>

የሱንዳን ወረራና ጥቃት ዛሬ እና ነገ?!? (ብስራት ወልደሚካኤል)

የሱንዳን ወረራና ጥቃት ዛሬ እና ነገ?!?
ብስራት ወልደሚካኤል
የሱዳን ጦር በጎንደር በኩል የኢትዮጵያ ድንበር ላይ የፈጸመው እና እየፈጸመ ያለው ወረራ እና ጥቃት በዋዛ መታየት የለበትም:: በተለይ በአቅራቢያው ያለው የአማራ ክልል አስተዳደር ጥቃቱን እንደ ተራ ትንኮሳ በማየት ምስኪን ገበሬዎች ብቻ ድንበር እንዲከላከሉ መተው ተገቢ አይደለም:: እንደ ህጉ ቢሆን ከድንበር ጋር በተያያዘ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት መጠበቅ እና ማስከበር የነበረበት የመከላከያ ሰራዊት ነበር:: ይህ በህወሓት የስልጣን ዘመን ባለ ሰራዊት የማይታሰብ ነው:: መከላከያ ሰራዊቱ ከተራ የህወሓት ቡድን ጥቅም ጥበቃ ወጥቶ ሙሉ ለሙሉ ብሄራዊ መከላከያ ተቋም ሆኖ እስኪዋቀር ድረስ የየአካባቢው ሚሊሻ እና “ልዩ ኃይል” ትንኮሳ እና ጥቃት በሚፈጸምበት ቦታ በተጠንቀቅ የሚቆም ኃይል ያስፈልጋል:: በተጨማሪም ከወረራው ጀርባ ማን እንዳለ እና ለምን ዓላማ እንደሆነም በተቀናጀ መልኩ መረጃ መሰብሰብ ደግሞ የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ ቀዳሚ መፍትሄ ይሆናል::
በስልጣን ላይ ያለው የሱዳኑ አልበሽር መንግሥት የህወሓትን ሰዎች ከተራ ሽፍትነት ጀምሮ እስከ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ያበቃ ቀጥተኛ የጥቅም ትስስር ያለው የህወሓት የቅርብ ወዳጅ እና ቀኝ እጅ መሆኑ መዘንጋት የለበትም:: ስለዚህ በሱዳን መንግሥት ወታደሮች በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በተለይም በጎንደር አካባቢ ቋራ: መተማ: አርማጭሆ: ወልቃይት: ሰቲት-ሁመራ እንዲሁም ቤኒሻንጉል አካባቢ ዳንጉር: ጉባ (የአባይ ግድብ ያለበት): ሸርቆሌ እና ኩሙክ ወረዳ አስተዳደር አካባቢ ሌላም ትንኮሳና ወረራ ሊፈጸም ስለሚችል የተጠቀሱት አካባቢዎች ከመደበኛው ነዋሪ: ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል በተጨማሪ በሙያ ስነምግባር እና ብቃት በታነፁ የደህንነት ኃይሎች በመታገዝ በብሔራዊ ስሜት: ጥቅም እና ዓላማ ባነገበ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ጥበቃ ያስፈልጋል:: ለዚህም ጥቂት ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል::
አዲሱ የዶ/ር አብይ አስተዳደር አቅመ ቢስ እንደሆነ ማሳየት …
1. ህወሓት ቀስበቀስ በሀገሪቱ ላይ የነበረው ፍጹም የበላይነት  በህዝቡ ትግል እየተናደ በመምጣቱና በመበሳጨቱ በቻለው መጠን ሁሉ ሃገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋት በመፍጠር ራሱን “ዘብ እና ሰላም አስከባሪ” እንደነበር ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ድንበር አካባቢ ከቀድሞ የነፍስ አባቶቻቸውና የጥቅም ወዳጆቻቸው ጋር በመመሳጠር (ያው የለመዱት ስለሆነ) አዲሱ የዶ/ር አብይ አስተዳደር አቅመ ቢስ እንደሆነ ማሳየት ይፈልጋል::
በህወሓት ሰዎች ከሱዳን ጋር ሲፈጸም የነበረው የጋራ የሌብነት ተግባር 
2.የኢትዮጵያ 80% የነዳጅ ፍጆታ ሲገዛ እና ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ከሱዳን (ቀሪው 20% ከኩዌት እና ከሳውዲ አረቢያ) ነው:: ይሄ ደግሞ በአዲሱም ሆነ በመጭው የኢትዮጵያ አስተዳደር ሊቀጥል አይችልም:: ምክንያቱም በነዳጅ ግዥው ዋጋ እና አቅርቦት ላይ በህወሓት ሰዎች ከሱዳን ጋር ሲፈጸም የነበረው የጋራ የሌብነት ተግባር በአዲሱ አስተዳደር ጉዳዩ እንዲፈተሽ መታቀዱ በህወሓት እና በሱዳን ባለስልጣናት ያልተገባ ጥቅም ማጋበስ አደጋ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትም እንዳለው በማሰብ::
ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ጥቅም ማጣት
3. በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ጋዝ እና ነዳጅ አውጥታ ቅድሚያ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ለማዋል ካሰበች ሱዳን በየዓመቱ በአማካይ ከኢትዮያ ስታገኝ የነበረው ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ጥቅም ስለሚቀርባት::
ፖለቲካዊ ቀውስን እንደ መሳሪያ የመጠቀም አዝማሚያ
4.ኢትጽያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ የስርዓት ለውጥ  ከመጣ እና በተለይ የአስፈፃሚ አካላት የህግ ተጠያቂነት ከሰፈነ 29 ዓመታት በፈላጭ ቆራጭነት በስልጣን ላሉ የሱዳን ባለስልጣናት በሀገራቸውና በቀጠናው ላይ በቀጥታ እና የእጅ አዙር ያላቸው ጣልቃ ገብ ሚና ቀንሶ የህዝባቸው የዴሞክራሲ ጥያቄ ተፋፍሞ የሚቀጥልና በአስከፊ ማዕበል ከስልጣናቸው የመገፍተር ዕድል ስላለው የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማዛባት ይረዳ ዘንድ ራስ ወለድ ፖለቲካዊ ቀውስን እንደ መሳሪያ የመጠቀም ዕድላቸው ሰፊ ነው:: ስለዚህ በሱዳን ድንበር አካባቢ ከአሁኑ በባሰ መልኩ ትንኮሳና ወረራ ሊፈጸም ስለሚችል ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሱዳን አዋሳኝ ድንበሯን በንቃት መጠበቅ አለባት::
በተለይ አሁን ከስልጣን ተገፋን የሚሉ አዛውንቶቹ የህወሓት እና የህወሓት-ብአዴኖች የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ስለነበሩ የሀገር ውስጥ አጋሮቻቸው አድርገው ሊሰሩ ስለሚችሉ ከአዲስ አበባ ውጭ ያለ የአዛውንቶቹ እንቅስቃሴዎቻቸው ክትትልና ትኩረት ሊደረግበትም ይገባል::
Filed in: Amharic