ብርሃነመስቀል አበበ ሰኚ – ዶ/ር
ለማ መገርሳ እና አብይ አህመድ ኦህዲድን ሲነጥቋቸው የከሰሩት ህወሃቶች ኦሮሞን በመያዝ ይፈነጩበትን የኢትዮጵያ የፓለቲካ ሜዳ አጥተዋል።ነገር ግን ህወሃቶች ይህን ያጡትን ቦታ መልሶ ለመያዝ የኦሮሞ ብሄርተኛ ነን የሚሉ ቡድኖችን በመያዝ የኦሮሞ ህዝብንም ሆነ የለውጥ ኃይሉን ሰላም እየነሱ ነው።
የህወሃቶች የአሁኑ የትግል ስልት የኦሮሞ ህዝብ የኦሮሞ ብሄርተኞች ናቸው ብሎ ከሚያምንባቸው ቡድኖችና ግለሰቦች መካከከል በለመዱት የግዥና ሽያጭ ፓላቲካ በመመልመል በኦሮሞ ህዝብና በቲም ለማ ላይ እያደራጁ ይገኛሉ። ህወሃት እነዚህ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ቡድኖችን ተጠቅሞ ቢያንስ ሶስት አላማዎችን ለማሳካት ያልማል።
- 1ኛ፣ ለህወሃት ከቦታዋ መነቀል ምክንያት የሆነውን የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ትስስርንና ህብረት ለማፍረስ እነዚህን የኦሮሞ ብሄርተኛ መሳይ ቡድኖችን መጠቀም። ለዚህ ደግሞ ኦሮሞና አማራን ያወዛግባሉ ብለው የሚያስቡትን ምልክቶችና ድርጅቶች ዋነኛ የህዝብ ማደናገሪያ አጀንዳ በመድረግ ሁለቱን ህዝቦች ማባላት። ህዝቡ ስለስረዓት ለውጥ ሳይሆን ስለ ምልክትና ድርጅት ለውጥ እንዲያስብ እይታውን ማሳነስ፣ እንዳይተማመን ማድረግ።
- 2ኛ፣ ኦሮሚያን በእነዚህ የኦሮሞ ብሄርተኛ መሳይ ቡድኖች በመጠቀም ያልተረጋጋች እና ሰላም ያሌላት የጦር ቀጠና በማድረግ ለህወሃት ዝርፊያ ምቹ የሆነች ማድረግ። ሰላም መንሳት። ከተቻለም ኢትዮጵያን በማፍረስ ኦሮሚያ ላይ እንነግሳለን የሚሉ ተስፈኞችን በገንዘብና በትጥቅ በመርዳት ማጃጃል።
- 3ኛ፣ በለማና አብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ አገር እንዳያሸጋግር በነዚህ ቡድኖች ማወክ። ህግና ስረዓት መከበር በሚደረግ ህደት የኦሮሞን ደም በኦሮሞ እንዲፈስና ኦሮሞ ተጨራረሰ ለማስባል። ኦሮሞን በሃይማኖትና በአከባቢ መከፋፈል። ከተሳካለቸው ለውጡን አጨናግፎ ህወሃት ወደ ስልጣን እንዲመጣ እነዚህን ቡድኖች እንደ መሰላል መጠቀም ናቸው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃትና ስራውን መሳት የለበትም። የ27 ዓመቱ መከራ አንሶ የኦሮሞ ህዝብ ደግም ለህወሃት መልዕክተኞች መሣርያ እንዳይሆን በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግዱትን ሌቦች ምላሳቸውንና ወሬያቸውን ሳይሆን ስራቸውንና አላማቸውን አጥብቆ መከታተል አለበት።