>
5:08 pm - Monday February 22, 7993

"ደርግን የጣለው ራሱ ደርግ ነው" ክቡር ጠቃላይ ምኒስትሩ እውነት ብለዋል፤ ህያው ምስክር ነኝ!!! (በቀለ ገብረየሱስ)

“ደርግን የጣለው ራሱ ደርግ ነው” ክቡር ጠቃላይ ምኒስትሩ እውነት ብለዋል፤ ህያው ምስክር ነኝ!!!
በቀለ ገብረየሱስ
     የሚገርማችሁ ነገር ዛሬ ያለወትሮዬ ዘና ብዬ ስለቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአጠቃላይ እና ፣ ስለ ቀድሞው አየር ወለድ ጦር በተለይ፣ ትንሽ ላወራላችሁ ስዘጋጅ፣ አንድ ወዳጄ መጥቶ ከሰላምታ በሁዋላ ምን እየሰራሁ እንዳለሁ ስነግረው እንደህ አለኝ
   ” በጦርነት የተሸነፈ ጄኔራል የጦር አማካሪ መሆን አይችልም” ሲባል አልሰማህም? ለምን ሽንፈታችሁን ተቀብላችሁ አርፋችሁ አትቀመጡም” አለኝ፣ ገረመኝ! በመጀመሪያ ይህ ወዳጄ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አጀንዳ ሲነሳ ደማቸው ከሚፈላና ስለ ቀድሞው ሰራዊት ምንም መልካም ነገር መስማት ከማይፈልጉት ገልቱዎች አንዱ መስሎኝ በጥርጣሬ አይቼው ነበር፣ ሆኖም በየዋህነት የሰጠው አስተያየት ስለነበረ እውነታውን በትእግስት ላብራራለት ወደድኩና እንዲህ አለኩት፣
      ያ ሰራዊት የሀገር ሉዐላዊነትና ዳር ድንበር፣ የህዘዝብን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ የተለየ ግዳጅ ያልነበረው፣ ለዛም የላብ፣ የደም የአካልና የህይወት መስዋእትነት ሲከፍል የኖረ ፣ ስለማይበገር ሞራሉ ስለ ውጊያ ችሎታና ብቃቱ ፣ የማይሸነፈውን እንዴት እንዳሸነፉት ተራ የወያኔና የሻቢያ ካድሬዎች ሳይሆኑ የዚያኔም ሆነ ዛሬ በጦር እዙ ላይ ከነበሩት በህይወት ካሉት ኢሳያስና የጦር መሪዎቹ፣ ከወያኔም በህይወት ካሉት ሳሞራ የኑስና  ስዬ አብረሃ እንዲሁም በህይወት ባይኖርም ሃየሎም አርአያ በሚገባ ያውቁታል፣ እናም በውጊያ መሳሪያም ሆነ በውጊያ ብቃት ከሻአቢያና ከወያኔ ሰራዊት አንሰን አለመሸነፋችንን ቢያንስ እነዚህ ሰዎች ህያው ምስክሮች ናቸው አልኩት፣ ደግሞም አንዳዶች እንደሚያስቡት የቀድሞው ሰራዊት የውጊያ ብቃት የሌለው ደካማ ቢሆን ኑሮ ሻቢያ 30 አመት ፣ወያኔ 17 አመት ሙሉ ለምን ሲንፏቀቁ ኖሩ ብዬ ጠየቅሁት፣ በነገራችን ላይ ጠንካራውን የሻእቢያ የባድሜ ግንባር ምሽግ ለወያኔ ማን እንደሰበረለት ታውቃለህ ? አልኩት፣  ወዳጄ በዝምታ ቢዋጥም እኔ ግን ማብራራቴን ቀጠልኩ፣
