን ተጠቅመው እንደሚጥሉት እንደመገልገያ ዕቃ ቆጥራቹህ ወያኔ የተውኔቱ መጨረሻ ቀን ደርሶ እስኪበላቹህ ድረስ ሰጥ ለበጥ ብላቹህ ወያኔን በትወናው ማገልገል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሞቱ ካልቀረልን ሁለትና ሦስት ተደራራቢ ሞት አንሞትም!” ብላቹህ ከትወናው በመውጣት ሴራውን ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ በማጋለጥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደርስልን ጥሪ በማድረግ ለወያኔ ብላቹህ ግፍ ስትግቱት የኖራቹህትን ሕዝብ በመካስ ታሪካቹህን ማደስ ስማቹህን መቀደስ ነው፡፡ እህ የትኛውን ትመርጣላቹህ??? በቀጣይ ጊዜያት ከድርጊታቹህ የምንረዳው ይሆናል፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic