>

ካሌብና ኢያሱ፤ ለትግራይ (አሰፋ ታረቀኝ  ሲድኒ - አውስትራሊያ)

ካሌብና ኢያሱ፤ ለትግራይ

አሰፋ ታረቀኝ  ሲድኒ አውስትራሊያ

እግዚአብሄር አምላክ እስራኤልን ለመታደግ ያወጣውን ዕቅድ ለመፈፀም አመራር ሰጪውን ያሰለጠነው እስራኤልን አምርሮ በሚጠላው በፈርዖን ቤት ነው። ሙሴ የእግዚአብሄርንና የእስራኤልን ቁርኝት ከእናቱ፤ በዘመኑ የነበረውን የትምህርት አይነት ከግብፅ ከጠላቱ እየተማረ ለቁም ነገር ብሎም አንድን ብሄር/ህዝብ ለመምራት ደረሰ።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና አካባቢውን ውጤቱን ለመገምገም ከሚከብድ ጥፋት ያድንና ይታደግ ዘንድ የሰው ልጅ ራሱን በድርጅት መልክ አዋቅሮ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ተመሳሳይ ሊገኝለት በማይችል ጭካኔ የተሞላና ርህራሄ መካን በሆነ ህወሃት ውስጥ /ለኔ ኢህአዴግ ሽፋን ነው/ አብይ የተባለ ወጣት ሸፍኖ አሳድጎ እነሆ ተዓምር እያሳየን ይገኛል። ዶ/ር አብይ አህመድ የተባለ ብላቴና ፍቅርን፤ ሰላምንና ይቅርታን መስበክ ሲጀምር ክርስቲያንና እስላም ነገድና ጎሳ ሳይለይ የኢትዮጵያ ህዝብም አብሮት መዘመር ጀመረ። የኢትዮጵያ ህዝብ የስሜት ረሀቡን የሚያስታግስለት አገኘና ደስ አለው። አብሮትም ተሰለፈ።

በበረሃው ጉዞ ዘመን እስራኤል ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ አሚሌቅ እንቅፋት እንደሆነበት ሁሉ፤ የጭካኔውን ወለል ለመለካት አስቸጋሪ የሆነው ህወሃት የትግራይን ህዝብ የዚህ አህጉር አቀፍ የሆነ ራዕይና የኢትዮጵያ ህዝብ ደስታ ተካፋይ እንዳይሆን አፍኖ ይዞታል። የህወሃት ‘ጄኔራሎች’ ድንፋታ አየሩን አጣብቦታል።

ይወርሷት ዘንድ እግዚአብሄር ለአባቶቻቸው ቃል የገባላቸውን የተስፋይቱን ምድር ይሰልሉ ዘንድ በእግዚአብሄር ታዞ አስራሁለት ሰላዮችን ሙሴ ላከ። አስሩ በተመለቱት ተደናግጠውና ተረብሸው ሲመለሱ ሁለቱ ብቻ – ካሌብና ኢያሱ – መውረስ እንችላለን ብለውና ተስፋ ሰንቀው ህዝቡን አንቀሳቀሱ። (ታሪኩ በኦሪት ዘእልቆ ምዕ. 13 ይገኛል።)

ህወሃቶች ለ44 ዓመታት ያፈሰሱት ደም ተጠራቅሞና ኩሬ ሰርቶ እየታያቸው ነው። የከተረው ደም ተኝተውም ይታያቸዋል። ሰላም ፍቅር ዕርቅ የሚሉት ሀሳቦች ለነሱ ባዕድ ናቸው። የፈፀሙትና ገና መጪው ትውልድ ሁሉ የሚዘግበው የግፍ ዓይነት ሰላም ነስቷቸዋል። ተደብቀው የሚያሴሩበትና በጎሳ የዜና አውታራቸው የሚደነፉት የቀኑ መምሸት ሳይገባቸው ቀርቶ አይደለም። የግፉ ተራራ የሰላሙን ሜዳ ጋርዶባቸው እንጂ።

የትግራይ ህዝብ የሰላምን ሜዳ የማየት እድሉን ጋርደው የነሱ መንፈሳዊ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጭንቀት ተጋሪ ሊያደርጉት በመጣር ላይ ናቸው። ቀለም ቀመስ የሆነው የትግራይ ተወላጅ /ሁሉም ባይሆን/ ሙሴ የላካቸውን አስሩን የሚወክሉ ይመስላሉ። የህወሃትን ሽብር ይጋራሉ። የሚታያቸው አማራና ኦሮሞ ተባብሮ ሲወራቸው እንጂ ኤርትራን ጨምሮ ኢትዮጵያ ጅቡቲና ሶማሊያ አንድ ሆነው ሰላም ሲሰፍን ህዝብ ያለገደብ ሲንቀሳቀስ አይደለም። ሰላም ሰፍኖ ህዝብ መንግሥትን እየተቆጣጠረ ሳይሆን ትግራይ ድምጥማጧ ጠፍቶ ‘ትምክህተኞችና ጠባቦች’ ሲዝናኑ ነው።

የመፅሐፍ ቅዱሶቹ ካሌብና ኢያሱ የእስራኤል ነገድ “በእግዚአብሄር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ” እንዳሉት “ደስታና መከራውን፤ ማጣቱንና ማግኘቱን ሰላምና ጦርነቱን ተካፍለን ካሳለፍነውና ከተዋለድነው ህዝብ አንለይም። በኢትዮጵያ ላይ ለደረሰው የግፍና የመከራ አዝመራ ተጠያቂው እራሱ ህወሃት እንጂ እኛ አይደለንም”  የሚሉና የትግራይን ህዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ለመደመር የሚያዘጋጁ የትግራይ ካሌብና ኢያሱ ከትግራይ ህዝብ መካከል መውጣት ግድ ይላል። በመደመር ተጋምዶና ተሳስሮ ዛሬን ለመሻገር ነገንም ለመኖር የትግራይ ህዝብ የራሱን ካሌብና ኢያሱ ማውጫው ጊዜ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፤ ሳይዘገይ በፍጥነት።

ፍቅር ያሸንፋል!

እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!

ሰኔ 2010 ዓ/ም

 

Filed in: Amharic