     በኤርትራ የተለያዩ ግምባሮች፣ከአስመራ ዙሪየ ጀምሮ በመንደፈራ፣በደቀመሃሪ፣በሃረዛ፣በባሬንቱ፣ በቦሾቃ፣ በወኪዛግር፣ በሀሊመንተል፣በአላ፣በከረን፣  ግዝግዛ፣ በአፍአቤት፣በማይሚዶ፣  አምባ፣  ቲክሲ በአልጌና ፣በናቅፋ በርና በምፅዋ ግንባሮች ስለተደረጉት የሞት ሽረት ፍልሚያዎች አጫወትኩት፣ በመሃል አገርም በአደዋ፣በሽሬ፣ በአላማጣ በቆቦ፣ ግራካሶ፣ ጎብዬ ፣ ዶሮግብር ፣አላወሃ፣ ወልዲያ ውጫሌ፣ ኩታበር፣ ጉና፣ደብረታቦር፣ጋሳይ፣ ጉጉፍቱ፣መራኛ፣ ካቤ፣ መዘዞ፣ዞማ፣ጣርማበር፣ ለሚ ፣አጋምሳ አምቦ……. እያልኩ እስከ 4 ኪሎ ቤተመንግስት ያለውን ትረካዬን ቀጥዬ በመጨረሻም በወቅቱ ፕረዘዳንት በጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ለእስካሁኑ አናመሰገናለን በሰላም ወደየቤተሰቦቻችሁ ሂዱ ተብለን እንዴት እንደቀልድ እንደተበተን ነገርኩት፣ በመጨረሻም ለምን አልተሸነፍንም እንደምለው እንዲረዳ እኛና ወያኔ የተፈታተሽንበትን ውጊያ በምሳሌነት ልነግረው ወደድኩ።
ጊዜው ነሃሴ1981  ቦታው ሰሜን ወሎ ዶሮ ግብር እና ጎብዬ ይባላል ፣ በወቅቱ ሁሉት አየር ወለድና አንድ ሜካናይዝድ ብርጌዶች  605ኛ ከሚባል ኮር ጋር በጠላት ተከበዋልና አስመራ የቀረው ሁለት አየር ወለድ ብረጌድ ወደወሎ መጥቶ ከበባውን እንዲሰብር ታዞ መጀመሪያ 6ኛ አየር ወለድ ብርጌድና ነበሮ ኮማንዶ ሻለቃ በተገኘው አውሮፐላን ተጓጉዘው አዲስ አበባ ከዚያም በተሽከርካሪ ወልዲያ ገባን ፣ የወልዲያ መወጫ በር ዶሮግብር ላይ በጠላት ተዘግቶ ስለነበር ማለፍ እይቻልም፣ እናም በጠላት ላይ ጎህ ሲቀድ ከጀርባ ገብተን ድንገተኛ ማጥቃት ለመፈፀም ዝግጅቱ ተጠናቆ  ከወልዲያ ሰሜን ምስራቅ ጉባርጃ ጊዮርጊስና ጉባርጃ ማርይም በመባል የሚታወቁትን ከፍተኛ ገዢ መሬቶቶች ያለምንም ውጊያ ተቆጣጥረን ስናስስ ያገኘነው በአንዲት ደሳሳ ጎጆ በራፍ ላይ የተቀመጡ አንድ አዛውንት ብቻ ነው፣ ህዝቡ አስቀድሞ ስለሸሽ ቦታው ባዶ ነበር፣  ” አባት እዚህ ቦታ የወያኔ ጦር ሰፍሮበታል አልተባለም እንዴ  የት ሄዱ” ብለን አዛውንቱን ጠየቅናቸው፣ ” ይሄ ቀይ መለዮ የሚለብስ የደርግ ጨካኙ ጦር ስለመጣ ለጊዜው ይሄን  ቦታ ለቀናል ብለው እቃቸውን ሰብስበው ለሊት ነው የወጡት ” አሉን ፣ወዳጄ ከዚህ የተረዳው ነገር ይኑር አይኑር ባላውቅም፣ ወያኔ አየርወለድን እንዴት ይፈራ እንደነበር ማሳያ ነው።
  ያም ሆነ ይህ ጉዞአችንን ወደተከበበው ጦር ቀጥለን ጎብዬ ስንደርስ ስለመሽ የመከላከያ ቦታ ይዘን ለማደር ወሰን ፣ሆኖም የሰው ሃይሉ ከ7000 እስከ 8000 የሚሆን ሶስት በርጌድ የወያኔ ጦር ሊከበንና ከዚያኛው የወገን ጦር ጋር እንዳንገናኝ ለማድረግ እንደተዘጋጀ መረጃ ደረሰን፣ እኛ ያለን አንድ ብርጌድ ከነብሮ ሻለቃ ጋር 2500 ሰው እንኳን አይሆንም ፣ተዘጋጅተው ስለጠበቁን ውጊያውን እነሱ ጀመሩት ፣ በዚህ ባልተመጣጠነ ሃይል ውጊያው ተጧጡፎ ያለማቋረጥ 16:45 ደቂቃ የያዝነውን መሬት ሳንለቅ ተፋለምን እኛ ተጨማሪ ሃይል ሳናገኝ እነሱ አለሌ ሱሉላ ከሚባል ቦታ አዲስ ሃይል አምጥተው አላውሃ ሜዳ ላይ ሲያሳርፉ እኛም ከበባውን ሰብረን በመውጣት አላውሃ ከጠበቀን አዲስ ሃይል ጋር የጨበጣ ውጊያ አድርገን ብዙ ምርጥና ብርቅ ጓዶቻችንን ገብረን በማለፍ  ከወገን ጋር ተቀላቀልን ፣ ይሄ ሁሉ ሲሆን ሶስት ከፍተኛ ጄኔራል መኮንንች የእርዳታ ጦር ሊልኩልን ሲችሉ ዝም ብለው የኛን ውጊያ ከፍተኛ መሬት ላይ ሁነው እንደ ፊልም ይመለከቱት ነበር፣ በዚህ አይነት ሁኔታ ነበር ወያኔ አሸነፍኳችሁ የሚለን አልኩት። በወዳጄ ፊት ላይ የሀዘን ጭጋግ አየሁ ፣
    በነገራችን ላይ ስለአየር ወለድ አወራልሃለሁ ስል ለካስ ጊዜው ሂዷል ስለዚህ በቃ ሌላ ጊዜ እንጨርሰዋለን ስለው ” አይቻልም ሳትጨርስልኝ አልለቅህም ” አለኝ፣ እንደ እውነቱ ከሆነ  በቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት በዚህ ዘመን በዚች ምድር ላይ በአየር በባህርና በየብስ ሃይል የተደረጉ ጥምር ውጊያዎች፣ የቀይ ባህር፣ የቀይ ኮከብና የባህረ ነጋሽ ዘመቻዎችም የሚረሱ አይደሉም፣ ሌላው  የደብረዘይት አየር ሃይልና አየር ወለድ ጎረቤታሞች ቢሆኑም በግሩፕ ጠብ ሲደባደቡ የደብረዘይትን ከተማ የሚያደምቁ የማይረሱ ትዝታዎች ሲሆኑ በግዳጅና በትምህት ዝላይ ጊዜም ጎረቤታሞቹ ተቀናጅተው ነበር የሚሰሩት፣ የአልጌና የዱከምና የስመራ አዲጓዳድ ዝላይም የተከናወኑት በአየር ሃይል አውሮፕላኖች ነው ፣
  የክፍል ቅናት፣የመለዮና የአርማ ፍቅር፣ ወታደራዊ ዲሲፕሊን አየር ወለድ የሚታወቅበት ባህሪው ነው።
ለዛሬ ታዲያ በደረቁ ከምለያችሁ ሴት የአየርወለድ አባሎቻችንን ላስተዋወቃችሁ፣ የመጀመሪያዋ ብቸኛ ሴት ባለ እሰታር ዊንግ አየር ወለድ የሺ ጎበና ትባላለች፣ አሁን በህይወት የለችም ፣ቀጥሎ 10 ወጣት ሴቶች ዝላያቸውን አጠናቀቁ ፣አሁን ሁለቱ ገነት በቀለና  ጥሩ ወርቅ  በህይወት ባይኖሩም ሌሎች ስምንቱ በተለያዩ የአለም ክፍል ይኖራሉ፤ እነዚህ ሴቶች የትም አለም ይኑሩ የት፣ ያለምንም ማጋነን ከባሎቻቸውና ከልጆቻቸው በላይ የሚወዱት እናት ክፍላቸው የሆነውን አየርወለድ ይመስለኛል።  እንግዲህ የኛ ምርጦች እነዚህ ናቸው በተረፈ ቸር እንሰንብት ለጊዜያችሁ አመሰግናለሁ።
Filed in: Amharic